Thursday, 25 November 2021 06:57

ፀሐይ ለምን ቢጫ ሆነች?

Written by  -ሌሊሳ ግርማ-
Rate this item
(5 votes)

  «ስራ ፈትነትም ስራ ነው» ብሏል ገጣሚው ሰለሞን ዴሬሳ፤ «ምክኒያቱም አእምሮ ከማሰብ ስለማይቦዝን…»
ጭልጥ ብዬ በሃሳብ የምጠፋበት ጊዜ አለ፡፡ ምን እያሰብኩ እንደሆነ ራሴን ስጠይቅ ነው ከሄድኩበት  የምመለሰው፡፡ የማይጨበጥ ሃሳብ እኔን እየሳበኝ ሊሆን ይችላል፡፡ የማላስታውሰውን ህልም እያለምኩ፡፡ ሄጄ እንደነበር የማውቀው ስመለስ ነው፡፡ ነብሴ በአእምሮዬ አማካኝነት አንዳች ነገር አስቦ ያልፋል - እኔን ሳያሳውቀኝ፡፡ ነብስ አካልን ከተጠቀመበት በኋላ ለሞት አሳልፎ ሰጥቶት እንደሚሄደው፡፡ አእምሮንም አስቦበት ያልፋል፡፡
ቡና ፉት እያልኩ ሳለሁ ነው ጭልጥ ያልኩት፡፡ የመለሰችኝ ቡናውን የቀዳችልኝ ልጅ ናት፡፡ «ተመልከት ሰውየው እንዴት እንደሚሆን» አለችኝ፡፡ ሁለመናዋ ወሬ ለማቀባበል ተወጥሯል፡፡
ከተቀመጥኩበት ብነሳ እና ፊቴን እሷ ወዳተኮረችበት አቅጣጫ ባደርግ የተባለውን ሰውዬ አየዋለሁኝ፡፡ ማየት ማመን ነው፡፡ ጥሩ ወሬኛ ከተገኘ መስማትም ማመን ነው፡፡ በአንደበቱ ጥሩ አድርጎ የሚስል ወግ አሳማሪ ከተገኘ መስማትም ጥበብ ይሆናል፡፡ ይጋነናል፣ ይኳሻል… ግን ውበት ሆኖ ከተራነት ወደ ተሸጋሪነት ይቀየራል፡፡
ከሃሳብ ጥበብ ለሰው ልጅ ይቀርባል፡፡ ሰው ስሜታዊ ፍጥረት ነው፡፡ ከእውነት ውሸት ዘመዱ የሆነው ለዛ ይሆናል፡፡ ጥበብ፣ እውነትን ለማጉያ የምንጠቀምበት የውሸት አይነት ነው ይላሉ፡፡
ከተቀመጥኩበት ብነሳ እና ፊቴና ባዞር እማኝ እሆን የነበረውን ነገር በእሷ አንደበት ሲነገረኝ ማድመጥ ፈለኩኝ፡፡ ምናልባት ራሴ ባየው ተራ የሚሆነው ነገር፣ ለእሷ ግን ሌላ ትርጉም አዋልዶ ሊያስገርመኝ ይችል ይሆናል በሚል ነው የታዘበችውን አንድትነግረኝ እድሉን የሰጠኋት፡፡ እያለሁ እንደሌለሁ መሆን ፈልጌያለሁኝ፡፡
«ሰውዬው የእጅ ሰዐቱን መሬት ላይ ከስክሶት እየደነፋ ነው» አለች፡፡ ፊቷ ላይ መደነቅ፣ መፍራትና ማቆብቆብን በተለያየ ሬሾ የቀላቀለ ገጽታ ተላብሳለች፡፡
«እብድ ነው?» አልኳት፡፡
«አይ ሰክሮ መሰለኝ፣ በደንብ ነው የለበሰው፡፡ አብራው ሴት አለች… እንትን ናት መሰለኝ…»
«ምንድን ናት?»
«በጣም ቀሚሷ አጭር ነው… እስትሬት ናት መሰለኝ… ሰውየው ገንዘብ አውጥቶ ሲበትንባት  እሷ እየለቀመች ነው… ሊስትሮዎቹ ሰዐቱን ከመሬት ሰብስበው ሲሰጡት ተቀብሎ መልሶ ከሰከሰው፡፡ ሴቷ ብሩን እየለቀመች ነው፡፡ ይሄንን ሁሉ ብር እያገኙ ሲለወጡ ግን አይታዩም… መጨረሻ ላይ ታመው መሞታቸው አይቀርም…»
‘እስትሬት’ ማለት የቡና ቤት ሴት ማለት መሰለኝ፡፡ ቡና ቤት ማለት ራሱ መጠጥ የሚሸጥበት ቦታ ማለት ነው፡፡ ቡና እየቀዳችልኝ ያለችው ነበረች፣ የቡና ቤት ሴት መባል የነበረባት፡፡ ቃላት ከግብራቸው የተፋታ ትርጉም ነው ያላቸው፡፡
 ድንገት የተራኪዋ ፊት ከጉጉት ወደ ነጭ ፍርሃት ተቀየረ፡፡ ለመሮጥ የተሰናዳች መሰለኝ፡፡ ልክ ሰውየው ወደ’ሷ አቅጣጫ እመር ብሎ እንደመጣባት አይነት፣ እጇን አፏ ላይ አደረገች፡፡«… ወይኔ ሊስትሮውን በጥፊ መታው» አለች፤ አፏ ላይ የከደነችውን እጇን አንስታ እያውለበለበች፡፡
«ስንት ሰዐት ነው?» አልኳት ድንገት፡፡
«እኔን’ጃ ስምንት ተኩል ቢሆን ነው… ቡና ልጨምርልህ?»
«አይ መሽቶ ከሆነ ብዬ ነው፡፡ የምሽት ትዕይንት ሆነብኝ፡፡ … አሁንስ ምን እያደረጉ ነው?» አልኳት፡፡ ቡናውን እንድትጨምርልኝ በምልክት ብጠቁማትም ቴርሞሱን ታቅፋ ቀርታለች፡፡ ትዕይንቱ ከምን እንደደረሰ ከፊቷ ላይ ለማንበብ ስጥር  ለሆነ ሰው ሃዘን የተሰማት መሰለኝ፡፡ በጥፊ ለተመታው ሊስትሮ ይሁን ሰዐቱን ለከሰከሰው ሰውዬ እርግጠኛ አይደለሁም፡፡ ነገር ግን ለወንዶቹ እንጂ ለሴቲቱ እንዳላዘነች ለራሴ እርግጠኛ ሆኛለሁኝ፡፡
«አሁንስ?» አልኳት፡፡ እግር ኳስን በሬዲዮ ሰው ለምን እንደሚከታተል በፊት አይገባኝም ነበር፡፡ አሁን በደንብ ግልጽ ሆነልኝ፡፡ ጆሮ ከአይን የበለጠ መስገብገብን ይፈጥራል፡፡
«አሁን ሊስትሮው ድንጋይ አንስቶ ሰውየውን ካልፈነከትኩ እያለ ነው… ሰውየውን እያንገላቱት ነው፡፡ … ምስኪን ምን አጋጥሞት ይሆን ይሄንን የመሰለ ሰውዬ… እንደዚህ የተዋረደው…»
«ደህና ሰውዬ ነው?» አልኳት፡፡
«… መኪና ያለው ይመስላል… ሱፍ ነው የለበሰው… ክራባቱን ይዘው ዱርዬዎች እየጎተቱት ነው»
«ልጅቷስ ባለ አጭር ቀሚሷ?»
ልክ ጥያቄዬን ሳቀርብ ቅልጥ ያለ የሴት ጩኸት ተሰማ፡፡ ባለ አጭር ቀሚሷ፣ መሬት ላይ ሰውዬው የበተነውን ገንዘብ ስትለቅም ነበር ቅድም ትረካው ያቆመው፡፡ አሁን፣ ብሯን እየለቀመች፣ አጭር ቀሚሷ የውስጥ ጭኗን እንዳያሳይባት እግሮቿን ገጥማ ቁጢጥ ባለችበት፣ እሪታዋን ስታቀልጠው በምስል መልክ ታየኝ፡፡ ቡና ቀጂዋ የነገረችኝን ቁራጭ ትረካ ተንተን አድርጌ በማያያዝ እያፍታታሁት እገኛለሁኝ፡፡
«ልጅቷ አይደለችም የጮኸችው፤ በመንገዱ ላይ የምታልፍ ሌላ ሴት ስር ሰውየው ሄዶ ተሸሽጎ ነው» ብላ የቡናዋ እመቤት ፍርስ ብላ ሳቀች፡፡ አሁን የቻርሊ  ቻፕሊን ፊልምን እያጣጣመ የሚገኝ ሰው በሚያሳየው መዝናናት ውስጥ ሆና ነው ትዕይንቱን የምትከታተለው፡፡ እሷ ከፊለፊቷ ያለውን እንደምትከታተለው እኔ ደግሞ የእሷን ፊትና ሁኔታ በጥንቃቄ እያስተዋልኩ ነው፡፡ ትረካዋ እየዘገየ ነው በአፏ የሚወጣው፡፡ መጀመሪያ እሷ ተመልክታ፣  የተመለከተችውንም ተረድታ፣ በተረዳችውም ተዝናንታበት ስታበቃ ነው ለእኔ ከአንደበቷ አውጥታ፣ የተረፈውን የምታካፍለኝ፡፡ እኔ በትዕግስት እጠብቃለሁ፡
«እየውልህ፣ሰውየው በኮት ኪሱ ብዙ የታሰረ ብር ይዟል፡፡ እና ዱርዬዎች አዘናግተው ሊወስዱበት ነው መሰለኝ…  አብራው ያለችዋ ጋለሞታይቱ ግን ምን አይነት ባለጌ ናት… አብራው አይደለች ቢያንስ አታግዝለትም?... ዝም ብላ ጥግ ላይ ቆማ ትመለከታለች፡፡ አብራ ከዱርዬዎቹ ጋር ተሻርካ ሳይሆን አይቀርም…»
«አንቺ እሷን ብትሆኚ ታግዢለት ነበር?» ብዬ ጠየኳት፡፡ አንዳንዴ እንደ አድማጭ ብቻ ሳይሆን እንደ ጠበቃም ሲያደርገኝ አይታወቀኝም፡፡
«አብሬው ከሆንኩኝ ዝም ብዬ እጄን አጣምሬ አላይም» አለችኝ፡፡ እጇን አጣምራ ያቀፈችው ፔርሙዝ በዛ አኳኋን ሲታቀፍ የመጀመሪያ ጊዜው እንዳልሆነ ግልጽ ነው፡፡ ልብ ሳትለው ለረጅም ሰዐት ያቀፈችው ስለሚመቻት ነው፡፡ ወደ ቤቷ ስትመለስም ፔርሙዙን አስቀምጣ የምታቅፈው ጨቅላ ሊኖራት ይችላል፡፡…. ብዬ ማያያዜን ቀጠልኩኝ፤ እሷም ወሬዋን ቀጥላለች፡፡
«ባሌ ከሆነ በተለይ እጄን አጣምሬ አላይም፡፡ ሰውዬው ግን ደህና ሰው ነው እኮ… ይኼኔ ከቤቱ ወይንም ከስራው አቃጥለው አስወጥተውት ነው ሰክሮ አጉል እንዲሆን ያደረጉት…» ብላ ከንፈሯን በቃለ አጋኖ መጠጠች፡፡
ትረካው አንዳንዴ ከሚተረከው ጉዳይ ባሻገር የተራኪውን ስነ ልቦናም አሻግሬ እንድመለከት ድፍረቱን ይሰጠኛል፡፡ መረጃው የሌለኝን፣ የማያገባኝ ጉዳይ ሁሉ ውስጥ እንዳጮልቅ መረን ይለቀኛል፡፡ ምናብ አጮልቆ ሲያልም ከእውነታ የራቀ አብስትራክት ይፈጥራል፡፡
እናም ቡና ሻጯ ባል የምትፈልግ መሰለኝ፡፡ …ሚስቱ ከቤት አቃጥላ ያባረረችው፣ ደህና የሚመስል ሰው ጎዳናው ይዞልኝ ይመጣል… ብላ የምትጠብቅ መሰለኝ፡፡ ሃሳብ ስራ ፈት ነው፡፡ ምናብ ደግሞ ግድንግድ ስራ ፈት ነው፡፡ ለሃሳብ ስራ ፈትነትም ስራ ነው ይላል ገጣሚው፡፡
«አሁንስ ምን ላይ ደረሱ?» አልኳት፡፡
«ሰውዬው ወደ ላይ እየሄደ ፖለሶች አገኘ፡፡ እያነጋገራቸው ነው…»
«ዱርዬዎቹስ፣ ሊስትሮዎቹስ?... ወይንስ ሊስትሮዎቹን ነው ዱርዬዎች ያልሽኝ?»
«ዱርዬዎቹ ብሩን ሊበሉት የነበሩት ናቸው፡፡ ሊስትሮዎቹና ሰውዬው ሲነታረኩ በመሃል ገብተው ነው ሰውዬውን የመቱት… አሁን ዱርዬዎቹ  የት እንደገቡ እኔ’ንጃ… ሰውየው ግን ያሳዝናል፡፡ በቀን እንደዚህ የሚጠጣው የከፋው ነገር ቢኖር ነው፡፡ ሰው ሁሉ እኮ ሆድ ብሶታል!»
« ገንዘብ እያለው ምን ሆድ ይብሰዋል?» አልኳት፡፡ አሁን ፊቷ ላይ ያለው የወሬ ጉጉት እየበረደ መጥቷል፡፡ ስታይ የቆየችው ነገር ከእይታ ክልሏ ወጥቷል ማለት ነው፡፡ አሁን ፊቷን ሙሉ በሙሉ ወደኔ መለሰች፡፡ በሃይል የምታወራኝ ከአሁን በኋላ ስለሚሆን ቶሎ መጥፋት አለብኝ፡፡
«… ገንዘብ ያለው ሰው እኮ ነው የበለጠ የሚከፋው፡፡ ለፍቶ ያመጣውን የሚቀራመት ከተነሳበት… ሆድ ለምን አይብሰውም? እኔም አረብ ሃገር ሰርቼ ያጠራቀምኩትን ገንዘብ ተበልቼ ስለማውቅ፣ የሰውየው ሃዘን ይገባኛል፡፡ ይቆረቁረኛል፡፡»
አንቺን ደግሞ ማነው የበላሽ… ብዬ የማያዛልቅ አዲስ ትረካ መክፈት አልፈለኩኝም፡፡ ግን እንዲሁ በግምት ህይወቷን መዝኜው ልጅ እንጂ ባል የሌላት መሰለኝ፡፡ ወይንም ያጠራቀመችውን ገንዘብ ይዞ የተሰወረው የሌላት ባል ይሆናል ብዬ በራሴ ግምት ረካሁኝ፡፡ እውነቱን ለማረጋገጥ መጠየቅ አልፈለኩም፡፡ ስንቱ ተጠይቆ ስንቱ ተደምጦ ይቻላል!
የታቀፈችውን ፔርሙዝ ዘንበል አድርጋ ቀዳችልኝ፡፡
«ፖሊሶቹ ሰውየውንና ሴቷን ይዘው ወደ ታች ወረዱ» ብላ ትረካዋን ቋጨችው፡፡ እኔም ወደ ቡናዬ ተመለስኩኝ፡፡ የሲኒውን ትኩስ ቡና ፉት ስል ሃሳቤ እንደገና ወደማይታወቅ አቅጣጫ ይዞኝ ለመሄድ ማንጎራጎር ጀመረ፡፡ እሱ ወደሚመራኝ የማይታወቅ አቅጣጫ ሳይሆን እኔ ራሴ ወደምቆጣጠረው መስመር ፈር ለማስያዝ ስል አንድ አልባሌ ጥያቄ ዝም ብዬ ሰነዘርኩበት፡፡ ምናልባት በጋሪ ብርቱካን እየገፋ ከሚያልፍ ሰው ላይ ነው ጥያቄዋን ያነሳኋት፡፡
«ብርቱካን ለምን ብርቱካን አይነት ሆነ?»
… ብርቱካን ሳይበስል ቀለሙ አረንጓዴ ነው፡፡ ከአረንጓዴ ተነስቶ ማረፊያው ለምሳሌ ‘ቀይ’ ከሆነ ቢጫ ወይንም ብርቱካን አይነት መሆኑ በመሃል ቤት አይቀርም፡፡ ሌላ ቀለም ሊሆን አይችልም፡፡ ብርቱካን ለመሆን ብርቱካን አይነት ቀለም የግድ አያስፈልገውም፡፡ ብርቱካን ሆኖ በሰለ ለመባል ግን ብርቱካን አይነት መሆን አለበት- አልኩኝ፡፡
ሃሳብ ግን መዘዘኛ ነው፡፡ አንድ የጥያቄ ሽንቁርን በአንድ መልስ ደፈንኩ ስትለው- በጄ ብሎ አይቀበልም፡፡ በሌላ በኩል በስቶ አዲስ ሽንቁር ያበጃል፡፡
«ፀሐይስ ለምንድነው ቢጫ የሆነችው?»
ቡናዬን ከፍዬ አመስግኜ ተነሳሁኝ፡፡ ህጻናት ምክኒያትና ውጤትን ማገናኘት ከመቻላቸው በፊት የሚመልሱትን አይነት መልስ መስጠት አሰኘኝ፡፡ ጸሐይ ቢጫ የሆነችው ስለምታቃጥል ነው አልኩኝ፡፡ ከዛም ቀጥዬ፣ ፀሐይ ቢጫ የሆነችው ከሰማይ በታች አዲስ ነገር ስለሌለ… የሚለውም ጥሩ መልስ የሚወጣው መሰለኝ፡፡ ወይንም ደግሞ  ቢጫ የሆነችው ‘እርድ ስለተነሰነሰባት’ ብሎም ጥያቄውን ማስኮረፍ ይቻላል፡፡
ወደ ጎዳና ወጥቼ መራመድ ስጀምር ቡና ፉት ስል የመጣብኝ የሃሳብ ስራ ፈትነት ወደ አላማ ተቀየረ፡፡ ባለ ቡናዋ ሴት የተረከችልኝን የሚመስሉ ተዋንያን በጎዳናው ላይ ፈልጌ አጣሁኝ፡፡
ፈጥራ ያወራችልኝም መሰለኝ፡፡ የተረከችልኝ ተከስቶ ይሁን አይሁን ማረጋገጥ አሁን አይቻልም፡፡ ከትረካው የበለጠ ተራኪዋ እውን ነበረች፡፡ ከተራኪዋም የበለጠ ግን የቡናዋ ጣዕም በምላሴ ላይ ሆኖ ዘለቄታ ላላቸው ቅጽበታት አብሮኝ ቆይቷል፡፡ ሴትየዋን ተነስቼ መራመድ ስጀምር እረስቻታለሁ፡፡


Read 799 times