Monday, 15 November 2021 00:00

በሁሉም መስክ ወረራውን መገዳደር!

Written by  አያሌው አስረስ
Rate this item
(0 votes)

  በደርግ ዘመን የአምስተኛውን የአብዮት በዓል ለማክበር መንግስት ከፍተኛ ዝግጅት እያደረገ ነው፡፡ የደርጉ ሊቀመንበር ጓድ መንግስቱ ኃይለ ማርያም ደራሲያንን ሰብስበው፣ መንግስት የሱማሌን ወራሪን ጦር በመደምሰስ የተያዘበትን ግዛት ማስመለሱንና ደንበር ማስከበሩን፣ አስመራን ለመያዝ ተቃርቦ የነበረውን የሻቢያን ጦር ወደ ኋላ እንዲመለስ ማደረጉን ወዘተ ዘርዝረው፣ የአብዮቱን ፍሬዎች ደራሲያን ለሕዝብ እንዲያሳውቁ መመሪያ ይሰጣሉ፡፡ በዚህ ስብሰባ ላይ ከተገኙት አንዱ የነበሩት ደራሲ መንግስቱ ለማ  እንዲህ አሉ፡-
“ጓድ ሊቀመንበር የድርሰት ሥራ፣ ሥራ ሚሆነው ከውስጥህ ፈንቅሎ ሲወጣ ነው። በአብዮቱ ይሄ ተደርገ ይሄ ተደረገ ማለት የጋዜጣ እንጂ የድርሰት ሥራ አይሆንም” ይላሉ አቶ መንግስቱ ለማ”
ጓድ ሊቀመንበርም፤ “አክብረን ጠየቅናችሁ እንጂ አንዴ በሳንጃ ብንወጋችሁ ትፅፋላችሁ! አሉ ተቆጥተው።
“አሁን ገና  እንጽፋለን” አሉ ይባላል- መንግስቱ ለማ፡፡
 አሜሪካና አጋሮቿ በፊት ለፊትም በጀርባም ከግብጽ ጎን መቆማቸው የታወቀ ነው፡፡ ግብጽ ደግሞ ኢትዮጵያ የተረጋጋ መንግስት ኖሯት ለልማትና እድገቷ የምትሰራበት ጊዜ እንድታገኝ አትፈልግም። ሻዕቢያ ለ30 ዓመት ባደረገው ጦርነት፣ ሶማሌ በከፈተችው የመስፋፋት ዘመቻ፣ ሱዳን ድንበር ልፋ የኢትዮጵያን መሬት ስትይዝ ወዘተ… የግብፅ እጅ ስለመኖሩ የሚጠራጠር አይኖርም፡፡ ከ2010 ዓ.ም ቀደም ብሎ ትህነግ እየተዳከመ በመጣበት ጊዜ በእሱ ቦታ የኦሮሞ የፖለቲካ ኃይሎችን ተክታ በዚህች አገር ሰላም እንዳይኖር ለመስራት አቅዳ እየተንቀሳቀሰች መሆኑን በዚሁ ጋዜጣ ላይ መጻፌን አስታውሳለሁ፡፡
ታላቁ የሕዳሴ ግድብን የምስራቅ አፍሪካ የሰላም ሥጋት አድርጋ በማቅረብ፣ ይሀን አጀንዳ ለአሜሪካና አጋሮቿ በመስጠት፣ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት  የፀጥታው ምክር ቤት በተደጋጋሚ እንዲሰበሰብ አድርጋለች፡፡ ከሰሞኑ ደግሞ የግብጽ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ሽኩሪ ከአሜሪካ አቻቸው ጋር በኢትዮጵያ ጉዳይ እየመከሩ መሆኑም ተዘግቧል፡፡
የአሜሪካ መንግስት የክፋት ሁሉ ምንጭ ከሆነው ከአሸባሪው ትሕነግ ጋር መንግስት መደራደር አለበት ብሎ ወጥሮ ይዟል። የኢትዮጵያን መንግስት ለማንበርከክ  በማሰብ በተከታታይ በኢኮኖሚና ወታደራዊ ጉዳዮች ላይ ማዕቀብ እየጣለ ነው፡፡ በአለም ዙሪያ ተደማጭነት ባላቸው የቴሌቪዥንና የሬዲዮ ጣቢያዎችና የዜና ተቋማት የሀሰት ወሬ እያራገበ ነው። “አዲስ አበባ አለቀላት” በሚል ዘገባም በአዲስ አበባ የሚኖሩ የውጭ አገር ሰዎችን ብቻ ሳይሆን ኢትዮጵውያንን ለማሸበር የሚችሉትን ሁሉ እያደረጉ ነው፡፡
ይህ በእንዲህ ላይ እንዳለ፤ የፕሬዝዳነት ባይደን የአፍሪካ ቀንድ ጉዳይ ልዩ መልዕክተኛ የሆኑት ጀፍሪ ፊልትማን አዲስ አበባ በተደጋጋሚ እየተመላለሱ፣ ከኢትዮጵያ መንግስት ከፍተኛ ባለስልጣናት ጋር እየተገናኙና እየተነጋገሩ ናቸው። ንግግራቸው እያስገኘ ስላለው ውጤት የታወቀ ነገር የለም፡፡ እኔ ግን እላለሁ “ከእባብ እንቁላል የእርግብ ጫጩት     ስለማይፈለፈል የኢትዮጵያ መንግስት አሜሪካንና አጋሮቿን ከጀርባ ሆና የምትፈልገውን ለማስፈፀም የምትጥረውን ግብፅ ጨምሮ ገለል በሉልኝ፤ ለራሴ ችግር ራሴ መፍትሔውን ልፈልግበት” ማለት አለባት፡፡ በግልፅ አማርኛ፤ ፊልትማን አዲስ አበባ ላይ ሆነው ቢያታከሱ እንጂ መፍትሔ ስለማያመጡ ወደ ኢትዮጵያ እንዳይገቡ ማድረግ ይኖርባታል፡፡
ኢትዮጵያ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ሥር ናት፡፡ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ኢትዮጵያን ለመታደግ መዋል አለባት፡፡ መንግስት አስቸኳይ አዋጁን ሽፋን በማድረግ በንፁሀን ዜጎች ላይ በደል አንዳይ ፈፅም መጠንቀቅ አለበት፡፡ በየትኛውም የኢኮኖሚና የኑሮ ደረጃ፣ ከየትኛውም የህብረተሰብ ክፍል ተጠርጥረው በሚያዙ ሰዎች የተነሳ ዘር እየተቆጠረ በሚቀርብበት ክስ መረበሽ ግን አይኖርበትም፡፡ ዛሬም በሰላም ውለው የሚገቡ በሺህ የሚቆጠሩ ትግራዋይ መኖራቸውን ማስረጃ በመስጠት ክሱን ፉርሽ ማድረግ ይጠበቅበታል፡፡ ይህ ተግባር ቸል መባል አይኖርበትም፡፡
ሕግ የማስከበሩ ዘመቻ እንደተጀመረ መከላከያ  ከሃያ ቀን ባነሰ ጊዜ ውስጥ መቀሌ መድረስ የቻለው ባለው ኃይል የበላይነት ብቻ ሳይሆን የትግራይ ሕዝብም ከትሕነግ  ለመገላገል በነበነረው ፅኑ ፍላጎት እገዛ ነው የሚል እምነት አለኝ፡፡ እምነቴ እንዲፈርስና ሕዝቡ ከአሸባሪው የትሕነግ ጎን እንዲሰለፍ ያደረገው መንግስት ሰባየትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር  አድርጎ የሾማቸውን ሰዎች ፈጥኖ ለመለወጥ ባለመቻሉና እነሱ ደግሞ በተግባር እንዳረጋገጡት ሲሠሩ የነበረው በመንግስት ባጀት ለትሕነግ ስለነበር ነው፡፡ “ያመኑት ፈረስ ይጥላል በደንደስ” የሚለው ተረት ነው እውን የሆነው፡፡ መንግስት በውስጡ ያሉትን ፀረ አንድነት ኃይሎች መመንጠር፣ አሸባሪውን ትሕነግን ለመፋለም ቆርጠው የተነሱትን ኃይሎች ማሰባሰብ  ማጠናከርና ማስታጠቅ ይኖርበታል፡፡
የድንበር ተዋሳኝ በመሆናቸው ምክንያት ለወራሪው ተጋለጭ መሆናቸውን ማስቀረት ባይቻልም፣ አሸባሪውን የትሕነግ ኃይል የመፋለሙ ተግባር በአማራና በአፋር ሚሊሺያና ልዩ ኃይል ትከሻ ላይ ብቻ መጣል የለበትም፡፡ መከላከያ እንዳለ ሆኖ የተጀመረው የሌሎች ክልሎች ልዩ ኃይልና ሚሊሺያ ሠራዊት ወደ ውጊያ ግንባር የማስገባት  ተግባር መቀጠል ይገባዋል፡፡ ወደ ግንባር የሚገባው የየአካባቢው ሚሊሺያና ልዩ ኃይል፣ ፋኖ ወዘተ ዲሽቃና መሰል መሣሪያዎችን ከታጠቀው የትሕነግ ኃይል ጋር የሚዋጋ  በመሆኑ ተመሳሳይ ትጥቅ እንደኖረው ማድረግ የግድ ነው። የነፍስ ወከፍ መሳሪያ የያዘን ወገን እስከ አፍንጫው ከታጠቀ ኃይል ፊት ለፊት አሳልፎ፣  ድል መጠበቅ ትክክል  ካለመሆኑ በላይ፣ ለወገን ሕይወት ዋጋ መንፈግ ሆኖ እንዳይቆጠር ሊታሰብበት ይገባል። ግልፅም ነው፡፡
ከአራት ወር በፊት  ምዕራባውያን ለትሕግ የሳተላይት መረጃ እንደሚሰጡ ጥርጣሬ የነበራቸውን ሰዎች አውቃለሁ። ከሁለት ወር በፊት ደግሞ በተለይ በወልዲያ ግንባር ላይ ከትሕነግ ጎን ተሰልፈው የሚዋጉ የውጭ አገር ሰዎች እንዳሉ (ሬሳቸው አንደተገኘ) መዘገቡን ትዝ ይለኛል፡፡ መንግስት ሁለቱንም ጉዳዮች ለሕዝብ ይፋ ያደረገው በዚህ ሳምንት ነው፡፡ መንግስት በመረጃ አሰጣጥ ላይ እያሳየ ያለው ቸልተኝነት በአገር ላይ ለከፍተኛ ጉዳት እያስከተለ መሆኑ በተደጋጋሚ ተነግሯል፡፡ መታረም አለበት! መታረም አለበት! አስር ጊዜ፡፡
ተራራው ወደ እኛ ስለማይመጣ እኛ ወደ ተራራው መሄድ ግድ አለበን፡፡ ሰሞኑን ወይዘሪት ብሌኒ ስዮም ከሲኤንኤን ቴሌቪዥን ጋር ያደረገት ክርክር መቀጠል አለበት፡፡ ጋባዥ ከተገኘ በግብዣ ካልተገኘም በግድ ጥያቄ በማቅረብ ላሰራጩት ዘገባ መልስ ወይም ማብራሪያ መስጠት አስፈላጊ መሆኑን በማሳመን ፍልሚያው መቀጠል ይኖርበታል፡፡ በተለይም ደግሞ የኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ሚኒስቴር ኃላፊነቱን መወጣት ይኖርበታል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ “ኢትዮጵያ አትፈርስም፤ ኢትዮጵያን የምታፈርሷት እኛ ከፈረስን በኋላ ነው”፤ ማለታቸውን አስታውሳለሁ፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለገቡት ቃል ታማኝ እንደሚሆኑ ተስፋ አለኝ፡፡
ቃላቸው እውን ሊሆን የሚችለው ግን መከላከያ ከአራት ወር በፊት  አቅርቦት ነበር በሚባለው ሃሳብ መሰረት ጦርነቱን ወደ ትግራይ ክልል መመለስ ሲቻልና ትሕነግ ከያዛቸው የአማራ አካባቢዎች ሲወጣ ነው፡፡ ትህነግ የሚወረው አካባቢ በሰፋ ቁጥር የያዘውን ለማስለቀቅ የሚጠይቀው መስዋዕትነት እጅግ እየከበደ እንደሚሄድ መታወቅ አለበት። መንግስት ትሕነግ በሚከፍተው የጦር ሜዳ ለመከላከል ከመዝመት ይልቅ የራሱን የጦር ሜዳ ከፍቶ ትህነግን ተከላካይ እንዲሆን ሲያስገድደው ይገባል። “ቆረጣ እችላለሁ” የሚለውን ይሄን ቡድን ደጋግሞ መቁረጥ የግድ ነው።
“አሁን አንፅፋለን” መታወቅ አለበት-ብለዋል። መንግስቱ ለማ- ለሊቀመንበር መንግስቱ ኃይለማርያም። እኔ ደግሞ የጦር ሙያተኛ ሆኜ ሳይሆን የሚታየኝን የሚሰማኝን ለመግለጥ ነው የተነሳሁት፡፡ ይህ የእኔ ሃሳብ ብቻ ሳይሆን የብዙዎች ነው ብዬ አምናለሁ፡፡ የምጮኸው የምንጮኸው ለመስማማት ነው። በአጭር  ጊዜም ድል ተገኝቶ ሰላማችንን ለመቀዳጀት!! ኢትዮጵያን ፈጣሪ ይጠብቃት!!


Read 8531 times