Sunday, 14 November 2021 00:00

በሦስት በሦስት ለምን? ምትሃተኛ ቁጥር ነው?

Written by  ዮሃንስ ሰ
Rate this item
(0 votes)

ቁጥር ያልተማረ ሰው፣ ሁለት ብርና ሦስት ብርን መለየት አያቅተውም። በንግግርም በጽሑፍም በጭራሽ ስለ ቁጥር አይቶም ሰምቶም የማያውቅ ሠው፣… ጨርሶ ስለቁጥር፣ ቅንጣት አያውቅም ማለት አይደለም።
በቀኝ በኩል ያሉት ሁለት ዛፎች፣ በግራ በኩል ካለው አንድ ዛፍ፣ የብዛት ልዩነት እንዳላቸው፣ በአይኑ በብረቱ ማየት ይችላል። ከፊት ለፊት የበቀሉ ሦስት ዛፎችን ሲመለከትም፣ ብዛታቸው ይገባዋል። ችግሩ፣ ከዚህ በኋላ ነው የሚመጣው።
አራት ዛፎችንና አምስት ዛፎችን አሳዩት። የብዛት ልዩነታቸውን ለመረዳት ይቸገራል - ቁጥር ያልተማረ ሰው። ስድስት፣ ሰባት ከሆኑስ? ከዚህ ከበረከቱማ፣ የትኞቹ እንደሚበዙ ማወቅ አይችልም። በአጭሩ፣… የብዛት ግንዛቤው፣… “1፣ 2፣ 3፣ 4፣…. ብዙ፣ በጣም ብዙ፣ እጅግ ብዙ”….  በሚያሰኝ ዓለም ውስጥ የታጠረ ነው ማለት ይቻላል።
አየን ራንድ (Ayn Rand)፣ ይህን እውነታ የገለፀችው፣ ከ50 ዓመታት በፊት ነው። ከዚያ ወዲህ እየተስፋፉ የመጡት ዘመናዊ የአንጎልና የአእምሮ ምርምሮችም (የኒሮሳይንስና የኮግኒቲቭ ሳይኮሎጂ ምርምሮችም)  እውነታውን አረጋግጠውታል።    
እዚህ ላይ ሦስት ቁምነገሮች አሉ።
አንደኛ ነገር፣ የሰዎች ቅፅበታዊና ቀጥተኛ የግንዛቤ አቅም፣ በጣት የሚቆጠር ነው፡፡ 1፣2፣3፣4 ከዚህ ብዙም አይበልጥም፡፡ በጣም ትንሽ ይመስላል - ከአፍንጫችን ብዙም ርቆ የማይሻገር ጠባብ አድማስ።
ግን በቃ! የተፈጥሮ እውነታ ነው - ይላሉ የኒሮሳይንስ ተመራማሪዋ ዶ/ር ሄለን አባዝ (Helen Abadzi)። ሁሉም እውቀትና ሃሳብ፣ በዚህ “ተፈጥሯዊ” አቅም ላይ የተመሠረተ እንደሆነም ያስተምራሉ። በሌላ አነጋገር፣ “መሰረታዊው” የግንዛቤ አቅም፣ የመጨረሻ አቅም አይደለም። “መነሻ” አቅም ነው።
በአጭሩ፣ “ተፈጥሯዊ፣ መሠረታዊና መነሻ የግንዛቤ አቅም” ተብሎ ሊሰየም ይችላል - “ኢምንትና ቅንጣት የመሰለው መነሻ አቅም”።
በቀጥታና በቅፅበት፣ የእውኑ ዓለም መረጃዎችን እናገኝበታለን - የእውቀትና የትምህርት ይዘት (content)፣ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ፣ ከዚህ ውጭ ሊሆን አይገባውም። ደግሞስ፣ ከእውነተኛ መረጃ ውጭ ምን አይነት እውቀትና ትምህርት ሊኖር ይችላል? ቢኖርስ፣ ምኑ እውቀት ይባል? ምኑስ ትምህርት ይሆናል? ይህም ብቻ አይደለም።
ቀጥተኛውና ቅፅበታዊው የግንዛቤ አቅም፣ በጣም ትንሽ ቢመስለንም፣ ኢምንትና ቅንጣት ሆኖ ቢታየንም፣ እዚያው ላይ መክኖና ደንዝዞ አይቀርም። የማወቂያና የመማሪያ ዘዴ (method) ለመፍጠር ይጠቅማል፤ ፈር መያዣ ይሆንልናል - ካወቅንበት። እናም፣ ስፍር ቁጥር የሌላቸው ሃሳቦችን በአይነትና በብዛት ለማፍራት፣ እጅግ ሰፊና ጥልቅ እውቀትን ለማበልፀግ ያገለግለናል።
ሁለተኛ ነገር፣ የሰዎች የእውቀት ምጥቀትና ጥልቀት፣ የሃሳቦች አይነትና ብዛት ሲታይ፣ ለማመን ይከብዳል። ይደንቃል። ታዲያ፣ ተፈጥሯዊ የግንዛቤ መነሻ አቅማችን፣ እንዴት እንደ ኢምንት ያነሰ፣ እንደ ቅንጣት የጠበበ ሊሆን ይችላል? ሊሆን አይችልም ያሰኛል።
( ……… )
ግን ደግሞ ይታያችሁ። ሃያ እና ሃያ አንድ ዛፎችን ስንመለከት፣ በእይታ ብቻ የብዛት ልዩነታቸውን ማወቅ ብንችል አስቡት። እንደዚያ አይነት ቅፅበታዊ የግንዛቤ አቅም ቢኖረን፣ “አንድ፣ ሁለት…” ብለን ቁጥር መማራችን ምን ይጠቅመናል?
( ………. )   
እንዲያውም፣ ሃያ እና ሃያ አንድ፣ በጣም ብዙ ነው። ከላይ በሁለት ቦታዎች፣ በቅንፍ ውስጥ  ያሉትን ነጥቦች ተመልከቱ። ሳንቆጥር፣ ብዛታቸውን ማወቅ አንችልም። ምን ለማለት ፈልጌ ነው? ነገርየው ያን ያህልም የተወሳሰበ ጉዳይ አይደለም። በገሃድ የምናየው እውነታ ነውና።
ነጥቦቹን አይተናል። ነገር ግን፣ በእይታ ብቻ፣ የዘጠኝ እና የአስር ነጥቦችን ልዩነት፣ በቅፅበት መገንዘብ አንችልም።
ደግነቱ፣ የቁጥር እውቀት፣ የቁጥር ዘዴ አለልን። በመጀመሪያው ቅንፍ ውስጥ ዘጠኝ ነጥቦች፣ በሁለተኛ ቅንፍ ደግሞ 10 ነጥቦች መኖራቸውን በቀላሉ በቆጠራ ለይተን ማወቅ እንችላለን። በእይታ ብቻ ግን አንችልም።
እንዲህም ሆኖ እይታና ቆጠራ፣ እርስበርስ ተደጋጋፊ ናቸው። በእነዚህ መሃል ግን፣ መሸጋገሪያ ድልድይ አለ። እይታ፣ መነሻ አቅም ነው። ቆጠራ የእውቀት ግኝትና ዘዴ ነው። በእነዚህ መሃል ምን አለ?
ሦስተኛ ነገር፣ ተፈጥሯዊው መነሻ አቅማችን፣ አዲስ የማወቂያ ዘዴ ለመፍጠር እንደሚያገለግል፣ በቀላል ምሳሌ እንመልከት።
(… … …)
የእነዚህን ነጥቦች ብዛት፣ በእይታ ብቻ፣ በቅፅበት ለመገንዘብ ይከብደናል? ዘጠኝ ናቸው። ዘጠኝ ብለን በስም ባንጠራቸው እንኳ፣ ሦስት ባለ ሦስት ነጥቦች መሆነቸውን፣ በእይታ ብቻ መረዳት አያቅተንም - ያለ ስሌት፣ ያለ ብዜት፣ በቅፅበትና በቀጥታ ልንገነዘበው እንችላለን።
አንድ ነጥብ ስንጨምርበት፣ ልዩነቱን ለመገንዘብ፣ ተጨማሪ አቅም አይጠይቀንም - በማየት ብቻ ልዩነቱ ይገባናል።
(… … … .)
እነዚህን ነጥቦች በእይታ ብቻ መገንዘብ የቻልነው አለምክንያት አይደለም። ዘጠኙን ነጥቦች ወደ ሦስት ማዕቀፍ፣ አስሩን ነጥቦች ወደ አራት ማዕቀፍ በቅጥ ማዋቀራችን ነው የጠቀመን። ሦስት ወይም አራት ነገሮችን ደግሞ በእይታ ብቻ መገንዘብ እንችላለን። ይሄ ወደ እውቀት ዘዴ ያሻግረናል፡፡
 ብዙ እልፍ አእላፍ ነገሮችን በሦስት ማዕቀፍ የማደራጀት ዘዴ፣ በሁሉም የእውቀት መስኮች ውስጥ የሚታይ እጅግ የተለመደ ዘዴ ነው።
በሦስት ፍርጅ የመተንተን ዘዴ፣ በሦስት ማዕቀፍ የማጠቃለል ዘዴ፣ በዘፈቀደ የመጣ  ዘዴ አይደለም። ከአእምሮአችን ተፈጥሮ ጋር የሚጣጣም ዘዴ ነው።
ብዙ ነገሮችን ስንቆጥር፣ 124፣ 125፣… እያልን 126 ጋ ስንደርስ፣ ትኩረትን የሚያናጥብና የሚያዘናጋ ነገር ቢገጥመን ምን እናደርጋለን?  በዝንጋታ እንዳንሳሳት፣…. ስንት ላይ እንደደረስን ማስታወሻ ነገር እንፅፋለን። ወይም፣ 126፣ 126 እያሉ፣ ቁጥሩን በቃል መደጋገምም ይቻላል - ላለመርሳት። ወደ ቆጠራ ስንመለስስ?
የቆጠርናቸውን ነገሮች ወደ ጎን ለይተን፣ አንድ ተጨማሪ አክለን፣ 127 ብለን እንቀጥላለን - ያልቆጠርናቸውን ወዲያ ለይተን።
ነገሮቹ እጅግ ብዙ ቢሆኑም፣ ዘዴ አበጅተናል። ሦስት ነገሮችን ብቻ ነው ማስታወስ የሚጠበቅብን - የእልፍ ነገሮችን ብዛት በቆጠራ ለማወቅ።
ከቀኝ በኩል ያስቀመጥናቸው ሁሉ፣ “የተቆጠሩ” ናቸው።
አንድ ተጨማሪ ስናክልበት፣ 127 ላይ ደርሰናል።
በግራ በኩል የተቀመጡት ሁሉ፣ “ያልተቆጠሩ” ናቸው።
እነዚህን ሦስት ነገሮች ማስታወስ እስከቻልን ድረስ፣ ቆጠራ አይከብደንም። አንድ ቢሊዮን፣ መቶ ቢሊዮን ወይም አንድ ትሪሊዮን በቁጥር ስንጽፍ፣ በሦስት በሦስት ቁጥሮች መሃል፣ጭረት እንጠቀማለን፡፡ ለምን? በእይታ ብቻ ቁጥሩን ለመገንዘብ ያመቻል። ስልክ ቁጥሮችን ስንጽፍም በጥንድ በጥንድ አጣምረን የምንጽፈውም በሌላ ምክንያት አይደለም- ለግንዛቤ ስለሚመች ነው።
ሶስት ምትሃተኛ ቁጥር አይደለም በሁለት ወይም በአራት ማዕቀፍ ማጣመርም ይቻላል እንደ ጉዳዩ ተፈጥሮ፡፡ ዋናው ነገር፣ አለመንዛዛቱ፣ ለግንዛቤ መመቸቱ ነው፡፡




Read 1141 times