Print this page
Saturday, 13 November 2021 14:43

"ሶስት ቀን"

Written by  ኦርዮን ሙስጠፋ
Rate this item
(4 votes)

   ውዴ፤ እጥረቴና ማነሴ ከእይታህ ሳይሰውረኝ እንደ ንስር ከፍ ብለህ በትህትና ሰማይ ላይ በአንክሮ ያስተዋልከኝ፣ የማታው ጽልመት ሳይጋርድህ፣ ከሺ ቆነጃጅቶች መሃል እኔን ነጥለህ በብርሃን ልብህ ያየኽኝ፣ ሞገስ አልባ ደቃቃው ሰውነቴ  ከእይታህ ሳያጎለኝ፣ ሰው ለመቅረብ ያፈረ የተርበተበተና በማነስ ትእቢት፣ በመዋረድ ሃፈረት በብቸኝነት አመል የጎረበጠው ሰብእናዬን በፍቅርህ መዳፍ እሾሁን ተወግተህ፣ እጆችህን ለእጆቼ፣ ቅርበትህን ለባይትዋርነቴ፣ ደስታህን ለሃዘንተኛው ማንነቴ የዘረጋህ የህይወት፣ የተስፋ ዳናዬ ነበርክ፡፡
አይተው እንደ ዋዛ የሚያልፉኝ፣ አውርቼ ቃሌ ከመጤፍ ያልተጣፈልኝ ሃሳቤ፣ ባለመደመጥ ዳዋ የተመታ ሞገሴ በመገፋት ውርጅብኝ ቅስሙ የተሰበረ ከአንድ ብቸኝነቴ በቀር ባለ እንጀራ አልነበረኝም፤ ከራሴው ጋር ወዬ ከራሴው ጋር የማድር፣ ራሴው አውርቼ ራሴው የምመልስ ጭምት እብድ ነበርኩኝ፤ ልቤን ለ ለሰው ልጆች ሃሳቤን ለተስፋ የዘጋው የሂወት ደጃፍ ላይ የተጣልኩኝ ብኩን።
ኣንድ ቀን ብሩህ ደማቅ ምሽት በዛች ቀጭን ወደ መንደሬ የምታደርሰው መንገድ ላይ  የሃጋይ ሃሩር  ላይ እንደሚጥል ዝናብ ድንገት ሂዎቴ ላይ እንደ መብረቅ ሆንክ፤ ብልጭ አልክ፤እየተራመድኩ ነበር፤ እረፍት ወደማላገኝበት ቤቴ እየነጎድኩ ነበር፤ ወደማያደርሰው ጎዳና ዘወትር ኣድካሚ አመላላሽ በሆነው፡፡
አንድ ምሽት ላይ እንዲህ ሆነ፦ አንድ ተባእት ከጎኔ እየሄደ ነበር፤ ጥላ ሞቱ በላዬ ላይ ሲያርፍ ይታወቀኛል፡፡
ድምጹን አለስልሶ አንገቱን ወደ እኔ አዝሞ፣ የሰላምታ ቃል እየሰጠኝ፣ አብሮኝ ይጓዝ ጀመር፤ እኔም ለአንዳፍታ እንኳ ዞሬ ሳላየው፣ የሰላምታ ቃሌን ብቻ በሚርበተበት አንደበት መለስኩኝ፡፡
በአቀራረቡ ወንዳወንድነት ሴትነቴ ሲፈተሽ ይታወቀኛል፤ ገርመም አድርጌ አየሁት፤ ንጹህ ቀና ፊት ነበረው፤ ኮስታራ ፊቱ ላይ የተሳለች ነቁጥ ፈገግታ ከዛ ኣስፈሪ የማይፈታ ኮስታራ ፊቱ ላይ የምትወጣ አትመስልም ነበር፤ በሳቅ ቃና የታጀበ ድምጹ ውስጥ ሲቃው ተደበስብሳ ትሰማለች፡፡
ለዓመታት ሴትነቴ ወንድን ዘንግቶ ነበር፤ እናም ከእሱ ጋር የማወራበት ኣግባብ ጠፋኝ፤ ግን ከአንደበቱ የሚወጡት ቃላት ለልቤ ተዓማኒነትን ያዘሉ ሆነው ይሰሙ ነበር፡፡
እናም እጆቼን ዘረጋሁለት፤ የተዘረጉት እጆቹ መዳፎቼን በናፍቆት አቀፋቸው፤ ተለያይተው እንደተገናኙ ተጠፋፍተው እንደተፈላለጉ ዘመዳሞች እጆቻችን በእውነተኛ የመገናኘት ስሜት ተነካኩ፤ በእጆቹ በኩል አንዳች ንዝረት መላው አካሌን ወረረው፤ ዓይኖቻችን ለቅጽበታት ተጋጩ፤ ተግባቦትና እርጋታን ያዘለ ሰላም መሃላችን ሰፈነ፡፡
የመጀመሪያ ቀን ሲሸኘኝ ከጥቂት እርምጃዎች በኋላ መሃላችን የነበረው የእንግድነት ስሜት ተኖ ጠፋ፤ ዘመናትን አብሮ እንደኖረ፣ የማይታክቱ የፍቅር ጎበዛዝት፣ ፍጹም በመላመድ የካበተ፣ መላመድ ይስተዋል ነበር፤ በመሃላችን፡፡
በሶስተኛው ቀን እንዲህ አኣለኝ-፡ ያን ቀን በጨለማ በሰው ልጆች የደነደነውን ብቸኝነቴን ታቅፌ ጥርጊያው ላይ ስራመድ፣ ከሩቅ አንቺን አየሁሽ፤ መንፈሴም ልቤም ነገረኝ፤ እንድቀርብሽ፤ ኣንዳች እውነት የሆነ መልእክት ወደ አንቺ ጠራኝ፤ ሰማሁት እና ወዳለሽበት አዘገምኩኝም፤ ፊትሽ ላይ ያዘነና የተከፋ ህይወት ይነበብ ነበር፡፡ ብዙ ከአወራንና መግባባታችን እርግጥ ከሆነ በኋላ፣ የሶስት ቀን ፍቅር እንድትሰጪኝ ጠየኩሽ፤ አንቺ ግን የልብሽን ሰገነት ወለል አድርገሽ ከፍተሽ፤ "ና ከቀናቴና ከፍቅሬ የፈለከውን ያህል ዝገን" አልሽኝ፡፡
እናም ሰጋሁ፤ ዘላለማዊ ሳይሆን በጣት የሚቆጠሩ ቀናትን ጠየኩሽ፤ ከጎንሽ መቼም ያለመጥፋትን ግብዝ ቃልኪዳንን ለልብሽ ልግተው አልዳዳሁም፤ ምክንያቱም ልባችን ሜዳው ላይ በነፋስ እንደሚርመሰመሱ ቅጠል ነው፤ የውበት የጊዜና የሃሳብ ማእበል ይንጠዋል፤ ካንቺ እንደተለየሁ መች ሌላ የፍቅር መብረቅ መቶት ኣይኔ በናፍቆት እንባ እንደሚያካፋ ኣላውቅም፤ እና ግሎ ያልበረደ ታይቶ ያልጠፋ፣ የወረት አውሬ ያልበላው፣ በፍቃድ በተገደበ ቀናት ውስጥ ያልተገደበ ፍቅርን አግኝቼ ልለይሽ ወሰንኩኝ፤ በመለያየት ውስጥ ያለውን አብረን ብንቆይ የማይታወቀውን ግን ሚስጥር የሆነ መገናኘትንና መለያየትን ቀይጄ ነበር፡፡
ለልባችን ላስተምረው ወሰንኩኝ፤ ለልብሽ ላሳየው አስብኩኝ፡፡ ይሄን እውነት፥ ይሄን ነጻነት፥ ፍቅራችንን በጸብ ሳይሆን በፍቃድ የመቋጨት ልምምድ፣ የሰውን ልጅ ሰውን የማጣት ትካዜ፣ እስከ ወዲያኛው የመሻር፣ የተቀመረብንን የአብሮነት ከንቱ ድንጋጌ የማፍረስ፤ እናም ያን ምሽት ፊትሽ ውስጥ ያየሁት የመገፋት ድቅድቅ ስሜት፣ የብቸኝነት ጽልመት፣ ራስን ወደ ማግኘት ብቻነት ብርሃን ልመልሰው ከጀልኩኝ። አንቺን ማፍቀሬን ባወቅሁብት ቅጽበት፣ ጥልቅ መሻቴ ሆነ፤ የኔስ ቁዘማ መንስኤው መች ከአንቺ ይለይ ነበር፤ ፊትሽን ሳየው ግን ይሄ ሃቅ በራልኝ፤ ኣስተምሬሽ አድኜሽ ልሄድ ወሰንኩኝ፡፡ ለራሴም አልኩት፡- ማፍቀሬን የምገልጽበት መንገድ ዛሬ ገና አገኘሁኝ፡፡
ፍጹም አትዘኚ፤ ዛሬ ስለይሽ ከጎንሽ ብለይም፣ ከውስጥ የማይጠፋ ስለ እኔ መልካሙን ብርሃን አኑሬ ነው፤ እውነተኛው ወዳጅ ብቸኝነት መንገድ ላይ ጸሃይ እንኳን ባይሆን ፋኖስ ሆኖ ጥርጊያ መንገድን ያበራል፤ ደና ሁኚ ብሎኝ የተያያዝንበትን መዳፍ በእርጋታ አስለቅቆ፣ ፈጠን ፈጠን ባለ እርምጃ ጥሎኝ ሄደ።
የኮቴው ዳና እና የአካሉ ምስል ቀስ በቀስ እየራቀ ሄደ፤ ራእዩ ግን ይበልጥ ቀረበኝ።
ሃዘኔና ናፍቆቴ ከሱ ጋር አብሮ ጥሎኝ ሄደ፤ በጊዜ የማይሰፈር መውደድን በሰው ልጅ የጊዜ፣ መለኪያ ሶስት ቀን በሚባሉ ወቅቶች ውስጥ ዘመናትን አኖረኝ፤ ከብቸኝነቴ ጋር የሰላም ቃልኪዳንን ኣስተሳሰረን፤ ከራሴ ጋር አጋባኝ፤ ሰው የራሱ ባለእንጀራ መሆን እንደሚችል አሳየኝ፤ በባይተዋርነት እርዛት የተራቆተችዋን ነፍሴን ከፍጥረተ አለሙ ቤተሰብ መሆኗን ገልጦልኝ ወዳጄ ተሰወረ፡፡ እኔም ሰው የመፈለግን ቅዠት ኣቁሜ፣ ራሰን የማግኘት ጎዳና ጀመርኩኝ።                                             


Read 1671 times