Sunday, 14 November 2021 00:00

“ከአድማስ ባሻገር”- የሥነ-ጽሑፋችን ንቅሳት!

Written by  ደረጀ በላይነህ
Rate this item
(3 votes)

  የታደለ አበባ ሲረግፍ ፍሬ አዝሎ- አሻራ አስቀምጦ ነው። የአበባነት መዐዛና ጠረኑ አየር ላይ ናኝቶ አይቀርም፤ በፍሬ ተጠቅልሎ በትውልድ ልብ ሌላ አበባ ይጸንሳል፤ ሌላ ፍሬ ይወልዳል!..
ለዘመናቸው ክንፍ በሚገባ ተፈናጥጠው ሕይወትን በውል የቃኙ፣ ዓለምን በሕሊና የዳኙ ከያንያንም ከከፍታቸው ማዕረግ፣ ከድካማቸው ስርቻ ፈልቅቀው የሰጡንን-ውበትና እውነት፤ በየዘመኑ እያየናቸው እንድንገረም፤ እያሰብናቸው እንድንረካ፣ በነፍሳቸው ጫፍ ያነጠፏትን ፀጋ እንድንፈነጥዝባት ይጋብዙናል።
ዲከንሰንና ሚልተን በግጥማቸው፣ ቶልስቶይና ደስተየቭስኪ በልቦለዳቸው፣ ኤመርሰንና መሰሎቹ በወጉ፣ ቫንጎግና ፒካሶ በስዕልና ቅርጻቅርጻቸው የዓለሙን የውበት ጉልላት ያደመቁት ደልዳላ ቀን አግኝተው ሳይሆን በወስፌ ጫፍ ላይ ቆመው ነው። የፒካሶ እናት “መነኩሴ ብትሆን ጳጳስ፣ ወታደር ብትሆን… ጀኔራል ትሆናለህ” ብላ ብትመኝለትም ሰዓሊ ሆኖ ፒካሶን፤ የሆነው በጥበብ ጸጋ ተጠምቆ፣ በምጥ ነበልባል ነድዶ እንደ ሰንደል ጤሶ ነው።
የኛ ሀገሮቹም በዓሉም ሆነ ሀዲስ፣ጸጋዬም ሆነ ገብሬ ፣ አፈወርቅም ሆነ ሌላው፣ የዚሁ ፅዋ ጠጪ፣ የዓለም የጥበብ አካል ሆነው አልፈዋል። እነርሱ አምጠው የወለዱትን፣ አበባ ሆነው ያቆዩትን እየተዋብንበት እያጣጣምነው፣ ነፍሳችን እየፈነጨችበት ነው።
የጥበብ ሰዎች ባለውለታዎቻችን ናቸው። በወስፌ ጥርስ ላይ ሮጠው፣ በደማቸው ላብ የጻፉልንን እኛ እንዋኝበታለን።
የኔ የዛሬ ቅኝትም ከነዚህ ጠቢባን አንዱ የሆነው በዓሉ ግርማ ፣ ጥሎልን ከሄደው ዛላ አንዱን መዝዞ ማየት ነው። ያም የበኩር ስራው የሆነው “ከአድማስ ባሻገር ነው።
ከአድማስ ባሻገር “በኢትዮጵያ ስነ-ጽሁፍ የዘመናዊው-አጻጻፍ ፈር ቀዳጅ ከሚባሉት ውስጥ አንዱ የሆነና በ1962 ዓ.ም የታተመ መጽሐፍ ነው። “ፍቅር እስከ መቃብርን” ተከትሎ ከ”አደፍርስ” ጋር (በቅርፁ የተለየ) የሀገራችን ስነ-ጽሁፍ የውበት ንቅሳት ነው።
“ከአድማስ ባሻገር” የሁለት ዓለም ሰዎች ግጭት፣ ባለ ዥንጉርጉር ቀለማት ግጥሚያ ነው። የሴራው - አፀቆች  የተሞሉት በዚሁ በተለያዩ የፍልስፍና ፣ የእምነትና የስነ-ልቦና ትንቅንቆች ነው። መርገብና መክረሩ ሁሉ፣ በዘመኑ ሰፍኖ የቆየውንና ስር የሰደደውን ርዕዮትና ስርዓት በሚቃወሙ አዳዲስ ቡቃያ ሕልሞች የታመቀ ነው።
በዓሉ ግርማ ግጭቱን በረቂቅና ተጨባጭ ህልሞች ከማድረጉ በፊት ገና  ወደ ታሪኩ መግቢያ ደፍ ላይ ጢንዚዛው፣ ከመሥተዋት ጋር ሲጋጭና መውጫ- ሲያጣ ያሳያል።… እናም ግጭቱ በጥንዚዛው ሕይወት ጀምሮ፣ ከሽጉጥ አፈሙዝ ወጥቶ ነፍስ እስከበላው የጥፋት አረር ይዘልቃል።
አበራ ወርቁ የሰዓሊነት ጽንስ ይዞ፤ ሀይለማርያም ካሳ ደራሲነቱን ጠንስሶ፣ ባንድ ሀዲድ ሲሄዱ፤ የአበራ ወርቁ ታላቅ ወንድም አባተ ወርቁና እናታቸው ወ/ሮ ባፈና ካግተለተሉት ፍርጎ ጋር ሆነው ትይዩነት ቆመዋል። የሚጋጩትም የሚወራጩትም በየራሳቸው ጎራ ቆመው ነው።
በአንድ በኩል የሰለጠነና በትምህርት የተገራ ትውልድ፣ በሌላ በኩል በዘርና በአጥንት በገዢነት መደብ የተኮፈሰ የጉልተኛው ስርዓት ቀንዶች ፍልሚያ ይዘዋል።
በዕድሜ የሰላሳ ሁለት ዓመቱ ወጣት አበራ ወርቁና ከሃምሳ ዓመት የዘለሉት አቶ ተሰማ ወርቁ የየጎራቸው መሪ ሆነው ግጭቱን ያፋፍማሉ። አንዱ ተልዕኮዬን መወጣት ተሰጥዖዬን አደባባይ ማውጣት አለብኝ - እያለ ከራሱ ሕሊና ጋር ሲፋለም፣ ሌላኛው ሚስት ማግባት፣ መውለድና ዘር ማቆየት፤ ከዚያ ባለፈ በዘርና በአጥንት ክብር ራስን ማማ ላይ ሰቅሎ መኮፈስ የሚል የየራሳቸው፣ የፍልስፍና እሳቤ አላቸው።
ማኅበረ ፖለቲካዊ ዐውድ “The greatest novelists have been so sharply aware of the political and social aspects of their time…” Ann Petry
ታሪኩ የተዋቀረው በከፊል ፊውዳልና ቡርዣ ስርዓት እንደሆነ የሚጠቁሙ ብዙ ምልክቶች አሉ። ይህንንም የምናውቀው ገና ታሪኩ ሲጀምር አካባቢ ብቅ  የሚሉትና…? የሚያንቋሽሹት ባለርስቱ አቶ አባተ ወርቁ ናቸው።
እኒህ ገፀ ባህርይ ባላቸው መሬትና ርስት ብቻ ሳይሆን በወላጅ አባታቸው ፊታውራሪነትና የተጋነነ ገድል በእጅጉ የሚኮፈሱ ናቸው። እምነት አለኝም ብለው አይፍሙም አይጸልዩም የሚሉትን፣ ያጣጥላሉ።
 ገጽ 23 ላይ ለዚህ ዋቢ የሚሆን ሀሳብ አወሳለሁ። የአበራ ወርቁ የሃያ ዓመታት ባልንጀራ ከሆነው ሃይለማርያም ካሣ ጋር አልግባብ ያሉት አቶ አባተ ሀይለማርያም  “ማንነት” በሚል ስለ ውስጥ ግጭት ያወራውን በግርድፍ ወስደው ስለወንድማቸው እንዲህ ብለዋል፡-
“ማንነቱን እንዴት አያውቅም! የጀግናወ ፊታውራሪ ወርቁ ባንት ይርጉ ልጅ ነው። ዘራቸው እንደ ወርቅ የጠራ፣ በለጋስነታቸውም በሃይማኖታቸው ጽኑነትም ሀገር ያወቃቸው ታላቅ ሰው ነበሩ” ይላሉ።
ይህ አንዱ ስለ ማኅበረ ፖለቲካዊ ዐውዱ ማሳያ ሲሆን፣ የአበራ ወርቁ እናት ወይዘሮ ባፈናም ተመሳሳይ እምነትና ፍልስፍና እንዳላቸው የሚያሳይ አጠር ያለ ማስረጃ እንውሰድ።
ከገጽ 59-60 ባሉት ገጾች ልጃቸው ስለሚያገባት ሚስት ያላቸውን አመለካከት ሲያንጸባርቁ፤
“ልጄ፤ አጥንቷ ጥሩ የሆነች ሚስት አግብተህ የልጅ ልጄን ስሜ፣ አያት ተብዬ እንድሞት ብታደርገኝ ምናለበት?” ይላሉ።
አቶ አባተም በተደጋጋሚ መሬት እየሸጡ አምስት ጊዜ ያህል ተሞሽረው በሰርግ ማግባታቸው ባለርስትነታቸውን ያሳያል። ርስትና ጉልት ደግሞ የፊውዳሉ ስርዓት አራማጅ ናቸው። ስርዓቱ  የነገሥታትና የመኳንንት ዘመን እንደነበር ለማሳየት ያህል እነዚህ በቂ ማሳያዎች ይመስሉኛል።… ከዚያ በኋላ የመጣው የወታደራዊው መንግሥት አገዛዝ በአዲሱ ብሔራዊ ዴሞክራሲያዊ አብዮት ፕሮግራም የሚመራ ስለነበር የግል ባለሀብትነትን ይቃወማል፤ በውስጡ በያዘው የባህል አብዮት ፕሮግራም ኋላቀር ባሎችና እምነቶችን ለማፍረስ ይሰራል።
ይሁንና የዚህ ስርዓት ጥንካሬ ወደ መላላት፣ ወደ መፍረክረክና ወደ ማብቃት የደረሰበት አካባቢ መሆኑን በመጽሐፉ የመጨረሻ ገጾች፣ አበራ ወርቁ እስር ቤት ከገባ በኋላ እዚያ የሚወራው ወሬ ይጠቁመና።
ገጽ -59 ላይ እንዲህ ይነበባል፡-
“ሊያምጽ ሲል ተያዘ… ሊያምፁ ሲል ነው ይባላል…ተማሮች ሽብር አንስተዋል የሚሉት ድምጾች ነገሩ ወደ መቋጫውና ማብቂያው እንደደረሰ፣ ክሩ እንደቀጠነ ማየት ያስችላል።
“ከአድማስ ባሻገር” እና “አደፍርስ” የተሰኑት ልቦለዶች። የታተሙት በ1962 ዓ.ም እንደመሆኑ መጠን በጊዜው የነበረውን ማኅበረ ፖለቲካዊ መልክ ይጋራሉ። ተመሳሳይ ሃሳቦች ብቻ ሳይሆን እንቅስቃሴዎች ይዋሰናሉ። ልዩነቱ “አደፍርስ” ጎላና ደመቅ አድርጎ መልሕቁን ሀገሪቱ ላይ በነበረው እንቅስቃሴ ላይ ጥሏል፤ “ከአድማስ ባሻገር” መሬት ሳይነካ በስሱ አየር ላይ ይንቀዋለላል። ለምሳሌ “አደፍርስ” ገጽ 325 ላይ የአደፍርስ መሞት ከተቃውሞ ሰልፍ ጋር የተያያዘ ነበር። ጥቂት አረፍተ ነገሮችን ልዋስ፡-
“መኪና መንገድ የተማሪዎች ሰልፍ፣ ሕጋዊ ያልሆነ መንገድን ይከተላል። ከወታደሮች ጋር ድንጋይ መወራወር ይጀምራሉ። ሰላማዊ ሰው ይመትታል፤ ይቆስላል። እያለ ይቀጥላል። ይህ የግብታዊው አብዮት መፈንጃ ዋዜማ መስተዋት ነው። ችግሩ አብዮቱ ነባራዊ ሁኔታው ለመፈንዳት ቢያጎጠጉጥም ሕሊናዊ ሁኔታው  ገና ጥሬ መሆኑ ነው። ጥሬነቱ ደግሞ አብዮቱን በወታደሩ እጅ ጥሎት ሌላ ጣጣ አምጥቷል።
ሦስቱ የዘመናዊው አማርኛ መጻሕፍት አእማድ፣ ዘመን ተመሳሳይ ስለነበር ፍቅር እስከ መቃብርም ተመሳሳይ መልክ ነበረው። የአብዮቱ ጥርሶች ብቅ ብቅ ብለው ባይታዩም የወተት ጥርስ ለማብቀል የውስጥ ሕመሞች ጉዱ ካሳ በተባው ገጸ ባህሪይ በኩል እንደ እሳት ገሞራ ይንተከተኩ ነበር።
ማኅበረ - ባህላዊ ዐውድ
በመጽሐፉ ውስጥ  በአብዛኛው ሃይማኖታዊ ጠረን ያላው ገጸ ባህርያት የዘመኑን ገዢ መደብ አካሄድ ያሳያሉ። ነባሩ የኢትዮጵያ ስርዓተ መንግስት (የፊውዳሉ ስርዓት) ከመንግስት ጋር ቁርኝት ስለነበረው የገዢው መደብ አባላት ይህንኑ እምነትና ፍልስፍና ያንጻባርቃሉ። በትምህርት ደረጃቸውም ሲመዘኑ ዘመናዊውን ትምህርት ያልቀሰሙ ምናልባትም የሚፈጥሩና የሚጸየፉ አይነት ስለሆኑ አሽሟጣጭ ናቸው።
 ይሁንና አንዳንዶቹ ገፀ ባህርያት ባንድ ወገን ጻድቃንና ፈጣሪን ሲያመልኩና በደባልነት ደግሞ ባህላዊ እምነቶችን ያንጠለጥላሉ። ለምሳሌ የዋናው ገፀ ባህርይ ወላጅ እናት ወይዘሮ ባፈና ብዙ ጊዜ “ተክልዬን” እያሉ ስማቸውን ቢጠሩም በሌላ በኩል ደግሞ ውቃቢ አምላኪ መሆናቸውን መጽሐፉ ይነግረናል።
ገጽ 26 ላይ እንዲህ ይነበባል።
“ከዚያ ሁሉ ጣጣና የራስ ምታት በኋላ የተገዛው በግ ዳለቻ ባለመሆኑ፣ ቤት ከመግባቱ በፊት ወይዘሮ ባፈና “ኧረ የተክልዬ ያለህ! ምን አመጣህብኝ!” በማለት ወዲያውኑ በርካሽ ዋጋ መልሰው ሸጡት። ውቃቢያቸው ጥቁር በግ አይወድም”
እንግዲህ ይህ የሚያሳየን የዘመኑን ማህበረ ባህላዊ ዐውድ ነው።
የዚህ ዓይነቱ ጉራማይሌነት በበዓሉ ግርማ ልቦለድ ብቻ ሳይሆን ዮናስ ታረቀኝ በተተረጎመውና “ባይተዋሩ ንጉሥ” የተሰኘው መጽሐፍ (ገጽ 35-36) ላይ ያስቃኘናል። በኾበርትውልክ የተጻፈው፡- ባህልን በሚመለከት ውጫዊና ቁሳዊ ገጽታውን ስናጤን የአበራ ወርቁ ታላቅ ወንድም አለባበስ ለዘመኑ መልክ ፍንጭ የሚሰጥ ወይም በሚገባ የሚያሳይ ይመስለኛል።
“ከአድማስ ባሻገር” ገጽ 18 ላይ እንዲህ ይነበባል፡-
“የለበሱት ከታች ካኪ ሱሪ፣ ከላይ ጥቁር የሱፍ ኮት ነው። በዚያ ላይ ቀጭን በጥቁር ጥለት የታጠረች ኩታ ደርበዋል።” ይላል። የዚህ ዓይነት አለባበስ የታሪኩን ዘመን (መቼት) የሚያሳይ እንደሆነ ለማወቅ ወደ ኋላ መለስ ብለን የቀደሙ የንጉሠ ነገሥቱን ዘመን መኳንንትና ተርታ ሕዝብ አለባበስ አይተን መመዘን እንችላለን።… መኳንንቱ አንዳንዴ በርኖስ ደርበው ካላየናቸው በቀር በለበሱት ኮት ላይ ኩታ ጣል ማድረጋቸው ግድ ነበር። ይሁንና አሁን ለእኛ ዘመን የዚህ ዓይነቱ አለባበስ፣ በቤተክህነት አገልጋዮች (ካህናት) በስተቀር፣ በተለይ በከተሞች አካባቢ ብዙ አይታዩም። አቶ አባተ ወርቁ ግን የአዲስ አበባ ከተማ ቀብራራ ነዋሪ ነበሩ።
ገፀ ባህርያት፡- (“Fictional characters … frequently seem to be part of the history that lies behind the story as part of our world”)
የታሪኩን ምሰሶ ጨብጣ እንደ ሳምሶን አጠቃላይ ታሪኩን የምትተውነው ሉሊት ታደሰ፣… በበቀል የሰከረች፤ በዓለማዊው ቅንዝር ውስጥ የቀበጠች ናት። ገድሉ በዛብህን የመሰሉ የንዋይ ሎሌዎችን እንፉርጉ አስከትላ የምታንገጫግጭ--- እንደ ጣዖት የምታስወግድና መስዋዕት የምትቀበል አፍሮዳየት ናት።
ውበቷ በደራሲው ሲገለጽ፣ ስልክክ አፍንጫ ያላት፣ ወደ ታች ሲደርስ ወደ ላይ የሚገለበጥ፣ ከንፈሮችዋ ሊፈነዳ የደረሰ  እምቡጥ ጽጌሬዳ የመሰሉ፣ ግንባሯ አጭር፣ ዓይኖቿ የነጠረ ብር የመሰሉ ናቸው። ባለችበት የማኅበረሰብ ደረጃ ልኬት የንግድ ስራ  ኮሌጅ ምሩቅ ናት። ውስጧ ላይ የደደረ ቂም ስላለ ወንዶችን ማንበርከክ ትወዳለች፤ መስዋዕት፤ የወንዶች ልብ ስብራት የባከነ ቀልብና የሚንበረከክ ጉልበት ነው፡፡ ለዚህ ምክንያቷ የእንጀራ አባቷ በወላጅ እናቷ ላይ ያደርስ የነበረው ስቃይ ሲሆን ሌላው አንድ ቀን፣ በአንዱ በማታውቀው ሰው በሃይል መደፈሯ ነው። በዚህም ወንዶች ጥፍር የሌላቸው፣ ቀንድ ያላወጡ አውሬዎች ወይም እንስሳት ሆነው ታዩዋት።
ይህ የልጅነት ቁስል ጠባሳ (Trauma) የዚህን ዓይነት ዓመጽ በውስጧ መትከሉ ለገፀባህርይዋ የባህርይ ቀውስ በቂ ምክንያት ስለሚሆን ጥሩ ተስላለች ብለን እንድንቀበል ያደርገናል።
በመጽሐፉ ውስጥ ከተሳሉት ገጸ ባህርያት የሃይለማርያም ካሳ የስነጽሑፍ ሰው መሆንና የዚያ ስሜት ነፀብራቅ ሆነው ለነገሮች ያለው ደንታ ቢስነት ገጸባህርይውን እንድንቀበለው የሚያደርግ ሌላኛው ጥሩ ምክንያት ነው፡፤
በተጨማሪ የአበራ ወርቁ ስሜታዊነትና ስስነት፣ የኪነጥበብ ሰውነት ድንኳን ውስጥ ባይከተት ኖሮ ለመቀበል ይከብድ ነበር። ይሁንና ከሰዎች በሰማው ወሬ ወዲያው በቅናት ተቅበዝብዞና ቱግ ብሎ እርምጃ ለመውሰድ ወደ ገጠር መናፈሻ ሆቴል መብረሩን “ሊያደርገው ይችላል!” ብለን እንድንቀበል የሚያደርገን ይኸው “የጥበብ ሰው ስስ ነው” የሚለው የቆየና አሁንም የሚታመንበት ባህርይ ነው።
እንዲያውም በቻርልስ ላምብና በመጠኑም ቢሆን በጆርጅ በርናንድ ሾው እና መሰሎቻቸው እየተገፉ ተቀባይነት አጣ አንጂ። “The exercise of the imagination is a kind of insanity” ተብሎ “ለስነጽሁፍ ባይተዋር ከሆነው ሰው ይልቅ  ወፈፌ ናቸው” በሚል የማርያም  መንገድ ይሰጣቸው ነበር።… ስለዚህ ሃይለማርያምም በሁኔታው ሁሉ ፈንገጥ ቢል ለምን ይሆናል? ለማለት ይከብድ ይመስለኛል።
ገፀ ባህርት በዘመናቸው እንደበቀሉ እፀዋት የኖሩበትን ማህበረሰብ መልክ እንደሚያንፀባርቁ የሚያሳየው የአቶ አባተ  ወርቁና የወይዘሮ ባፈና አስተሳሰብና ገቢር፣ የዕለት ተዕለት ኑሮና ፍልስፍና፤ የነተሰማ ደጀኔ የወሬ ነፋስነት፣ የእነገድሉ በዛብህ አሸርጋጅነት ዘመኑንና ወቅቱን የመሰለ ቀለም መፍጠሩ ለገጸባህርይ አሳሳሉ ተዐማኒነት ቦታ የሚሰጥ ይመስላል።
የአቶ አባተና የወይዘሮ ባፈና ለአበራ ሰርግ ዕዳ ውስጥ መዘፈቅ፣ መጨነቅና መጠበብ የአንድ ገፀባህሪ መልክ ከሆነው ማኅበረሰብ የሚወስደውን ማንነት ለማሳየት ጠቃሚ ገጽታው ስለሆነ፣ እነዚህ ትስስሮች መጽሐፉ ውስጥ ለተፈጠረው ታሪክና ለታሪኩ የማይጎረብጥ ፍሰት አስተዋጽኦ ይኖረዋል። ምናልባትም ከማህበረሰቡ አካባቢና ዐውድ ባፈነገጠ ሁኔታ ሲሄድ የሚሰማኝ ምቾት ማጣት እንዲቀንስ ያደርጋል ባይ ነኝ።
የመፅሐፉ ታሪክና ተዓማኒነት
“Literary realism is that attempts to represent subject matter truthfully, avoiding speculative fiction and supernatural elements.”
ታሪኩ እውነት ላይ የተመሰረተና የገሃዱ ዓለም ነፀብራቅ በመሆኑ የምናያቸው ነገሮች በታሪኩ ውስጥ ያሉት ድርጊቶችና ግጭቶች፣ ስኬቶች ውድቀቶች በምክንያትነት የተሰናሰሉና አሳማኝ ምክንያቶች ያሏቸው ሊሆኑ ይገባል።
የበዓሉ ግርማ “ከአድማስ ባሻገር” ከምገምተውና ከዚህ በፊት በተደጋጋሚ ሳነብበነው ባላየሁት ሁኔታ የተዓማኒነት ጥያቄዎች ያየሁበት መጽሐፍ ነው። እመለስበታለሁ።

Read 1816 times