Tuesday, 23 November 2021 00:00

“ከአድማስ ባሻገር”- የስነጽሑፋችን ቀለም

Written by  ደረጀ በላይነህ
Rate this item
(2 votes)

    “ አዎ፤ ችግር ረሀብና ስቃይ ምን እንደሆኑ አውቃለሁ። አባቴ የመንደር እድርተኞች ለፋፊ ነበር። እርሱ ደህና በነበረበት ጊዜ በቀን አንዴ እንኳ ቢሆን እንጀራ በዶኬ እንቀምስ ነበር። ታሞ አልጋ ላይ ከዋለ በኋላ ግን ጥሬ እንኳን ባቅሙ ያርብን ነበር።”
                 
           ባለፈው ሳምንት እንደ መንደርደሪያ ባነሳሁት ሀሳብ፣ በእውነታዊ ስነ-ጽሁፍ ውስጥ ገጸ ባህርያት አካባቢያቸውን፣ ቤተሰባቸውን፣ ባህል ወጋቸውን ያጣቀሰ ማንነት እንደሚኖራቸው ፍንጭ ሰጥቻለሁ።… በርግጥም ገጸ-ባህርያት በተለያዩ ሞረዶች ቅርፃቸውና ሰብዕናቸው ሊለወጥ ይችላል። ከትምህርት ጀምሮ ጊዜያቸውን የሚሰጡትና የሚያሳልፉበት ሁኔታና አጋጣሚ ማንነታቸውን ይፈጥረዋል።
የስነ-ልቡና ምሁራንም እንደሚሉት፤ “There are no heriditary factors which may not be modified by enviromental forces and, similarly; environmental factors can only begin to work on the biologically heriditary organism.”
ስለዚህ ከቤተሰብ  የወረስነው ነገር በአካባቢያችን  ይቀረጻል፣ ይሳላል ማለት ነው። ይህ እውነት በተመሳሳይ  ሁኔታ በልቦለዶቻችንም ውስጥ ያታያል። ያለምክንያት ያለ ማህበራዊ መልክ  አንድን  ሰው ያፈነገጠ ወይ የተለየ አድርገን መቅረጽ የለብንም፤ ቢሆን እንኳ ሰውየውን አፈንጋጭ ያደረጉትን፣ የጋን ስር ጠጠሮች ማሳየት ይጠበቅብናል።
የበዓሉ ግርማን “ከአድማስ ባሻገር” መቆሚያ ዓምዶች በመጠኑ ያየነውን ያህል ባይሆንም ዛሬ ተዓማኒነቱ ላይ ያተኮሩ ሃሳቦችን ለማንሳት እሞክራለሁ። ይህን ያህል ምንጣፍ መዘርጋቴም፣ ድንገት ዘው ማለት እንዳይሆንብኝ ነው።
እስቲ መጀመሪያ የመጽሐፉ ዓበይት ገጸባህርያት ወደሆኑት አበራ ወርቁና ኃይለማርያም ካሣ ጎራ እንበል! መጽሐፉ ስለ ሁለቱ ጓደኝነት ኢ-ርቱዕ በሆነና ርቱዕ በሆነ መንገድ ምን ይላል?
ገጽ 19 ላይ የአበራ ወርቁ ወንድም ወግ አጥባቂው አቶ አባተ፣ የኃይለማርያምና የአበራ ስር የሰደደ ባልንጀርነት ስለደነቃቸው እንዲህ በማለት ይጠይቁታል፣
“ከተዋወቃችሁ ስንት ዓመት ይሆናል?”
ለዚህ ጥያቄ መጽሐፉ መልስ የሚሰጠው  በተከታዩ ገጽ 20 ላይ ነው። የመጽሐፉ ተራኪ በሶስተኛ መደብ አንጻር እንዲህ ይነበባል… “በአስፋወሰን ትምህርት ቤት ለአምስት ዓመት፤ በጄኔራል ዊንጌት ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ለአራት ዓመት፤ በካሊፎርኒያ ዩኒቨርስቲ ለሁለት ዓመት አብረው ቆይተዋል።” ይህ አብረው ያሳለፉበትን  የጊዜ ቁጥር የሚያሳይ ነው። በአጠቃላይ ለሃያ ዓመታት በጓደኝነት እንደቆዩም ኃይለማርያም ተናግሯል። ከዚህ ባሻገር ከጊዜ ቁጥር በላይ ቅርበታቸውን ሲያስረዳ፤  “ይህን ሁሉ ዘመን ክፍል ጎን ለጎን ነበር የሚቀመጡት፣ የሚያጠኑት ባንድ ላይ ነበር።” ይላል (ገጽ 20)
ይህ ማለት የ32 ዓመት ወጣት የሆነው፣ አበራ ወርቁ፣ ከዕድሜው የሚበልጠውን  ጊዜ ያሳለፈው ከቤተሰቦቹ ጋር ሳይሆን ከጓደኛው ከኃይለማርም ጋር ነው። በሰዓት ከተሰላ ደግሞ ከቤተሰቦቹ ጋር ምናልባት መኝታ ውስጥ ሆኖ ለእንቀልፍ የሚያሳልፈውን ሰዓት እንቆጥር ይሆናል እንጂ በትምህርትና በጥናት የሚቆየው ከኃለማርያም ጋር ነው።
እንግዲህ ይህንን እውነት የሚቃረንና ለማመን የሚያስቸግር ነገር ፊታችን ድንቅ የሚለው ገጽ 48 ላይ ነው። እስቲ እንየው፡-
ኃይለማርያም አበራን “… ከልጅነትህ ጀምረህ እስካሁን ድረስ ከሰው ትከሻ ወርደህ አታውቅም። ፍርሀትህ ይገባኛል። ድህነትና ችግር ምን እንደሆኑ አታውቅም… አልቀመስከውም።” ሲለው፡-
አበራ መልሶ “አንተ ቀምሰሃል?” ይለዋል።
አሁንም ኃይለማርያም “ አዎ፤ ችግር ረሀብና ስቃይ ምን እንደሆኑ አውቃለሁ። አባቴ የመንደር እድርተኞች ለፋፊ ነበር። እርሱ ደህና በነበረበት ጊዜ በቀን አንዴ እንኳ ቢሆን እንጀራ በዶኬ እንቀምስ ነበር። ታሞ አልጋ ላይ ከዋለ በኋላ ግን ጥሬ እንኳን ባቅሙ ያርብን ነበር።”
እንግዲህ ሃያ ዓመታት አብረው የኖሩ ጓደኛሞች እንዴት ሆኖ ያሳለፈውን ሕይወት፣ ያየውን አበሳ ሳይነግረው ቀረ ብለን እንቀበል? ለመደባበቅ ሃያ ዓመታት አልበዙም? ለመደባበቅ ሃያ ዓመታት አልበዙም?... ለዚያውም ደራሲው ራሱ እጅግ በጣም ግልጽ መሆኑን የመሰከረለትን ሃይለማርያምን ያሳለፈውን ሕይወት ለሃያ ዓመታት ሳይነግረው ቆይቶ በወሬ መሀል በልጭ ማድረጉ ተዓማኒነቱን እጅግ አይጎዳውም? ፈጽሞ በምንም ማሳመኛና ሰበብ ብናጥረው፣ ለማንም ገራም ሰው እሺ ብሎ የሚዋጥ ምክንያት አናገኝለትም!
ኃለማርያም´ኮ አበራ ወርቁን “ስራህን ተውና የኔ ደሞዝ ይበቃናል። ያለው ከወንድም የሚተካከል ባልንጀራ ነው!!... እና ለሃያ ዓመታት የአባቱን ሥራ፣ የቤተሰቦቹን ኑሮ ደብቆ ኖረ ማለት እጅግ ለምናብ ይርቃል።
ሌላኛው የተዓማኒነት ጥያቄ የሚፈጥረው ክፍል የቀደመውን ያህል ግዙፍ ባይሆንም “እንዴት” የሚያሰኝ ነው። ይህ ደግሞ ገጽ 130 ላይ መነሻ የሚያደርግ ነው፡፤ እዚህ ቦታ አበራ ወርቁ፣ ታሪኩ ፍፃሜ አካባቢ ወደ እስር ቤት የገባበትን ወንጀል ለፈጸመበት መነሻ የሆነ ነው። ይህ መነሻም ከተሰማ ደጀኔ የተገኘ ወሬ ነው። ይሁንና መጽሐፉ ገጽ 68 ላይ እንደሚነግረን፣ ተሰማ “ምን ላውራ?” ብሎ ያገኘውን ወሬ ፈጥሮም የሚያወራ ንፋስ ነው። ይሁንና በኋላ ግን ያንን ወሬኝነቱን የሚያውቀው አበራ ወርቁ፤”ሉሊት ከሌላ ወንድ ጋር ትወጣለች” ብሎ በነገረው ወሬ ወደ ሉሊት ቢሮ መክነፉንና ቢሮ ሲያጣት እርሱ ወደነገረው ኮተቤ ገጠር መናፈሻ ሆቴል ሽጉጥ ይዞ መሄዱን እናያለን።
ለመሆኑ አንድ ሰው ሀገር ስም የሰጠውን ወሬኛ፣ ወሬ ሰምቶ የሰው ነፍስ እስከ ማጥፋት ድረስ የዘለቀ እርምጃ ለመውሰድ ይይችላል? ጉዳዩስ ምን ያህል አሰማኝ ነው?
ለዚህ ጥያቄ ተወዳጁ ደራሲ በሕይወት ቢኖርና ብጠይቀው ደስ ባለኝ!... ይሁንና በዓሉ ከዚህ በኋላ በርካታ መጻሕፍትን ጽፎልን እሱ አልፏል።
ሞት እንኳ ጨክኖ ወስዶ ከሚያስቀረው፣ ምናለ በዓሉን ዳግመኛ ቢፈጥረው የሚያሰኝ ተወዳጅነትና ክብር ያለው ደራሲ ነው፡፡ በዚህ ጉዳይ ይበልጥ ተጠያቂ ቢሆኑና መልስ ቢሰጡ የምለው በመፅሐፉ ላይ ዳሰሳ የሰሩ ሰዎችን ነው?...አንባቢያን የመፈተሽ አቅም እንዲይኖረን፣ ደጅ እንኳን ለማንኳኳት ለመጠየቅ አለመሞከራቸው ቅር ያሰኛል!….
የደራሲዎቻችንን ሥራ ስንፈትሽ ከውዳሴ ባለፈ በቅንነት ጉድለቶችን ለማየት ብንሞክር ለደራሲውም ለእኛም ጥቅም ነው፡፡ አንዳንዴ ደራሲው በምናብ ሠረጋላ ተፈናጥጦ ትልልቅ መርከቦች ላይ ሲቀዝፍ፣ ከሥሩ የሚሾልኩ ትንንሽ ነገሮች ስለሚኖሩ ታማኝ አርታኢና ከሕትመት በኋላም ቀና ሀሳብ ያለው ትጉህ ኃያሲ ሊያግዘው ይችላል!....
ከአድማስ ባሻገር ውስጥ የተዓማኒነት ጥያቄ የሚያስነሱት ጉዳዮች ወርድና ቁመናቸው ይለያያል እንጂ ከላይ የጠቀስኳቸው ብቻ አይደሉም፤ ሌሎችም አሉ፡፡ ለምሳሌ በመፅሐፉ ውስጥ ትልቅ ድርሻ ያላት ሉሊት ታደሰ የተባለችው ገፀ-ባህሪ፣ ብዙ ስነ-ልቦናዊ ምስቅልቅል ያለባት፣ የበቀል ስሜት የጠነሰሰችና በወንዶች ሥቃይ የምትረካ ናት፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ራሷን ጣዖት በማድረግ ቅብጠቷ ልክ ያጣና ሌሎችን ዝቅ አድርጋ የምትታይ ናት፡፡
ይሁንና በመፅሐፉ ውስጥ ድንገት ያን ሁሉ እሾህዋን አራግፋ የሠከነች ሴት ሆና እናገኛታለን፡፡ ገራሚው ነገር ያ ብቻ አይደለም፡፡ አበራ ወርቁን የሚያህል ሰውዬ ለረዥም ጊዜ ሲፈራው የኖረውን ሥራ ትቶ ወደ ሰዓሊነት ጥሪው የመመለስ ውሳኔ ባንድ ጊዜ እርግፍ አድርጎ ሲተው ይታያል!.....የተወው ደግሞ የሉሊት ታደሰን ደሞዝ ተማምኖ ነው፡፡
ለመሆኑ ሉሊትን ለመተማመን የሚያበቃ ምን ጠንካራ ምክንያት አለ?... ለዚያ ለዚያ የሃያ ዓመት ባልንጀራው ሀይለማርያም “የኔ ደሞዝ ይበቃናል! ሥራህን ተው” ብሎት አልነበረ?...ይህችን ከብዙ ወንዶች ጋር አንሶላ የተጋፈፈችና ያልተረጋጋች ሴት፣ ለገንዘብ ብላ ከገድሉ በዛብህ ጋር መወስለት የለመደች ሴት ባንዴ ታምና፣ አበራ ወርቁ ጥቅልል ብሎ እጇ ላይ መውደቁ እንደ እኔ በቂ ምክንያት አይመስለኝም፡፡
ሌላው በሴራው ጉንጉን ውስጥ ገዘፍ ያለ ስፍራ የነበራቸው ሰዎች ማለትም እነ አቶ አባተና ሀይለ ማርያም ካሳ ባንድ ጊዜ የተገዳደሉበት ሁኔታ ጥርት ያለ መልክ የሌለውና ታሪኩን ለመቋጨት ሲባል የፈጠነ የሚመስል ነው፡፡… አቶ አባተ፤ ሀይለማርያምን እስከ መግደል ያደረሳቸው ምንድን ነው?....ቀድሞ በነበራቸው ጥላቻ እንኳ ቢሆን እርሱን ገድለው ራሳቸውን የሚደግሙ ከሆነ፣ እንዴት እንደዚህ  ባጠረ ሁኔታ ይወስናሉ?....ራስን መግደል ቀላል ሆኖ የሚታየው ከልጅነት ወደ ወጣትነት ባለው የዕድሜ ሽግግር እንጂ  ኑሮን ያጣጣሙ ሰዎች በቀላሉ አያደርጉትም። ብዙ ታላላቅ ሰዎች በጠላቶቻቸው እጅ የሚወድቁት ወይም የሚማረኩት ሞትን ፈርተው ነው፡፡
የዚህ ዓይነት የታሪክ አፈፃፀም ላይ የጥድፊያ ሞት ማብዛት የበዓሉ ግርማ ብቻ ሳይሆን ድርሰቱ የተፃፈበት ዘመን ልምድ ብልሃት ይመስለኛል፡፡
ሌላው ቀርቶ የሀዲስ አለማየሁ “ፍቅር እስከ መቃብር” ተመሳሳይ ፍጻሜ እንደነበረው ማየት ይቻላል። ለምሳሌ “ፍቅር እስከ መቃብር” ገጽ 489 ላይ ተመሳሳይ ነገር እናያለን። እንዲህ፡-
“ዋጋዬ የፊታውራሪን ሬሳ በፈረስ ጭኖ እያለቀሰ እቤታቸው ሲደርስ፣ ከጥቂት ጊዜ በፊት የዘፈን የውካታ ቤት የነበረው ያዘን ቤት ሆኖ ቆየው፡፡ ወይዘሮ ጥሩ አይነት ከቤታቸው እያለቀሱ የሚቆሙበትን ሳያስተውሉ ሮጠው ወደ ቤተ ክርስቲያን እንደሄዱ፡- እየሮጡ የቤተ ክርስቲያኑን ደረጃ ወጥተው ሲጨርሱ አፈንግጦ በቆየ ድንጋይ ላይ ቆሙና ተገልብጦ ጣላቸው፡፡ ከዚያ ባላንባራስ ምትኩም ደንግጠው ይዞ ለማንሳት ሳይችሉ ቀርተው ወይዘሮ ጥሩ ዘቅዝቀው ሲንከባለሉ፣ ሌላኛው ደረጃ እያነጠረ ለታችኛው እያቀበለ አስራ ሁለቱም ደረጃ በሙሉ አንድ ላይ እንዳሴረባቸው ሁሉ ደብድቦ እታች ጣላቸው፡፡”
እንግዲህ ሁለቱም የመፅሐፍ ዓበይት ገፀ ባህሪያት የሞቱት ባንድ ጊዜ፣ በዚህ ዓይነት አጋጣሚ ነው፡፡…ይህ ምናልባት የዘመኑን ስነ-    ፅሑፍ ስንገመግም በዘመኑ ዓውድ መሆን አለበት በሚለው የሚወሰድ ይመስለኛል፡፡ ዞሮ ዞሮ ግን ተዓማኒነቱ የሰው ልብ ላይ ጠብ አይልም!
ከአድማስ ባሻገር ውብ በሆነ አጻጻፍ የተፃፈ፣ዘመናዊ አጻጻፍን የተከተለ ድርሰት ነው፡፡ ቋንቋ አጠቃቀሙና ገለጻውም ያማረና የቆነጀ ነው፡፡ በተለይ አነጻጻሪ ዘይቤን በመጠቀም ያስጌጣቸው ብዙ ናቸው፡፡
የመፅሐፉን አጠቃላይ ዓላማና ግብ ስንመለከት ግን ለአንባቢው ያስቀመጠው ሕያው ነገር አለ ማለት ያዳግታል፡፡ ሁለቱ ገፀ ባህሪያት አበራ ወርቁና ባልንጀራው ሀይለ ማርያም የጥበብ ሰዎች ሆነው ጥሪያቸውና እንጀራቸው መፋለማቸውን አሳይተውናል፡፡ ይህ የኪነት ሰዎች ሕይወት ነው፡፡ የውስጥ ግጭታቸው  ብልጭታ ወደ ማህበረሰቡ ዘልቆ ሁከት መፍጠሩ በተለይ ባልሰለጠኑ ማህበረሰብ ውስጥ ተቃውሞ ማስነሳቱ ትክክል ነው፡፡
ግን ደግሞ እነዚህ ሁለት ገፀ ባህሪያት ያንን ሁሉ ጊዜ ለትምህርታቸው ሰጥተው፣ በተማሩበት ትምህርት አንድም ቀን ሀገራቸውንና ወገናቸውን ሲጠቅሙ አላየንም፡፡ በዚህ ድርሰት መሰረት የአንድ ሰው መማርና ማወቅ፣ለሕብረተሰቡ የሚኖረው ፋይዳ ምንድን ነው?....ምንም!....ወይስ የአበራ ወርቁን ዓይነት የቀበጠ ወሲባዊነት?....እኔ በበኩሌ፤ ትምህርት ያፈራውን አንድ ዛላ ማየት አልቻልኩም፡፡ ….ስለዚህ አንድ ድርሰት ሰባኪ ባይሆን እንኳ አንድ ፋይዳ እንዲኖረው የሚጠበቅ ዘውግ ስለሆነ ጎተራ ውስጥ የሚኖረው ነገር ያስፈልግ ነበር፡፡
ከላይ እንደጠቀስኩት፤ ይህ መፅሀፍ በዘመናዊ የአተራረክ ስልት ውብ በሆነ ቋንቋና ገለፃ የተጻፈ ነው፡፡ ገፀ ባህሪያቱም የየራሳቸው መልክ እንዲኖራቸው ተደርገው እንደተቀረጹ ባለፈው ማሳያ ሰጥቻለሁ፡፡
የታሪኩ ፍጥነት ለምሳሌ የሉሊት ቶሎ ተለውጦ ወዲያው መጋባት፣ ተጋብቶ ወዲያው የአበራ ሥራ መለቀቅ፣ ወዲያው ወደ ግድያና እስር ቤት መግባት…  ረዥም ልቦለድ ተዝናንቶ በመተረክ ነገሮችን በምክንያት አብላልቶ አሳማኝ በሆነ መንገድ ወደ ግብ መድረስ እያለ፣ መፍጠኑ መጠነ ርዕዩን ያጠበበው ይመስለኛል፡፡
አንድ ምግብ ከጉሮሮ ጨጓራ ደርሶ ሳይፈጭ ወደ ትንሹ አንጀት ደርሶ ወደ ሰውነት የመሰራጨት ያህል ቸኩሏል፡፡ በሂደት የሚፈፀሙ ነገሮች ሁሉ በግርድፉ አልቀዋል፡፡ ምናልባትም በልጅነታችን ሆዱን ዘልለን፣ እግሮቹን ከአገጩ ጋር እንደምናገናኘው፣ የዘለላቸው ነገሮች ብዙ ናቸው። ከጀማሪ ደራሲ ችግሮች ተርታ ልንመድበው አችንችላለን ሁነቶችን በፍጥነት እንዲከንፉ የሚያደርግ ትኩሳት ነው ብለን ልንጠረጥርም እንችላለን፡፡ ምክንያቱም በዓሉ ግርማ በሌሎቹ ተከታታይ መፃፍቱ ከማንም በተሻለ ሁኔታ አብስሎ አንገዋልሎ፣ በጥልቀትና በአሳማኝ መንገድ ሲፅፍ አይተናልና!እንዲህም ሆኖ በዓሉ ግርማ በመጀመሪያ ድርሰቱ የዘመናዊ የአማርኛ ስነ-ፅሑፍ ዓለም ያፈካ ኮከባችን ስለሆነ ሁልጊዜ እናከብረዋለን፤ እንወደዋለን፤ እንዘምርለታለን! በዓሉ በኔ ልብ የማይከስም የዝንታለም ኮከቤ ነው!!    


Read 1295 times