Wednesday, 24 November 2021 00:00

በኬንያ ከፍተኛ የኮንዶም እጥረት ተከስቷል

Written by 
Rate this item
(0 votes)

  #ከትዳር ውጭ የሚወለዱ ኬንያውያን ውርስ አያገኙም;

               በኬንያ የተፈጠረው የኮንዶም እጥረት በከፍተኛ ሁኔታ መባባሱንና በአሁኑ ወቅት በአገሪቱ በወር 455 ሚሊዮን ኮንዶሞች የሚያስፈልጉ ቢሆንም መንግስት ግን እያቀረበ ያለው 1.6 ሚሊዮን ብቻ መሆኑ ዜጎችን ለከፋ የጤናና ማህበራዊ ችግር ሊዳርግ እንደሚችል መነገሩን ዘ ኔሽን ጋዜጣ ዘግቧል፡፡ ዘ ኔሽን ጋዜጣ ከትናንት በስቲያ ባወጣው ዘገባ እንዳለው፣ በአገሪቱ የሚገኙ የጤና ተቋማት፣ ሆስፒታሎችና ሌሎች ተቋማት ለደንበኞቻቸው በነጻ የሚሰጡትን ኮንዶም ማሰራጨት ካቆሙ አንድ አመት ያለፋቸው ሲሆን፣ ባለሙያዎች ለኮንዶም እጥረቱ መከሰት ምክንያት ነው ብለው የሚተቹት የአገሪቱ መንግስት ከፍተኛ ቀረጥ መጣሉን ነው፡፡
ከኮንዶም እጥረቱ ጋር በተያያዘ ጥንቃቄ በጎደለው የግብረ ስጋ ግንኙነት ለእርግዝና የሚጋለጡ ወጣት ሴቶችና ለተለያዩ በሽታዎች የሚጋለጡ ዜጎች ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ ማደጉን የጠቆመው ዘገባው፣ ለጋሽ ድርጅቶች በበቂ መጠን ኮንዶም እንዳያቀርቡ ከፍተኛ ቀረጥ እንቅፋት እንደፈጠረባቸውም አክሎ ገልጧል፡፡
የአገሪቱ የኤችአይቪ ኤድስና በወሲብ የሚተላለፉ በሽታዎች ቁጥጥር ቢሮ፣ አገሪቱ 2.1 ሚሊዮን ያህል ኮንዶሞችን ለመግዛት 4.6 ሚሊዮን ዶላር እንደሚያስፈልጋት መናገሩንም ዘገባው አመልክቷል፡፡
በሌላ ዜና ደግሞ፣ በኬንያ ከህጋዊ ትዳር ውጭ የሚወለዱ ልጆች፣ ወላጆቻቸው በሚሞቱበት ጊዜ ሃብታቸውን እንዳይወርሱ የሚከለክል አዲስ ህግ ከቀናት በፊት ጸድቋል፡፡ ህጉ ከትዳር ውጭ የወለዱ ቅምጦችም የሃብት ውርስ እንዳያገኙ እንደሚከለክል የጠቆመው ዘገባው፣ በርካታ ኬንያውያን ህጉ በስራ ላይ መዋሉን በመደገፍ በማህበራዊ ድረገጾች ድጋፋቸውን እየሰጡት እንደሚገኝ የዘገበው ኦልአፍሪካን ኒውስ፣ አንዳንዶች ግን እንደኮነኑት አልሸሸገም፡፡

Read 431 times