Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Saturday, 15 September 2012 13:32

የግብፅና የሊቢያ ረብሻ 20 አገራትን አዳረሰ

Written by 
Rate this item
(2 votes)

እስልምናን ያንቋሽሻል ከተባለው ፊልም ጋር ተያይዞ በግብፅና በሊቢያ የተቀሰቀሰው ረብሻ ትላንት በአራተኛው ቀን ወደ ሃያ አገራት የተስፋፋ ሲሆን፤ የአሜሪካ፣ የእንግሊዝና የጀርመን ኤምባሲዎች የተቃዋሚዎች የጥቃት ኢላማ ሆነዋል፡፡የአሜሪካ ኒውዮርክና ዋሺንግተን ከተሞች የተፈፀሙት የሽብር ጥቃቶች 11ኛ አመት በሚከበርበት ማክሰኞ ቀን ነው ረብሻው በግብፅ የተለኮሰው። በጥቂት ሰዎች የተጀመረው ረብሻ በካይሮ የሚገኘው የአሜሪካ ኤምባሲን በመጣስ ባንዲራ አውርደው ያቃጠሉ ሲሆን፤ በዚያው እለት ወደ ሊቢያም የተሻገረው ረብሻ ግን በታጣቂ ቡድኖች የተመራ እንደነበር ተዘግቧል። ምሽቱን በሊቢያ ቤንጋዚ ከተማ በሚገኘው የአሜሪካ ቆንስላ ላይ ወረራ የፈፀሙ ታጣቂ ቡድኖች ግቢውን ያቃጠሉ ሲሆን፣ የአሜሪካ አምባሳደርን ከፍተኛ ዲፕሎማትን ጨምሮ አራት አሜሪካዊያን በጥቃቱ ተገድለዋል።

በቤንጋዚ የሊቢያ የፀጥታ ጉዳዮች ሃላፊ እንደተናገሩት ከሆነ፤ ረብሻው የተቀሰቀሰው እስልምናን ያንቋሽሻል ከሚባለው ፊልም ጋር ተያይዞ ሲሆነረ፤ ጥቃቱ ግን ቀደም ተብሎ የታቀደና ፊልሙን ሰበብ በማድረግ የተፈፀመ የሽብር ድርጊት ነው ብለዋል።የፊልሙን ይዘት አናንቀው የተናገሩት የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሂላሪ ክሊንተን፤ ነገር ግን የአመፅና ድርጊት በማንኛውም ሰበብ ሊመካኝ አይገባውም ብለዋል። የሊቢያ የፀጥታ ሃይሎች በወሰዱት እርምጃ ተጠርጣሪዎችን በቁጥጥር ስር እንዳዋሉ የገለፁ ሲሆን፤ የአሜሪካ የምርመራ ቡድን አባላትም ሊቢያ እንደገቡ አሶሼትድ ፕሬስ ዘግቧል።

ይሁንና በግብፅ ረብሻው ለተከታታይ ቀናት ሲቀጥል፤ ተመሳሳይ ረብሻዎች በየመን፣ በሱዳን፣ በቱኒዚያ እንዲሁም በትናንትናው እለት ከደርዘን በላይ ወደ ሚሆኑ ተጨማሪ አገራት ተስፋፍቷል። በአብዛኛዎቹ አገራት የታየው ተቃውሞና ረብሻ በጥቂት መቶ በሚቆጠሩ ሰዎች የተካሄደ እንደሆነ የዘገበው ዘ ኢንዲፐንደንት፤ በአንዳንድ አገራት ግን ረብሻው የሰዎችን ህይወት የቀጠፈና ቃጠሎዎችን ያስከተለ እንደሆነ ገልጿል።ጥቃቱ በአብዛኛው ያነጣጠረው በአሜሪካ ኤምባሲዎች ላይ ቢሆንም፤ በተለያዩ አገራት የጀርመንና የእንግሊዝ ኤምባሲዎችም የጥቃቱ ኢላማ ሆነዋል።

በአፍጋኒስታን ምስራቃዊ ከተማ ጃላላባድ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች በአደባባይ ተቃውሞአቸውን የገለፁ ሲሆን በኢንዶኔዥያ ሰልፈኞች “ሞት ለአይሁዶች”፣ “ሞት ለአሜሪካ” የሚሉ መፈክሮችን በአሜሪካ ኤምባሲ ደጃፍ ላይ አሰምተዋል፡፡ ነገር ግን በሁለቱም አገራት እንዲሁም በህንድና በፓኪስታን፣ በማሌዢያና በአፍጋኒስታን ለተቃውሞ የወጡት በመቶ የሚቆጠሩ ሰዎች ተቃውሟቸውን የገለፁት በሰላማዊ መንገድ እንደሆነ ዘገባዎቹ ያስረዳሉ።በግብፅ፣ በሊቢያ፣ በቱኒዚያ፣ በሱዳንና በየመን የተካሄዱት ተቃውሞዎች ግን በረብሻ የታመሱ ሆነዋል። በግብፅ ለተቃውሞ የወጡ ሰዎች የቢን ላደንን ፎቶ ይዘው የታዩ ሲሆን፤ ባለፈው አመት በአረብ አገራት የተቀጣጠለው አብዮት እውን ለአካባቢው አገራት የተሻለ ነገር ይዞ መጥቷልን የሚሉ ጥያቄዎች እንዲነሱ አድርጓል።

በቱኒዚያ፣ በሱዳንና በየመን የአሜሪካ ኤምባሲዎችን ጥሰው ያለፉ ተቃዋሚዎች፤ መስኮቶችን እንደሰባበሩና እሳት እንዳቀጣጠሉ የተዘገበ ሲሆን፤ የየአገሮቹ ፖሊሶች በበኩላቸው ጥቃቶቹን በማውገዝ ኤምባሲዎቹን ለመከላከል እርምጃ መውሰዳቸውን ገልፀዋል። በአንዳንድ አገራትም በፖሊሶችና በተቃዋሚዎች መካከል በተፈጠሩ ግጭቶች፤ በፖሊሶችና በተቃዋሚዎች ላይ ጉዳት ደርሷል፤ ህይወት ጠፍቷል።

 

 

Read 4655 times Last modified on Saturday, 15 September 2012 13:39