Print this page
Thursday, 25 November 2021 06:36

የእኛ ሙሽራ ኩሪባቸው፣ በእንግሊዝ አናግሪያቸው!

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(1 Vote)

  እንዴት ሰነበታችሁሳ!
ስሙኝማ…የፈረንጅ ወዳጅ ‘ሲፋቅ’ ምን እንደሆነ አየነው አይደል!
“ወ/ሮ እከሊት እንደው ሁልጊዜ እጠይቅሻለሁ እያልኩ እርስት እያደረግሁት--”
“ምኑን?”
“ያቺ ልጅሽ እንዴት ነች? እንደው እዛ ሰው ሀገር ተመችቷት ይሆን?!”
“የትኛዋን ነው የምትዪኝ?”
“ያቺ እንግሊዝ ሀገር ያለችው…”
“እስከዛሬ አልነገርኩሽም እንዴ!”
“ምኑን?”
“እሷማ ፈረንጅ አገባች እኮ…”
እልልልልልል! ለእንደዚህ አይነት ዜናማ ለንደን ድረስ የሚሰማ እልልልታ ነው የሚያስፈልገው፡፡ ልከ ነዋ…ፈረንጅ ነዋ ያገባችው!
እንዲህ ነው ነገሩ፡፡ ማንም ሰው ከማንም ጋር ቢጋባ የሁለቱ ሰዎች ጉዳይ ነው፡፡ ብዙዎቻችን “ፈረንጅ” ለምንላቸው ያለን አመለካከት..አለ አይደል…ብዙ የሚጎድለው ነገር አለ፡፡ የምር እኮ “ፈረንጅ” መምሰል የምንፈልገው እኮ መአት ነን! አሁንም እዚቹ አዲስ አበባ ውስጥ ፈረንጅነትን ‘ጎሮሮውን አንቀን’ የራሳችን ንብረት ለማድረግ መከራችንን የምናይ መአት አይደለን እንዴ!
ማነህ፣ እንትና... ‘የሲፕ ፕሮግራሜን’ አበላሻችሁ አትበለንና......እባክህ ጥቁሩን የፀሀይ መነጽር ከጨለማው ቡና ቤት ስትወጣ መልሰህ ታደርገዋለህ፡፡ ሰውዬ! እኛም እኮ ቀጭኑ ድራፍት አልገባልን አለ! ከምሽቱ ሦስት ሰዓት ነዋ! ማነሽ እንትናዬ  በእዚህ በነሀሴ ብርድ ነፋሱ በጆሯችን አጠገብ እየጮኸ እያለፈ ‘ባክ አውት’ ነው ምን የምትሉት ‘የጀርባ ራቁት ልብስ’ (ሎካል ስም ለመስጠት ያህል ነው፣) ተለብሶ ይወጣል! በኋላ ብርድ አጠናፍሮሽ ወዳጆሽን ላይ ታች እንዳታሯሩጪ! ደግሞ ትንሽ ስፖርት ቢጤ ሥሪና ከጀርባ የሚታየው ‘ፒዩር’ አጥንት ላይ ትንሽዬም ቢሆን ሥጋ ነገር ጨምሪበትማ! በሆነ ባልሆነው “እሷ እኮ እንደፈረንጅ ነው የምትለብሰው!” እያሉ ሳሩን ሳታዪ ወደ ገደሉ እየወሰዱሽ ነው፡፡ ምን ይደረግ...
የእኛ ሙሽራ ኩሪባቸው
በእንግሊዝ አናግሪያቸው
ሲባል በተኖረበት ሀገር በ‘ፈረንጅ አፍ’ መናገሩ መግባቢያ መሆኑ ቀርቶ የ‘ፍርንጅና’ አንዱ መልኩ ነበር፡፡ እናላችሁ... ሀቅ ሃቁን እንነጋገር! “ፈረንጅነት” የሰው ልጅነት የ‘ፕላቲነም’ ደረጃ ነገር የሚመስለን ከላይ እስከ ታች መአት ነን፡፡
ስሙኝማ…ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ…ከብዙ ዓመታት በፊት በተለይ አንዳንድ እህቶቻችን ቆዳቸውን የ”ፈረንጅ” ለማስመሰል  ያደርጉ የነበረው ሙከራ ግርም የሚል ነበር፡፡
“በቃ፣  ሙሉ ፊትሽን በደንብ አድርገሽ ትቀቢውና ቅዳሜና እሁድ ከቤት ዝር ማለት የለም፡፡ ሰኞ ምን የመሰለች ፈረንጅ ሆነሽ ባትወጪ ምን አለች በዪኝ!”
ሰኞ ሲመጣ እሷዬዋ አትወጣም፣ በሚቀጥለው ሰኞም አትወጣም፣ በሦስተኛውም ሰኞ…ብቻ ምን አለፋችሁ ‘ዲስአፒር’ ታደርጋለች፡፡ እንዴት ትውጣ! ያቺን የመሰለች ልጅ…ጀማሪ የፕላስቲክ ቀዶ ጥገና ሀኪም የተለማመደባት መስላ እንዴት አደባባይ ትውጣ! ‘ቶክ ኦፍ ዘ ታውን’ ምናምን ትሆናለቻ!
“እናንተ፣ እንትናን አያችኋት?”
“እሷ ልጅ ግን ምን ሆና ነው? አሲድ የፈሰሰበት የጋራዥ ቱታ መስላለች እኮ!” ቂ...ቂ...ቂ.... (ግን ማን ነበር ይቺን አባባል የነገረኝ? ተጨማሪ ጥያቄዎች ስላሉኝ ነው፡፡) ፈረንጅ እንሆናለን ብለው ከምኑም ያጡ ያሳዝናሉ፡፡ አሁንም በሆነ ነገር “ፈረንጅ” እንመስላለን ብቻ ሳይሆን እንሆናለን ብለን መከራችንን የምናይ መአት ነን፡፡
ስሙኝማ…ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ…በብዙ ነገር ለ‘ፈረንጅ ቅድሚያ” የሚሰጥባት ሀገር ነች፡፡ ለምን ይዋሻል ማለት እዚህ ላይ ነው፡፡ የምድረ ፈረንጅን ጉድ እያየን “እንዴት እንዲህ ያደርጉናል!” “እንዴት ይሄን ሁሉ ሴራ ያስቡብናል!” የምንለው እኮ ለምን መሰላችሁ… ‘ሳናውቃቸው፣ ያወቅናቸው’ ሲመስለን ስለኖረ ነዋ!
በፈረንጅ ስም ሁሉንም በአንድ ሙቀጫ ከትቶ ዘነዘና ፍለጋ መሄድ አሪፍ አይደለም፡፡ አይደለም እኛ ላይ ሴራ ሊሸርቡ፣ ፖለቲከኞቻቸውና ጋዜጠኞቻቸው የሚያስቧቸውን ተንኮሎች ሊያስቡ ይቅርና ከእነመኖራችን የማያውቁ ብዙ ሚሊዮኖች አሉ፡፡ ሀቁ ይሄ ነው፡፡ ሰሊጥና ኑጉ ቦታ ቦታቸውን ይያዙ ለማለት ያህል ነው፡፡
ግን እዚህ ሀገር ራሳችን በራሳችን ላይ የምንፈጽመው ጭቆና ምን መሰላችሁ… “ኬኩ ለፈረንጅ፣ ፉርኖው ለእኛ፣” የሚሉት ነገር፡፡ እንግዳ መቀበል ሌላ፣ ራስን በተዘዋዋሪ መንገድ ማሳነስ ሌላ! ከላይ እስከ ታች በፈረንጅነትና በሀበሻነት መሀል የሆነ የተሰመረ የሀሳብ መስመር ያለ ነው የሚመስለው፡፡ (እኔ የምለው… እግረ መንገድ ለጠቅላላ እውቀት ያህል…ጂኦግራፊ ነው ምናምን ትምህርት ላይ “የሀሳብ መስመሮች” ይባሉ የነበሩ ነገሮች እስካሁን ‘ሀሳብ ብቻ’ ናቸው እንዴ! አሀ…ጉልበተኛና ነጣቂ የበዛበት ዘመን ስለሆነ፣ እነሱንም ወስደዋቸው እንደሁ ብዬ ነው፡፡)
ታዲያላችሁ… ሆቴል ምናምን ገብታችሁ ሀያ ምናምን ደቂቃ ማንም አስተናጋጅ አጠገባችሁ ዝር አይልም፡፡ እናም “ወይ ሥራ በዝቶባቸው ይሆናል” በሚል መምጣታቸው አይቀርም ብላችሁ ትጠብቃላችሁ፡፡ መምጣቸውማ አይቀርም፣ ግን መጀመሪያ ከሠላሳ ሴኮንዶች በፊት የገባ ፈረንጅ ስላለ ለእሱ ቅድሚያ መስጠት አለባቸው፡፡ ፈረንጅዬው እኮ ሦስት፣ አራት አስተናጋጆች በአንድ ጊዜ ግር ሲሉበት ገና በቅጡ እንኳን አልተቀመጠም! እንዲህ ነን፡፡
ለፈረንጅ ሰፍ የማለት ነገር ሲነሳ ትዝ የሚለኝ አንድ ክስተት አለ፡፡ ከአራት፣ አምስት ዓመት በፊት የሆነ ነው፡፡ የሆኑ ወጣት ወንድና ሴት ምኒልክ አደባባይ አጥሩን ደገፍ ብለው ፎቶ ይነሳሉ፡፡ ይኸኔ ሁለት ጸጥታ አስከባሪዎች መጡና እያካለቡ አባረሯቸው፡፡ ምኒልክ ሀውልት አጠገብ “እዚህ አካባባ ፎቶ ማንሳት በጥብቅ የተከለከለ ነው!” የሚል ነገር የለም፡፡ እሺ ይሁን እንደዛ ያደረጉት ምክንያት ቢኖራቸው ነው ብሎ ማለፉ ቀላል ነበር...የሆኑ “ፈረንጆች” ባይመጡ ኖሮ!”  
ድፍን አምስት ደቂቃ ሳይሞላ ሰብሰብ ያሉ “ፈረንጆች” ይመጣሉ፡፡ የካሜራው ብዛት ተዉት፡፡ ገና እዛው የነበሩት ሁለቱ ጸጥታ አስከባሪዎች ምን ቢያደርጉ ጥሩ ነው? የራሳቸውን ብቻ ሳይሆን ከሌሎች መአት ሰዎች ፈገግታ ተውሰው የጊነስ ሰዎች ባለማየታቸው በሚያስቆጭ ፈገግታ ተቀበሏቸው፡፡ ካሜራ ሁሉ እምዬ ምንሊክ ላይ ተደቀነ፡፡ እንደ ወጣቶቹ አጥር መደገፍ ምናምን ሳይሆን ሰተት ብለው ሀውልቱ ድረስ እንዲሄዱ ተፈቀደላቸው፡፡ በእርግጠኝነት መናገር የሚቻለው “ለፈረንጅ ፍቀዱ፤ ለሀበሻ አትፍቀዱ” ትእዛዝ ተሰጥቷቸው ሳይሆን...አለ አይደል...በቃ፣ “ፈረንጆቹ” ፈረንጅ ስለሆኑ ነው፡፡
እናማ...ምን መሰላችሁ፤ በዚህ አስቸጋሪ ወቅት ራስን መለስ ብሎ ማየት አስፈላጊ ነው፡፡ ቀደም ስንል የተለማመድናቸውን ሳይታወቀን ራሳችንን ዝቅተኛ ደረጃ ላይ ያስቀመጥንባቸውን ነገሮች መለስ ብለን ማየት ነው፡፡
“ችሱ ፈረንጅ ነው፤ ቀጠሮ ያከብራል፡፡”
“እረ እሱ እንዲህ አይነት ነገር አያውቅም፣ ፈረንጅ ነው እኮ!”
“የእሷ አለባበስ ይምጣብኝ፡፡ ፈረንጅ እኮ ነች!”
አሀ... ጥሩ፣ ጥሩውን ነገር ሁሉ ለፈረንጅ ሰጥተን ለእኛ ምን ሊተርፈን ነው! ኮሚክ እኮ ነው...የራሳችን የሆነውን ንቀን ከርመን ዞሮ ሲመጣ የምንሻማው እኮ “ከፈረንጅ ስለመጣ” ነው፡፡ በፊት እኮ በተለይ ከተማ ውስጥ የተነቀሰች ሴት ማየት የሚያስጨበጭብ ሳይሆን “ንቅሳቷ ብታዩት  እኮ ጋዜጣ በሉት!” እየተባለ መሳሳቂያ ነበር፡፡ (በነገራችን ላይ... በተለያዩ የሀገራችን ክፍሎች የምትደረግ እያንዳንዷ ንቅሳት ትርጉም አላት፡፡ በካታሎግ እየተመረጠና እነ እከሌ ስላደረጉት ብቻ ተብሎ የሚደረግ አልነበረም፡፡) አሁን ስንቀልድበት በኖርነው፣ ዘጠና ምናምን የሰውነታችንን ክፍል  ልናዥጎረጉር!  አንቺ... በቀደም መሀል ከተማ አራት አምስተኛ አካልሽ ‘ልብስ ለምኔ’ ሆኖ ያየንብሽ ልጅ፣ የንቅሳትሽን ትርጉም በቲክቶክ ልቀቂልንማ፡፡ አሀ... የሆነ አራስ ልጅ የተረተረው የልብስ ስፌት ክር መስሏል እኮ!
የእኛ ሙሽራ ኩሪባቸው
በእንግሊዝ አናግሪያቸው
አይነት ፈረንጅነት፣ ለእስክስክታ ካልሆነ በቀር የትም አያደርሰንም ለማለት ያህል ነው፡፡
ደህና ሰንብቱልኝማ!


Read 1395 times