Sunday, 14 November 2021 00:00

ሆ ብዬ መጣለሁ!

Written by  ሌሊሳ ግርማ
Rate this item
(0 votes)

  ማሳያ አንድ
በሞላ ባስ ውስጥ ሆነን እየሄድን ነው። የወንበሮቹን ብረት በግራ እና በቀኝ እጄ ጨብጬ በጀርባዬ የሚገፋኝን ሰው ለመቋቋም እግሬን አስፍቼ ቆሜያለሁ፤ ወደ ውጪ እየተመለከትኩ ነው፡፡ ባሱ ዳገት እየወጣ ሲጎተት አንድ ሰው ከመንደር ውስጥ ወጥቶ በነብስ አውጪኝ ሩጫ የባሱን ፍጥነት ተስተካከለው፡፡ አሯሯጡ ለባሱ እንዳልሆነ ግልፅ ሆኖልኛል፡፡ አባራሪዎቹ ሶስት ወጣቶች ወደ እይታዬ ከመድረሳቸው አስቀድሞ የሚወረውሩት ድንጋይ እሩምታ የባሱን አካል ማንጓጓት ጀምሯል፡፡
ወጣቶቹ ተከሰቱ፡፡ እየሮጡ ድንጋይ ይለቅማሉ፡፡ እየሮጡ ይወነጭፋሉ፡፡ ለነብሱ የሚሮጠው ሰው ወጣት አይደለም። እንዲያውም የመከበሪያ እድሜ ላይ የደረሰ ነው፡፡ ፀዳ ብሎ ነው የለበሰው፡፡ እንደዛ የሚያክል ሰውነት ይዞ ከባሱ ፍጥነት እኩል የምታስሮጠው ነብስ፣ እድሜ ደረጃ እንደሌላት ታስታውቃለች፡፡ ነብስ አካልን በአስፈላጊው ፍጥነት ማስሮጥ ይችላል፤ ከጭንቀት እንዲያስጥለው ከፈለገ፡፡
የሚወረወረው ድንጋይ ከባሱ ድምፅ በልጦ በሰውየው አጠገብ እያፏጨ ሲያልፍ ይሰማኛል፡፡ ቆሜ እየተጓዝኩ ባለሁበት ቦታዬ፡፡ የፊልም ትዕይንትን የምቀርፅ ሲመስለኝ ይሰማኛል፡፡ ሯጩም አባራሪዎቹም ከመስታወቱ ስር ሆነው ይታዩኛል፡፡ ወጣቶቹ የእግር አሳሳባቸው ያስፈራል፡፡ እየደረሱበት በመጡት መጠን እያነሱ የሚወረውሩት ድንጋይ ኢላማውን ማግኘት ጀመረ፡፡ ኢላማው የሰውየው ጭንቅላት ስለመሆኑ ምንም ጥርጥር የለኝም። ድንጋይ ጭንቅላትን ሲመታ የሚወጣው ድምፅ ምንጣፍ ተሰቅሎ በመጥረጊያ እንጨት ሲነረት ከሚወጣው ድምፅ ትንሽ ከፍ … የከረንቦላ ድንጋዮች ሲጋጩ ከሚሰማው ድምፅ ትንሽ ዝቅ ይላል። ግን እንደ ምንጣፍ የሰውም ጭንቅላት ሲፈረከስ የሚበንን ነገር አለው። ሲፈረከስ ነጭ ነገር ከፀጉሩ ውስጥ ብቅ ይልና … ተመልሶ በፀጉር ይሸፈናል፡፡
ሰውየው ሲመታ ያጎነብስና.. በሁለት እጁ መሬቱን ተደግፎ፣ ተንደፋድፎ ባሱን ተንተርሶ ወደ ሩጫው ይመለሳል። ባሱ ላይ ለመንጠልጠልም የሚሞክር ይመስላል፤ በእጁ መስታወቱን ይቧጥጣል። ድንጋዩ ባሱን ከሰውየው ሳይነጥል ያንጓጓዋል፤ የእኔንም ነብስ አንድ ላይ፡፡ ሹፌሩ ፍሬኑን ያዘው፤ ያለ ፌርማታው፡፡ በሩን ግን አልከፈተም፡፡ ወጣቶቹ ድንጋያቸውን አስቀድመው ሊደርሱለት ሲል… ባሱን የሙጥኝ ብሎ የነበረው ነብስ የት እንደደረሰ ሳይታወቅ ድንገት ተሰወረብኝ፡፡ የት ገባ ብዬ ለመጠየቅ ጊዜ ሳላገኝ … የገባበት አሳዳጆቹ ተከትለው ሲገቡ አየሁዋቸው፡፡ ባሱ ጎማ ስር፡፡
ግን ከባሱ ጎማ ስር ስበው ያወጡት ፍጥረት  ሲሮጥ የነበረውን ሰውዬ አይመስልም፡፡ ልብሱም ተቦጫጭቋል፤ በደም ተነክሯል። ፀንቶ መቆም አይችልም፡፡ መከላከልም የሚችል አይመስልም፡፡ ከሶስቱ አንደኛው በጭካኔው ይበረታል፡፡ ሁለቱ ወደ ህሊናቸው የተመለሱ ይመስል፣ ማምለጥ ፈልገዋል፡፡ ሁለቱ፣ አንደኛውን በግድ እየገፉ ከቆመበት የሰውዬው ጭንቅላት ላይ አወረዱት፡፡ አሁን ደግሞ ሶስቱ በተራቸው ወደታች ቁልቁለቱን መሮጥ ጀመሩ፡፡ አሯሯጣቸው እንደ ሰውዬው አይነት አልነበረም፡፡ እንደ አባራሪ እልህ የተሞላበትም፣ እንደ ወንጀለኛ ፍርሀት የነገሰበትም፣ እንደ ስፖርተኛ የተዝናናም፣ እንደ አረፈደ ሰው የቸኮለም አይደለም። እየሮጡ በተለያየ አቅጣጫ ተበታተኑ፡፡ የባሱ ነጂ ወደኋላ በሚያሳየው መስታወት ሲከታተል የቆየውን እኔ ደግሞ በጎን መስታወት ተከታትያለሁ፡፡ የባሱ ነጂ በሩን ከፍቶ ወረደ… ትኬት ቆራጭዋም መስታወቷን አንሸራተተች፡፡ ወደ ወደቀው ሰውዬ ቀስ እያሉ የሚጠጉ ሰዎችም በረከቱ፡፡ በቂ ሰው ሲሰበሰብ … ፖሊስም መድረሱ አይቀርም። የባሱ ሹፌር ሰውየውን እንዳልገጨ ሲያረጋግጥ ወደ ስራ ገበታው ተመልሶ … ማርሹን በቦታው አስገባ፡፡ መኪናውም እኔን ይዞ ወደምሄድበት ተንቀሳቀሰ፡፡
ማሳያ ሁለት
እዛ ሜዳ በምንውልበት ዘመን ከተማው ውስጥ የነበረው ረብሻ በጋዜጣ ካልሆነ በውን ገጥሞን አያውቅም ነበር፡፡ እኛ በ97 ምርጫም ሆነ ከዛ በተከታይ ባሉት ዓመታት መንፈሳዊ ማሰላሰል ውስጥ ተዘፍቀን ጫታችንን ከሜዳው ሰላም ጋር አብረን የምናመነዥግበት የጥሞና ጊዜ ነበር፡፡
ከእነዚሀ ወቅቶች በአንዱ፣ ቀትር አካባቢ፣ አንድ ወጣት እና አንድ ሰማያዊ ዥንጉርጉር የለበሰ ፌዴራል ሲተናነቁ አየን፡፡ የተናነቁት በእኩል አኳኋን ቢሆንም ፌዴራሉ ወጣቱን እግሩን እያነሳ ሊመታው ይሞክራል፡፡ ቅልጥሙንም ከታች ይመታዋል፡፡ በጉልበት ቢመጣጠኑም ታክቲክ ግን ከመንግስት ጋር ነበረች፡፡ ግን መንግስት እና ህዝብ ብሎ ሁለቱን መወከል አደገኛ ሊሆን ይችላል፡፡ ብቻ ተናንቀው ለመጣጣል ሲሞክሩ ትንሽ ቆዩ፡፡ ወጣቱ ልጅ አንቆ ከመያዝ በስተቀር የመምታት ምንም ሙከራ አላደረገም፡፡ እጅ የመስጠትም እንደዚሁ፡፡ በዚህ መሀል ሁለተኛው ፌዴራል መሳሪያውን ደግኖ ደረሰ፡፡ ሊተኩስ መስሎን እኛ ካለንበት ርቀት ጆሯችንን ጉልበታችን መሀል ቀበርን፡፡ ግን አልተኮሰም፡፡ መሳሪያው ገልብጦ ወጣቱን ከተጣበቀበት ባልደረባው ላይ እየጨፈጨፈ ፈቅፍቆ አወረደው፡፡ ከወረደ በኋላ ሁሉም ቀላል ነበር፡፡
ብዙ እግሮች በአንድ የተንበረከከው ወጣት ላይ ወረዱ፡፡ እግር ሰደፍ … ሰደፍ … እግር፡፡ … የዱላ ድምፅ … ትንሽ ቆይቶ እንደ ገደል ማሚቶ ያስተጋባል፡፡ ሁሌ አንድ ነገር በሀይል ሲመታ እንደ ጢስ መሳይ ቡናኝ ነገር አለ፡፡ የሚመታው ወጣት ትኩስ እንደሆነ ያስታውቃል፡፡ መልኩ ባይታይም ፊቱ ያብረቀርቃል፡፡ በእጁ የሚመጣበትን ምት መከላከል ሲያቅተው በተንበረከከበት ጭንቅላቱን በእጆቹ ከልሎ ተደፋ፡፡ ሰደፉን የሚስተካከል ዱላ ከየት የመጀመሪያው ፌዴራል እንዳገኘ አይታወቅም፡፡ እኛ  በማምለጥ እና አድፍጦ በመቀመጥ መሀል ግራ ተጋብተናል፡፡ የምናየው ዱላ ወደኛ ቢዞርስ? የሚል ፍርሀት ትዕይንቱን ከመታዘባችን ጋር ቅፅበቷ ላይ ነግሷል፡፡
ከብቶቹ ሜዳው ላይ እየጋጡ ነው። ዱላውን እንደኛ ልብ አላሉትም፡፡ ሰው እንስሳን ሲመታ እንደማይሰማው እነሱም ሰው ሲመታ አይሰማቸውም፡፡ በተለይ ሰው ሰውን ሲመታ፡፡ ድንጋጤያችን አልፎ እስክንረጋጋ … ተመልሰን ወሬ እስክንጀምር ድረስ ልጁ መቀጥቀጡን ቀጥሏል። መቺዎቹም መስጠት፣ ተመቺውም መቀበል አላቃተውም፡፡ እኛ ከሩቅ ሆነን ደከመን። … ለእነሱ ደከመን፡፡ እኛ ድሮውንም ደካማ ነን፤ ቶሎ ይደክመናል። ከብቶቹ ማመንዠግ ባይደክማቸው ራሱ እኛ ለእነሱ ይደክመናል፡፡
እኛ ደክሞን ወደ ሌላ ጨዋታ ሄድን፡፡… ከፊት ለፊታችን የምናየውን የመሰለ የዱላ ታሪክ ላይ ተሞክሯችንን መቀያየር ጀመርን፡፡ ብዙ አወራን፡፡ አውርተን ጨርሰን ወደ ግጥም ፅሁፋችን፣ ወደ ጥሞና እና ማሰላሰል ሄድን፡፡ ወጣቱ እየተደበደበ ነው፡፡ ከመደፋት ወደ መጠቅለል ቅርፁን ቀይሯል፡፡ ቀጪዎቹ ዱላና ሰደፋቸውን ከአንድ እጅ ወደ ሌላ ያዘዋውራሉ፡፡ የደረታቸው የትንፋሽ እንቅስቃሴ ከላሞቹ ቀንድ በላይ ከፍ፣ ከበጎቹ ላት በታች ዝቅ የሚል እና የሚደጋገም ይመስላል፡፡
ያን ቀን ስለ ከዋክብቶቹ ግርማ ሞገስ የሚገልፅ ግጥም ፅፌ ከሜዳው ተነሳሁ፡፡ ግጥሙን በመጻፍ ላይ ሳለሁ … ፌዴራሎቹ ወጣቱን ከተጠቀለለበት ፈትተው፣ በሰደፉ እየደቀደቁ ሲነዱት በጨረፍታ አይቼ እንደነበር ትዝ ይለኛል፡፡ ታዲያ ሲነዱት ትከሻውን ሰፋ አድርጎ በኩራ ከተሞላ አረማመድ አረማመድ ለመጓዝ ሲሞክር ይታወሰኛል፡፡ ለከዋክብቱ በግጥሜ ያወረስኳቸውን ግርማ የተዋስኩት ከወጣቱ መሆኑን ለራሴ አሁንም ቢሆን አልደብቅም፡፡ የወጣቱን ኩራት ለመቀነስ በካልቾ መንቁር እግረ እግሩን እየተከተሉ ሲተገትጉት… ከዋክብት እና ጨለማ ያላቸው ንፅፅርን ለመስራት አግዞኛል። ግን በስተመጨረሻ ኮከብ እና ጨለማ በሜዳው ላይ ወርደው ካደረጉት ፉክክር ያሸነፈው ማን እንደሆነ አልተዳኘልኝም፡፡ ያልገባኝ የእኔ ስፍራ ነው፡፡ ተመልካች ብርሃን ነው ወይንስ ጨለማ? ተናጋሪ እሆን እንጂ ዱለኛ አይደለሁም፡፡ ለነገሩ ብርሀን እና ጨለማ ተመልካች ወይ አድናቂ እና ነቃፊ ከሌላቸው ብቻቸውን ምንም ናቸው፡፡ ለእኔ ብለው በጠራራ ጸሀይ … ኮከብ እና ጨለማ በሜዳዬ ላይ ወርደው ትዕይንት አስጨብጠውኝ ሄዱ፡፡
ማሳያ ሶስት
በዛው ቀን፣ ወጣቱ እና ፖሊሶቹ በተያያዙበት ወቅት፣ ደክሞኝ በነበረበት ቅፅበት ከተለዋወጥናቸው ተሞክሮዎች መሀል የአንዱ ጀዝባ ወሬ አሁን ድረስ ትዝ ይለኛል፡፡ ያኔ ይህ ጀዝባ ወዳጃችን ሥራ ላይ ያልነበረበት ወቅት ነው፡፡ አሁን ስራው ወደ በባህር ማዶ አድርጓል፡፡ ሁሉም የሥራ ሁኔታ አልመች እያለው በመላው ኢትዮጵያ ተንከራቷል፡፡
አንዱ ስራው ውሀን በገጠር በሚያስፋፋ መንግስታዊ ያልሆነ ድርጅት ውስጥ ሹፌር ሆኖ መስራት ነበር፡፡ መሄድ መሄድ ሲለው ሹፌር ይሆናል፡፡ መቆም መቆም ሲለው ይጀዝባል፡፡ ሹፌር ሆኖ ወደ ሰሜን ሸዋ መስመር (ትክክለኛ ቦታው አሁን ተዘንግቶኛል) በሚሰራበት ወቅት በአንድ የገበሬዎች መንደር ሲያልፍ … ከእርሻቸው ወጥተው አውራ ጎዳናውን መሀል የሚጓተቱ ሰዎች ይገጥሙታል፡፡ ፍጥነቱን አብርዶ መሪውን አጠምዝዞ ከማለፉ በፊት የተመለክተውን ለእኛ አጫወተን። እሱ ሲያጫውተን ሜዳው ላይ ደግሞ ፌደራሎቹ ወጣቱን እያጫወቱት ወይንም እየተጫወቱበት ነበር፡፡  እየተመለከትን፣ የትመለክተውን እንዲህ ብሎ ነበር ያኔ የነገርን፡፡
 ሁለቱ ሰዎች የሚጓተቱት በማጭድ ተያይዘው ነው፡፡ …አንደኛው ገበሬ በሌላኛው ገበሬ ጀርባ ላይ ማጭዱን ሰክቷል፡፡… ሌላው ደግሞ በሰኪው አንገት ላይ የራሱን ማጭድ ተክሏል፡፡… የሰኩትን አውጥተው እንደገና ለመሰካት ሲጥሩ ማጭዱ አልወጣ ብሎ … ክርክሩ የገባበትን ስጋ እየጎተተ አስቸግሮ ነው… ከእርሻ ወደ አውራ ጎዳና ተያይዘው የወጡት፡፡ … ገላጋይ በአካባቢው አልነበረም። መኪና ይዞ ያልፍ ከነበረው ጀዝባ ውጪ ሌላ ሰው በቦታው የለም፡፡ ጀዝባው …ከማለፉ በፊት ቆም አድርጎ ተመለከታቸው። ሊገላግል እንደማይችል ገብቶታል፡፡ ሽጉጥ ይዞ ለመስጠም የሚንፈራፈርን ነፍስ ዋና ቢቻል እንኳን ማትረፍ ያስፈራል፡፡ የሰዎቹን ሁኔታ ሲገልፀው (አገላለጹ  በዛው ቅፅበት ከሜዳው ባሻገር በአለፈረ ገዳም እየታዘብን ካለነው የተደባዳቢው ልጅ ስቃይም  የሚሰቅቅ ነበር፡፡ ጆሮ ከአይን የበለጠ የማሰቀቅ አቅም እንዳለው ያኔ ሲገባኝ ተሰምቶኛል፡፡)
‹‹ማጭዱ በተሰካበት ሁለቱም አቅጣጫ ደም ወደ ላይ እንደተሰበረ ቧንቧ ፊን እያለ ይወጣል፡፡ ይወጣል … መኪናዬን እንዳይነኩ ለማራቅ እየተዘጋጀሁ … ተመለከትኳቸው። በማጭዳቸው እንደተቆላለፉት … ባጎረጠ አይናቸውም እርስ በርስ ተናንቀዋል፡፡ ሁለቱም ቅንጭርር ያሉ… ቁምጣ የለበሱ አጫጭር ሰዎች ናቸው፡፡ ማን መጀመሪያ እንደሰነዘረ … ማን አፀፋ እንደመለሰ አይታወቅም … ሁለቱም በእልህ እኩያ ናቸው፡፡  አንደኛው ከሌላኛው ቀድሞ መሞት ብቻ ነው ነውሩ እና ውርደቱ። ቀድሞ መግደል ደግሞ ኩራታቸው፡፡ ኩራታቸው እስኪያዩ ድረስ አይሞቱም … አይደክሙም፡፡ ኩራታቸውን አይተው እንዳይሞቱ ያግዳቸው የማጭዱ አፈጣጠር ነው፡፡ ማጭዱ ቆልማማ ባይሆን እና ክርክር ባይኖረው … አንዳቸው ድል ይቀዳጁ ነበር። ለጥል የመረጡት መሳሪያ ነው ድሮኑ … ጥላቸውን አዝጋሚ፣ ሞታቸውን ሩቅ ያደረገው›› ብሎ ነበር ትዝታውን የተረከልን።
ገበሬዎቹ እንደተያያዙ ትቷቸው በቅርብ ወደሚገኘው ደሳሳ ፖሊስ ጣቢያ በፍጥነት አመራ፡፡ ያገኘውን ፖሊስ ስለ ሁኔታው እየጮኸ ነገረው፡፡ ፖሊሱ ብዙም የደነገጠ አይመስልም፡፡ መኪና አለመኖሩን ነግሮት … የእሱን መኪና ለፖሊስ አገልግሎት የሚያውል ከሆነ … ተመልሰው ጉዳዩን እልባት መስጠት እንደሚችሉ አስረዳው። ወዳጃችን አልተስማማም፡፡ ጥቆማ ከመስጠት ባለፈ መሳሪያ የያዘ በማይጫንበት የኤን ጂ ኦ መኪና … የፖሊስ እና አምቡላንስን የስራ ድርሻ ለማከናወን እንደማይፈቀድለት ገልፆ … ወደ ስራው አቅጣጫ ተፈተለከ። ገበሬዎቹ ምን እንዳጋጠማቸው ስራውን አጠናቆ በሚመለስበት ወቅት፣ መንገድ ላይ ሰው አቁሞ መጠየቅ እንኳን አስፈራው፡፡ እንዲያውም ስመለስ ገበሬዎቹ በቀድሞው ስፍራ… እንደ ቁስላም ፈረስ በዝንብ ተወርረው… በማጭድ እንደተቆላለፉ ቆመው ቢጠብቁኝስ? እያለ እየሰጋ ቦታው ላ ሲደርስ ሽው ብሎ አለፈው፡፡ ምናልባት ሽው ብሎ ሲያፍ ከመንገዱ ፈቅ ብለው በቆሙበት… ቁስላቸው ላይ ያረፈውን ዝንብ የሽውታው ንፋስ ሊያባርርላቸው ይችል ይሆናል፡፡
‹‹ሁሌ ግን አኳኋናቸው ትዝ ይለኛል›› ብሎኝ ነበር በዛ ደባሪ ቀን … ያንን ደባሪ ትዕይንት እየተመለከትን በተቀመጥንበት። ‹‹ሁሌ ማጭዳቸውን ከሰኩበት ለማውጣት እየሞከሩ … ሲያቃስቱ በህልሜ ይመጡብኛል፡፡ ምናልባት ሰው አግኝቷቸው አላቋቸው በህይወት ሊተርፉ ይችሉ ይሆናል፡፡ ከተረፉ፤ አብረው ቢተርፉ፣ ከሞቱ ደግሞ አብረው ቢሞቱ ይሻላል፡፡ ካልሆነ ቂም በቀል ..እንደያዙ  ከሞት በኃላም በደርሱበት ገሃነም ሆነ ገነት አይላቀቁም፡፡ ደም ለመመለስ  እንዳይጠባበቁ… አብረው ቢሞቱ ይሻላል፡፡ ደግሞ ልጆቻቸውም ደም መላሽ ለመሆን በአባቶቻቸው እግር ሊተኩ ይችላሉ፡፡
… እና አስቡት እስቲ? እኔ ስራ ብድጋሚ ጀምሬ… በዛ መንገድ ሳልፍ… ከዓመታት በኋላ የእነሱ ልጆች እዛው መንገድ ላይ በአዲስ ጉልበት እና በአዲስ ማጭድ … ድሮ የተከሰተውን ነገር እየደገሙ ቢገጥሙኝ?›› ብሎን አማተብና ወደ ጫቱ ተመለሰ፡፡ ጫቱን እየቀመለ .. አልፎ አልፎ ከሜዳው ባሻገር የሚደበደበውን ልጅ ቀና እያለ ሲመለከት ትዝ ይለኛል፡፡
ማሳያ አራት
ይሄኛው ትዝታ ድግሞ በምሽት ቦሌ  አካባቢ በእግር ሳዘግም የገጠመኝ ነው፡፡ መንገዱ ጥግ ከቆመች መኪና ውስጥ አንዲት ሴት ቦርሳዋን አንጠልጥላ፣ በሩን ክፍት ጥላ ስትንደረደር ችግር እንዳለ  ገብቶኛል፡፡ ወንድየው ከመኪናው ወጥቶ መዞር ከብዶት ይሁን ቸኩሎ ከመሪው ወንበር በጎን ተስቦ እሷ በወጣችበት በር እየዳኸ ወጣ፡፡ ሳትርቅ ደረሰባት፤ በጠረባ ሴት ይመታል ወይንስ አይመታም? ብሎ ለመጠየቅ እንኳን ህሊና የሚሰራበትን ያህል ክፍተት ያሻል፡፡ መሬት ከመውደቋ በፊት አየር ላይ ሁሉም ነገሯ ሲራገፍ ቆጠርኩ፡፡ ጫማዋ፣ ቦርሳዋ ውስጥ ያለው ደብተር፣ መስታወት፣ ሊፕስቲክ … (ሳምሰንግ ጋላክሲ) … የተራገፈው ብዙ ነው። ለመውደቅ ብዙ ጊዜ ወሰደባት፡፡ ጠረባ፣ በሚያውቅ ሰው ሲከወን የመንሳፈፊያው ቆይታ ዘለግ ይላል፡፡ ከአመታቱ ብርታት የተነሳ… ስትወድቅ ቀሚሷ የት እንደገባ አላወቅኩም፡፡ በጠረባ መትቶ የሴቶችን ፓንት ማውለቅ እንደሚቻል አላውቅም ነበር፡፡ መሬት ከማረፏ በአካባቢው የነበሩ ሰዎች … ብዙ ሆነው እሱን ማረፊያ አሳጡት። አንዱ በቡጢ፣ ሌላው በቴስታ … ሚስቱን ከሰደደበት ርቀት በላይ የመላክ አቅም ያላቸው  በየሰፈሩ አሉ፡፡ የእግዜር ፍርድ ሰኮንድ በማይሞላ ርቀት አጸፋው ይመለሳል ብዬ ከዚህ ቀደም አላሰብም ነበር፡፡
‹‹አንተ የሴት ልጅ … ሆነህ ሴት … ት .. መታለህ … ት … መታለህ፡፡ እ --- ናት --- እ … እ … እ ናትን .!››
መጀመሪያ በጠረባ የተመታችው ልጅ መሬት በተዘረረችበት ቦይፍሬንዷ … ‹‹ወይኔ አይኔ ፈሰሰ›› የሚል ጩኀት አሰማ። ያለ ጫማዋ እና ከተሰወረበት ያልተገኘው ቀሚሷ … በጠረባው ምክንያት የደርሰብት ያልታወቀው የውስጥ ሱሪዋ ጉዳይ ሳይገዳት … በምን ምትሀት እንደደረሰችለት አይታወቅም፡፡ በወደቀበት ላዩ ላይ ተደረበች። ዱላው እሷ ላይ አረፈ፡፡ አንስተው ወደዛ ለማድረግ ሲሞክሩ ጉልበቷን አልቻሉትም፡፡ በቦይፍሬንዷ የአካል መጠን ልክ የራሷን ትንሽ ሰውነት ለጥጣ ሙሉ ከለላ ሰጠችው፡፡
በከለላው ምክንያት ዱላው ቆመ፡፡ ዱላው ሲቆም … ቦይፍሬንድየው የከለለችውን ገላ እንደሚያውቅበት ከላዩ ላይ ድንገት ወረወራትና ወደ መኪናው ተፈተለከ፡፡ በወጣበት በር ዳይቭ ገብቶ ሞተሩን አስነሳ። አሰቃዮቹ ሳይደርሱበት መኪናዋን እንደ አውሮፕላን ወደ ሰማይ ተኮሳት፡፡ ተወርውሮ የገባበት በር በመኪናዋ ፍጥነት በራሱ ሃይል ተመልሶ ተዘጋ፡፡
የእግዜር የቅጣት እጆች ከመኪናው ኋላ ወይ ስር ትንሽ ከሮጡ በኋላ ተስፋ ቆርጠው ቆሙ፡፡ ታርጋውን ለመያዝ አልሞከሩም። ልጅቱን ከወደቀችበት አነሷት፡፡ … ጠፍቶ የነበረው ቀሚሷ ወገቧ አካባቢ ተሸብሽቦ ተገኘ፡፡ በእጇ ዝቅ አደረገችው፡፡ ከቀሚሷ በኃላ… ቦታውን ስቶ የነበርውን ፓንቷን ከፍ አድርጋ ታጠቀች፡፡ ሰዎች ለቅመው የሰጧትን እቃ በቦርሳዋ ከተተች፡፡ አይኗ ግን ልጁ ወደከነፈበት አቅጣጫ ተሰክቶ ቀርቷል፡፡ የራሷን ጉዳት ሳይሆን የእሱን ነው እያዳመጠች ያለችው፡፡ ቁጢጥ ብላ ማልቀስ ጀመረች፡፡ ‹‹ጌትዬ የኔ ፍቅር … ይቅር በለኝ… I didn’t mean for this to happen›› ብዙ አለቀሰች፡፡ የለቅሶዋን መልዕክት ሲሰሙ በዙሪያዋ ሲያፅናኗት የነበሩት ሁሉ ‹‹ይበልሽ … bitch›› እያሉ ተዘባብተው ሄዱ፡፡ ሲሄዱላት የሚበቃትን ያህል አልቅሳ ስትጨርስ … በተሰበረ ስልኳ ደጋግማ መደወል ጀመረች፡፡ ጌትዬ ስልኩን አያነሳም፡፡ ጭንቅላቷን በእጇ ቀብራ ማልቀሷን ጀመረች፡፡ ጌትዬ ስልኩን አያነሳም። ጭንቅላቷን በእጇ ቀብራ ማልቀሷን ቀጠለች፡፡
ማስረጃ
አራቱን ማሳያዎች ከገለፅኩ በኋላ በውስጤ ጥያቄ ተጫረብኝ፡፡ ምንድነው የዚህ ሁሉ ጭካኔ ትርጉም? የሚል ጥያቄ። ነገሮቹ በተገለፁበት ሁኔታ ተከስተዋል። ግን ምንም የሚገልፁት ነገር የላቸውም፡፡ አለም የከፍተኛ ጭካኔ መድረክ መሆኗም ከማረጋገጥ በስተቀር፡፡ ጭካኔ እንደ ጭካኔነቱ … ጉልበተኛም እንደ ጉልበቱ ይዘልቃል ብሎ ተስፋ ራሴም ለመቁረጥ አንባቢንም ከማስቆረጥ ውጭ ትርጉም የለውም፡፡ ስለዚህ ለራሴም ለአንባቢም … ለፍትህ ፅንሰ ሀሳብ ስልም ሌላ መግለጫ መጨመር አሰኘኝ። ነሸጠኝ፡፡ አምስኛ ታሪክ ያስፈልጋል፡፡ የጎደፈውን የሚያነፃ … ንፁህ የሆነ መስሎን የነበረውን ደግሞ የሚያጎድፍ። ሚዛን የሚያስተካክል አምስተኛ ታሪክ ያስፈልጋል። ስለሚያስፈልግም እነሆ ፃፍኩት፡፡
አምስተኛ ማሳያ
ሜዳ ላይ ከአስር ዓመታት በፊት የተከሰተውን ያየነው አራት ጓደኛሞች … ከአስር ዓመት በኋላ ተገናኘን፡፡ እንደ ከአስር ዓመት በፊቱ አሁን ሁላችንም በማህበረሰቡ ውስጥ የምንሸከመውን ሃላፊነት ‹‹ስራ›› በሚል ስያሜ አግኝተን … ያገኘነውንም ተቀብለን መኖር ጀምረናል፡፡ እንደ ድሮው በየቀኑ ሲያሰላስሉ መዋል እንደማያዋጣ የተማርነው ተምረንም የተማርነው ሊዘልቀን ያልቻልነው ማሰላሰሉን እና ከማሰላሰሉ ተርፎ የምንከትበውን ፅሁፍ አጠንክረን ይዘን ጸሐፊ ሆነናል፡፡ ጸሐፊ ከሆኑት መሀል አንደኛው እኔ ነኝ (ይሄንን ታሪክ እየዘከርኩ ያለሁት) ሌላኛው ደጀኔ ነው፡፡ የተቀሩት ሁለቱ ወደ ሌላ የሥራ ዘርፍ ቁርጣቸውን አውቀው ሄደዋል፡፡ አንደኛው መምህር ሆኗል፡፡ ሌላኛው ግን ስራውን በውጭ አገር አድርጓል፡፡
ከአስር ዓመታት በኋላ መልሶ ያገናኘን ጉዳይ ውጭ ሀገር የቆየው ወዳጃችን መመለስ ነበር፡፡ መመለሱ … ያልሄድነውንም አጠራርቶ አስተሳሰረን፡፡
መተሳሰሩ ከጫት ሰዓት ጀምሮ እስከ እኩለ ሌሊት በጭፈራ ቤቶች እስከ ማምሸትም ይዘልቃል፡፡ ስፖንሰሩ ማን እንደሆነ ለሁላችንም ግልፅ ነው፡፡ እንደዛ ከመሰሉት ምሽቶች በአንዱ ላይ … በወሬ መሀል ስለ ጭካኔ ታሪኮች በድጋሚ አነሳን … ያነሳንበት ምክንያት በወቅቱ በነበርንበት ቤት ውስጥ ያልተጠበቀ አምባጓሮ ከሆነ አቅጣጫ በመቀስቀሱ ምክንያት ነበር፡፡ አምባጓሮ መቀስቀሱን ከማወቃችን በፊት ክፍሉ ውስጥ የነበረው አየር በቅፅበት በቢራ ጠርሙስ ተሞላ፡፡ ሁለቱ ጸሐፊዎች በአንድ አቅጣጫ ተሰወርን፡፡ እኔ እና ደጀኔ ጭንቅላታችንን በሁለት እጃችን ከልለን ተከታትለን ያመራነው ወደ ሽንት ቤቱ ነው፡፡ ሽንት ቤቱ አስቀድሞ በገቡ ሰዎች ተሞልቷል፡፡ ቢሆንም … እኛም ተጨመርን። ሌላ እኛን የመሰለ ሰው እንዳይመጣ የሽንት ቤቱን በር ገብተን ሸጎርነው፡፡ ፀጥ ብለን ጠበቅን፡፡ ከተወሰነ ቆይታ በኋላ ጋብ ማለቱን ለማረጋገጥ አንገታችንን አስቀድመን ወጣን፡፡
እንደዛ በሰው ጉንዳን ተጨናንቆ የነበረው ቤት ጭር ብሏል፡፡ መሬቱ በተሰበረ ጠርሙስ እና በፈሰሰ መጠጥ ተሞልቷል፡፡
ከአንድ ሰው በስተቀር በቦታው ላይ እንደቀድሞው ሳይነቃነቅ ተረጋግቶ ተገኝቷል፡፡ እንዲያውም ከብጥብጡ በፊት አዞት የነበረው ምግብ ማን እንዳመጣለት ባይታወቅም … በተረጋጋ መንፈስ አጎንብሶ እየበላ ነው፡፡ ከአራታችን መሀል አንዱ የሆነው አስተማሪ ነው፡፡ እየተሸማቀቅን ዙሪያ ገባውን በጥንቃቄ እየተማርን ተቀላቀልነው፡፡ ከተመጋቢው በግራ እና በቀኝ በኩል ተቀመጥን፡፡ አፍረናል። በመፍራታችን ነብሳችን እንድናወጣት ለጠየቀችኝ ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት ሽንት ቤት ገብቶ እስከመደበቅ ድረስ መዝቀጣችን አሸማቆናል፡፡
ስፖንሰራችንም ቀስ ብሎ ተከሰተ … እሱ ደግሞ ምናልባት ጣራ ላይ ወጥቶ ሊሆን ይችላል፡፡ ሲወርድ አላየነውም፡፡ ስላላየነው የነገረንን አመንነው ‹‹ሲጋራ ልገዛ ወጥቼ ነበር … ምን ተከስቶ ነው?›› አለን ግራ የተጋባ መስሎ … የተመሰለውን ደግሞ ሆኖ። ቀስ በቀስ ሰዎች መመለስ ጀመሩ፡፡ ማን እንደተጎዳ ማን እንደጎዳ ማወቅ ያስቸግራል። ሁሉም ጀግና ይመስላል፡፡ ሁሉም አምባጓሮውን እልባት የሰጠ ይመስላል፡፡ በቀውጢው ወቅት ማን የት እንደነበረ አይታወቅም፡፡
እየተመገበ ኮራ ብሎ የጠበቀን ወዳጃችን ከዛ በኋላ ያለውን የምሽቱን ጊዜ እኛ ላይ በማላገጥ አሳለፈው፡፡ ‹‹ፈሪ ሁላ ሽንት ቤት ገብተሸ ትደበቂያለሽ? … እሱ (ወደ ዲያስፖራው እየጠቆመ) እንኳን እንደው ንብረት እና ላይፍ አለኝ ብሎ ቢደበቅ ያምርበታል፡፡ ሁለታችሁ ምን አላችሁ አይ ጸሐፊ … አይ ገጣሚ … ለእነሱ መጠጥ አትጋብዛቸው … እዛው የተደበቁት የራሳቸውን ሽንት ጠጥተው ጠግበው ወጥተዋል …›› እያለ ሲያፌዝብን አመሸ፡፡
ከፌዙ በተጨማሪ እኛ በተደበቅንበት ቅፅበት የተከስተውን ነገር ተራ በተራ ተረከልን፡፡ ማን እንደተፈነከተ … ማን ደግሞ እንደፈነከተ፡፡ ማን በፈንካች እና ተፈንካች መረጃ ያለ አንዳች ፍርሀት ገብቶ እንዳገለገለ ተረከልን፡፡ አገልጋዩ እሱ መሆኑ ነው፡፡ እሱ እና በስራው ባህርይ ምክንያት ሊሸሽ የማይችለው ምስኪኑ አስተናጋጅ፡፡
ሌላ ጊዜ ወደ ቤታችን የምንበታተን ሁሉ የተሰማንን መሸማቀቅ ለመክፈል ከተለመደው በላይ መጠጣት አስፈለገን፡፡ ከቢራ ወደ አልኮል ዞርን፡፡ ብቸኛው ደናሽ ብቸኛው ፎካሪ እና ብቸኛው ፀጥታ አስከባሪ አስተማሪው ሆነ፡፡   
ጭራሽ ወደ በኋላማ የፖለቲካ ስብከት ሁሉ ጀመረን፡፡ ‹‹እናንተ ናችሁ አሁን ኢህአዴግን በምርጫ እንቀይረው የምትሉ? … ኢህአዴግ እኮ ሽንት ቤት የሚደበቅ ፓርቲ አይደለም … አንተስ ብትሆን የዲያስፖራ ፖለቲካ ምናምን የምትል … ሽንታም ሁላ?...››
እየተሰደብንም እየተሸማቀቅንም መጠጣታችንን አላቋረጥንም፡፡ አሁን እያስፈራን ያለው አብረን ሜዳ የዋልነው … አብረን አጥተን … አብረን ጠጥተን … ግጥም አገጣጥመን ሁሉን ችግር ያሳለፍን የምንለው ጓዳችን ነው፡፡ አቫተር ከድሬ መሆኑን አረጋገጥን፡፡ ብናረገጋጥም መለያየት አቃተን፡፡
ከሌሊቱ አስር ሰዓት ገደም ሲሆን .. የነበርንበት ቤት የመዘጋት አዝማሚያ አሳየ። አስተማሪው መሪያችን  ባለመኪናውን ዲያስፖራ ወደ ሀያሁለት ማዞሪያ አቅጣጫ እንዲሾፈር አዘዘው፡፡ ያኛው የታዘዘውን አደረገ፡፡ ዲያስፖራው ያረፈው ወላጆቹ ቤት በመሆኑ ለመመለስ ፍላጎት ነበረው። አድርሶን ሰላም መሆናችንን አረጋግጦ ለመሄድ በተጠቀሰው አልቤርጎ ደጃፍ መኪናውን አቆመ፡፡ መኪናዋ ከመቆሟ አስተማሪው ወርዶ የሆቴሉን በር ማንኳኳት ጀመረ፡፡ የሚያንኳኳው ደግሞ በእግሩ ነው፡፡ ሶስታችን ከመኪና ውስጥ ሆነን እየተመለከትነው ነው፡፡ ማንኳኳቱን ጋብ አድርጎ ከበሩ በስተጀርባ ካለ ሰው ጋር ማውራት ጀምሯል፡፡
‹‹አቦ ክፈት አልጋ ይዘናል… አልቋል ትለኛለህ እንዴ?››
ብዙ ተነታረኩ፡፡ አልቋል ሲባል ድሮ አመስግኖ ይመለስ የነበረው ልጅ አሁን ምን ወይንም ማን አይዞህ እንዳለው ባይታወቅም በሩን በእርግጫ መርገጡን ቀጠለ፡፡ ‹‹አይዞህ›› ቢባልስ ታዲያ እንደዚህ አይነት ስነ ምግባር ከየትኛው ማንነቱ ጎን ነው ያፈለቀው፡፡ ያደገውም ሆነ የተማረበትን እናውቃለን። ያሳደጉትንም ሆነ ያስተማሩትንም እንደዚሁ። ሰይጣን ተጠናውቶት ካልሆነ … ወይንም ከጭንቀት ያመጣው የህመም ምልክት ካልሆነ ልጁ በአስርም ይሁን በመቶ አመት ውስጥ የዚህን አይነት ፈጣን የትዕቢት እድገት ሊያስመዘግብ አይችልም፡፡
ከብዙ እርግጫ በኋላ በሩ ተገነጠለ። ሲገነጠል እኛ መኪናው ውስጥ ሆነን እየተመለከትን ያለነው ደነገጥን፡፡ አጅሬ ምንም አልመሰለውም፡፡ ደጀኔን ጠራው። ደጀኔ፣ ድሬ ድሬ፣ እግዜር ቢጠራው እንኳን ሳያሰላስል እመር ብሎ የሚሄድ ልጅ አልነበረም፡፡
አስር ዓመት ሁሉንም ሰው ለውጧል። ደጀኔም እንደ አስተማሪው ሆኗል። ምናልባት የፅኁፍ ችሎታው እየጠፋ የመጣው ለዚህ ሊሆን ይችላል፡፡ ሲጠራ ተስፈንጥሮ የሄደበት አኳኋን ከዚህ በፊት ተጠርቶ መሄዱን … ተልኮ መላኩን ያረጋግጣል፡፡ አስተማሪው ተመልሶ ወጥቶ ባለመኪናውን ዲያስፖራ በምልክት መስኮት ዝቅ እንዲያደርግ ጠቆመው፡፡ ‹‹አንድ ወይ ሁለት ሺ ብር ስጠኝና ነገ እሰጥሀለሁ… ኤ. ቲ.ኤም ስለተዘጋ ነው››
ዲያስፖራው ለጓደኝነት ሲል ይሁን ለስጋቱ በፍጥነት የውስጥ ኪሱ ገብቶ ብር መቁጠር ጀመረ፡፡ እየቆጠረ እንዳለ ካድሬው ጓደኛችን በሙሉ ብሩን እየነጠቀው ‹‹በእኔ እና በአንተ መሀል መቆጣጠር አለ እንዴ?.... አብረን ሜዳ እና ገደሉን እውነትን ፍለጋ ስንባዝን ትዝ አይልህም ልበል? ሰለሞን ዴሬሳን ስንቀኝ ትዝ አይልህም፡፡
“ጓደኝነት መከፋፈል ነው ሳይቆጣጠሩ
መርዝ መጋራት ሳይጠራጠሩ
በህብረት መፍራት ነው ሳይተፋፈሩ
መገናኘት ነው ሳይፈላለጉ
መጣላት ላይበጅ መራራቁ
መራራቅ ሳይገማመቱ …
“ትዝ አይልህም? … አሜሪካ አበላሽታሃለች ማለት ነው! …  አንተስ አትመጣም›› አለኝ እኔን፡፡
‹‹አይ እኔ ሌላ ቦታ ልቆይና … ሊነጋ ስለሆነ ጠዋት ቤት ገብቼ ልተኛ›› አልኩት
‹‹ልትጠጣ ነው?››
‹‹እንደ ምርጫዬ››
‹‹ሽንት ቤት የጠጣኸው እንትንህ አይበቃህም?››
ስቆብን በጉልበት ወደ ከፈተው በር አመራ፡፡ ደጀኔ በፍጥነት ተከተለው። ከገቡ በኋላ በሩ ተዘጋ፡፡ ዲያስፖራው ግርም ብሎታል፡፡ መኪናውን ወዲያው አላንቀሳቀሰም፡፡ እንዲያውም ሲጋራ ለኩሶ ወደ ውጭ ወጣ፡፡ ለእኔም አቀበለኝ፡፡ መኪናዋ ላይ ተደግፈን ማጨስ ጀመርን፡፡ የመኪናዋ መብራት የሆቴሉ በር ላይ ቦግ ብሎ በርቷል፡፡
‹‹ይሄ ልጅ አሁን ያደረገው ነገር ትክክል ነው?›› አለኝ፡፡ በጣም ተገርሟል፡፡
‹‹ያደረገው ስትል … ገንዘብህን መንጠቁ ነው ወይንስ እብሪቱ››
‹‹አይደለም…. የተዘጋ በር በእርግጫ ሰብሮ መግባት አሁን ከአስተማሪ የሚጠበቅ ነው፡፡
‹‹መች አስተማሪ ነው፡፡ አስጠቋሪ ነው›› አልኩት፡፡
ደስ የማይል ፈገግታ አሳየኝ፡፡ ነገሩ ገብቶታል፡፡
በፀጥታ አጭሰን ስንጨርስ አንድ ነገር ተከሰተ፡፡ የሆነ ድምፅ ከሆቴሉ በር ጀርባ መስማት ጀመርን፡፡ መጀመሪያ የጭቅጭቅ ድምፅ ነበር፡፡ ጭቅጭቁን ከፍ ባለ ድምፅ የሚሰማው ነው፡፡ በኋላ የዱላ ድምፅ ተሰማ.. ከዛ በግቢው ውስጥ የመሯሯጥ ድምፅ … የደጀኔ ድምፅ ጩኸት አወጣ …. እንደዛ አይነት ጩኸት ጥሩ አይደለም፡፡
አስተማሪው ሲሮጥ የጨዋ ሰው ኮቴ ይለያል፡፡ ሮጦ ሮጦ ቅድም ሰብሮ የገባው በር ጋር ተጠመደ መሰል ሳይከሰት ቀረ፡፡ ዱላው ጀመረ፡፡
‹‹በፍልጥ .. በፍልጥ … እኔን በፍልጥ … ማን እንደሆንኩ አሳያችኋለሁ፡፤ … እሺ እወጣለሁ…››
በደብዳቢዎቹ ጎን ምንም ንግግር አይሰማክ፡፡
ዲያስፖራው ወደ በሩ ሄዶ የአስተማሪውን ስም ይጠራ ጀመር፡፡
‹‹በአጥር ግቡልኝ … እነዚህ ሰገጤዎች ሊገድሉኝ ነው›› ይላል አስተማሪው፤ ዱላው ቀጠለ፡፡ ለአስተማሪው ላይ ያረፍው ድብደባ  ወደ ሰላሳ ደቂቃ ያህል ሳይወስድ አይቀርም። ደጀኔ አልቅሶ ‹‹እኔ የለሁበትም እሱ ነው›› ብሎ ‹‹ጋዜጠኛ ነኝ … የመንግስት ጋዜጠኛ” ብሎ ጮሆ በአስር ደቂቃ ድብደባ ተገላገለ፡፡
ዱላው በስተመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች አንድም ድምፅ ከአስተማሪው ትንፍሽ ያልተባለባቸው ነበሩ፡፡ ከመጨሻዎቹ ደቂቃዎቹ በፊት ባለው ጊዜ ግን ሚስጢር ብሎ የያዘውን ነገር በሙሉ ተናግሯል። ከልጅነት እስከ እውቀቱ፡፡ ከቅንጅትነቱ ሚስጢር እስከ ኢህአዴግነቱ፡፡
በሩ ተከፍቶ ሲወጡ … በሩጫ ሁለቱም ከተፈተለኩ በኋላ ቆም ብለው በመኪና እስክንመጣላቸው ጠበቁ፡፡፡ መኪናውን አስነስተን ደረስንላቸው፡፡ በግራና በቀኝ፣ በቅልጥፍና ከኋላ ወንበር ተሳፈሩ፡፡ ማንኛችንም፣ በተለይ እኔ እና ዲያስፖራው አንድም ቃል ለመተንፈስ አልደፈርንም፡፡ እፍረተ ቢሱ ተናገረ፡፡
‹‹ወንድ ነኝ ብቻዬን እኮ አምስት ሆነው ተቋቁሜያቸው ነበር፡፡ እናንተ ግቡልኝ፤ እያልኳችሁ ዝም ትላላችሁ፡፡ ሽንታም ሁላ››
ደጀኔ አይኑ አብጧል፡፡ ማበጥ እየቀጠለም ነው፡፡ በመኪናው መስኮት ወደ ውጭ ይመለከታል፡፡ አንድም ቃል አይተነፍስም፡፡
ጠቅላይ ማስተሳሰሪያ
ከአራተኛው ታሪክ በፊት የነበረው የስነምግባር ትርጉም ከአራተኛው በኋላ ለእኔ ተለወጠብኝ፡፡ የአውቶብሱ ትእይንት፣ የሜዳው፣ የሁለቱ ፍቅረኛሞች እና የአራቱ ጓደኛሞች ወደ አንድ ሚዛን መምጣታቸው ታወቀኝ፡፡
እንዴት አትሉኝም?!
ሜዳ ላይ በፌዴራሎች ሲቀጠቀጥ ያየነው ወጣት ብርታቱን እኔ እና እናንተ እኩል አድንቀን ነበር፡፡ ነገር ግን ያው ወጣት በአውቶብስ ስር ነፍሱን ለማትረፍ እየሮጠ የነበረውን ሰው በድንጋይ ሲያባርር እንደነበር ተገንዝባችኋል? … እኔም አልተገነዘብኩም ነበር፡፡ የቲሸርቱን ቀለም ማመሳሰል ይቻላል፡፡ ይሄ ወጣት ከሁለቱ ጓደኞቹ የበለጠ ጭካኔው አይሎ ተሳዳጁ ሰውዬ ሰውየውን ከሞተም በኋላ ጭንቅላቱ ላይ ቆሞ አልወርድ ያለው ነበር፡፡
በሰሜን ሸዋ  ሁለቱ ገበሬዎች ማጭድ ተወጋግተው በተያያዙበት መፍትሄ ለመስጠት ወደ ፖሊስ ጣቢያ የሮጠው ጓደኛችን ዲያስፖራ ሆኖ የተመለሰው ነው። ምናልታበት መፍትሄ የማፈላለግ ርህራሄ ስላለውም ነው ህይወቱ የሰመረለት። ደጀኔን እና አስተማሪውን የመቱት የገጠር ወጣቶችም የዛው ሀገር ሰዎች ናቸው ልንል እንችላለን፡፡ እነሱ በወላጆቻቸው ላይ የደረሰባቸውን በደል ካለ በአስተማሪው ላይ አስተካክለዋል፡፡
ቦሌ አካባቢ በወንድ ጉዋደኛዋ የተመታችው ኮረዳ መመታትን ስለምትወድ ብቻ ነው፡፡ ፍቅርዋን የምትለካው ባረፈባት ዱላ መጠን ነው፡፡ አሁንም አብረው ያሉ ይመስለኛል፡፡
4.ይህን ሁሉ ከላይ የጻፍኩት፣ ለሰው ልጅ ጭካኔ ሳቢያ እና ምክኒያት ለማፈላለግ ስል ነበር፡፡ ጭካኔ ግን የሰው የማይለወጥ ተፈጥሮው ነው፡፡ አራቱን ማሳያዎች የሚያስተሳስራቸው  ብቸኛው ነገር የሰው ልጅ ምክኒያት አልቦ የጭካኔ ተፍጥሮ ብቻ ነው፡፡  

Read 303 times