Tuesday, 23 November 2021 00:00

''ያመነበትን ጽፎና ተናግሮ ያለፈ ጀግና!;

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

 “ጋሽ ሙሉጌታ የተዋጣለት ጸሐፊ፣ ተቺ፣ ገምጋሚ ነበር፡፡ በሥራው ባሕርይ የተነሳ ኢትዮጵያን በአብዛኛው ዞሮ ያየ ሰው ነበር፡፡ የሚጽፈው የሚያውቀውን የሚያምነውን ነበር፡፡ እምነቱ ደግሞ መሠረት፣ ጥልቀት ካለው ባሕር የሚቀዳ እንጂ ከድስት የሚጨለፍ አ ልነበረም… በ ስደት ባ ይሆን ጥ ሩ ነ በር!!--ያ ደግሞ የአገራችን አካልና አ ምሳል ገ ላጭ ባ ሕር ሆ ኗል!--;
           
          አንጋፋውን ጋዜጠኛ፣ ኃያሲና ተንታኝ ሙሉጌታ ሉሌ ደስታን የምናስታውስበት በርካታ ምክንያቶች ይኖሩናል፡፡ የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት መምርያ ኃላፊ ነበር፡፡ በኢትዮ ሶማሊያ ጦርነት ጊዜም ወደ ምስራቅ በመዝመት ሀገሩ ከሱ የምትፈልግበትን አስተዋጽዖ አበርክቷል፡፡ በቀይ ኮከብ ዘመቻ የዕውቁ ደራሲና ጋዜጠኛ በዐሉ ግርማ ምክትል ሆኖ በምድረ ኤርትራ ከርሟል፡፡ በ1983 ዓ.ም ኢህአዴግ ሥልጣን ሲይዝ ሙሉጌታና በርካታ ታዋቂ ጋዜጠኞች ከሥራ ገበታቸው ተሰናብተዋል፡፡ ከሥራ እንጂ ከዕውቀትና ሙያ ባለመሰናበቱ ከሙያ አጋሮቹ ጋር በመሆን ጦቢያ መጽሔትን መሥርቶ ሲሰራ ቆይቷል፡፡ ኅትመቱ እስከተቋረጠበት ጊዜ ድረስም በተነባቢነት ዘልቋል፤መጽሔቱ፡፡
አንጋፋው ጋዜጠኛ ሙሉጌታ ሉሌ፤ ኢትዮጵያዊነቱን እጅግ የሚወድ ለዚያም መስዋዕትነት የከፈለ በሳል ባለሙያ እንደነበር የሥራ ባልደረቦቹ ይናገራሉ፡፡ ትውልዱና እድገቱም ሀገር ወዳድነቱን ያጎለመሰለት ይመሥላል፡፡ምንጫቸው ከጎጃም ከሆነ ነጋዴ ቤተሰቦቹ የተወለደው የጣሊያን ወራሪ ከኢትዮጵያ በተባረረበት ዓመት ሐምሌ 5 ቀን 1933 ዓ.ም ግንደበረት ነው፡፡ የአንደኛ ደረጃ ትምህርቱን አምቦ በማዕረገ ሕይወት ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ትምህርት ቤት፣ ሁለተኛ ደረጃን ደግሞ ደብረብርሃን ኃይለማርያም ማሞ ከተማረ በኋላ አዳማ በሚገኘው ባይብል አካዳሚ ገብቶ ተምሯል፡፡ በመቀጠልም ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የመጀመርያ ዲግሪውን አግኝቷል፡፡
ወደ ናዝሬት/አዳማ ተመልሶ በተማረበት ባይብል አካዳሚ በቋንቋ መምህርነት ካገለገለ በኋላ ነው ወደ ጋዜጠኝነት የገባው፡፡ በቀለም ትምህርት ካስተማራቸው ታዋቂ ሰዎች መካከል የቀድሞው የኢፌዲሪ ፕሬዚዳንት ዶክተር ነጋሶ ጊዳዳና አንጋፋው የታሪክ ምሁር ዶክተር ላጲሶ ጌ.ዲሌቦ ይገኙበታል፡፡ ባለፈው ቅዳሜ ኅዳር 4 ቀን 2014 ዓ.ም ረፋድ ላይ ሙሉጌታ ሉሌ የተዘከረበትና የተወዳጅ ሚዲያ እና ኮሚዩኒኬሽኑ ዕዝራ እጅጉ ያዘጋጀው የጋዜጠኛውን ታሪክ የያዘ ሲዲ የተመረቀበት ሥነሥርዓት በኢትዮጵያ ብሔራዊ ትያትር ተከናውኗል፡፡ በመርሃግብሩ “ሙሉጌታ ሉሌ፤ የኢትዮጵያ ባለውለታ” በሚል ርእስ ከቀረበው የ22 ሰዎች ቃለ ምልልስ የተካተተበት የ120 ደቂቃ ሲዲ ሌላ ቅንጭብ ተውኔት፣ የባልደረቦቹና አድናቂዎቹ ትውስታና ሌሎችም ዝግጅቶች ቀርበው ነበር፡፡ ቃለምልልስ ከተደረገላቸው ግለሰቦች መካከል አንጋፎቹ ጋዜጠኞች አዲሱ አበበ፣ ክፍሌ ሙላት፣(የአዲስ ዘመን አድማስ ገጽን ያዘጋጅ የነበረው)፣ ይንበርበሩ ምትኬ (ኢትዮጵያ ሬዲዮ ስፖርት)፣ አጥናፍሰገድ ይልማ ይገኙበታል፡፡
አንጋፋው ጋዜጠኛ አጥናፍሰገድ ይልማ ከሙሉጌታ ጋር በቅርበት ከሠሩ ባለሙያዎች አንዱ ነው፡፡ ለስልሳ ዓመት ነው ትውውቃቸው፡፡ አንጋፋው ጋዜጠኛ የሙሉጌታ ሉሌን ባሕርይ ሲገልጽ #የሚስማማው ሊስማማ ሲችል ብቻ; መሆኑን ጠቅሷል፡፡ አጥናፍሰገድ አንድ ወቅት በተደረገ የመዋቅር ለውጥ ሙሉጌታ የሱ አለቃ መሆኑን ሲገልጽ “በተደረገ የመዋቅር ለውጥ እሱ የመነን መጽሔት ዋና አዘጋጅ፣ እኔ ምክትል ዋና አዘጋጅ ሆኜ ስመደብ ተቃወምኩ፡፡ በአገልግሎት ስለማይበልጠኝ አለቃዬ ሊሆን አይገባም ብዬ ተቃወምኩ፡፡ ካልሆነ ሥራውን እለቃለሁ አልኩ፡፡ ልብ በሉ፤ አመጼ ከሥርዓቱ አንጻር የተቃወምኩት ሥርአቱን እንጂ ሙሉጌታን አይደለም፡፡ ስለዚህ ከሙሉጌታ ጋር ማታ ማታ እንገናኝ ነበር፡፡ ‘አርፈህ ቤትህ ተቀመጥ’ ብሎ መጽሐፍ አምጥቶ ይሰጠኝ ነበር” ካለ በኋላ አጥናፍሰገድ እስር ቤት ሆኖ ከእስር ቤት ውጪ ላለው ሙሉጌታ በሚታጠብ ልብስ ኮሌታ ውስጥ የተጻፈበት ወረቀት በስልት በመጠቅጠቅ መረጃ ያቀብለው እንደነበርም ገልጧል፡፡
ሙሉጌታ ከመነን መጽሔት ወዲህ ባለው ጊዜ በተለይ የፕሬስ መምርያ ኃላፊ በነበረበት ጊዜ በእሱ ኃላፊነት ለሚታተሙት አዲስ ዘመን፣ ዘ ኢትዮጵያን ሔራልድ፣ በሪሳ እና አልአለም ጋዜጦች ኤዲቶርያል ውይይት ይቀርብ የነበረው በሚያውቃቸው ቋንቋዎች የተጻፉትን ራሱ በማንበብ፣ በሌሎቹ የተጻፉትን ደግሞ በማስተርጎም ነበር፡፡ ከዚህም ሌላ ፋታ በማይሰጥ የመምርያ ኃላፊነት ሥራ ላይ ሆኖ ለጋዜጦቹ ርእሰ አንቀጽ ከመጻፉም ሌላ ለተለያዩ ጋዜጦችና መጽሔቶች ጽሑፍ ያቀርብም ነበር፡፡ በኃላፊነት ሥራው ላይ የእያንዳንዱን ጋዜጠኛ ብስለት አውቆ እንደየ ዐቅሙ በማሰማራት የጋዜጠኞቹን ብቃት ከማሳደጉም በላይ ማንም ይጻፈው ማንም አንድ ጽሑፍ ካልጣመው #እንጨት እንጨት ይላል; ብሎ ይተች እንደነበርም በሲዲ ምርቃቱ ወቅት ተገልጧል፡፡ ይህንኑ አስመልክቶ አብሮት የሠራው አንጋፋው ደራሲና ጋዜጠኛ ዶክተር ታደለ ገድሌ፤ “ጋሽ ሙሉጌታ በኢትዮጵያ ጋዜጠኝነት ታሪክ ተወርዋሪ ኮከብ ናቸው፡፡ የእያንዳንዱን ጋዜጠኛ ችሎታም ጠንቅቀው ያውቃሉ፡፡” ብሏል፡፡
በዚያውም መጠን የሐሳብ ልዩነትን እንደሚቀበል የመሰከሩት አንጋፋው ጋዜጠኛ አያሌው አስረስ፤ አብረው ይሠሩ በነበረበት ጊዜ የጋሽ አያሌው ጽሑፍ አፈንጋጭ ቢሆንም ተዉት ይል እንደነበር አስታውሰዋል፡፡
ልዩነትን ማቻቻልና ማክበርን በተመለከተ ልጁ ዔዶም ሙሉጌታ ሉሌ ስለ አባቷ ስትገልጽ፤ “ብዙ ጊዜ ፓስተር አካባቢ ወደሚገኘው ቤታችን ስንሔድ መኪና ውስጥ አልፎ አልፎ የፕሮቴስታንት መዝሙር ይከፍትና፣ ዮሐንስ ቤተ ክርስትያን (የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ) ስንደርስ መዝሙሩን ዝቅ አድርጎ ኮፍያውን በማውለቅ ይሳለም ነበር፡፡ ለዚያም ይመስለኛል ድፍረት አግኝቼ የዘመኑ ጀግና የሆነውን ዶክተር እስማኤል ሸምሰዲን ሃሰንን ለማግባት ድፍረት ያገኘሁት፡፡” ብላለች፡፡
እሱን ለመጨበጥ ዕድሉን አግኝቼ ነበር የሚለው የአሀዱ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ዋና ሥራ አስኪያጅ ጋዜጠኛና ደራሲ ጥበቡ በለጠ፣ የዩኒቨርሲቲ ተማሪ ሆኖ በሙሉጌታ ጽሑፎች ላይ ይወያዩ እንደነበርና ከሙሉጌታ የብእር ስሞች አንዱ የሆነው ጸጋዬ ገብረመድሕን አርአያ ብዙ ሰዎች ናቸው አንድ ሰው? ብለው መሟገታቸው የሙሉጌታን ታላቅ ብዕረኛነት ያሳያል ብሏል፡፡ ስለ እለቱ ዝግጅትም ሲናገር፤ “በብዙ የሚመነዘረውንና አርአያ የሆነውን አንጋፋውን ጋዜጠኛና ተንታኝ ሙሉጌታን በመዘከራችሁ ምስጋና ይገባችኋል” ሲል ተወዳጅ ሚዲያና ኮሚዩኒኬሽንን አመስግኖ፣  “ሙሉጌታ ብዙ ጋዜጠኞች አፍርቷል፡፡ የጋዜጠኝነትን ጣራ አሳይቶናል፡፡ የበዓሉ ግርማ ከአድማስ ባሻገር መጽሐፍ ላይ መጀመርያ ሂስ የሰጠው ሙሉጌታ ነው፡፡ የሙሉጌታ ሂስ እስካሁንም የሚጠቀስ ነው” ብሏል፡፡
ሙሉጌታ የሥነጽሑፍ ሂስ ብቻ ሳይሆን መንግሥትንም በወቅቱ በመሸንቆጡ ይታወቃል፡፡ በተለይ በህወሓት ይመራ የነበረው የኢህአዴግ መንግሥት አሥራ ስድስት ጊዜ አስሮታል፡፡ ቀድሞውኑ ያለጥፋት በመታሰሩም ሲታሰር ሲለቀቅ ኖሯል፡፡ በመኪና የግድያ ሙከራ ተደርጎበትም በጽኑ ቆስሎ ተርፏል፡፡ እሱን ማሰር መፍታቱ አልሆን ያለው መንግሥትም፤ ያለ ሙሉጌታ ፍቃድ ወደ ውጪ ሀገር እንዲሰደድ አድርጎታል፡፡
ከዚያ በፊት በደርጉ የማስታወቂያ ኮሚቴ አብረው በቅርበት ይሰሩ እንደነበር ያስታወሱት ደራሲ ገስጥ ተጫኔ እና ኮለኔል ናደው ዘካርያስ ከዘመነ ኢህአዴግ በፊት የነበረውን ሙሉጌታ ሉሌን አብረው በመሥራታቸው በሥራዎቹና በሰብዕናው እንደሚያደንቁት ነው የተናገሩት፡፡ ኮሎኔል ናደው በተጨማሪም፣ ለዓመታት ታስረው ሲፈቱ፣ ከአሜሪካ መጀመርያ ደውሎ የጠየቃቸው ሙሉጌታ ሉሌ እንደሆነ አስታውሰዋል፡፡
በዚያው ጊዜ የነበሩት ብርጋዲየር ጄነራል ካሳዬ ጨመዳም ሙሉጌታን አስመልክቶ ሲናገሩ፤ “በኤርትራ ‘ኢትዮጵያ’ የሚባል ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ ነበር፡፡ በብስራተ ወንጌል ሬዲዮም ሠርቷል፡፡ ከፍተኛ አንባቢ ስለነበር የንባብ እውቀቱን ለጽሑፍ ዝግጅቱ ይጠቀም ነበር፡፡ ዛሬ ሳያነቡ የሚጠይቁ ጋዜጠኞች ከሱ ሊማሩ ይገባል፡፡ በሥሙም ማስታወሻ የሚሆን ሀውልትና ማዕከል ሊኖር ይገባል” ብለዋል፡፡
በእርግጥም ከተሰደደ በኋላ ለተወሰነ ጊዜ ሲያገለግልበት የነበረው የኢሳት የዋሺንግተን ዲሲ ስቱዲዮ፣ በስሙ የተሰየመ ትልቅ ቤተ መጻሕፍት እንዳለው፣ በቅዳሜው የ#ሙሉጌታ ሉሌ የኢትዮጵያ ባለውለታ; ሲዲ ምርቃት ላይ ተጠቅሷል፡፡
በ1933 ዓ.ም ተወልዶ በ2008 ዓ.ም በስደት በአገረ አሜሪካ ያረፈውን የሙሉጌታን ሥራዎች በዝርዝር በጋዜጣ ላይ መተንተን አይቻልም፡፡ ሆኖም ለማስታወስ ያህል ይህን ጻፍኩ፡፡
የማጠቃልለው በዚሁ በአዲስ አድማስ ጋዜጣ ነፍስ ሔር አሰፋ ጫቦ በጻፉት እና “ሰው ስንፈልግ ባጀን” በተሰኘው የሙሉጌታ ሉሌ መጽሐፍ የጀርባ ሽፋን ላይ በሠፈረው ጽሑፍ ቅንጭብ ነው፡፡
“ጋሽ ሙሉጌታ የተዋጣለት ጸሐፊ፣ ተቺ፣ ገምጋሚ ነበር፡፡ በሥራው ባሕርይ የተነሳ ኢትዮጵያን በአብዛኛው ዞሮ ያየ ሰው ነበር፡፡ የሚጽፈው የሚያውቀውን የሚያምነውን ነበር፡፡ እምነቱ ደግሞ መሠረት፣ ጥልቀት ካለው ባሕር የሚቀዳ እንጂ ከድስት የሚጨለፍ አልነበረም… በስደት ባይሆን ጥሩ ነበር!! ያ ደግሞ የአገራችን አካልና አምሳል ገላጭ ባሕር ሆኗል! ዋናው ነገር እንዴት ሞተ መሆን ያለበት አይመስለኝም፡፡ ’እንዴት ኖሮ ነበር!’ ነው፡፡ ሙሉጌታ አንገቱን ቀና አድርጎ ያመነበትን በግልም በአደባባይም ተናግሮም ጽፎም ያለፈ ጀግና ነው፡፡” ብለዋል፤ አሰፋ ጫቦ፡፡
**
ከአዘጋጁ፡- ጸሃፊውን በኢ-ሜይል አድራሻው፡- This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it. ማግኘት ይቻላል፡፡

Read 765 times