Thursday, 25 November 2021 06:29

እሾህን በእሾህ ጠላትን በጠላት መንገድ

Written by  -አያሌው አስረስ-
Rate this item
(4 votes)


         “የክልሉ ህዝብ ራሱን ለመጠበቅ ሲሰለጥን አቁሙ እያሉ የመንግሥት ሰዎች ይከለክሉናል። አመራሮቹ መሳሪያ በመጋዘን አከማችተው ስጡን እንዝመት ስንል ባዶ እጃችሁን ሂዱ ይሉናል። መንግሥት የሴራው አንድ አካል ነው? ስንል ጭፍን ደጋፊዎች ይጮኹብናል”
             
        አንድ ሰው ማድረግ የሚፈልገው ነገር አለው። እንዳሰበው ቢፈጽመው በቅርብና ሩቅ ዘመዶቹ ወይም ጓደኞቹ ወይም በሰው ሁሉ ዘንድ የሚያስነቅፍ የሚያስወግዝ ሊሆን ይችላል። እየፈለገ ከድርጊቱ ሊታቀብ ይገደዳል። ነገሩን የሚተወው  ድርጊቱን መፈጸሙ በወደፊት ዘመኑ ላይ የሚያስከትለውን ጉዳት አስቦ ነው። ይህ ይሉኝታ ይባላል። ከዛሬ ይልቅ መጪው ጊዜ ይበልጣል ብሎ ስለ ወደፊቱ የማሰብ የመጨነቅ፣ የይሉኝታ ፅንሰ ሐሳብ በትግርኛ ቋንቋ ውስጥ አለመኖሩን  ብዙዎች ይናገራሉ።
የትምህርት ሚኒስትሩ፣ የኢዜማ ሊቀ መንበር ፕ/ር ብርሃኑ ነጋ፣ ሰሞኑን የኢቲቪ የቀይ መስመር እንግዳ ሆነው ቀርበው ነበር። የኢትዮጵያ ሕዝብ አብዮታዊ ፓርቲ (ኢህአፓ) የትጥቅ ትግል ለማካሄድ፣ የኢትዮጵያ ሕዝብ አብዮታዊ ሰራዊት አቋቁሞ ወደ ጫካ ሲገባ፣ ትግራይ ውስጥ አሲምባ በሚባል አካባቢይዟቸውከገባውታጋዮች አንዱብርሃኑነጋነበሩ፡፡      “ስለ ወያኔ በምደርስበት ድምዳሜ ተሳስቼ አላውቅም” የሚሉት ፕ/ር ብርሃኑ፤ የወያኔን መሰረታዊ ባህሪዎች  ረገጥ አድርገው ነግረውናል። በመጀመሪያ የነገሩን ወያኔዎች የፈለጉትን  ለማድረግ  ምንም  አይነት ወንጀል ከመፈጸም የማይቆጠቡ መሆናቸውን ነው። በእነሱ ዘንድ ለሞራል ህግ  መገዛት ብሎ ነገር አለመኖሩን የነገሩን፣ በማስረጃነት ኢትዮጵያዊነትን ከትግራይ ሕዝብ አእምሮ ውስጥ ለማውጣት  ካህናትን ሳይቀር በአደባባይ ቆባቸውን እያስወለቁ ይሰድቧቸው ያንገላቷቸው እንደ ነበር በመጥቀስ ነው። ሌላው የወያኔ ባህሪ ብለው የገለጡት የሚፈልጉትን ለማግኘት ወይም ከፈለጉት ቦታ ለመድረስ ማድረግ  ያለባቸውን  ሁሉ ከማድረግ የማይመለሱ መሆናቸውንም ነው። በዚህ ቁርጠኛ ናቸው ብለዋል። ስለዚህም  ነው የትግራይ ህዝብ፣ ከአጎራባቹ የአማራና የአፋር ሕዝብ ጋር የሚኖረው የነገው ሕይወት የማያሳስባቸውና የማያስጨንቃቸው፤ ማጥፋትና ማውደም የሚችሉትን ሁሉ ያለ ርህራሄ የሚያጠፉትና የሚያወድሙትም።
ስለዚህም ነው አካባቢያቸውን ለቀው መሰደድና መፈናቀል ያልፈለጉና ያልቻሉ ሰዎችን በሚያገኙበት ጊዜ፣ ነገ ሃይል ያበጃል የሚሉትን ወጣት እየለቀሙ የሚገድሉት፤ አባትን እንደወጣ የሚያስቀሩት፤ በእናቶችና በሴት ልጆች ላይ ልዩ ልዩ ጥቃት የሚያደርሱት፡፡ ምናልባት በፈጣሪ እርዳታ ከሞት ተርፈው የነገ ሕይወታቸውን “ሀ” ብለው እንዳይጀምሩ ጥሪት ለማሳጣት በማሰብ ከብቶቻቸውን የሚገድሉት፤ ቤቶቻቸውን የሚያፈርሱት።
 ዶ/ር ብርሃኑ አጠንክረው የተናገሩትና መታለፍ የሌለበት ጉዳይ፣ ትሕነግ የሚፈልገውን ለማድረግ ምንም አይነት የሞራል ግዴታ የማይሰማው አሸባሪ ቡድን በመሆኑ፣ እሱን  ለማጥፋት የሚቻለው እንደ ራሱ ሞራል አልባ በመሆን ነው።  ይህ  ህሊና የለሽ አሸባሪ ቡድን ያሰማራቸው ሰዎች፣ የመከላከያ ሰራዊታችን ክልሉ ውስጥ በነበረበት ጊዜ፣ በአይኑ በርበሬ እስከ መሞጀር፣ “ጥቃት እየደረሰብን ነው” ብለው  ጦሩ ለጥቃት እንዲጋለጥ እስከ ማድረግ መሄዳቸውን ከሠራዊቱ አባላት አንደበት መስማታችንንም አንዘነጋም።
ከተማረኩት የትሕነግ መሪዎች አንዱ የሆኑት ኮሎኔል ግኡሽ፣ መሳሪያ ከያዘው እኩል  የሆነ ሰው  ቁጥር ባዶ እጁን የሚዘምት  መሆኑን ተናግረዋል። ይህ ባዶ እጁን የሚንቀሳቀስ የሰው ኃይል ቁስለኛ ለማንሳት፣ ከሞተ ሰው ላይ መሳሪያ አንስቶ ለመዋጋት ብቻ ሳይሆን፣ በሲቪል አለባበስ ንፁህ ሰው በመምሰል፣ በመከላከያው በልዩ ኃይሉና በሚሊሽያው ላይ ጉዳት ለማድረስም ጥቅም ላይ የሚውል መሆኑን አለመጠርጠር የዋህነት ነው።
አውሬ ለሆነው አሰራራቸው ሊጠብቃቸው የሚገባው፣ ያለምንም እርህራሄ ለአውሬ የሚገባው ጥቃት ነው። በአጭር አማርኛ፣ በሚገባቸው ቋንቋ ማናገር ነው።
አንድ ገጠመኜን አስታውሼ ከጎጃም አንድ ወዳጄ ወደ አደረሰኝና መግቢያዬ ላይ ወዳሰፈርኩት ሀሳብ ልመለስ።
በ1992 ዓ.ም የሁለተኛ ደረጃ መልቀቂያ ፈተና ለመፈተን፣ ደቡብ ክልል ወደሚገኘው አማሮ ኬሎ ሄጄ ነበር። አማሮ ኬሎዎች የዘር ግንዳቸውን ከጎንደር እንደሚስቡ ተነግሮኛል። የልዩ ወረዳው ከተማ ውስጥ እንደ ማንኛውም የኢትዮጵያ ከተሞች ሁሉ ብዙ አማራዎች ይኖራሉ። በወቅቱ አየር ሃይል ምልመላ እያካሄደ ነበር። በአካባቢው ከተወለዱ የአማራ ልጆች አንዱ የአየር ኃይል አባል ሆኖ ለመቀጠር ይጠይቃል። ቅድሚያ ለብሔረሰቡ ልጆች ነው ተብሎ ይመለሳል። ከብሔረሰቡ ተወላጆች አንድም ሰው ብቅ አይልም። የመመዝገቢያው ጊዜ አልቆ ከመዘጋቱ በፊት ተመልሶ ይሄዳል። አሁንም ቅድሚያ ለብሔረሰቡ ነው የሚል መልስ ይሰጠዋል። የደረሰበት መገፋት የመረረው ይህ ሰው፤ “ለሀገሬ ለመሞት ትከለክሉኛላችሁ ወይ?” አላቸው፡፡
ደሴ ኮምቦልቻና ሌሎችም አካባቢዎች ከአሸባሪው መዳፍ ነጻ ሲወጡ በሚደረገው ጥናት የሚገኘው ውጤት ገና የሚደረስበት መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ፤ እስከ አሁን በተደረገው የዳሰሳ ጥናት፣ በአማራ ክልል በትህነግ እጅ ተይዘው በነበሩ 45 ወረዳዎች፣ ሁለት መቶ ሰማንያ ቢሊዮን ብር የሚገመት ዋጋ ያለው ንብረት መውደሙን፣ በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ዜጎች መገደላቸውን፣ ስድስት ሚሊዮን የሚሆኑ ሰዎችም መፈናቀላቸውን ክልሉ አሳውቋል። ይህ ሁሉ የሆነው የትግራይን ወራሪ ኃይል መግታትና ወደ ክልሉ መመለስ ባለመቻሉ ነው።
ጎጃሞች ደግሞ የመሰልጠን እድል እየተነፈጉ፣ ለመዝመትም ሲያስቡ ያለመሳሪያ ባዶ እጃቸውን እንዲሄዱ እየተደረጉ መሆኑን እየተናገሩ ነው። ሌላውም አካባቢ ተመሳሳይ ችግር ሊኖር ይችላል። በአንዳንድ አካባቢዎች የሚሰማው ይህ ቅሬታ ፈጥኖ መፈታት፣ መልስ ማግኘትም አለበት።
የትም ፍጪው ዱቄቱን አምጪው ይባላል። አሁን ያለው ትልቅ ሥራ ተጨማሪ የአማራና አፋር  አካባቢዎች በአሸባሪው እንዳይያዙ መከልከል፣ የተያዙትን ደግሞ ማስለቀቅ፣ ትሕነግን ወደ ክልሉ መመለስ ነው። በተግባሩ አውሬ ለሆነው ትሕነግ፣ አውሬ ሆኖ መነሳት የግድ ነው። እሾህን በእሾህ!  

Read 1904 times