Print this page
Saturday, 20 November 2021 14:25

አዲስ አበባን ከህገወጥ ተግባራት የማፅዳቱ ዘመቻ ተጠናክሮ ይቀጥላል -ፖሊስ

Written by  መታሰቢያ ሳሣዬ
Rate this item
(1 Vote)

   - በአንድ ሳምንት ብቻ በርካታ አደንዛዥ እፆች፣ በ10 ሺዎች የሚቆጠር ጥይት፣ ክላሽንኮቭ ጠመንጃዎችና ሽጉጦች ከ270 በላይ ሲም ካርድ ተገኝተዋል
    - ፖሊስ በአስክሬን ሳጥን ተቀበረ የተባለው ጦር መሳሪያ አለመሆኑን አረጋግጧል አረጋግጫለሁ ብሏል።
                 
             አዲስ አበባን ከህገ-ወጥ የጦር መሳሪያና ህገ-ወጥ ተግባራት የማፅዳቱ ስራ ተጠናክሮ መቀጠሉን ፖሊስ አስታውቋል። በአንድ ሳምንት ብቻ ከግለሰቦች በተገኘ ጥቆማና ጥርጣሬ ፍተሻ በተደረገባቸው ቤቶች፤ በ10ሺዎች የሚቆጠሩ ጥይቶች፣ ክላሽንኮቭ ጠመንጃዎችና ሽጉጦች፣ አደንዛዥ ዕጾች ሀሰተኛ ሰነዶችና ለሰነድ መስሪያ የሚያገለግሉ ህገ-ወጥ መሳሪያዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ተገልጿል።
ከአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን የተገኘ መረጃ እንደሚያመለክተው፤ ከህዳር 5 ቀን 2014 ዓ.ም ጀምሮ በአዲስ አበባ ከተማ በተለያዩ አካባቢዎች ከህብረተሰቡ በደረሱ ጥቆማዎች፣ በተደረገ ፍተሻ፣ በርካታ ህገ-ወጥ መሳሪያዎች፣ አደንዛዥ ዕጾች፣ ፈንጂዎችና ቦንቦች፣ የተለያዩ አገራት ገንዘቦች፣ ወርቆችና ሀሰተኛ የመሳሪያ ፍቃዶች ተገኝተዋል።
 በለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ ወረዳ 13 ምስራቅ ሎቄ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ በአንድ ግለሰብ ቤት በተደረገ ፍተሻ፣ መሬት ውስጥ ተቆፍሮ በላስቲክ ተጠቅልሎ የተቀበሩ ሽጉጦች፣ ጥይቶች፣ ሳንጃ፣ ገንዘቦችና የወርቅ ጌጣጌጦች ተገኝተዋል። በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ወረዳ 8 ልዩ ቦታው ሸራ ተራ የካቲት 23 ት/ቤት አካባቢ፣ በአንድ ግለሰብ ቤት በተደረገ ድንገተኛ ፍተሻ፤ 276 ሲም ካርዶችና ሃሰተኛ የጦር መሳሪያ ፈቃድ እንዲሁም የሽጉጥ ጥይቶች ተገኝተዋል።
በየካ ክፍለ ከተማ ለአሸባሪው ህውሃት ድጋፍ ሊውል እንደነበር የተገለጹ 37ሺ የአሜሪካ ዶላርና የጦር መሳያዎች በፍተሻ ተገኝተዋል። በልደታ ክፍለ ከተማ ቀበሌ 10 ውስጥ በተደረገ ድንገተኛ ፍተሻ፤ በርካታ ህገወጥ ሃሰተኛ ሰነዶች ከነመሳሪያዎቻቸው በቁጥጥር ስር ውለዋል።
የቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 7 አስተዳደር ወሳኝ ኩነት ምዝገባ የስራ ሂደት ላይ ተመድቦ ሲሰራ የነበረ አንድ ግለሰብ ቤት በተደረገ ፍተሻ፤ በህገወጥ መንገድ የተሰሩ በርካታ ሰነዶች ሃሰተኛ ክብ ማህተምና ቲተሮች መገኘታቸውንም የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን አስታውቋል።
ፖሊስ በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ወረዳ 1 ልዩ ቦታው አሜሪካን ግቢ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ፣ ከብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት፣ ከፌደራል ፖሊስና ከህብረተሰቡ ጋር በመቀናጀት ባደረገው ድንገተኛ ፍተሻ፤ በላስቲክ ቤት ውስጥ በመሆን የተለያዩ ሰነዶችን ሃሰተኛ ፓስፖርችን የተለያዩ የቀበሌ መታወቂያዎችን ሲያዘጋጅ የነበረ ግለሰብ ከነኤግዚቢሽኖቹ በቁጥጥር ስር ውሏል። ተጠርጣሪው ግለሰብ የሽብር ቡድኖቹን እኩይ አላማ ለማስፈጸምና ለሰርጎ ገቦች ምቹ ሁኔታ ለመፍጠር በማሰብ ህገወጥ ሰነዶችን ሲያዘጋጅ እንደነበርም ፖሊስ አመልክቷል።
አራት ኪሎ በሚገኘው የተቅላይ ቤተ ክህነት ግቢ፣ በንብረት ግምጃ ቤት ውስጥ የተቀመጡ ከ1ሺ 800 በላይ ጥይቶችን በቁጥጥር ስር፣ ማዋሉን የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ያስታወቀውም በዚሁ በያዝነው ሳምንት ውስጥ ነው። በአራዳ ክፍለ ከተማ ወረዳ 9 ውስጥ በሚገኘው የጠቅላይ ቤተ ክህነት ዕቃ ግምጃ ቤት ውስጥ የተገኙት 1ሺ 363 የብሬን እና 493 የሽጉጥ ጥይቶችና  2 የጥይት  ማስቀመጫ ሳጥኖች፣ 1 የክላሽንኮቭ ጠመንጃ ካዝና መያዙም ተገልጿል።
ከጉዳዩ ጋር በተያያዘም አንድ ተጠርጣሪ ግለሰብን በቁጥጥር ስር ማዋሉን ፖሊስ አስታውቋል።
ሰሞኑን በአዲስ አበባ ከተማ ልደታ ክፍለ ከተማ ተክለሃይማኖት ቤተክርስቲያን ውስጥ በአስከሬን ሳጥን ተደርጎ የተቀበረ የጦር መሳሪያ ተያዘ በሚል በተለያዩ ማህበራዊ ሚዲያዎች የተናፈሰው ወሬ ትክክለኛ መረጃ አለመሆኑን ፖሊስ አረጋግጫለሁ ብሏል። ፖሊስ ከልደታ ክፍለ ከተማ አገኘሁት ባለው መረጃ መሰረት፣ ግለሰቡ ከኢትዮጵያ ውጪ በመሞቱ ምክንያት ተክለሃይማኖት አካባቢ ሟቹን የሚያቁት ነዋሪዎች አስፈላጊውን ህጋዊ ሂደት ተከትለው ከውጪ እንዲመጣ በማድረግ አስክሬኑ በተክለሃይማኖት ቤተ ክርስቲያን እንዲያርፍ አድርገዋል። ቀብሩ በተፈጸመበት ወቅት ጥቂት ሰዎች የተገኙ በመሆኑና የአስክሬን ሳጥኑ ከመደበኛውና ከሚታወቀው ለየት ያለ መሆኑ ያጠራጠራቸው የህብረተሰብ ክፍሎች ለፖሊስ መረጃ እንዲደርስ ማድረጋቸውን ፖሊስ አመልክቷል።
ፖሊስ የደረሰውን መረጃ መነሻ በማድረግ ኮሚቴ አዋቅሮ ከቤተ ክርስቲያን አባቶች ጋር በመሆን ፍተሻ በማረግ በተቀበረው የአስክሬን ሳጥን ውስጥ የሰው አስክሬን እንጂ ምንም ዓይነት የጦር መሳሪያ አለመገኘቱን ማረጋገጡን አመልክቷል።
አዲስ አበባን የማጽዳቱ ተግባር አሁንም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ያስታወቀው ፖሊስ፤  ህብረተሰቡ ማንኛውንም አጠራጣሪ ነገር በሚመለከትበት ወቅት ለፀጥታ አካላት የማሳወቁን ተግባር አጠናክሮ እንዲቀጥል አሳስቧል።


Read 11241 times