Print this page
Saturday, 20 November 2021 14:33

“አጓጉል ትውልድ ያባቱን መቃብር ይንድ”

Written by 
Rate this item
(6 votes)

   ከዕለታት አንድ ቀን አንድ ልጅ ሁልጊዜ መኝታ ቤቱን ይዘጋና ይፀልያል፡፡
 “አምላኬ ሆይ ያባቴን የንጉሱን መንግስት ወራሽ እሆን ዘንድ እባክህ ያረጀውን አባቴን በግዜ ከዚህ አለም አሰናብትልኝ” ይላል። ይህንን የልጁን ፀሎት የሰማው አባት፤ አንድ ቀን በጨለማ መልዕክተኛ መላዕክት ተመስሎ፤ “ወጣት ሆይ፤ ፀሎትህ ተሰምቶልሀል፤ አባትህ ከእንግዲህ በህይወት የሚቆየው ጥቂት ጊዜ ነው” አለው። ከዚያን ቀን ጀምሮ አባት የታመመ መስሎ ተኛ። በግራም በቀኝም ልጁ ላይ ጠላቶች ተነሱበት። መንግስቱንም ለመገልበጥ ያሴሩ ጀመር። ልጅ ጭንቅ በጭንቅ ሆነ። አምላኩንም ይማጠን ገባ፡- “አምላኬ ሆይ፤ ከውስጥም ከውጭም ተከበብኩ፤ ምን ባደርግ ይበጀኛል?”
አምላክም እንዲህ አለው ወደ አባትህ ዘንድ ሂድምክርንም ጠይቀው፤ መዳኛህ የርሱ ምክር ነው፡፡
ልጅ እየሮጠ ወደ  አባቱ ሄደ።
 “አባቴም ክርህን እሻለሁ” አለው። አባትም “በመጨረሻ ወደ እኔ መጣህ፤ አሁንም አልረፈደም የምልህን አድርግ” ብሎ ጀመረ።
በመከራ ሰአት የቅርብ ሰው እንደሚያስፈልግህ አትርሳ፤ ከቶውንም ለውርስ ብለህ ያባትህን ሞት አትመኝ፤ ተጣጥረህ በግንባርህ ወዝ ብላ እንጂ ባቋራጭ መንገድ ለመበልፀግ አትሞክር፤ አባትህ መመኪያህ ነው፤ ማዕረግህ ነው፤ ማስፈራሪያህ ነው አባትህ የኋላ ታሪክ ያለው ስለሆነ ባላንጣዎች ሁሉ አንተን ባለታሪክ አድርገው ያዩሀል፣ ይፈሩሀል፤ ድንበርህን አይነኩም ጠላትህን አትናቅ፤ በራስህ ተማምነህ በራስህ ቆመህ አገርህን በትክክል እንድትመራ፤ የሚያደርግህ ያ ብቻ ነው፡፡
እንደውነቱ ከሆነ ዋነኛው የታላቅነታችን ምልክት አበው የሚሉንን ማዳመጣችን ነው። አገር የምትድነው ትላንትናዋን መሰረቷን አጥብቃ ይዛ ስተትጓዝ ነው። ህዝብ ነገውን የሚያውቀውና አምኖ የሚራመደው ታሪኩን ሲገነዘብ ነው፤ ወዴት እንደሚሄድ የማያውቅ ህዝብ፣ ዳፍተኝነት ያጠቀቃዋል፡፡
ተስፋ ለመቀርቀብ እንቅፋት ይበዛበታል። ስለዚህም በምንም መልኩ ቢሆን ወዴት እንደሚሄድ   ማወቅ ግዴታ ነው። መንግስት ይለዋወጣል እንጂ ሕዝብ አይለዋወጥም፡፡ ከውድቀቱ የሚማር ብቻ ነው የብልህ መንግስት። ልጆቹም የተማሩ የበቁና የላቁ የሚሆኑት፣ ለጥበብ ቅድሚያ ሲሰጡ ነው፡፡
ጥበብን ያልያዙ ልጆች እድገታቸው የቀጨጨ ይሆናል፡፡ በምንም አይነት ያባታቸውን ማንነት ያልያዙና ያላበለፀጉ ልጆች ለመበርገግ ቅርብ ናቸው። ስለዚህ ፅናትም ቅናትም እንዲኖራቸው ማድረግ ተገቢ ነው፡፡
ያለበለዚያ “አጓጉል ትውልድ ያባቱን መቃብር ይንድ” የሚለው ብሂል ይከሰታል፡፡ ስለዚህ ዛሬ ላይ ቆመን ነገን እናስብ ነገ ላይ እናተኩር፤ ለማደግ ቅርብ የምንሆነው ስለ ነገ ስናውቅ ነውና!


Read 13316 times
Administrator

Latest from Administrator