Thursday, 25 November 2021 06:36

ኤፒክቲተስ- ታላቁ የስቶይክ ፈላስፋ

Written by  -ያዕቆብ ብርሃኑ-
Rate this item
(0 votes)

በእርሱ ዘመን ከነበሩት ፈላስፎች በተለየ መልኩ ኢፒክቲተስ ይህንን ዓለም ለመረዳት ከመታተር ይልቅ የተሟላ ሕይወት ለመምራት የሚያስችሉ የሞራል ልህቀቶች ማርቀቅ ላይ በርትቷል፡፡ የልህቀቱ አስተሳሰብ፤ አስኳል የሞራል እድገትን በማከናወን ለሞራል ልከኝነት መብቃት የሚል ነበር፡፡
                
            የተሟላና ደስተኛ ሕይወት መኖር የምችለው እንዴት ነው?
  ጥሩና መልካም ሰው የምሆነውስ..?
      እነዚህን ኹለት ጥያቄዎች በተሟላ ሁኔታ መመለስ የታላቁ የስቶይክ ፈላስፋ፣ የኤፒክቲተስ የሕይወት ዘመን ነጠላ ተልዕኮ ነበር፡፡ በእኛ ዘመን ይህን መሰሉ የሕይወት አረዳድ በመዳከሙ አስተሳሰቡ ዝነኛ ባይሆንም ቅሉ ለኹለት ምዕተ ዓመታት በታላላቅ ፈላስፎች እሳቤዎች ላይ ሳይቀር ተጽዕኖ ማሳረፍ የቻለ ታላቅ ሰው ነበረ - ኤፒክቲተስ፡፡
ኤፒክቲተስ ፍልስፍና እንደ አርስቶትል ከንጉስ መዓድ የሚቆርስበት ዕድል ብታቀርብለትም፣ እርሱ ግን ሰው ለመሆን መታገልን መረጠ። ዘመኑን ሙሉ በደሳሳ ጎጆ ውስጥ ኖረ። ለኤፒክቲተስ ፍልስፍና ከባርነት ነፃ አውጥታዋለች። እርሱም በምላሹ የምዕራቡ ዓለም ለምሥራቁ አቻው በኩራት የሚያቀርባት ብቸኛ ሰው ሰው የምትሸት ምንድን ከሚል ከፊል ድንቁርና የታከከው ጥያቄ ጥርቅም የተላቀቀች ልሳን አስታጠቃት።
ኤፒክቲተስ፤ ሰው በሁለት ፍፁም ተፃራሪ ኃይሎች መሳሳብ የሚንገላታ ግንዝ ፍጥረት እንደሆነ ቀድሞ የተረዳ አሳቢ ነበር። ከራሱ ከሰውየው ውስጣዊ ማንነት የሚመነጭና ከሰውየው ቁጥጥር ውጪ በሆነ በምልዓተ ዓለሙ የሚታዘዝ ኃይል… ውጫዊውን ኃይል ልትቆጣጠረው ስለማይቻልህ ውስጣዊውን ኃይልህን በሚገባ መግራት አለብህ። ኤፒክቲተስ፤ “እንድትከፋ የሚያደርግህ ክስተቱ በራሱ ሳይሆን ለክስተቱ የምትሰጠው ምላሽ ነው።” ይላል።
‹‹ከእርስዎ አቅም በላይ የሆነ ነገር ሲከሰት በእጅዎ ያለና ሊቆጣጠሩት የሚችሉት ብቸኛ ነገር ለተፈጠረው ነገር የሚኖረዎ አስተሳሰብ ብቻ ነው፡፡ ወይ ይቀበሉታል ወይ ይበግኑበታል፡፡ የሚያስፈራን፤ የሚያሽመደምደን ነገር ክስተቱ ብቻውን ሳይሆን ስለ ክስተቱ የሚኖረን ግንዛቤም ጭምር ነው፡፡ የሚረብሹን ክስተቶቹ ብቻ አይደሉም፡፡ ክስተቶችን በአዕምሮአችን የምንተረጉምበት መንገድ እንጂ፡፡››
 በኤፒክቲተስ አስተምህሮ መሰረት፤ ሰው ከመሰሎቹ፣ ከዓለም፣ ከስነ ተፈጥሮ ጋር መናበብ ሕብር ይኖረው ዘንድ ራሱን፣ ራስን መግዛትን ማሰልጠን አለበት።
አስተምህሮዎቹ ለዚህ የስክነት መሻት የሚመሩ መመሰጦች ናቸው። ዛሬ ዓለም በተረበሸ ባህር ላይ እንደምትንገላወድ ታንኳ መናወጥ ውስጥ የገባችው ራስን መግዛትን በቅጡ ሳይለማመዱ ዓለምን ለመግዛት በሚጣጣሩ ግለሰቦች ነሲብ ውሳኔ ነው።
 ኤፒክቲተስ ከክርስቶስ ልደት በኋላ በ54 ዓ.ም በምሥራቃዊ የሮማዊያን ግዛት በሂሪያፖሊስ በባርነት ቀንበር ሥር ተወለደ፡፡ ባሪያ አሳዳሪው ኢፓፍሮዲቱስ የሮማው ንጉሥ ኔሮ የአስተዳደር ጸሐፊ ነበር፡፡ ገና ከልጅነቱ ጀምሮ ኤፒክቲተስ በሚያሳየው የአዕምሮ ንቃት የተደነቀው ኢፓፍሮዲቱስ ይማር ዘንድ ታዳጊውን በዘመኑ ታላቅ ወደነበረው ስቶይክ ፈላስፋ ጋይውስ ሙሰይስ ሩፉ ዘንድ ወደ ሮም ላከው፡፡ በግሪክ ቋንቋ የተገኘው የመምህሩ ሩፉ አስተምህሮ እንደሚያወሳው፤ ኢፒክቲተስ ስለ ሰው ልጆች እኩልነት አስተሳሰብ ያዳበረው ራፉን ተጠግቶ በመማሩ ሳይሆን አይቀርም፡፡ ኢፒክቲተስ የራፉ ዝነኛ ደቀ መዝሙር ነበረ፡፡ በዚሁም ሰበብ ከባርነት ነጻ ወጥቷል፡፡
     ንጉሥ ዶሚሻን ፈላስፎችን ማሳደድ እስከ ጀመረበት እስከ 94 ዓ.ም ድረስ ኢፒክቲተስ በሮም አስተምሯል፡፡ ቀሪውን የሕይወት ዘመኑን በግሪክ ሰሜን ምዕራብ ዳርቻ በኒቂያፖሊስ አሳልፏል፡፡ በዚያም የማስተማሪያ ማዕከል አቋቁሞ በክብር እና በሕብር የመኖርን ጥበብ ያስተምር ነበር፡፡ በጣም ከታወቁት የኤፒክቲተስ ተማሪዎች መካከል በኋላ የሮማ ገዥ የሆነው ማርከስ አውሬሊየስ አንቶኒየስ ይገኝበታል፡፡ አውሬሊየስ በኢፒክቲተስ ስቶይክ ፍልስፍና ቀመሮች መነሻነት በርካታ ተምሰልስሎታዊ ሐቲቶችን (Meditation) ጽፏል፡፡  
      ኢፒክቲተስ የላቀ የክርክር እና የሎጂክ ዐዋቂ ቢሆንም ለይስሙላ ይህንን ክህሎቱን ለማሳየት ሲል ብቻ ተጣጥሮ አያውቅም፡፡ ግድየለሽነትን አብዝቶ ይቃወማል፡፡ ተማሪዎቹን ኑሯቸውን በትኩረትና በብልሐት ይኖሩ ዘንድ ይመክራል፡፡ ኢፒክቲተስ የሚናገረውን ነገር በተግባር ይኖረዋል፡፡ ምንም የዝና፣ የሐብትና የቅንጦት ፍላጎት ሳይኖረው ዘመኑን ሙሉ በትንሽ ጎጆ ውስጥ ነበር፡፡ በ135 ዓ.ም አካባቢ በዚያው በኒኮፖሊስ አረፈ፡፡
      የኢፒክቲተስ የፍልስፍና ዋነኛ ዓላማ፤ ተርታው ሰዎች በሕይወታቸው ውስጥ የሚገጥሟቸውን ፈተናዎች፣ ሐዘን፣ ብስጭት፣ ምስቅልቅሎች ሁሉ የሚፋለሙበት ምክንያታዊነትና የስሜት ብስለት ማስታጠቅ ነበር፡፡ የሞራል አስተምህሮዎቹ ይሉኝታን፣ ጽድቅን፣ የሕይወትን ፍሬ ከርስኪ ሁሉ የሚደመስሱ ነበሩ፡፡
     ብዙው አንባቢ በሐይማኖት አስተምህሮ ላልታጠረ መንፈሳዊ ዕድገት ንባብ ወደ ምሥራቅ ሲያማትር፣ ምዕራቡ ጠቃሚ ምናልባትም ዘመን አይሽሬ የሕይወት ልምምድ ተግባራዊ ማተማሪያ አለው፡፡ የወግ ዐዋቂው ኢፒክቲተስ ሥራዎች ከሰው ልጆች ታላላቅ ሥነ - ጽሑፋዊ የሥልጣኔ ሥራዎች መካከል ይመደባሉ፡፡ አስተምህሮዎቹ ለቡድሂስቱ አስተምህሮ ዳማማፓም እና የላኦ ቱዙ ታኦ ቴ ቹንግ የተሰነዘረ የምዕራቡ ዓለም ምላሽ ነው፡፡ የምዕራቡ ዓለም ፍልስፍና ረቂቁን የሕይወት ፈርጅ የማይዳስስ፣ እጀ ሰባራ አድርገው የሚያስቡ ሰዎች ስለ አዕምሮ ሰላምና ስለ በሕብር መኖር የሚሰብከውን የኢፒክቲተስን ‹የሕይወት መመሪያ መጽሐፍ› ሲያገኙ ሊደነቁ ይችላሉ፡፡
     በሚያስገርም ምናልባት ባልተጠበቀ መልኩ ‹የኢፒክቲተስ የሕይወት መመሪያ› በምሥራቃዊና ምዕራባዊ አስተሳሰቦች የተጌጠ ነው፡፡ በአንድ በኩል የማይካድ ምዕራባዊ ቅርጽ አለው፡፡ ጥብቅ ኃይለኛ፣ ምክንያታዊና ሞራላዊ ነው፡፡ በሌላ በኩል፤ ኢፒክቲተስ የምልዓተ ዓለሙን ሥሪት ተግባር በሚያወራበት ወቅት የምሥራቃዊው አስተምህሮ ቀለማት ብቅ ይላሉ፡፡ ለምሣሌ ዘለዓለማዊ እውነታ የሚዋልልና የማይጨበጥ ነው የሚለው አስተሳሰብ በሚያስገርም ሁኔታ ታኦይስት ቅሪት ነው፡፡
      ለኢፒክቲተስ ደስተኛ ሕይወትና የደግነት ሕይወት የማይነጣጠሉ ናቸው፡፡ ደስተኝነትና ግለሰባዊ ተሟላዊነት ትክክለኛውን የሕይወት ክንውን የማድረግ ውጤቶች ናቸው፡፡ በእርሱ ዘመን ከነበሩት ፈላስፎች በተለየ መልኩ ኢፒክቲተስ ይህንን ዓለም ለመረዳት ከመታተር ይልቅ የተሟላ ሕይወት ለመምራት የሚያስችሉ የሞራል ልህቀቶች ማርቀቅ ላይ በርትቷል፡፡ የልህቀቱ አስተሳሰብ፤ አስኳል የሞራል እድገትን በማከናወን ለሞራል ልከኝነት መብቃት የሚል ነበር፡፡
      የኢፒክቲተስ የሕይወት አስተሳሰብ የሚያማልሉ ሐሳቦች ጥርቅምቅም አይደለም፡፡ ይልቁንስ ድርጊቶቻችን አስተሳሰቦቻችን ሁሉ ከተፈጥሯዊ የሕይወት ሥሪት ጋር የማናበብ ምሪት እንጂ… ነገርየው መልካም ተግባራትን በመከወን በሰዎችም ሆነ በአማልክት ዘንድ መልካም መስሎ የመታየት ምኞት አይደለም፡፡ የውስጣዊ ሰላምን የመፍጠርና ግለሰባዊ ነጻነትን መጎናጸፍ ማሻት እንጂ…
      መልካምነት ሁሉም ሰው ሐብታም፣ ድሃ፣ የተማረ፣ ያልተማረ ሳይል በእኩል ይከውነው ዘንድ የተሰጠ የጋራ ተግባር ነው፡፡ መልካምነት ለመነኮሳት፣ ለጻድቃን፣ ለባሕታዊያን ብቻ የሚተው ተግባር አይደለም፡፡
     ኢፒክቲተስ የደግነትን ጽንሰ - ሐሳብ ወደ ቀላልና በዕለት ተዕለት የኑሮ ክንውን የሚገለጽ ተግባርነት አውርዷታል፡፡ ከአስደናቂ በጀብድ የተሞላ፣ ኑረት ይልቅ ሳይቆራረጥ በመለኮታዊው ምሪት እየተዳኙ መኖርን ይመርጣል፡፡ የእርሱ የመልካምነት መሠረቶች ሦስት ናቸው፡፡
፩. ምኞቶቻችንን መቆጣጠር፡፡
፪. ግዴታን በተገቢ ሁኔታ መወጣት፡፡
፫. በሰው ለሰው እንዲሁም ከሥነ - ተፈጥሮ ጋር ባለን መስተጋብር ግልጽ አስተሳሰብን ማዳበር ናቸው፡፡
      ለኢፒክቲተስ የዕለት ተዕለት ሕይወት በየደረጃው በተለያየ ፈተና የተሞላች ነች፡፡ ሙሉ ሕይወቱን የኖረው በማንኛውም ሁኔታ ውስጥ ቢኮን ወደ ደስታ፣ ምልዑነትና ስክነት የሕይወት ጥግ የሚያደርሡ መንገዶችን በመፈለግ ላይ ነው፡፡ አስተምህሮዎቹ ከጥንታዊነት የዘመን ቀርነት ለሚያነጻቸው ለዘመናዊውም ዓለም ሕይወት የሚበጅ ነገር አላቸው፡፡ አንዳንድ ጊዜ አስተሳሰቦቹ ዘመናዊውን ሥነ-ልቡና የሚያስንቁ ሆነው ብቅ ይላሉ፡፡ በእርግጥም የኢፒክቲተስ አስተሳሰቦች፣ የዘመናዊው ዓለም ሥነ-ልቡናና ራስን መግዛት መሠረቶች ናቸው፡፡

Read 273 times