Monday, 22 November 2021 00:00

የእጣ ፈንታችን ቀመርና ስሌት ይሄውና!

Written by  ዮሃንስ ሰ
Rate this item
(1 Vote)

   በምኞት ብቻ እውን ሊሆኑ የማይችሉ ነገሮችን ከወዲሁ መተንበይ ይቻላል።ምን ሲሆንና ምን ሲደረግ፣ ምን ሊከሰት፣ ምን ሊከተል እንደሚችልም፣
የእውቀታችን ያህል መተንበይ አያቅትም።
             
            የሰው ልጅ እጣፈንታ፣ ከምን ከምን ቅመም እንደሚጠነሰስ፣ ከምን ከምን ቀመር እንደሚሰላ፣ ከምን ከምን ጥምረት እንደሚወለድ ማወቅ ቢቻል!
በአንድ በኩል አይቻልም። “የሰውን የነገ ተግባር ለመተንበይ አትሞክሩ” ቢባል፣ ትክክለኛ ምክር ነው።
ለምን ቢባል፣ ሰው ማለት ራሱን የሚሰራ ፍጥረት ነው።
ፍጥረትም ፈጣሪም፣ ሕንፃም አናፂም ነው- የሰው ልጅ። ራሱን ይቀርፃል። ይሄ፤ ከሰው ልጅ መሰረታዊ የተፈጥሮ ባሕርይ ነው። በተወሰነ አይነትና ልክ፣ “የመምረጥ አቅም” የተጎናፀፈ ነው - ሰው።
ሃሳቡን የመመርመርና እውቀቱን የማበልፀግ፣ የነገ ግብና ተግባሩን አስተካክሎ የመምረጥ፣ የነገ ማንነቱን አሳምሮ የመቅረፅ፣…. “የግል አቅም” አለው። ማለትም፣ “የተወሰነ የምርጫ አቅም” አለው - የሰው ልጅ።
ወደ ጭፍንነት፣ ወደ ጠማማ መንገድ፣ ወደ ብልሹ ባህርይ የመንሸራተት ምርጫም አለው - እያንዳንዱ ሰው።
“ሁሉን ቻይ” አይሆንም። ነገር ግን፣ በተወሰነ መልክና ልክ፣ “እጣፈንታውን የመምረጥ አቅም” አለው።
አነሰም በዛ፣ የነገ ሕይወቱን፣ ወደ ክፉም ወደ ደጉም፣ የመምራት ምርጫዎች ሁሌም ይኖሩታል። እናም፣ “የሰውን የነገ ተግባር፣ ቁርጡን ለመተንበይ አትሞክሩ፤ ከመሞከር ተቆጠቡ” እንበል ትክክል ነው።
ግን ደግሞ፣ “የመምረጥ አቅም” ገደብ የለሽ አይደለም። ሁለገብ፣ ሁሉን አቀፍ፣ ሁሉን ገዢና ሁሉን ቻይ አቅም አይደለም።
በተፈጥሮ ውስጥ ነው፣ ሰው የሚኖረው። ተፈጥሮ ሁሉ፣ በቦታም በጊዜም፣ በአይነትና በመጠን፣ የተወሰነ ባሕርይ አለው። ጠባብና ሰፊ፣ ብዙና ጥቂት፣ ትልቅና ደቃቅ፣ ሃያልና ደካማ፣ ሸካራና ልሙጥ፣… በመልክና በመጠን ይለያያል።
ግን፣ ሁሉም ነገር፣ ልክ አለው።
ቁጥር ስፍር የሌለው “የትየለሌ” ማለት፣ እንዲሁ እጅግ ብዙ፣ እጅግ ትልቅ ለማለት ካልሆነ በቀር፣ ቁጥርና ስፍር የሌለው ነገር የለም (የትም የሌለ ነው)።
የሰው ምርጫም፣ የራሱ ልክ አለው። በተፈጥሮ ውስጥ ሆኖ፣ በቀጥታ ወይም በተዘዋዋሪ ከተፈጥሮ ከሚመነጩ አማራጮች ውስጥ ነው፣ መምረጥ የሚቻለው።
በአንድ ጊዜ፣ አገር ውስጥና ከአገር ውጭ፣ መሃል ከተማና ጠረፍ ዳር ላይ መገኘት አይችልም።  ይሄ፤ ከምርጫ ውጭ ነው። በእርግጥ፣ በከንቱ መመኘት ይችላል። ነገር ግን፣ በምናብ፣ ከተፈጥሮ ለመኮብለል መመኘት ምን ትርፍ አለው?
በአንድ ቅፅበት፣ አራምባና ቆቦ፣ ሎሳንጀለስና ላይ- አርማጭሆ፣ ኦስሎና ዶምቢዶሎ፣ ሞያሌና ቦሌ ላይ መገኘት አይችልም - የሰው ልጅ። በቃ! የማይሆን ነገር፣ አይሆንም።
ደግሞም፣ የተፈጥሮ ሕግ፣ እንዲህ ፅኑና አስተማማኝ መሆኑ፣ “ተመስጌን” ነው።
አለበለዚያ፣ “ሆረር” ነበር የሚሆነው።
የማይሆን ነገር፣ በዘፈቀደ፣ በራሱ ጊዜ፤ “እውን” የሚሆን ከሆነ፣ አስቡት። የቆረሳችሁት ዳቦ ጊንጥ ሲሆን፣ አረፍ ብላችሁ የተኛችሁበት አልጋ እልም ያለ ውቅያኖስ ሲሆን ይታያችሁ። በረንዳው፣ በውሃ ጥም የምትሞቱበት አውላላ በረሃ ሲሆንባችሁ፣ አልያም ከእባብና ከአንበሳ የማታመልጡበት ጫካ ሲሆንባችሁ አስቡት።
ደግነቱ፣ የማይሆን ነገር፣ ፈፅሞ አይሆንም።
እፎይ! እሰይ! ተፈጥሮ አስተማማኝ ነው። ለነገሩ፣ እንዲወላውል እንዲቃዥ ብንመኝ እንኳ፣ ከተፈጥሮው አይዛነፍም።
እልፍ ጊዜ “ይቻላል! ይቻላል!” እያልን ራሳችንን ብናነሳሳ፣ ሁሉም ነገር ይቻላል?
“እመኑ፣ እውነት ይሆንላችኋል” ብለን ጥዋት ማታ ብንሰብክ፣ ሁሉም ነገር እውን ይሆናል? እልፍ “የፖዝቲቭ ትንኪንግ” መፅሐፍ ብንገዛስ?… ምኞታችን በተፈጥሮ ላይ ለማመፅና ተፈጥሮን በምኞት ለመጠምዘዝ ከሆነ፣ ከንቱ ድካም ነው።
ይልቅስ፣ “ይቻላል!” የሚለው “ፖዘቲቭ” አባባል፣ በትክክለኛ ምርጫዎችና በእውነተኛ ችሎታዎች ላይ እንድናተኩር፣ የማንቂያ ደወል ቢሆንልን ይሻላል። ደግሞም ሊሆንልን ይችላል።
በእውኑ ተፈጥሮ ላይ የማመፅ ምኞትን የሙጢኝ ይዞ “ማመን”፣ ከእውነት ጋር ያራርቃል እንጂ፣ “እውነት ይሆንላችኋል” የሚያስብል አይደለም። “ማመን” ማለት፣ “ለእውነታ መታመን” ማለት ካልሆነ፣ ምን ዋጋ አለው?
ማመን ማለት ለእውነታ መታመን ከሆነ ግን፣ በእርግጥም፤ ዓለም ሁሉ በመዳፋችሁ ውስጥ ይሆናል ያስብላል። ብዙ ተዓምር ይሰራሉ።
ጥቂት ሰዎች ስንትና ስንት ተዓምር ሰርተዋል። የሰውን ታሪክ ቀይረዋል።
ፖዚቲቭ ትንኪንግ (አዎንታዊ አስተሳሰብ)፣ በእውን ፋይዳ የሚኖረው፣ በእውነታ ላይ ከተመሰረተ ብቻ ነው - ከእውነታ ጋር የሚጣላ ከሆነማ፣ ምኑ “እውናዊ”፣ ምኑ “አዎንታዊ” ይባላል?
በአጭሩ፣ “የማይሆን ነገር”፣ በሰው ምኞት ብቻ፣ “እውን” አይሆንም። ትናንት ሊሆን አይችልም ነበር። ዛሬም አይችልም። ነገም፣ ሊሆን አይችልም። በአንድ ጊዜ፣ በሁለት ቦታ ላይ መገኘት አትችልም። ይህንን በእርግጠኛነት መተንበይ አይከብድም። መሠረታዊ የተፈጥሮ ሕግ ነው።
ሰው ያለ ምንም ቴክኖሎጂና ያለምንም የኃይል ምንጭ፣ ሽቅብ እንደማይመነጠቅ፣ አየር ላይ እንደማያንዣብብም፣ አያጠራጥርም። የተራቀቀ የትንበያ ጥበብ አያስፈልገውም።
አየር ሳይተነፍስ፣ ምግብ ሳይበላ፣ ፈሳሽ ሳይጠጣ፣… በሕይወትና በጤና፣ ከአመት አመት ያድርሰው ብለን ብንመኝም፣ ሌላ ትርጉም አይኖረው። በተፈጥሮ ላይ የማመፅ ከንቱ ምኞት ነው። በእውን፣ ከዓመት ዓመት መሻገር አይችልም - ያለ እህል ውሃ፣ ያለ አየር ያለ ትንፋሽ። ይህን መተንበይ ያቅታል? አያቅትም።
ነገር ግን፣ በእውን የማይሆኑ ነገሮችን፣ በምኞት ብቻ እውን ለማድረግ መሞከርና አለመሞከር፣ የእያንዳንዱ ሰው ምርጫ ነው። የእያንዳንዱ ሰው ምርጫ፣ ምን እንደሚሆን፣ ምን መርጦስ ምን እንደሚያደርግ መተንበይ ሌላ ጉዳይ ነው።
በምኞት ብቻ እውን ሊሆኑ የማይችሉ ነገሮችን ከወዲሁ መተንበይ ይቻላል።
ምን ሲሆንና ምን ሲደረግ፣ ምን ሊከሰት፣ ምን ሊከተል እንደሚችልም፣ የእውቀታችን ያህል መተንበይ አያቅትም።
 የሰው እጠፈንታስ! የነገ ሃሳብና ተግባሩስ? የነገ ስብዕናውስ? ከወዲሁ ይታወቃል? አይታወቅም። መተንበይ አይቻልም። ጠቋሚ ነገሮችን ማወቅ ይቻላል። ሌሎች የሚታወቁ ነገሮም አሉ።
እንዲህና እንዲያ ከፈለገና ከተመኘ፣
ያንን አላማና ያንን ግብ ከመረጠ፣
 ይህንና ያን ለማድረግ የመወሰን ሃላፊነት ይጠብቀዋል … ብለን መናገር እንችላለን።
ይህንና ያን ለማድረግ ከወሰነ …
በዚህ መልክና በዚያ መጠን ሊተገብር፣ ሊሰራና ሊጥር ይችላል።
በዚህ መልክና መጠን ይህን ተግባር ካከናወነ፣
በዚያ መንገድና ልክ፣ ያን ውጤት ያገኛል፣ ያን መዘዝ ያስከትላል።….
ይህንን መናገር እንችላለን። ግን ከትንበያ ይለያሉ።
“እንዲህ ከተደረገ፣ እንዲያ ይሆናል” የሚል ቅርፅ አላቸው። “if… then…” በሚል የተጣመሩ ናቸው። የሩድያርድ ኪፕሊን ግጥም አልመጣባችሁም? የሰው ልጅ የእጣ ፈንታ “ቀመር” ብንለው አይበዛበትም። If you can keep your head
when all about you
Are losing theirs and
blaming it on you,
If you can trust yourself
when all men doubt you,
But make allowance for
their doubting too;
If you can wait and not be
tired by waiting,
Or being lied about, don’t
deal in lies,
Or being hated, don’t give
way to hating,
And yet don’t look too
good, nor talk too wise:
If you can dream – and
not make dreams your
master;
If you can think – and not
make thoughts your aim;
If you can meet with
Triumph and Disaster
And treat those two
imposters just the same;
If you can bear to hear the
truth you’ve spoken
Twisted by knaves to
make a trap for fools,
Or watch the things you
gave your life to, broken,
And stoop and build ’em
up with worn-out tools:
If you can make one heap
of all your winnings
And risk it on one turn of
pitch-and-toss,
And lose, and start again
at your beginnings
And never breathe a word
about your loss;
If you can force your heart
and nerve and sinew
To serve your turn long
after they are gone,
And so hold on when there
is nothing in you
Except the Will which
says to them: “Hold on!”
If you can talk with
crowds and keep your
virtue,
Or walk with Kings – nor
lose the common touch,
If neither foes nor loving
friends can hurt you,
If all men count with you,
but none too much;
If you can fill the
unforgiving minute
With sixty seconds’ worth
of distance run,
Yours is the Earth and
everything that’s in it,
And – which is more –
you’ll be a Man, my son


Read 9622 times