Print this page
Saturday, 13 November 2021 14:43

የአላዋቂ ‘አዋቂነት...’

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(2 votes)

     “--በዓለማችን ላይ ለመጀመሪያ ጊዜ በምስራቅ አፍሪካዋ ሀገር፣ አንድ ግለሰብ በራሱ ላይ እድሜ ይፍታህ ፈረደ!” በዚህ ሰበር ዜና ሲ.ኤን.ኤን. ስንት ተመልካች ባማለለ ነበር፡፡ ቤኪ አንደርሰን የበቀደሙን አይነት ‘ቃለ መጠይቅ’ ከምታደርጊ፣ እንደዚህ አይነት ‘ወሬ’ እስኪገኝ ብትጠብቂ ባልተጠቋቆምንብሽ! ነበር፡፡--"
                    እንዴት ሰነበታችሁሳ!
ስሙኝማ፣ ምን ችግር አለ መሰላችሁ... ‘አዋቂው’ ሁሉ እዚችኛዋ የዓለም ክፍል ብቻ ተሰበሰበና ከትንሽ ዓመታት በኋላ የተቀረው ዓለም በአዋቂ እጥረት የተነሳ ደግሞ ወደ ሌላ ዙር ዘመቻ እንዳይገባብን ያሰጋል!
እኔ የምለው... ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ...የዘመቻ ነገር ከተነሳ ዘንድሮ የሚታየው ነገር ጉድ እኮ ነው! ምንም ማጋነን ሳይኖር እውነቱ ምን መሰላችሁ... በቅርብ ጊዜ ትንሹም፣ ትልቁም ሚዲያ የሚባለው፣ ፖለቲከኛ የሚባለውም እኛ ላይ እንደተነሰነሰ ማን ላይ ተነሰነሰ! ኸረ ሼም ነው! እንደው በሰው ሀገር ጉዳይ ምን ያገባናል እያልን ነው እንጂ፣ ወጣቶቹ እንደሚሉት በ‘ፈጣጤ’ ጥልቅ ብንል ኖሮ አጅሬ ትረምፕን “ያኔ ደጋግመው ‘ሲ.ኤን.ኤን. ፌክ ኒውስ!’ ሲሉ የተሳለቅነው በእውቀት እጥረት ስለነበር፣ አሁን አቋማችንን አስተካክለናል፣” እንላቸው ነበር፡፡ ፌክ ብቻ! ደግሞ እኮ እንደው ሲያዩዋቸው ወደ እኛ ቀረብ ይላሉ ያልናቸው ዋነኞቹ ናቸው የብዕር ጦር ሰባቂ የሆኑት፡፡ ኒማ ኤልባጊር ምንም እንኳን የድርጅትሽን አቋም ስታቀርቢ የነበርሽ ብትሆኝም፣ በዛ ያሉ ቀይ መስመሮች ያለፍሽ አይመስልሽም?
ስሚኝማ ኒማዬ፣ የሆነ ነገር ትዝ ብሎኝ...በዛ ሰሞን ጥበቃ ላይ በነበሩ ወታደሮቻችን ፊት ጮክ ብለሽ “ሲ.ኤን.ኤን!  ሲ.ኤን.ኤን!” እያልሽ የተወንሽው የኮሜዲው ፊልም ቀረጻ ተጠናቀቀ እንዴ! በኮሜዲ ትወና ጥሩ ችሎታ እንዳለሽ እስከዛሬ አለቆችሽ ወይም የሥራ ባልደረቦችሽ ያልነገሩሽ ከሆነ ምቁነት ነውና እኛ በነጻ ሎቢ ልናደርገልሽ ፈቃደኞች ነን፡፡ ምንም ቢሆን የዛሬውን አያድርገውና፣ የእነ መሀመድ ወርዲ ሀገር ሰውም አይደለሽ!
የምር ግን፣ እንደው በመልክም ለእኛ ቀረብ ይላሉ ብለን የምናስባቸው የዘመቻ ፊትአውራሪ ሲሆኑ፤ እኒህ ሰዎች በቃ ማንም ቢያገኛቸው ደስ የሚለው አገልጋዮች ናቸው ብንል አይፈረደብንም፡፡ አሀ... “እሺ  እሺ!  እሺ!” ናቸዋ! እዛ ‘ነጩ ቤት’ ሲኬድ ራይስ ነች ምናምን የሚሏት ሴትዮ፣ ይኸው ለስንት ዘመን እንደነከሰችን አለች፡፡ ለነገሩ እኮ...እንግዲህ ዘንድሮ ነገር መፈለግ አይደል፣ በመልክ እኛ አንቀርባትም ነበር! ተይ ግዴለሽም በኋላ “በሴት አያቶቻችን ደጅ ማን እንዳለፈ እናውቃለን የተባለውን ነገር አንቺ ላይ እንዳንጠቀምና...ብቻ ይቅር! እኔ የምለው...የሆነ ነገር ትዝ ብሎኝ ነው፤ እሷ ሴትዮ ገዥው ፓርቲ መቶ በመቶ አሸነፍኩ ስላለው ‘ያ ምርጫ ስትናገር፣’ መደረክ ላይ የሳቀችው፣ ያ ‘ሂስቶሪክ’ ሳቅ እስካሁን በ‘ጊነስ ቡክ ኦፍ ሬከርድስ’ አለመካተቱ አይገርማችሁም?
ደግሞላችሁ በዚህ በየጊዜው ስለ እኛ እየተሰበሰበ ሌላ ለ‘ጊነስ ቡክ ኦፍ ሬከርድስ’ የሚሆን ታሪክ እየጻፈ ያለው ድርጀት ውስጥ ያለችው ሴትዮስ! ጥያቄ አለን...በግል ጉዳይ እኛ አካባቢ የሆነ ‘ነርቯን የነካው’ ሰው ካለ ትንገረንና እኛም ጥያቄ ከመደርደር እፎይ እንበል፡፡ እንዴ ጭራሽ በእኛ ጉዳይ እንደ መበሳጨት አደረጋት እኮ! ደግሞ “በሁለቱም ወገን ጥሩ ሰው የለም፣” ነው ምናምን አለች የተባለው ነገር ፣ጭራሽ አሁን የጥሩና መጥፎ የበቃት ማረጋገጫ ሆና አረፈችው! እንደው እግረ መንገድ ተሳሰተን አንጀሊና ጆሊንም በክፉ ዓይን እንዳናይ ፈርተን ነው እንጂ ለሴትዋ በራሷ ቋንቋ... “ሉክ ሁ ኢዝ ቶኪንግ!” ባልናት ነበር፡፡
እኔ የምለው...እኛ አካባቢ ስለ ‘አዋቂ’ ሰው መብዛት ማውራት ጀምረን ምን ስናደርግ እዚህ ውስጥ ገባን! እናላችሁ...በበጎ ፈቃደኝነት ‘አዋቂነትን’ የምንቀላቀል ስንበዛ... አለ አይደል... መነጋገርም፣ መደማመጥም ያስቸግራል፡፡ አለ አይደል... “አወቅሽ፣ አወቅሽ” ሲሏት መጽሀፉን አጥባው ቁጭ እንዳለችው ምስኪን በሆነ ነገር “ኢሮ! ኢሮ!” ሲሉን ወላ ቢጫ መስመር የለ፣ ወላ ቀይ መስመር የለ በአስራ ምናምነኛ ማርሽ መሸምጠጥ ነው፡፡ ከእለታት አንድ ቀን ስለ ዓለም ሙዚቃ ሲጠየቅ፤ “ምን ሙዚቃ አለ፣ ራፕ ብቻ ነው...” እንዳለው ወቅቱ አንጋፋ ‘አዋቂ’ ሙዚቀኛ  የሀይቁን ጥልቀት ሳያውቁ ዘው ማለት፣ አሁን በዛ አላለም ብላችሁ ነው! ግን ደግሞ ተጠያቂውስ ምን ያድርግ! ስለ ዓለም ሙዚቃ ስትጠይቀው መልስ መስጠት ነበረበት፡፡ እኛ ዘንድ አላውቅም ብሎ ነገር የለማ! “ይቅርታ ስለ እሱ ብዙም የማውቀው ነገር የለም...” ማለት በዳኛ ወንበር ላይ ተቀምጠን በራሳችን ላይ “እድሜ ይፍታህ! እንደ መፍረድ ይቆጠራላ!
“በዓለማችን ላይ ለመጀመሪያ ጊዜ በምስራቅ አፍሪካዋ ሀገር፣ አንድ ግለሰብ በራሱ ላይ እድሜ ይፍታህ ፈረደ!” በዚህ ሰበር ዜና ሲ.ኤን.ኤን. ስንት ተመልካች ባማለለ ነበር፡፡ ቤኪ አንደርሰን የበቀደሙን አይነት ‘ቃለ መጠይቅ’ ከምታደርጊ፣ እንደዚህ አይነት ‘ወሬ’ እስኪገኝ ብትጠብቂ ባልተጠቋቆምንብሽ! ነበር፡፡ እኔ የምለው...ግርም የሚል እኮ ነው፣ ሰዎቹ በስብሰባ አዳራሽ ውስጥም፣ ስቱድዮ ውስጥም በእኛ ጉዳይ ‘ተበሳጭተው’ ማለቃቸው ነው እኮ! ይህን ያህል ነገሮችን አበላሽተንባቸዋል እንዴ! እናማ...አለ አይደል... “ይቅርታ ስለ እሱ እንኳን የማውቀው ነገር የለም...” በማይባልበት ዘመን ‘አዋቂ’ መሆን አስፈላጊ ነው፡፡
“ተመልካቾቻችን የዛሬው እንግዳችን ላለፉት አስር ዓመታት በምግብ ዝግጅት ሙያ ሲያገለግል የኖረና በበርካታ ሆቴሎችና ሬስቱራንቶች የሠራ ነው፡፡ እንግዳችን ግብዣችንን ተቀብለህ ስለመጣህ እናመሰግናለን፡፡”
“እኔም ስለጋበዛችሁኝ አመሰግናለሁ፡፡”
“እሰይ! ምናልባት የክፉ ቀን ወዳጃችን ሹሮ ወጥን እንዴት ማጣፈጥ እንደሚቻል ይነገረንና ከእሜቴ እማወራ ጋር ጭቅጭቁ ይቀርልናል፡፡
 “ይሄን ሹሮ እንደው የሆነ ጣፈጥ የሚያደርግ ነገር ብትጨምሪበት ምናለበት!”
“የቀረብልህ ምን ሆነ ለማለት ነው?” ያበጠው ይፈንዳ!
“የሹሮው ዱቄት እኮ በወጥነት የተሠራ ሳይሆን እንደ አብሽ ላይ ላዩን የተነሰነሰበት ነው የሚመስለው!”
“ካልጣፈጠህ ኩሽና ገብቶ መሥራት ነዋ!”
በስስ ብልት መግባት ማለት ይሄም አይደል! እና እንደ ሹሮ የተንተከተከችውን ሳይሆን ‘እንደ አብሽ ከተነሰነሰችው’ ሹሯችን ጋር ማዝገም ነው፡፡ እንኳንም የምግብ ባለሙያ ጋበዙልን፡፡
እንደው ብልጅነትህ የምግብ ባለሙያ እሆናለሁ ብለው አስበህ ታውቃለህ?”
እዚሀ ላይ እሱን ከምትጠይቀው እኛን “ተመልካቾቻችን ለዚህ ጥያቄ መልሱን በስልክ ቁጥራችንና በኤስ.ኤም.ኤስ.  ላኩልን፣” ብትል ይቀላት ነበር፡፡ “አዎ፣ ድክ ድክ ማለት ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ ሳድግ ዓለም አቀፍ እውቅና ያለው ሼፍ እሆናለሁ ሲል ነበር፣” እንልሽ ነበር፡፡ የምር እስቲ ልብ በሉ... “እዚህ ሙያ ውስጥ እንዴት ገባህ ሲባል... “እኔ መሰማራት የምፈልገው በሌላ ሙያ ነበር፡፡ ያ  አልሳካ ሲል የእንጀራ ነገር ሆነና እዚህ ሙያ ውስጥ ገባሁ፣” የሚለው ስንት ነው? እናም ነገርዬውን እንደምንም ወደ ልጅነት ዘመን መልሶ... “በቃ እናቴ ማንጎራጎር በጣም ትወድ ስለነበር፣ ገና መዳህ ሳልጀምር እሷ ስታንጎራጉር በደስታ እስቅ ነበር ይሉኛል፡፡” ቆዪማ፣ የእኛ ቆንጆ...  ውይይቱ እየገፋ ሲሄድ... “እንደውም ከዛ በፊት...” ብለሽ ወደ ማህጸን እንዳትመለሽ የፊተኛውን አምነንሻል፡፡
እናላችሁ... የምግብ ዝግጅት ባለሙያው ተመሳሳይ መልስ ከሰጠ በኋላ “አሁን ወደ ዋናው ጉዳይ ልንገባ ነው፣” ብላችሁ ስታስቡ ጠያቂዋ ምን ልትል ትችላለች መሰላችሁ... “እንደሚታወቀው ዓለም በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ለመበላለጥ ውድድር ላይ ነው፡፡ እንደው በአንተ አመላካከት ይህ ነገር ወዴት የሚያመራ ይመስልሀል?”
ኸረ እንደው ጠዋት ለቁርስ ‘ኢን’ ባደረግሽው ቋንጣ ፍርፍር ይዘንሻል! የሆነ ንግርት ይዘሽ ነው እንዴ ስቱድዮ የገባሽው? “የሚቀጥለው እንግዳሽን ስለኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ካልጠየቅሽው የሚቀጥሉት ሦስት ዙር የደሞዝ እድገቶች እንደሚያልፉሽ በራዕይ ታይቶኛል ያለሽ ‘አዋቂ’ አለ እንዴ! (መቼም ዘንድሮ ለአቅመ ራዕይ ያልደረስነው እኛ፣ እኛ ብቻ ነን!)
እናማ... የምግብ ዝግጅት ባለሙያው ስለ ምግብ አዘገጃጀት ቤሳ ቤስቲኒ ሳይናገር፣ ስለተጠየቃቸው ነገሮች ብዙ ተናግሮ፣ ምንም ሳይል አቅራቢዋ... ተመልካቾቻችን በዛሬው ውይይታችን እንደተደሰታችሁ ተስፋ በማድረግ...” በሚል ቆሽታችሁን አክስላላችሁ ነገርዬው ያበቃል፡፡ አማወራዎች “ካልጣፈጠህ ኩሽና ገብቶ መሥራት ነዋ!” የሚሉት ‘ስለሚታያቸው’ ነው፡፡
ታዲያላችሁ... ይሀ በራስ ተነሳሽነት አላዋቂ አዋቂ መሆንና በግዳጅ የአዋቂነት ሚና የምንጫወተው በዛንና መደማመጥ ጠፋ፡፡ እሱ ብቻ መሰላችሁ እንዴ! እንዲህም ሆኖ እርስ በእርሳችን ስንናናቅስ!
“እሱን ስለነ ኑሮ መወደድ ትንታኔ እንዲሰጥ የሚጠይቁት ሆዱን ይሙላ እንጂ ምን ያውቅና ነው!”
“እንትና ፖለቲካውን የስሙኒ ኳስ ሲያደርገው አየኸው! የዚህ ሀገር ነገር እኮ ያበቃለት እነሱ ፖለቲከኛና ተንታኝ ሲሆኑ ነው!”
ብቻ...ምን አለፋችሁ... የአላዋቂ ‘አዋቂነት’ ብዙ ነገሮች ውስጥ እየገባ የሌለ ደረታችንን ‘እያስገለበጠን ያለበት ሁኔታ ነው ያለው።’ እኔ የምለው... “ያለበት ሁኔታ ነው ያለው” የሚሏት ነገር ቀረች እንዴ!
ደህና ሰንብቱልኝማ!

Read 1561 times