Saturday, 20 November 2021 14:42

አትላንቲክ ማዶ ኾኖ የኢትዮጵያን ችግር መፍታት ይቻላልን?

Written by  -ተስፋ በላይነህ-
Rate this item
(0 votes)

       (“ለኢትዮጵያ ኅልውና ተቆርቋሪዎች” የተሰጠ ግላዊ ምላሽ)
                                
                በአቶ ያሬድ ጥበቡ አማካኝነት ኢትዮጵያን ከጥፋት ለመታደግ የቀረበ የሰላም መነሻ ሐሳብ በሚል ጥብቅ እና አስቸኳይ ጥሪ መልዕክት፣  ህዳር 5 ቀን 2014 ዓ.ም በርዕዮት ሚዲያ ላይ ቀርቧል፡፡
የዚህ ጽሁፍ ዓላማ ይህንን ሃሳብ ወይም መልዕክት ምናልባትም ለወደፊት ታሪክ ተሳስቶ እንዳይረዳው፣ ለመጭው ትውልድ ቀናዒ የሆኑ መስለው ሊታዩ የሚችልበት አጋጣሚ ከተፈጠረ፣ በጊዜው የነበረውን ተጨባጭ ሁኔታ ለማስገንዘብ ያህል ነው፡፡
በቅድሚያ የግለሰቦቹ ዓላማ ከአገራችን ወቅታዊ ሁኔታ (Contemporary politics) ከችግሩ ምንጮች አቋምና ፍላጎት ጋር ፈጽሞ አይገናኝም፡፡ ሊመልሷቸውም ሆነ ሊያነሷቸው የሚገቡ ዋና ነጥቦች እያሉ፣ እነሱ ግን ትኩረታቸው ሌላ ላይ ነው፡፡ በሎጂክ ሲጋራ ያነቃቃል ብቻ ተብሎ አይነገርም፡፡ ከጅምሩ ሲጋራ ጎጂ - ገዳይም ነው ተብሎ መነገር አለበት፡፡ የሽግግር መንግስት ናፋቂዎቹ፣ ይሄ አይነት ችግር ይታይባቸዋል፡፡
እያሉን ያሉት በአጭሩ የሽግግር መንግስት ይቋቋም ነው፤ የሃሳቡ ሙሉ ምስልም፣ የብልጽግና ፓርቲን ከህውኃት ሽብር ቡድን ጋር እኩል/ አንድ ዓይነትም አድርጎ ከመውሰድ - ከመበየን ይጀምራል፡፡ በአጭሩ ሐሳቡ Sugar coated pill (በስኳር የተሸፈነ መርዝ) የሚባለው ዓይነት ነው፡፡
ከጅምሩ ልንግባባቸው ከሚገቡ ነጥቦች ውስጥ፤አንደኛ፤ ሕውኃት የሽብር ቡድን መሆኑን የመቀበል ያለመቀበል ጉዳይ ሰፊ ትንታኔን የሚጠይቅ ነው፡፡ የአንድ ክልል ህዝብ እወክላለሁ የሚል ቡድን፣ ሽብርተኛ መባል የለበትም ብለው የሚከራከሩም አሉ፡፡ የኢትዮጵያን መከላከያ ሠራዊት የወጋ ቁጥር አንድ የነውጥ ኃይል፣ በዴሞክራሲያዊ ውይይት የማያምንና እኩልነትን  የማይቀበል ቡድን መሆኑን ግን መካድ አይቻልም፡፡
የቀዳማይ ወያኔ 1930ዎቹ መጀመርያ ዓመታት የብሔረተኝነት ትርክቱ ጥንስስ መሆኑ ይነገራል፤ ይሕንን እንደ መነሻ በማድረግ የዘመኑ ወጣት ብሔረተኞች፣ ኢትዮጵያን እንደ ኢምፓየር በመቁጠር፤ የኢትዮጵያ ሕልም ከትግራይ ብሔረተኝነት ሕልም ጋር የሚቃረን መሆኑን በግልፅ ይናገራሉ፡፡ ይህም ከ2009ኙ የአመራሮች ለውጥና ሪፎርም ማግስት የሕውኃትን ኃይል ወደ መቀሌ እንዲያመራና እንዲሰበሰብ፤ የጥላቻ ፕሮፓጋንዳ እየነዛ ለሁለት ዓመት ያህል ራሱን ለጦርነት እንዲያዘጋጅ አድርጎታል፡፡ በራሱም ጭምር ተመርጦ  ወደ ሥልጣን የመጣውን የለውጥ አመራር #አሃዳዊ መንግስት; እያለ ሲያጥላላ ከርሟል፡፡ የለውጥ አመራሩ ፣አብዮታዊ ዴሞክራሲን እንደ ርዕዮተ ዓለም ይዞት እንደማይቀጥል ይፋ ማድረጉን ተከትሎም፣ ግልጽ የመስመር ልዩነት  ገሃድ ወጥቷል፡፡
ለእኔ ከህውኃት እና መሰሎቹ ጋር ውይይትና ድርድር ማድረግ  ልክ “ጨለማንና ብርሃንን እንደ ማዋሃድ” አሊያም ፤ “ዲያብሎስን ከፈጣሪው ጋር እንደ ማስታረቅ” ተደርጎ የሚቆጠር  ነው፡፡
በደጋፊዎቻቸውም በጉልህ የሚታየው ስህተት (Elephant in the room) እንደሚሉት፣ ዋናውን ችግር ጠረጴዛ ላይ አስቀምጦ፣ ተሙለጭላጪ ሃሳብ የመያዝ ጉዳይ ነው፡፡ የህውኃትም ሆነ የኦነግ ሸኔ ኢትዮጵያን እንደ ኢምፓየር የማየት ስሌት፣ “ኢትዮጵያ የአገራት ስብስብ እንጂ፣ የኢትዮጵያን የረዥም ታሪክ ባለቤትነት በሚያምን መንግስት ሥር ልትተዳደር የምትችል አገር አይደለችም!” ብለው እንዲያምኑና ኢትዮጵያዊ ማንነትን እንዲክዱ  አድርጓቸዋል፡፡
የሆኖ ሆኖ የኢትዮጵያ ችግር ከአትላንቲክ ማዶ ባሉ ፖለቲከኞችና በተለይ በምዕራባዊያን ጣልቃ ገብነት እንደማይፈታ መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡
የእነ ኸርማን ኮህን የጡት ልጅ የሆነው፣ የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲ (ኢ.ህ.አ.ዴ.ግ) አንድ አገርን እየመራ ግንባርና ነጻ አውጭ ሆኖ፣ “አብዮታዊ ዴሞክራሲ” የሚል አያዎ  ተሸክሞ፤  ድንቁርናንና ጽንፈኛ ብሄረተኝነትን እያቀነቀነ ኢትዮጵያን ‹‹የአፍሪቃዋ ዩጎዝላቪያ›› ለማድረግ ለ27 ዓመታት ሲተጋ ኖሯል፡፡ የማታ ማታ ግን ከራሱ ውስጥ በወጡ አካላት፣ ከሥልጣኑና ተጽዕኖ ፈጣሪነቱ ተወግዶ፣ በብልጽግና ፓርቲ ተተካ! ይህ ለኢትዮጵያውያን ትልቁ የታሪክ ስኬት ነው፡፡
የብልጽግና ፓርቲ ምስረታ ለኢህአዴግ ፈጣሪዎች  የፖለቲካዊ ሞት መርዶ  ነበር ማለት ይቻላል፡፡ ለዚህም ነው ፓርቲውን  እንደ ጨፍላቂና ፍጹም አምባገነን፣ የትግራይ ህዝብ ጠላት፤ የሕገ-መንግስቱ አፍራሽ፣ እንዲሁም የአሃዳዊነት አቀንቃኝ አድርጎ መቁጠር የጀመረው፡፡ ህወኃት በመከላከያ ላይ ጥቃት ፈጽሞ ጦርነቱን በይፋ ከመጀመሩ አስቀድሞ የፈፀማቸው አንዳንድ ነገሮች በጥቂቱ ምን እንደሚመስሉ እናስታውስ፡፡
1/ የዘጠኝ ፓርቲዎች ብልጽግናን መመስረትና የሕውኃት ብቸኛ መነጠል?
2/ የአስተዳደር ወሰንና የማንነት ጉዳዮች ኮሚሽን አዋጅ ተቃውሞ፣ በትግራይ ክልል የህዝብ ተወካዮች አባላት?
3/ ብቸኛው የትግራይ የክልል መንግስት ክልላዊ ምርጫ?
3/ የፌደራል ፖሊሶች እገታ ድራማ?
4/ የሰሜን እዝ አዛዥ ክልከላ?
እነዚህ አበይት ክስተቶች እንዲሁም ከጅምሩ ኢትዮጵያ ትበተናለች የሚለው የአደባባይ ዲስኩር፣ የጦርነቱን አይቀሬነትና ጦርነቱ ከአንቀጽ 39 ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት እንዳለው አመላካች ነበር፡፡ “የሽግግር መንግስት ናፋቂዎቹ” እነዚህን ጥያቄዎች ፈጽሞ ማንሳት አይፈልጉም፡፡ ለዚህ ነው ዝርዝር ሐሳባቸውን እዚህ አምጥቶ አንባቢን ማሰልቸት ተገቢ የማይሆነው፡፡
“ሕገ-መንግስቱን አትንኩብኝ፤ የድንበር አስተዳደር ጉዳይን አታንሱብኝ! ከነካችሁብኝ ኢትዮጵያን አፈርሳታለሁ፤እበትናታለሁ!” ብለው ከማሉና ከተገዘቱ ፣ ለዚያም ሌት ተቀን ከሚሰሩ ቡድኖች ጋር እንዴት ያለ ውይይትና ድርድር ነው የሚካሄደው? ምን ዓይነት የሽግግር መንግስት ነው የሚመሰረተው? የጦርነቱ መነሻም መድረሻም የሉአላዊነት ጉዳይ ነው፡፡ ኢትዮጵያን ከመበታተን የማዳን ያለማዳን፡፡ የመሆን አለመሆን ጉዳይ!
 ለዚህ መፍትሄ ከባህር ማዶ የምንጠብቅ ከሆነ፣ ዩጎዝላቪያን በአፍሪቃ ለማየት ከወዲሁ መዘጋጀት ይኖርብናል፡፡   
በአንድ ወቅት ከአትላንቲክ ማዶ ሆኖ የኢትዮጵያን የፖለቲካ ችግር መፍታት አይቻሉም ያሉት ፖለቲከኛው አቶ ልደቱ አያሌው ነበሩ! እኛ ደግሞ እንላለን፤ ከአትላንቲክ ማዶ ዘንዶ እንጂ በጎ ነገር ፈፅሞ አይመጣም፡፡   
ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር!


Read 3401 times