Thursday, 25 November 2021 06:43

በክብር ስለ “ክብር”

Written by  -በረከት ዘላለም
Rate this item
(0 votes)

--ሰው ለራሱ ጨው በመሆን ሕይወቱን ሲያጣፍጥ ክብሩ እንደሚገለጥ ያምናል፡፡ ሰው ራሱን ካላሳደገ በቀር ሰው ብቻ መሆኑ ትርጉም የለሽ     የሚሆንበት ፍጹምን እናያለን፡፡--;
                
               “ክብር” የተሰኘው የደራሲ ቃል ኪዳን ኃይሉ መጽሐፍ፣ በ166 ገጾች የተቀነበበ ልብ ወለድ ነው። ቃል ኪዳን ከዚህ ቀደም የተለያዩ  የድርሰት ሥራዎቹን አስነብቦናል፡፡ አሁን፥ “ክብር” በተሰኘ ልብ ወለዱ ሲመጣ በተለየ ቅርጽ ሲሆን ፍቅር፣ ቅናት፣ መስዋዕትነትና ክብርን በተለያዩ ገጸባህርያቱ አማካኝነት  ያስቃኘናል፡፡  
ልብ ወለዱ ውስጥ ያለውን ታሪክ የተከፋፈሉት ገጸባህርያት የራሳቸው ማንነት መያዛቸው፣ የማያምታታ ግልጽ ቅርጽ ውስጥ ሀሳብን ለማፍሰስ (ለደራሲው)፤ መልከ ብዙ ዕይታን ለማግኘት (ለተደራሲው) አመቺ ሆኖ አግኝቼዋለሁ፡፡ በወጣቱ ላይ የሚታየው ግልጽ የሽምቅ ትዝብት ለስሜቱ መውጣትና መውረድ አመክንዮ እየሆነ እስከ መጨረሻው መዝለቁም ታሪኩ  በሙቀት የተመላ እንዲሆን አድርጓል፡፡  
ጭብጦች
ጭብጥ 1- በመኖር ውስጥ መመጻደቅ እና ማህበረሰባችን የማይነጣጠሉ መሆናቸውን “ክብር” ትመሰክራለች፡፡ ስለምን ቢባል፥ የሕብረተሰብ ባሕርይ ተንታኞች (person is the result of the eco system) በማለት፣ ከአስተሳሰብ እስከ አረማመድ ድረስ ግለሰብ፥ ከሕብረተሰቡ በካርቦን የሚቀዳ ውጤት መሆኑን በኢኮሎጂካል ሞዴል ያስረዳሉ፡፡ በ“ክብር” የማየው ይህን ነው፡፡ ለሴት ልጅ ባል የሚሆነው ምን አይነት ወንድ እንደሆነ የራሄል እህት ሰናይት ስትመጻደቅ ለጉድ ነው፤ ድንግልና- በተሰኘ ርእስ ስር ሴቶች ጥሎባቸው እርስ በእርስ ከመደጋገፍ ይልቅ መቀናናት እንደሚወዱ በመተንተን፣ ፍጹም እንደ ጉድ ይመጻደቃል (ሴት ሆኖ ሳያውቅ) ፤ አፍቃሪዋ ፍጼ ለብዙ ጊዜ የታመመው በድሎ መለየት ባለመፈለጉ እንደሆነ ራሄል እጥፋት በተሰኘ ምዕራፍ ስር እየተመጻደቀች እናገኛታለን፡፡ ይህ ሁሉ አለነገር አይደለም፡፡ በሰው ጉዳይ ውስጥ ገብቶ ማማሰል ግልጽ የማህበረሰባችን መገለጫ እንደሆነ ማሳየቱ ነው፡፡ ማሕበረሰቡም የራሱን ለራሱ ቢያጐርሱት መች ይጠግባል?
ጭብጥ 2- መከራ የደረሰበት ሰው፥ ፈተናውን የሚቀበልበትና የሚያስተናግድበት መንገድ አጓጊ ነው፤ በተለይ ለእኔ፡፡ ለምሳሌ አንድ አርብቶ አደር የሚሳሳላትን ግመል እያያት ስትሞት፥ የምትሞተው በአካል ብቻ አይደለም፡፡ ልቡ ውስጥ የምትሞተው ሌላ ሞት አለ፡፡ ሰውየው ላይ ግን ስለማዘኑ በግልጽ የሚታይ ነገር ላይኖር ይችላል፡፡
“እቱ የእናቴ ልጅ አይምሰልሽ ከቶ
አይምሮም ይሸሻል ከሰው ተቆራኝቶ
ዝም ብለሽ ታዘቢ ያንቺም ቀን ይመጣል
ትዕግስት አብሮሽ ይደር ሁሉም ነገር ያልፋል” ሲል… ልቡ የተነካው ፍጹም፥ ፈተናን የሚቀበልበትና የሚያስተናግድበትን የቁስ ሳይሆን የሕሊና ስፋት እናያለን፡፡
ጭብጥ 3- መቼም ሰው ሲፈላለግ፥ የግል መመዘኛ  አለው፡፡ ቃል ኪዳን በብዕሩ፥ አንድ ሰው ከመሬት ተገኝቶ ባል፤ ወይም አንዲት ሴት ከመንገድ ተገኝታ ሚስት አትሆንም እያለ ነው፡፡ ያለ መመዘኛ ምርጫ ቢከወንማ ዓለም እንዴት ጥሩ በሆነች አስብሎኛል፤ “ክብር”፡፡ በሌላ በኩል፤ ሌባ ሌባ ነኝ እንደማይልና አመንዝራውም አመንዝራ ነኝ እንዲለን መጠበቅ እንደሌለብን ስር ለስር እየሄደ ብዙ ያስተምረናል፡፡
ጭብጥ 4- ባሕርይ በመኖር የሚቀሰምና የሚንጸባረቅ መሆኑን ሁላችንም እናውቃለን፡፡ “ክብር” አንድን ጠባይ በጉልበት ሰው ላይ በመግጠም አዎንታዊ ውጤት ማግኘት እንደማይቻል ሲነግረን፤ በሌላ በኩል operant conditioningን እየተዟዟርን እንድናጤነው መንገድ ይከፍታል፡፡ ለምሳሌ አንዲት ሴት ፈገግ አለች ማለት እንዲያናግሯት መንገድ ሰጠች የሚል መልእክት አለው፤ አያከራክርም፡፡ በግልባጩ አንድ ተማሪ አርፍዶ ትምህርት ቤት ሲገኝ፥ ቅጣት መስጠት ደግሞ ነገ እንዳይደግመው አሉታዊ ጫና በማሳደር ባሕርይን መቅረጽ ይሆናል፡፡ ነገር ግን “ክብር” ፥ አንዲት ሴት ኮራች ወይም ተንቀባረረች ማለት እምቢ ማለቷ ሳይሆን አንዳች ጫና (reinforcement) እየፈለገች/እየጠበቀች መሆኑን ይነግረናል፡፡  
ጭብጥ 5- ከአይሁዳውያን ቤተሰብ የተገኘው ማስሎው በHumanistic psychology እንዳስረዳው ሁሉ፣ “ክብር” ውስጥ ዋናው ገጸ ባሕርይ ወጣት ፍጹም፤ «ብቻን ብልጥ መሆን የለም፡፡ ተመሳሳይ መንገድና ስልት እየተጠቀሙ ሁሌ ማሸነፍ የለም፡፡ የማይጠበቅ ጥሩነት እያሳዩ ሰውን መግዛት አይቻልም፡፡ ሰው አእምሮ ያለው ፍጡር ነው፤ ያስባል፡፡» ይለናል፡፡ የራሱን ሕይወት፥ ባለበት ቦታ፣ ጊዜና ሁኔታ ውስጥ እየቀረጸ፤ ለማደግና ተለውጦ ለመቅረብ ሲጥር እንመለከታለን፡፡ ማግኘት ነበረና ማጣት አለ ወደሚል ድምዳሜ ደርሶ በቀጣይ ስላለ ያልተነካ ተስፋ ሲጓዝ እንመለከታለን፡፡ ሰው ለራሱ ጨው በመሆን ሕይወቱን ሲያጣፍጥ ክብሩ እንደሚገለጥ ያምናል፡፡ ሰው ራሱን ካላሳደገ በቀር ሰው ብቻ መሆኑ ትርጉም የለሽ የሚሆንበት ፍጹምን እናያለን፡፡ ማንም የራሱን እጣ ፈንታም ሆነ ባሕርይ በራሱ የመጻፍ መብቱን በመጠቀም ክብሩን እንዲያሳይ ይጠቁማል፡፡  
አንዳንድ ነገሮች
መታማት… ማማት፣ መመጻደቅ… መቅናት፣ መከፋት… ማቄምና ሌሎችም ስሜቶች ሰው የራሱ ብቻ ሳይሆን የማሕበረሰብ ሥሪት መሆኑን መስካሪ ናቸው፡፡ ዋና ገጸ-ባሕርይ የተላበሰው ወጣት በአፍላነቱ የጀመረው የፍቅር ግንኙነት፣ እምነትና ንጽሕና መነሻዎቹ ነበሩ፡፡ በጊዜ ሂደት እልህ እና ክብር ይፋለማሉ፡፡ ታሪክ ቀጠለ፡፡ ግምት ልክ አልሆነም፡፡ ትክክለኛነት ምን ማለት እንደሆነ በአንጻራዊነት መነጽር ብዙ ይታይበታል፡፡
መከበር በከንፈር የሚሰኘው ብሂል ክብር ምላስ ላይ እንዳለች ያስረዳል፡፡ ቃል ኪዳን ከአንደበት ባለፈ፥ ድርጊትና ሀሳብ የመንፈስ ልእልና መሰረት መሆናቸውን ጨምሮ አሳይቶናል፡፡ በሌላ በኩል፤ ከዓይን የራቀ ከልብ እንደሚርቅ የሚያስረዳ ብሂልን ሲሰማ የኖረ ሰው መለያየት ሞት አለመሆኑን የሚረዳበትን እይታ “ክብር” ውስጥ ያገኛል፡
እሳትና ውሃ በተሰኘው ምእራፍ መሰረት አለባቸው ፥ «መቼም ሰው የሚወደውን ክዶ ሌላ ያገባል ብዬ ማሰብ ይከብደኛል» ስትል ምን ያለ አሞራ ከዛፍ ይሟገታል፣ ከሚወዱት ጋራ ማን ሲኖር አይቶታል ሲባል አልሰማችም ማለት ይከብዳል፤ ማወቅ እና መኖር ስለሚለያዩ መሆኑን “ክብር” ታሳብቃለች፡፡  
ስለ ሰው ሲነገር አንድም በማወቅ አንድም ባለማወቅ ቢሆን ነው፡፡ ገጸባህርያቱ ሰዎች ስለሚሉት ሊያውቁም ላያውቁም ይችላሉ፤ ይህ እንደ ጥፋት አይታይም፡፡ ደራሲው ሁሉ አዋቂ/አላዋቂ መሆኑን ሲነግረን ነዋ፡፡
ጥቂት ስለ ሽቱ
ጠረን “ክብር” ውስጥ ሕይወት አለው፤ ትዝታም ነው፡፡ በመንፈሳዊ አንድምታ በፆም፣ በጸሎት፣ በብህትውና እና በተጋድሎ የሚገኝ መልካም ጠረን የጽድቅ መገለጫ እንደሆነ በርካታ ቅዱሳን ድርሳናት አስነብበውናል፡፡ መልካምና ነፍስን የሚመስጥ ጥዑም መዓዛን ለማቅረብ፥ በሰማይ (የሰማይ ካህናት) ፤ በምድር (ካህናተ ምድር) ይደክማሉ፡፡ በተቃራኒ፥ ርኩስ መንፈስ ያለበት ሰው ደግሞ የሚከረፋ ሽታ ተላብሶ፣ በዚህኛውም ሆነ በዚያኛው ዓለም እንደሚኖር ተጽፎ አለ፡፡ ለምሳሌ ጥንዶችን ዓይነ ጥላ መንፈስ ከተቆራኛቸው በሩካቤም ሆነ በቅርርብ ጊዜ የሰውነታቸውን ጠረን በመቀየር እንዲለያዩና እንዲጠላሉ ያደርጋቸዋል፡፡ ከዚህ ጀርባ ግን ሽታ በህሊና ውስጥ ክብር የመስጫና መንፈጊያ ሚዛን መሆኑን ቃል ኪዳን በ“ክብር” በተለየ መንገድ አቅርቦልናል፡፡
ሰዎች መልካም ቢያጡ እንኳ መጥፎ ጠረን አያጣቸውም፡፡ በምድራዊ ሕይወት በፈተና ቦታ ሴቶችን ከሽቱ ጋር ማዛመድ የተለመደ ቢሆንም፣ የወንድ ገጸ ባህርይ ከጠረን ጋር የተቆራኘ ማንነት ይዞ ሲኖር “ክብር” በተለየ መንገድ አቅርቦልናል፡፡ አንድ ወንድ ማን፣ ምን ቦታ፣ ምን ተቀብቶ/ታ እንደነበር ከልጅነት እስከ እውቀቱ ከገጠመኞቹ ጋር አሰናስሎ ሲጓዝ ማየት አስደናቂ ነው፡፡ በፍቅር ሕይወቱ ከአንዲት ልጅ ጋር ፍቅርን እየተቋደሰ ያለፈው ፍጹም፥ አስተውሎቱን ከሽቱ ጋር እየሰፋ መጓዙ ያለምክንያት አልነበረም፡፡ ሌሎች ገጸ ባሕርያትም ቢሆኑ አነሰም በዛ ሽቱ ተቀቢ መሆናቸው ደራሲው፥ የፍጡራኑን ታሪክ የማያያዣ አይነተኛ ሀረግ  እንዳበጀ አድርገን እንድንመለከት ያደርገናል፡፡ የሆነው ሆኖ ከልጅ እስከ አዋቂ ድረስ በ“ክብር” የተሰደሩት ባለታሪኮች ለየጠረኑ ያላቸው ምልከታ ክብራቸውን ያሳያልና የልብ ወለዱ ርእስ “ክብር” መባሉን ይበል! የሚያሰኝ ነው፡፡
መጠቅለያ
“ክብር” ያልተለመደ የሥነ ጽሑፍ ቅርጽን ተላብሶ፤ በተለያዩ ንኡስ ርእሶች፥ የተለያዩ ግለሰቦችን ወክሎ፤ ቀዝቃዛ ሴራን በሞቃት ቃላት ያሰናሰለ የልብ ወለድ ሥራ ነው። እኔ፥ በዚህች ወፍ በረር ጽሑፍ ከሞላ ጎደል ይዘትና ጭብጦችን ለማካፈል የተጠቀምኩበት መነጽር የሰው የባሕርይ ጥናት ግኝቶች ላይ ማተኮሩ አንድም የጽሑፉ ይዘት ወደዚያ መርቶኝ፤ አንድም ወቅታዊ ውሎዬ ከሥነ-ባሕርይ የምርምር ጽሑፎች ጋር በመቆራኘቱ ሊሆን ይችላል፡፡
“ክብር” በጥቂት ገጾች ብዙ የምንሸምትበት መጽሐፍ ነው። እንደ እኔ፣ ከተለመደ ቅርጽ ወጥቶ በአዲስ መልክ ሥራ መጀመር፣ ራስን ቀዶ እንደ መስፋት ያለ ነው ብል አላገነንኩም። ከመልእክት አኳያ ግን የማናችንም እውነት ከኖርንበት ከባቢ፣ ካለን ልምድና እውቀት የሚመነጭ በመሆኑ፥ ከሌሎች እውነታ ጋር የሚኖረን መስተጋብር በማስተዋል ሊቃኝ እንደሚገባው ማሳየቱን የምታነቡ ሁላችሁ እንደምትመሰክሩ እምነቴ ነው፡፡  

Read 1274 times