Saturday, 20 November 2021 15:06

ለፕሬዚዳንት ጆ ባይደን ደብዳቤ የፃፉት ፖለቲከኛ ምን ይላሉ?

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(0 votes)

   - የአሜሪካ እርዳታ ነው የሚያድነን የሚለው እሳቤ የተሳሳተ ነው
       - ይህ ሁሉ ርብርብ በኢትዮጵያ በኩል የአፍሪካን ተስፋ ለማጨለም ነው

         አሜሪካ በኢትዮጵያ የሰሜኑ ክፍል እየተካሄደ ከሚገኘው ጦርነት ጋር በተያያዘ እያንጸባረቀች ያለችውን  የተሳሳቱ አቋሞች አስመልክቶ በቀጥታ ለአሜሪካው ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን  የጻፉት  አንጋፋው ፖለቲከኛ ኢ/ር ዘለቀ ረዲ፣ ከአዲስ አድማስ  ጋዜጠኛ አለማየሁ አንበሴ ጋር ተከታዩን ቆይታ አድርገዋል፡-

          ለፕሬዚዳንቱ ደብዳቤ ዓላማ ምንድን ነው?
ለተተኪው ትውልድ ጥላቻ እንዳይተላለፍ ስጋት አለኝ። በተለይ አሁን ዓለም ያለችበት ሁኔታ እንደ ድሮው አይደለም፤ ህዝቡ የነቃ ነው። አሜሪካ ደግሞ ለራሳቸው ጥቅም ሲሉ ሀገር በማፍረሱ በኩል  ከሚታወቁት አገራት ቀዳሚዋ ናት።
ይህ ሁሉ ነገር ሲጠረቃቃቀም ለትውልዱ ቀላል የሚባል እዳ አይደለም የሚጥለው። በተለይ ኢትዮጵያ የአፍሪካውያን ሁሉ ተምሳሌትና መሻገሪያ እንደመሆኗ፣ ኢትዮጵያን መንካት የበለጠ ጥላቻን እንደሚያስከትልባት ተገንዝበው መሪዎቿ ለቀጣይ ትውልዳቸው አስበው እንዲሰሩ ለማሳሰብ ነው- ደብዳቤው የተጻፈው።
በደብዳቤዎ ታሪካዊ ጉዳዮችን ያነሳሉ፤ የአሜሪካና ኢትዮጵያ  የረዥም ዘመን ግንኑነትንም ይዳስሳሉ።  ለአሜሪካ በዋናነት ሊያስገነዝቡ የፈለጉት ጉዳይ ምንድነው?
የአሜሪካና ኢትዮጵያ ወዳጃዊ ግንኙነትን ስንመለከት፣ ወደ መቶ ዓመት ገደማ እድሜ እያስቆጠረ ነው። በዚህ የተነሳ ብዙዎች አሜሪካንን የኛ ሁነኛ አጋር አድርገው ይመለከታሉ። ነገር ግን ይህ ትንሽ የግንዛቤ እጥረት ያለበት ነው። በዚህ ወደ 100 ዓመት በሚጠጋ ግንኙነታችን፣ አሜሪካ የሰራችልን አንድ ድልድይ እንኳ የለም። ዘመኗን በሙሉ በዲሞክራሲ ሰበብ በኢትዮጵያውያን መካከል መለያየትን ስትፈጥር ነው የኖረችው። ይህን በግልጽ መንገር ማስታወስ ያስፈልጋል። በሌላ በኩል በደብዳቤዬ በዋነኝነት ላስተላልፍ የፈለግሁት መልዕክት፣ ለትውልዳቸው ጥላቻን እንዳያተርፉ ለመንገር ነው። በተለይ እኚህኛው ፕሬዚዳንት ሲመረጡ ከቀድሞው ፕሬዚዳንት ትራምፕ የተሻለ ነገር እናገኛለን በማለት ትውልደ ኢትዮጵያውያን እንዲመርጧቸው ብዙ ቅስቀሳዎችንና ድጋፎችን ስናደርግ ነበር። ግን ሰውየው ከተመረጡ በኋላ ወዲያው ነው ኢትዮጵያ ላይ ጥላቻቸውን ማራመድ የጀመሩት። ስለዚህ ከዚህ ጥላቻ ወጥተው እውነታችንን እንዲረዱ፣ ሁለተኛ ነገር እኛ ሃቅ እንዳለን በተለይ ህውኃት የኢትዮጵያን መከላከያ ሰራዊት በአሰቃቂ ሁኔታ መግደሉን አውቀው እንዳላወቀ መሆናቸውን ትተው፣ ከአሸባሪው  ሃይል ጎን መሰለፋቸውን በማቆም ከኢትዮጵያውያን ሁሉ ጎን እንዲቆሙ ለመጠየቅ ነው። ኢትዮጵያውያን ደግሞ እያንዳንዳችን ብቻችንንም ቢሆን የምንችለውን ሁሉ ጥረት አድርገን ኢትዮጵያን ለማዳን ጥረት ማድረግ እንዳለብን ግንዛቤ ለመስጠት ነው፤ የደብዳቤው አላማ።
በደብዳቤዎ ካነሷቸው ጉዳዮች መካከል ኢትዮጵያ በታሪኳ የውጭ ወራሪ ሃይሎችን አሸንፋ አሳፍራ መመለሷን የተመለከተው ተጠቃሽ ነው። ይህን ታሪክ  የጠቀሱበት ምክንያት ምንድን ነው?
በደብዳቤው እንደጠቀስኩት፤ እኛ በታሪካችን ጉልበት አለን ብለን የሰው ሃገር ወርረን አናውቅም፤ እንደ እድል ሆኖ ግን ተደጋጋሚ ወረራ በውጭ ሃይሎች ተፈጽሞብናል። ነገር ግን ወራሪዎች በፍጹም ኢትዮጵያን አሸንፈዋት አያውቁም። አሁንም አሜሪካኖች ጅቡቲ ሆነው ወያኔን ለማገዝ፣ ኢትዮጵያን ለመውጋት ያላቸው ፍላጎት እነሱን ትዝብት ውስጥ ከመክተቱ ውጪ ህውሃትንም አያድንም። ለአሜሪካም ታሪክ ጥሩ እንደማይሆን በማመላከት፣ ግልጽ የሆነ ማንኛውንም ወረራቸውን እንዲያቆሙ ለማሳሰብ ነው። እዚህ ዜጎች አሉን የሚሉም ከሆነ እነሱን ማስወጣት እንጂ የሰው ሃገር ላይ የራሳቸውን ዜጎች ከጥቃት እንከላከላለን የሚል ሙከራ ማድረግ የዲፕሎማሲ ህግም አይፈቅድም። ከዚህ አንጻር ያልተገባ የማጥቃት እንቅስቃሴ ውስጥ እንዳይገቡና አሜሪካ ልክ እንደ ጣሊያን በዓለም ፊት እንዳትዋረድ ለማሳሰብ ነው። በዚያው ልክ ነገሮችን በአግባቡ ተረድታ ከኢትዮጵያ ጋር ወዳጅነቷን ማጠናከር ላይ እንድትሰራ ለማሳሰብ ነው።
በደብዳቤዎ እንደጠቀሱት የአሜሪካ መንግስት  በአብዛኛው ኢትዮጵያ ላይ የተቃጡ ጥቃቶችን ሲደግፉ ነው የኖሩት፤ ለምን ይመስልዎታል በክፉ ወቅት አሜሪካ  ከኢትዮጵያ በተቃራኒው መቆምን የምትመርጠው?
 እውነቱን ለመናገር የአሜሪካውያንን የዘመናትም ሆነ አሁን ያለውን አካሄድ ብዎቻችን በግልጽ እየተረዳነው አይደለም። በተለይ አዲሱ ትውልድ ታሪክን እንይማር፣ የኢትዮጵያ እውነተኛ ወዳጆች እነማን ናቸው የሚለውን በአግባቡ እንዳይረዳ ተደርጓል። ምዕራባውያን አፍሪካን ለመቀራመት መክረው የየድርሻቸውን ሲወስዱና አንጡራ ሃብት ሲዘርፉ ኢትዮጵያ የጣሊያን ድርሻ ሆነች። ጣሊያን ስትመጣ ኢትዮጵያ  አድዋ ላይ ወራሪውን አንበርክካ በመመለሷ ምዕራባውያኑ ብዙ ነገራቸው ነው የተበላሸው። ብዙ ሃገሮች ኢትዮጵያን ምሳሌ አድርገው ባካሄዷቸው ትግሎች ከቀጥተኛው ቅኝ ተገዥነት ነጻ ወጡ። አሁን ደግሞ ብዙዎቹ በእጅ አዙር ቅኝ ተገዥነት ስር ነው ያሉት።
ምዕራባውያኑ አሁን ያላቸው አንድ ተስፋ፣ በእጅ አዙር ያላቸው የቅኝ ገዥነት ሚና ነው። ለምሳሌ ቦትስዋናን ብንመለከት፣ ትልቁ የአልማዝ ማዕድን ማውጫ የአሜሪካ ኩባንያ ነው። በዚያ በአልማዝ ማውጫው አካባቢ ማንኛውም ቦትስዋናዊ ማለፍ አይችልም። መካከለኛው አፍሪካን ስንመለከት፣ በካካዋ ምርቷ በጣም የታወቀች ነች። አንደኛው መሪያቸው “ከዚህ በኋላ ካካዎአችንን ለራሳችን ነው የምናመርተው” ብሎ ሲናገር፤ ፈረንሳዮች እንዴት አድርገው የእንቅልፍ መድሃኒት ሰጥተውት፣ የማምረት ስራቸውን ማንም ሳይቀናቀናቸው እስካሁንም እንደቀጠሉበት እንረዳለን። ስለዚህ ጦርነቱ የቅኝ ግዛት ነው። ኢትዮጵያ አሁን የተደገሰላትን የቅኝ ግዛት ካመለጠችና አንድነቷን አስጠብቃ ከወጣች፣ ሌሎች የአፍሪካ ሃገሮችንም ከእጅ አዙር ቅኝ ግዛት እንዲወጡ መንገድ ትመራብናለች የሚል እሳቤ አላቸው። ይሄን በምሳሌ ባስረዳ፣ አሁን ኢትዮጵያ የአባይን ግድብ መገደቧ አሜሪካ ላይ ምን ጉዳት ሊያመጣባት ይችላል እና ነው ውሃው እንዳይገደብ ሽንጧን ገትራ የምትሟገተው? በዚህ ውስጥ ፈረንሳይ፣ እንግሊዝና ሌሎች ምዕራባውያን አሉበት። ከዚህ አንጻር ይህ ሁሉ ርብርብ በየአቅጣጫው የሚደረገው በኢትዮጵያ በኩል የአፍሪካን ተስፋ ለማጨለም ነው። አንዳንዶች እርቅ ሲባል “ይሄ የተቀደሰ ሃሳብ ነው፤ ይሄ መንግስት እርቅ አይወድም “ይላሉ። ነገር ግን ይሄ ጸብ ዝም ብሎ የሁለት ወገኖች ጸብ አይደለም። ጉዳዩ የሕግ ተገዥነት ጉዳይ ነው፣ ጉዳዩ የባርነትና የነጻነት ጉዳይ ነው። ከባርነት ደግሞ በእርቅ ብቻ ነጻ አይወጣም። አሜሪካ በርካታ ዲፕሎማቶችን የምትልከው ኢትዮጵያውያን ጉዳዩን የተረዱበትን መንገድ ስለምታውቅ ነው። አንዳንድ ዲፕሎማቶች “ተው ኢትዮጵያውያንን  እንደ ሌሎች ማሸነፍ አይቻልም፤ ግዴላችሁም ጉዳያቸውን ለራሳቸው ብትተውላቸው ነው የሚሻለው” ማለት ጀምረዋል። አሜሪካ ይሄን ምክር  ብትሰማ ጥሩ ይሆናል። አሜሪካኖችን አሁን ላይ በጣም እያበሳጫቸው ያለው ጉዳይ፣ አጎዋን ስትከለክለን አሁንም አንረታ ማለታችን ነው። አጎዋ ለ1 ሚሊዮን ኢትዮጵያውያን የሥራ እድል የሚሰጥ ነው። ኢትዮጵያ ደግሞ የ120 ሚሊዮን ህዝብ ዜጎች ሃገር ነች። ስለዚህ ኢትዮጵያውያን “የ1 ሚሊዮን ሰው ጥቅም ይቅርብንና የ120 ሚሊዮን  ህዝብ ሃገር በሰላም ትኑር”  በማለታቸው  ነው፣ አሁን የሚያደርጉት አጥተው እየተበሳጩ ያሉት። የተለያዩ ስልቶችን ቀይሰው እየተጫወቱ ያሉት ጨንቋቸው ነው። በነገራችን ላይ በደብዳቤዬም እንደጠቀስኩት፣ አሜሪካ በጣሊያን ወረራ ጊዜ በቀጥታ ኢትዮጵያ ላይ ማዕቀብ በመጣል ለጣሊያን  ያገዘችበት ተረክ አለን፤ በሌላ ጊዜ ደግሞ ንጉሡ የገዙትን የጦር መሳሪያ በቀጥታ ለዚያድ ባሬ ሰጥታ ነው ያስወረረችን። በወቅቱ  ራሽያ ነበረች ከኢትዮጵያ ጎን የቆመችው። በሶስተኛ ደረጃ በእርቅ ስም ወያኔን እንዴት በኢትዮጵያ ህዝብ ላይ እንደጫነችው የቅርብ ጊዜ ትውስታ ነው። በወቅቱ በእርቅ ስም እያደራደረች በጎን የወያኔን ጦር ግፋ እያለች፣ ኮ/ል መንግስቱ ኃ/ማርያምን ከሃገር እንዴት እንዲወጡ እንዳደረገች ይታወቃል። ከዚያ በኋላ ለ27 ዓመት የኢትዮጵያ ህዝብ ያ ሁሉ መከራ ሲደርስበት፣ አሜሪካ አንድም ጊዜ ስታወግዝ ሰምተን አናውቅም። አሁንም መከላከያ ሰራዊታችን ህውሃትን ሲያሯሩጥ አሜሪካም ጩኸቷን ትጨምራለች፤ እነሱ ገፍተው የመጡ ሲመስላት ደግሞ ዝም ትላለች። በቀጥታ ጦርነቱንም በተለያየ መንገድ እየመራች ያለችው አሜሪካ ነች። ግን በዚህ ሁሉ መሃል ኢትዮጵያ ትፈተናለች እንጂ በእርግጠኝነት በመጨረሻ አሸናፊ ሆነን እንወጣለን። ይህን ደብዳቤ ምናልባት ጆ ባይደን ባያነበው እንኳን ነገ ከነገ ወዲያ አሜሪካውያን፣ ሃገራቸው እየሰራችብን ያለውን  ግፍ እንዲረዱት ያደርጋል።
ከአሜሪካ ጋር ውዝግቦች እየተበራከቱ መምጣታቸው ቀጣይ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነቱን አደጋ ላይ ይጥላል፤ በጥንቃቄ መያዝ አለበት የሚሉ ሃሳቦች ይሰነዘራሉ…
እውነት ለመናገር በእርዳታ ያደጉ ወይም በአሜሪካ እርዳታ ያደጉ ሃገሮችን አንድም መጥቀስ አንችልም፤ ሁለተኛ እርዳታቸው የሚያሳድግ አይደለም፤ እንደውም ላለማደግ መስመር ነው የሚዘረጉት። ስለዚህ የአሜሪካ እርዳታ ነው የሚያድነን የሚለው እሳቤ የተሳሳተ ነው። ያለ አሜሪካ እርዳታ ያደጉ ሃገሮችን ምሳሌ አድርገን መነሳት እንችላለን። ለምሳሌ እነ ቻይና፣ ኮሪያን መጥቀስ ይቻላል። የእነሱ እርዳታ ዲሞክራሲ የሚል ካባ የለበሰ ነው። ገንዘቡም ለስልጠና ለመሳሰለው ነው የሚውለው። በዚያው ልክ በዚህ ሰበብ የሚገቡ ሰዎቻቸው ሰላዮች በመሆናቸው እርስ በእርስ የምንጋጭበትን፣  ልዩነታችን  የሚሰራበትን መስመር ነው የሚዘረጉት። እንደው አንዳንድ ጊዜ ጠንከር ያለ መንግሥት ኖሮን፣ ለውጪ አካላት ዝግ  የሆነ ሃገራዊ ፖሊሲ ብንከተል እላለሁ። የፋሲል ግንብን የገነባነው ይህን ፖሊሲ በተከተልንበት ወቅት እንደነበር ታሪክ ያስረዳናል። ከዚህ አንጻር ሁኔታው እኛ ወደ ውስጣችን እንድንመለከት ይረዳናል። በዲፕሎማሲ ረገድ ካየንም አሜሪካ  የምትቀርባቸውን ሃገሮች እንዳያመልጧት ብዙ ጥንቃቄ በማድረግ ላይ የተመሰረተ አካሄድን ነው የምትከተለው። ከዚህ አንፃር የአሜሪካ ዲፕሎማሲ ለኛ በብዙ መልኩ አይጠቅመንም። አብዛኛው እርዳታቸው በመንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች የሚውልና በአመዛኙ  በሆቴል መዝናኛና አበል የሚያልቅ ነው። እኛ አሜሪካን ላይ አንድም ቀን ድንጋይ ወርውረን አናውቅም። በአንጻሩ  እሷም አንድም ቀን ከችግራችን ጎን ቆማ አታውቅም።

Read 4725 times