Print this page
Saturday, 20 November 2021 14:41

“ብቻዬን እቆማለሁ” “ኢትዮጵያ ብቻሽን አትቆሚም”

Written by  ናፍቆት ዩሴፍ
Rate this item
(0 votes)

    የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ባህል ኪነ-ጥበብና ቱሪዝም ቢሮ፣ ረቡዕ ምሽት በብሔራዊ ቴአትር “ብቻዬን እቆማለሁ” በሚል መሪ ቃል ሁሉን አቀፍ የኪነ-ጥበብ (ሁባሬ ጥበባት) ምሽት አሰናድቶ ነበር። በምሽቱ ግጥም፣ ስዕል፣ ሰርከስ፣ ዲስኩርና ሙዚቃን ሌሎች ጥበባዊ ዝግጅቶች ቀርበዋል። ሰለሞን ሳህለ፣ ሱራፌል ተካ፣ ኤልያስ ሽታሁንና ተስፋዬ ማሞ ግጥም ሲያቀርቡ፣ ዶ/ር ወዳጄነህ መሃረነ ደራሲና ጋዜጠኛ ጥበቡ በለጠ፣ ሙሃዘ ጥበባት ዲያቆን ዳንኤል ክብረት፣ የሙዚቃ ባለሙያ ሰርፀ ፍሬ ስብሃትና መሃመድ ካሳ ሀገራችን ያለችበትን ወቅታዊ የህልውና ፈተና፣ ከኪነ-ጥበብና ጥበበኞች፣ ከታሪክ፣ ከሃይማኖት አስተምህሮ፣ ከስነ-ልቦናና ከአጠቃላይ ተጨባጭ ሁኔታ ጋር በማነጻጸር ድንቅ ትምህርት የሰጡበት  ሲሆን ምሽቱ ልብን ከሚያሞቁ የጀግንነት ሙዚቃዎችና ከአስደናቂዎቹ የሸገር ሰርከሶች ድንቅ ትርኢት ጋር ተዳምሮ ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያዊነትን ከፍ ያደረገ አስደነቂ ምሽት አልፏል። በዚሁ ምሽት ላይ የታደመችው የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ ናፍቆት ዮሴፍ፤ ተወዳጆቹ የኢትዮጵያ ልጆች ካደረጉት ልብ ኮርኳሪ ንግግር የጥቂቶቹን እንደሚከተለው አጠናቅራዋለች።

                 “ኢትዮጵያ ፈፅሞ ብቻሽን አትቆሚም”
                          ሙሃዘ ጥበባት ዳንኤል ክብረት

           ወደዚህ መርሃ ግብር የጋበዙኝ ሰዎች “ብቻዬን እቆማለሁ” በሚል ዙሪያ ስለ ኢትዮጵያ ንግግር ታደርጋለህ አሉኝ፡፡ እኔ ደግሞ ትንሽ ልገልብጠውና “ብቻሽን አትቆሚም” የሚል ርዕስና ሃሳብ መርጫለሁ፡፡ ኢትዮጵያ ፈፅሞ ብቻሽን አትቆሚም፤ ሰው ቢጠፋ ፈጣሪሽ አለ፤ አብሮሽ ሁልጊዜም የሚቆም፤ ደግሞም ብዙ ልጆች አሉሽ፡፡ አንዳንዴ ለሰዎች ስለማይገለፅ እንጂ ኢትዮጵያ ፈጽሞ ብቻሽን አትቆሚም፡፡ ገበሬው የማዳበሪያ እዳውን ሳይከፍል ምርጥ ዘር በነፃ ባትሰጪው፣ ኢትዮጵያ ተነካች ሲባል ግልብጥ ብሎ ወጥቶ እንደተመመ ብታይው ብቻሽን አትቆሚም፡፡
የመንግስት ሰራተኛውን ብታይው፡፡ በቀደም ከሀረሪ ክልል ፕሬዚዳንት ጋር ስናወራ ምናለኝ፣ “የሀረሪ ፖሊሶችን ሰብስብን ሀገር እንዲህ ዓይነት ችግር ገጥሟታል፤ እስኪ ከእናንተ መካከል መዝመት የሚፈልግ እጁን ያውጣ ብለን ስንጠይቅ፣ በሙሉ እጃቸውን አወጡ፡፡ ይሄማ ከሆነ ሀረሪን ማን ሊጠብቅ ነው ስለዚህ በተራ በተራ እናድርገው፤ እሺ መጀመሪያ መሄድ የምትፈልጉ ስንል ሁሉም እጁን አወጣ፡፡ አይ ከዚህ በፊት በሌላ ዘመቻ ያልተሳተፋችሁ ለእናንተ ቅድሚያ እንስጥ ስንላቸው፤ ለምን? ለሀገር ዝመቱ ነው የተባልነው እንሂድ፤ ህዝቡ ራሱን ይጠብቅ፤ እኛ ኢትዮጵያን እንጠብቃለን አሉ” ብሎ ነገረኝ፡፡ እንዲህ አይነት የሀረሬ ዘማቾች ያሉሽ ሀገር፤ ፈፅሞ ብቻሽን አትቆሚም፡፡
በቀደም አይታችኋል ደቡብ ከ1ሺህ በላይ ከወረዳ እስከ ክልል ያሉ አመራሮች ካልዘመትን ብለው ፕሬዚዳንቱን አንቀው ያዙ፡፡ የለም ቢሮውም ሰው ይፈልጋል፤ በተራ በተራ እናድርገው ተባሉ፤ የለም እንሄዳለን  ጦርነቱ ቢያልቅስ አሉ፡፡ በጣሊያን ጊዜ የሆነውን ታስታውሳላችሁ አይደል? እንዳሁኑ መንግስት ትራንስፖርት ስለማያቀርብ ሁሉም በእግሩ ነበር የሄደው፤ አድዋ ሲደርሱ ጦርነቱ ተጠናቅቆ ደርሰው በጣም የተበሳጩ አሉ ይባላል፤ “እንዴት አንድ እንኳን ፋሽስት ሳናገኝ ጦርነቱን ትጨርሱታላችሁ?!” ብለው እና አሁንም የደቡብም አመራሮች ተሰብስበው በተራ እናድርገው ሲባሉ “ጦርነቱ ቢያልቅስ? ብለዋል፡፡ እንዲህ ያሉ ልጆች እያሉሽ ብቻሽን አትቆሚም፤ ፈፅሞ ብቻሽን አትቆሚም፡፡
ኦሮሚያ ሂዱ ደግሞ፡፡ በአንድ በኩል ከውስጥ እስከ ድንበር ኢትዮጵያ የደከመች እለት ነው፤የምንሸነፈው ቅድም ዶ/ር ወዳጄነህ እንዳለው ሰውነታችን ሲደክም  የሚነሱ በሽታዎች አሉ፤ ጊዜ እየጠበቁ ማለት ነው፡፡ እና ጊዜ ጠብቀው ብድግ ያሉ፣ ከእነሱ ጋር በአንድ በኩል እየተፋለሙ በሌላ በኩል ደግሞ ካልዘመትን ብለው ይህን የኢትዮጵያ የክፉ ቀን ልጅ (መቼም ልጅ ነው ምን እንበለው መቼም ከልጅም ክፉ አለኮ!) ሁለተኛ እንዲህ አይነት ክፉ የማይወጣበት ትምህርት እንስጠው ብለው ዛሬ ግንባር ላይ ከሌሎች ወንድሞቻቸው ጋር ዋጋ እየከፈሉ አግኝቻቸዋለሁ፡፡ ዳባት በሄድኩበት ጊዜ ዳባት ሆስፒታል ላይ ብዙ የኦሮሚያ ልዩ ሀይል አባላትን አግኝቻለሁ፡፡ ጭና በሄድን ጊዜ የጭና ገበሬዎችን “እንዴት ነበር ጦርነቱ?” ብለን ስንጠይቃቸው፤ “አይ ብትኖሩ ብታዩ ነበር” እንጂ እንዴት አድርገን እንነግራችኋለን፡፡ ባያድላችሁ ነው እንጂ ኖራችሁ ብታዩት ደግ ነበር ነው፤ ያሉን፡፡  ይህን ካሜራ ይዛችሁ መምጣታችሁ ካልቀረ ምን ነበር ያን ጊዜ ብትኖሩ” ያሉን፡፡
 “የእኛ መከላከያ እኮ ፍትፍት እየጎረሰ መድፍ እየተኮሰ ነው የተዋጋው” ነው ያሉን እናቶች፡፡ የእኛ እናቶች መድፍ ሥር ቁጭ ብለው  ፍትፍት ለሰራዊቱ፣ እያጎረሱ ሰራዊቱ ለጠላቱ መድፍ እያጎረሰ ነው የተዋጋው፡፡ እንዲህ አይነት እናቶች እያሉሽ ኢትዮጵያ ብቻሽን አትቆሚም፤ በጭራሽ ብቻሽን  አትቆሚም፡፡
ጋምቤላ  ነቅሎ  መጥቷል፤ ሲዳማ፣ ወላይታ  ነቅሎ መጥቷል፤ ሶማሌም ሌላውም ነቅሎ መጥቷል አሁን መንግስት የተቸገረው የሚዘምት አጥቶ ሳይሆን የሚዘምት በዝቶ ነው፡፡ አሁን የዘማች እጥረት የለብንም፤ የቀሪ እጥረት ነው ያለው፡፡ አሁን ሰው ደሙ ፈልቶ ተንተክትኮ ጦርነቱ ላይ ሳልደርስ ጦርነቱ እንዳያልቅ የሚል ስሜት ውስጥ ናቸው፡፡ ልጆችሽ በዚህ ሁኔታ እያሉ ምድር እያንቀጠቀጡ፣ ኢትዮጵያ እንዴት ብቻሽን ትቆሚያለሽ፤ በጭራሽ ብቻሽን አትቆሚም፡፡ እስኪ አፋሮቹን እዩአቸው፡፡ በቅርቡ የአፋር እናቶች ታሪክ እኮ ነው የሰሩት፡፡ ልክ እንደ እቴጌ ጣይቱ፡፡ ተዋግተው ተዋግተው  እንደምታውቁት በአፋር በረሃ ውሃ ውድ ነው፡፡ ውሃውን የያዘ ነው የሚያሸንፈው፡፡  እነዚህ እናቶች ሄዱና የውሃ ጉድጓዶችን ቆርጠው ያዙባቸው፡፡ ጠላት ምን ይጠጣ? “እባካችሁ ውሃ አጠጡን” አሏቸው፡፡ የአፋር እናቶች ምናሉ? “ክላሻችሁን ስጡንና!” እንዲህ አይነት “ጁንታው ሚሌን ከሚይዝ ግመል ቀንድ ብታወጣ ይሻላታል” የሚሉ ጀግኖች እያሉሽ፣ ኢትዮጵያ ፈጽሞ ብቻሽን አትቆሚም፡፡
የኪነ-ጥበብ ባለሙያው ካልዘመትኩ ብሎ የሚያስቸግርባት አገር እኮ ናት፡፡ በቀደም የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ስብስባ ነበራቸው፤ ተወያይተው ሲጨርሱ “እንዝመት፤  እኛ እዚህ ቁጭ ብሎ ህግ ማውጣት፣ ህግ ማርቀቅና ማፅደቅ ምን ይጠቅማል?!” አሉ፡፡ አቶ ታገሰ ጫፎ ቆይ እስኪ ቆዩ እኛ እዚህ ስራ እንሰራለን አሉ፡፡ አይ የለም እንዝመት፤ እኛ የምንሞትም ከሆነ የተረፋችሁት ህጉን ታወጡታላችሁ፤ እንዲህ ባለ ጊዜ እዚህ እንደመቀመጥ ያለ ሃጢያት የለም” የሚሉ ዜጎች ያሉብሽ ሀገር፤ ፈፅሞ ብቻሽን አትቆሚም፡፡
እስኪ የልጆቻችሁን የሕፃናቱን ልብና መንፈስ ልብ በሉት፡፡ እንዴት ነው ስለ ኢትዮጵያ እየተንገበገበ ያለው፡፡ ዕድሜና አቅማቸው ሁኔታዎች አልፈቅድ ብሎ እንጂ  ህግም እድሜም የሚፈቅድ ቢሆን፣ አገር እንዲህ ሆና ህጻን ቁጭ ይል ነበር? እነዚህ ሁሉ ተንገብግበው የሚነሱልሽ ኢትዮጵያ፤ ብቻሽን አትቆሚም፤ ቆመሽም አታውቂም! ብታጪ ብታጪ ፈጣሪ አታጪም! ዛሬ የኢትዮጵያ ልጆች እንደ እሳት የተነሱበት ጊዜ ነው፡፡ በነገራችን ላይ የኢትዮጵያን ታሪክ ዝም ብላችሁ ስታዩት አንዲት ነጥብ አለች፡፡
የጠላት ግፍና ትዕቢት እያየለ፣ እያየለ እየጨመረ ሄዶ፣የኢትዮጵያውያን ትዕግስትና ቻይነት እያለቀ ሄዶ፣ የሚገናኙበት አንዲት ነጥቦች አለች፡፡
 ያቺ መገናኛ ነጥብ የደረሰች ቀን፤ ከኢትዮጵያ ሰራዊት ፊት ከመቆም ገለባ ከእሳት ፊት ቢቆም ይሻለዋል፡፡ ቅቤ የጋለ ብረት ምጣድ ላይ ቢቀመጥ የመትረፍ እድል አለው፡፡ በዚያን ጊዜ በኢትዮጵያ ሰራዊት ፊት ከመቆም ቅቤ ብረት ምጣድ ላይ ሆኖ መልሶ የመገኘት እድሉ የሰፋ ነው፡፡ አለች ያቺ ነጥብ፤ ያቺ እስክትደርስ ይታገሳል ይችላል፣ ለአንዳንዶቻችን ምስጢር እስከሚሆንብን ድረስ! “አልገባውም ተሸውዷል” እስክንል ድረስ! እንዳይመስላችሁ፣ አለች ያቺ ነጥብ፡፡
ብሎ ብሎ፣ብሎ ታግሶ ቷ ብሎ የሚነሳበት! ከተነሳ ማንም አይመልሰውም፡፡ እንኳንስ ጠላቱ መሪውም አይመስለውም ያን ጊዜ፡፡ እኔ ግን ይህች ቀን በጣም የደረሰች ይመስለኛል፡፡ ስለዚህ ኢትዮጵያ ፈጽሞ ብቻሽን አትቆሚም!!

________________

                “ጃንሆይ ጀኔቫ ለአቤቱታ ሲሄዱ ብቻቸውን ነበር የቆሙት
                           ጥበቡ በለጠ / ደራሲና ጋዜጠኛ /

            ወቅቱ ኢትዮጵያዊነት ለ27 ዓመት እንዲከስም ተደርጎ የነበረበት ጊዜ አልፎ ኢትዮጵያዊነት እንደገና እያበበ ያለበት ጊዜ ነው። አሁን የሀገር መከላከያ ማርቺንግ ባንድ በልጅነታችን ስንሰማ ያደግናቸውን፣ ነገር ግን ሆን ተብሎ እንዲጠፉ የተደረጉትን እንደ “ተነሳ ተራመድ ክንድህን አበርታ” አይነት ወኔና ኢትጵያዊነትን ከፍ የሚያደርጉ ጣዕመ ዜማዎችን ሲያሰማ መንፈሴ ሁሉ ተደስቷል። ከ1983 በፊት የወሎው ላሊበላ፣ የጎንደሩ “ፋሲለደስ” የጎጃሙ “ጊሸ አባይ” ሌሎችም የምዕራቡና የምስራቁ የኪነት ቡድኖች ይሰሯቸው የነበሩ ትልልቅ ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያዊነትን ከፍ የሚያደርጉ ስራዎች ከ1983 ዓ.ም ወዲህ ጠፍተው ነበር፡ ዛሬ በዚህ መድረክ ባንዱ ያሰማው ጣዕመ ዜማ ያንን የናፈቀኝን ኢትዮጵያዊነት የመለሰልኝ ያህል ተሰምቶኛል ደስም፤ ብሎኛል።
“ብቻዬን እቆማለሁ” የሚለው የመጀመሪያው መሪ ቃል በጣም ጥሞኝ ነበር። “ለአገሬ እቆማለሁ”  “ብቻዬን እቆማለሁ” ያው ናቸው። አፄ ኃይለሥላሴ በፋሽዝም ወረራ ከሀገራቸው ተሰድደው በለንደን ከዚያም ጄኔቫ ያኔ “ሊግ ኦፍ ኔሽን” የሚባለው የአሁኑ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት በሚባለው ስብሰባ ላይ ንግግር በሚያደርጉበት ሰዓት የጣሊያን ጋዜጠኞች፣ ጣሊያንያዊያንና የእነሱ ደጋፊዎች፣ ወይንም ኢትዮጵያ እንድትወረር የሚደግፉ አገራት፣    ጃንሆይ ንግግር  እንዳያደርጉ  ይረብሿቸው ነበር። አፀያፊ ስድቦችንም ይሰድቧቸው ነበር። ያን ጊዜ በትዕግስት ቆመው የፀጥታ ሃይሎችና ፖሊሶች እስኪመጡ ድረስ ጠብቀው፣ እነዛን የሚረብሹና የሚያውኩትን  ካስወጡ በኋላ፣  አፄ ኃይለሥላሴ እንደገና እጅ ነስተው ነው፣ ንግግር ማድረግ የጀመሩት። ያን ጊዜ ብቻቸውን ነበሩ።
“አገሬ በፋሽዝም ተወርራለች፣ ብዙ ህዝቤ እያለቀብኝ ነው” እያሉ አቤቱታ ያቀረቡበት እጅግ ታሪካዊ ንግግር ነበር። ዓለም ላይ በእጅጉ አነጋጋሪ የነበረና በብዙ ቋንቋ የተተረጎመ ነበር። “እንዲያውም ዛሬ ፍርዳችሁን የማትሰጡኝ ከሆነ እግዚአብሔርና ታሪክ ፍርዳችሁን ሲያስታውሱት ይኖራሉ”።  ይሄን ግግራቸው በእንግሊዝኛ ወዲያው ተተርጉሞ የዓለማችን ጋዜጦች፣ መፅሔቶችና ሌሎች የሚዲያ አውታሮች “ God and History Will Remember your Judgment” የሚል ርዕስ ተሰጥተውት ትልቅ መነጋገሪያ ሆኖ ነበር። ከዚያም “ትልቁ አሳ ትንሹን አሳ ይዋጠውም የምትሉ ከሆነ ነገ በእናንተ ሲደርስ ታዩት የለምን?” ብለዋቸው ነበር። ናዚ ተነስቶ አውሮፓንና ዓለምን እንዴት እንዳመሰው አፄ ኃይለሥላሴ እዛ መድረክ ላይ ተናግረው ነበር። ታዲያ ብቻቸውን ነበሩ። ለሀገራቸው ብቻቸውን ቆመው ነበር።ከዚያ ተነስተው ነው እንግዲህ ህዝባቸውንም ትልቅ የዲፕሎማሲ ስራም ሰርተው በሰሜን አሜሪካ የሚገኙ ጥቁሮችን፣ አፍሪካዊያንን እንዲሁም በካሪቢያን ውስጥ የሚገኙ ጃማይካውያንንና ሌሎችንም ወደራሳቸው ሊያመጡ የቻሉት። በነገራችን ላይ ጥቁሮች ማለትም ጥቁር አሜሪካኖች ወደ ኢትዮጵያ በበጎፈቃደኝነት ተመዝግበው ለመምጣት ጥረት ሲያደርጉ፣ ያን ጊዜ የአሜሪካ መንግስት ከመርከብ ላይ ያወርዳቸው ነበር። ወደ ኢትዮጵያ እንዳይመጡና እገዛ እንዳያደርጉ። እንደ ኮሎኔል ቦብ ሮቢንሰን ዓይነት የተወሰኑ ሰዎች ናቸው ኢትዮጵያ ውስጥ መጥተው የኢትዮጵያን አየር ሃይል እየገነቡ፣ ከኢትዮጵያ ጎን የቆሙት። የአሜሪካ መንግስት ያን ጊዜም፣ በዚያን ወቅትም ብዙዎች በጎ ፈቃደኛ ሆነው እንዳይመጡ አድርጓል። ነገር ግን ኢትዮጵያውያን ደም አጥንታቸውን ሰጥተው፣ ኢትዮጵያን ከዚያ የአውሮፓ ሃይል ወረራ ነፃ አውጥተዋል። ስለዚህ ኢትዮጵያዊያን በየትኛውም ዘመን ብናይ፣ ሀገራቸውን ለማንንም ወራሪ ሃይልም ሰጥተውም ሆነ ለውጪ ተፅዕኖ ያልተንበረከኩ እንደሆኑ ታሪክ ይነግረናል። የኢትዮጵያ ታሪክ በሙሉ የሚናገረው ይሄንኑ ነው። የጀግኖች ምድር መሆኗን በየትኛውም ሃይል ያልተደፈረች አገር መሆኗንም ጭምር ታሪክ ይናገራል። ስለዚህ የኪነ-ጥበብ ሰዎቿም እንደዚሁ በያሉበት በተሰማሩበት ቦታ ጀግኖችን ሲያበረታቱ የኖሩ ናቸው። የኢትዮጵያ ደራሲያንን ብናይ፣ እነ ስንዱ ገብሩን የመሳሰሉ ሴት ደራሲያን፣ በፋሽዝም ወረራ  ወቅት ጀግኖችን በጦር ግንባር በማበረታታት ይሰሩት የነበረውን ገድል እናውቃለን። በዛ ጊዜ ተማርከውም ከዚያ ተለቀውም ከዚሁ ከአርበኝነት ያልወጡ እንደነ ሀዲስ ዓለማየሁ፣ ተመስገን ገብሬ አይነት ታላላቅ ደራሲያን ሀገራቸውን ከፋሽዝም ወረራ አድነዋል።
ዛሬም እዚህ ላይ የምታዩአቸው ወደ ግንባር እንሄዳለን የሚሉት የኪነ-ጥበብ ሰዎች የእነዛ ልጆች ስለሆኑ ነው። ኢትዮጵያ በልጆቿ ዛሬም ትደምቃለች፤ ዛሬም የተቃጣባትን ወረራና አዲሱን ቅኝ ግዛት በኢኮኖሚ፣ አገር ውስጥ ያሉ ባንዳዎችን በመፈልፈል፣ ጥፋትና ውድመት በማምጣት የማዳከም ሴራ ብዙ ጊዜ በኢትዮጵያ ተሞክሮ አልሆን ያለ ጉዳይ ነው። አፍሪካን በሙሉ ወደ ነፃነት እንዲሄዱ ያደረጋቸው የኢትዮጵያውያን የድል ታሪክ ነው። ይሄ ድል አሁንም ይመጣል፤ ይታያል። ጀግኖች ከያሉበት እየተሰባሰቡ ነው። ይሄም መድረክ የጀግኖች መሰባሰቢያና ጀግኖችን እያፈራን የምንልክበት ታላቅ መድረክ ስለሆነና እዚህ በመጋበዜ እግዚያብሔር ይስጥልኝ፤ አመሰግናለሁ፤ ኢትዮጵያ ታሸንፋለች።
_____________________

                “ሰውነታችንን በደንብ ካልተንከባከብን ጊዜ ጠብቀው ትንንሽ በሽታዎችም ያጠቁናል”
                     ዶ/ር ወዳጄነህ ማህረነ


            ይህንን መድረክ ያዘጋጁትን አካላት በእጅጉ አመሰግናለሁ። ኢትዮጵያዊነት ከፍ ብሎ የሚቀነቀንበት ስለሆነ ደስ እያለኝ ነው የመጣሁት። ለእኔ ኢትዮጵያ  የተለየ ውለታ አድርጋልኛለች። ሀይስኩል ቦሌ ስማር በነፃ አስተምራኛለች፤ ምንም አልከፈልኩም። አዲስ  አበባ ዩኒቨርስቲ ጥቁር አንበሳ ህክምና ስማር ለመመዝገቢያ 30 ብር ብቻ ነው ያስከፈለችኝ። መኝታ  ሰጥታ፣ ቁርስ ምሳ እራት አብልታ ህክምናን የሚያክል ነገር በነፃ  ነው ያስተማረችን።
ከዚያ ተመላልሼ አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ስማር ነፃ  በሚባል ደረጃ ነው ያስተማረችኝ። ስለዚህ በተለየ መንገድ ውለታዋ አለብኝና ሀገሬ ከፍ የምትልበት መድረክ ላይ ስጋበዝ ደስ ይለኛል።
ሀሳቤን ለማስረዳት ትንሽ ከሙያዬ እንድጨልፍ  ለሶስት አራት ደቂቃ ትፈቅዱልናላችሁ። በሰውነታችን ውስጥ ያለውን የመከላከያ ሀይል ብታዩት እጅግ  አስደናቂ ነው። “ኢሚዩን ሲስተም” (ኢሚዩኒቲ) የሚባል የበሽታ መከላከያ አለ። በጣም የተቀናጀ ነው። ብታጠኑት የምትደነቁበት ነው። ይሄ በሽታ መከላከያ ስርዓታችን። ሊንፋቲክ ሲስተም የሚባ ነገር አለ፤ ውሃ መሳይ ፈሳሽ ነው። ከላይ እስከ ታች በሰውነታችን ውስጥ አለ። ልክ እንደ ደም ይዘዋወራል። በዚህ ፈሳሽ ውስጥ ነጭ የደም ሴሎች አሉ። የሚገርማችሁ እነዚህ  ሴሎች በዚህ ሊንፋቲክ ሲስተም ውስጥ እየዞሩ ችግር ካለ ይፈልጋሉ። ባክቴሪያ ከገባ፣ ቫይረስ ከገባ እየዞሩ መከታተል ነው ስራቸው።
አሁን ለምሳሌ እኔ ሰውነት ውስጥ ባክቴሪያ ከገባ ይለዩና ወዲያውኑ ፋጎሳይትስ የሚባሉ ሴሎች ይላካሉ። እነዚህ ፋጎሳይትስ ይሄዱና የገባውን ባክቴሪያ ይውጡታል። ይውጡና ይፈጩታል። ከፈጩት በኋላ አንቲጅኑን ይለያሉ። ይህን የሚያደርጉት የባቴሪያውን አይነት ለመለየት ነው። ከዚያ ወደ ማዕከላዊ እዝ (ሴንትራል ኮማንድ) ይላካል። ሴንትራል ኮማንድ ውስጥ በመጣው አንቲጂን መሰረት ወዲያው ሴሎች ይራቡና ጦር ወዳለበት ቦታ ይላካል። በሌላ በኩል፤ በመጣው አንቲጅን ላይ ተመስርቶ አንቲቦዲ ይፈጥራል። ከዚያ ሴሎቹና አንቲቦዲዎቹ ተጋግዘው ባክቴሪያውን ያጠፋሉ። በጣም የተቀናጀና አስደናቂ የመከላከያ ሀይል ነው በውስጣችን ያለው። ኢንፌክሽኑ ካለፈ በኋላ ቂመኛ የሆኑ “ሜሞሪ ሴልስ” የሚባሉ አሉ። በሽታውን ያስታውሳሉ። ያ ባቴሪያ ሌላ ጊዜ ደግሞ ከመጣ፣ ሜሞሪ ሴሎቹ በፍጥነት           አንቲቦዲ ሴሎች እንዲፈጠር ያደርጉና ይከላከላሉ። በፍጥነት እንዲወገድ ያደርጋሉ። ክትባት የሚሰራውም በዚህ መንገድ ነው። ይህንን የተቀናጀ ሀይለኛ የሰውነት መከላከያ ሀይላችንን (ኢሚዩን ሲስተም) ልንከላከለው የሚገባ ነው።
የተመጣጠነ ምግብ በመመገብ ፣ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ በመስራት፣ ቫይታሚኖችን በመውሰድ ራስን ከጭንቀት በመከላከል ልንንከባከበው ይገባል።
ምክንያቱም ሲደክም ችግሮችን ያመጣል። ለምሳሌ ኤችአይቪን ብንወስድ ተንኮለኛ የሚያደርገው ቀጥታ ሴንትራል ኮማንዱ ጋር በመግባት “ሊንፎሳይትስ” የሚባሉትን ሴል የሚያመነጩትን ነው ቀጥታ የሚመታቸው። ሴንተሩ ጋ  ነው የሚሄደው። ከዚያ ሰውነት ይደክምለታል።
ይሄ የውስጥ መከላከያ ሃይላችን በምግብ፣ በቫይሚን ከጭንቀት ነፃ በመሆንና የአካል ብቃት እንቅስቃሴ በመስራት ካልተንከባከብነውና ከተዳከመ ችግር ይፈጠራል። ሌላ ጊዜ የማይዙን እንደ ቲቢ፣ ፈንገስ ኢንፌክሽኖች፣ ሌላ ጊዜ የማያጠቁን የባክቴሪያ አይነቶች  ሁሉ መከላከያ ሃይላችን ሲዳከም ይደፍሩናል። ይህ እንዳይሆን መከላከያ ሃይላችንን በጣም በጣም መንከባከብ አለብን።
ጉዳዩን ወደ ሀገርም ስናመጣው እንደዚሁ ነው። በሀገራችንም የተቀናጀ መከላከያ አለ። ችግር ሲፈጠር ሄደው አንቲቦዲ የሚፈጥሩ፣ ሀገሮችም የተቀናጀ መከላከያ አላቸው፤ ሁሉም አገሮች ይሄ አላቸው። ለምሳሌ አሜሪካን እናንሳ። የኢንተለጀንሲን ጉዳይ ካየን፣ ዩናይትድ ስቴትስ ኦፍ አሜሪካ በመንግስት ሥር የሚተዳደሩት 17 የኢንተለጀንሲ ኤጀንሲዎች አሏት። CIA FBI እያሉ የሚቀጥሉ 17 ኤጀንሲዎች አሏት-በመንግስት ብቻ የሚተዳደሩ። በነዚህ ደህንነቷን ትጠብቃለች። ለምን? አስፈላጊ ስለሆነ። ለኢንተለጀንሲ ስራ በዓመት ከ60-80 ቢ. ዶላር ይመድባሉ። የተለያየ የፖሊስ አደረጃጀት አላቸው። ፖሊሳቸውን በደንብ ያደራጃሉ፤ እስከ 115 ቢ. ዶላር ዓመታዊ በጀት ለፖሊሳቸው ይመድባሉ። ለምን? በጣም አስፈላጊ ስለሆነ።
“US Army Force” ለሚባለው ለመደበኛው፣ ለብሔራዊ ጋርዱ፣ ለኤርፎርስ (አየር ሀይል) 750 ቢ. ዶላር በዓመት መድበው ጦራቸውን ያጠናክራሉ። እነዚህን የሚደርጉት ያለ ደህንነት፣ ያለ ፖሊስና ያለ ጦር ሃይል መኖር እንደማይችሉና ህልውናቸው እንደማይቀጥል ስለሚያውቁ ነው። ከዚያ በተጨማሪ ህዝቡም ይጠብቃል።
ኢትዮጵያም የደህንነት፣ የፖሊሲም ሆነ የጦር ሃይል አላት። ኢትዮጵያ ሀገር ሆና እንድትቀጥል ከፈለግን ሳንሸኮረመም ደህንነቱን፣ ፖሊሱንና ጦሩን ማጠናከር አለብን። ይሄ የግድ ነው።
እኛ ከደርግ ስርዓት ጀምሮ የነበረውን የደህንነት ሃይል በአሉታዊ መልኩ ነው የምናውቀው። ለምሳሌ ማዕከላዊ ትዝ የሚለን የደህንነት ጉዳይ ሲነሳ ነው። የኢህአፓ ሰዎች አፋቸው ውስጥ ካልሲ ተጠቅጥቆ ተገልብጠው ሲገረፉ፣ ደህንነቱን በዚያ መልኩ ነው የምናስበው።
እኔ ኢትዮጵያ ውስጥ እስካሁን የመይገባኝ ነገር፣ ኮዳ ማንጠልጠል የሚባል ነገር ነው። አስቤ… አስቤ አስቤ እስካሁን አልገባኝም። ቶርቸር እንዳለ አውቃለሁ፤ አሜሪካም አለ። የመስጠም ስሜት እንዲሰማቸው ዘቅዝቀው ውሃ ውስጥ ይከትቷቸዋል። ብዙ አይነት ቶርቸሮች አሉ። የኮዳው አይገባኝም። ስለዚህ ደህንነት ሲባል ለኢትዮጵያ መቀጠል ወሳኝ ከሆኑት አንዱ የደህንነት ሃይላችን ነው። ሁለተኛ የፖሊስ ሃይላችን ሊጠናከር ይገባል።
እኔ ከዚህ አዳራሽ ስወጣ ፖሊስ ሳይ ደስ ይለኛል እንጂ አልደነግጥም። እኔን ለመጠበቅ ነው የቆሙት። እኔን “አንተ የሃይማኖት ሰው ሆነህ እንዴት እንደዚህ ትላለህ” ይሉኛል። ከእግዚአብሔር በታች ቤተ-ክርስቲያኑን የሚጠብቀው ማነው? ፖሊስ ነውኮ። መስጊዱን ከአላህ በታች የሚጠብቀውኮ ፖሊስ ነው። እነሱ ከሌሉ እሳት በእሳት ነው የምንሆነው። ፍንዳታ በፍንዳታ ነው የምንሆነው፤ እነሱ ከሌሉ። እነሱን የማንደግፍበት፣ የማንንከባከብበት ምክንያት ምንድነው? በግንባር እየተዋደቀ ያለው የሀገር መከላከያ፣ አየር ሀይሉ፣ በተለያየ አደረጃጀት ያለው ሃይላችን መጠናከር አለበት። እኛም መደገፍና መንከባከብ አለብን። ይህ ካልሆነ የተደበቁ ቀን የሚጠብቁ ትንንሽም ቢሆኑ ጠላቶች መዳከማችንን አይተው ይደፍሩናል። ይህ በደንብ ሊታሰብበት ይገባል። አመሰግናለሁ።
__________________

                “ብቻችንን ቆመን ህልውናችንን እናረጋግጣለን”
                          ሰርፀ ፍሬ ስብሃት / የሙዚቃ ባለሙያ/

            አገር የህልውና ፈተና ሲገጥማት የኪነ-ጥበብ ባለሙያዎች ቀድመው ደራሾችና የመጀመሪያ  ደወል ደዋዮች ናቸው ማለት ይቻላል። ይህንን በተለያየ የሀገራችን ታሪክ ውስጥ ደጋግማችሁ የምታዩት ነው። በተለይም የቅርብ ጊዜውን ብናነሳ፣ የዛሬ 85 ዓመት የሀገር ፍቅር ማህበርን በመመስረት፣ ዛሬ “አድዋ ዜሮ ዜሮ” (አድዋ ማዕከል) ብለን እየገነባን ያለነው ቦታ ላይ የወልወሉን ግጭት ተከትሎ ጠቢባን፣ የሃይማኖት ሊቃውንትና ታላላቅ ተናጋሪዎች በመሰብሰብ ከፍ ያለውን የሀገር ፍቅር ስሜትና ግለት መሃሏ ኳስ መጫዎቻ ቦታዋ ላይ ነው የፈጠሯት።
ከዚያ በኋላ ያንን የእሳት ግለት ስሜት ይዘው ጦር ሜዳ ድረስ ሄደዋል። በተለይ “ህይወቴና የኢትዮጵያ እርምጃ” በተሰኘውና ጃንሆይ ራሳቸው በጻፉት መፅሐፋቸው ላይ እንደምናነበው፤ ብዙዎቹ ጠቢባን በህይወት አልተመለሱም። በማይጨው ጦርነት ላይ የብዙዎቹ ህይወት አልፏል። ማነሳሳትና መትጋት ብቻ አይደለም፤ ከፍተኛ የሀገር ፍቅር ስሜት ግለት ይዘው አውደ ውጊያው ድረስ እስከ መሄድና የህይወት መስዋዕትነት እስከ መክፈል ድረስ ስራ ሰርተዋል።
ያንን  የአያቶቻቸውን የአባቶቻቸውን መሰረት የያዙ የጥበብ ባለሙያዎችም አሁንም ተሰባስበው በመሄድ በአውደ ውጊያዎች ስራዎቻቸውን እያቀረቡ ይገኛሉ። አሁንም ይሄ መድረክ እንዳለ ጦር ሜዳ ላይ የምናየው መድረክ ይሆናል። ይህን ለማድረግ ያላቸውን ስምምነት የመጀመሪያውን ማብሰሪያ ዛሬ እዚህ መድረክ ላይ ያደርጉታል። ይህንን መድረክ ስናዘጋጅ የሙያ ማህበራት እገዛ አለ፣ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደርም በትልቅ መዋቅር እየደገፈና ክብርት ከንቲባዋ ጭምር እየመሩት  ይሄ ኮሚቴ ይህንን መድረክ እውን ሊያደርግ ችሏል።የዕለቱ ሀይለ ቃል ደግሞ “ብቻዬን እቆማለሁ” የሚል ነው፡ ብዙ ሰው ደንገጥ ብሏል፤ “ምንድነው ብቻዬን እቆማለሁ ማለት” በሚል። ብዙ ሰው የተባበረበትን ጉዳይ እንዴት ብቻዬን እቆማለሁ  ይባላል የሚል ስሜት ሰጥተውታል።
ሁለት ምክንያቶች ናቸው “ብቻዬን እቆማለሁ” የሚል ርዕስ እንድንመርጥ ያደረጉን። አንደኛው፤ ትልቁና በታሪክ የሚደነቁት አምባሳደር ብርሃኑ ድንቄ፤ “ I Stand Alone” (ብቻዬን ቆሜያለሁ) የምትል መፅሐፍ አለቻቸው። ይህንኑ ሃሳብ ከ17ኛው ክ/ዘመን ከአንድ ቅኔ ጋር አገናኝተው ደግሞ “አልቦ ዘመድ ቅኔ ተዋርዶ” በምትል ቅኔ አምጥተውታል። ባጡ በነጡ ጊዜ ወዳጅ የለም የሚል ስሜት ያላት ናት። አንዳንድ ጊዜ የሀገር ሉአላዊ ጥያቄ በሚመጣበት ጊዜ ብቻችንን የምንቆምበት ጊዜ አለ። ይሄ በእኛ ብቻ የተከሰተ አይደለም። ለሃይማኖት መፈጠር ምክንያት የቆሙ ሊቃውንትን ሄደን፣ ብናይ ብቻቸውን የቆሙበት አጋጣሚ ነው፤ ዛሬ ትልቅ ህብረት እንዲኖር የሆነው። ኢትዮጵያ ይህን ሁሉ ትልቅ ነገር ያገኘችው ብቻዋን በቆመችባቸው ጊዜያት እንጂ ሌሎች አገራት ባጀቧት ጊዜያት አይደለም።
አድዋ፣ ማይጨውና ሌሎችም አውደ ውጊያዎችና ድሎች ብቻችንን እንድንቆም በተገደድንባቸው ጊዜያት ብቻችንን ቆመን ያገኘናቸው ናቸው።
በነዚህ ሁሉ ጥረቶችና እንቅስቃሴዎች ብቻችንን ቆመን ያገኘነው ድል ግን ለእኛ ብቻ ሳይሆን ለአፍሪካውያን ሁሉ ኩራት ነው የሆነው።  ይህን  ተምሳሌትነት በመያዝ እንደ ሀገር ነው ብቻችንን የቆምነው። በአሁኑ ሰዓት የሚመለከተውም የማይመለከተውም ሁሉ በእኛ ላይ ፊቱን ያዞረበት ጊዜ ነው። አቅም ያለውም የሌለውም ፊቱን የመለሰበት ጊዜ ነው። አፍሪካዊያን ወንድሞቻችንም በሄድ መለስ ውስጥ ናቸው። ያም ሆኖ ግን ብቻችንን ቆመን ህልውናችንን እናረጋግጣለን። የዛሬው ሁባሬ ጥበባትም አጠቃላይ ዝግጅቱ ይህንን ከላይ የገለጽኩትን መንፈስ የተላበሰ ነው።


Read 1898 times