Saturday, 27 November 2021 13:32

የጠ/ሚኒስትሩ ወደ ጦር ግንባር መዝመትና የውጭ መገናኛ ብዙኃን የተዛቡ ዘገባዎች

Written by 
Rate this item
(2 votes)

  “የጠ/ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አህመድ መንግስት በህወኃትና ግብረ አበር አማፂያን ተከቧል፤ በቅርቡ መውደቁ አይቀርም” ሲሉ የሰነበቱት ዓለማቀፉ የውጭ መገናኛ ብዙኃን፤ የጠ/ሚኒስትሩን ወደ ጦር ግንባር መዝመት በአብዛኛው አዛብተው ነው የዘገቡት።
ህወኃት በጦርነት ድል የቀናው ሲመስላቸው ዝምታን የሚመርጡት አሊያም በመንግስት ላይ ጫና በሚፈጥሩ ተግባራት የሚጠመዱት የተባበሩት መንግስታትና የአሜሪካ መንግስት ከትናንት በስቲያ ባወጡት አስቸኳይ መግለጫ፣ የጠ/ሚኒስትሩን ወደ ጦር ግንባር  መዝመት በማጣጣል፣ በአስቸኳይ ጦርነቱ እንዲቆም  አሳስበዋል።
ጦርነቱን አስመልክቶ በሚያቀርባቸው ለአንድ ወገን ያደሉና ሚዛናዊነት የጎደላቸው ዘገባዎች ሳቢያ በመላው ዓለም በሚገኙ ኢትዮጵያውያን ሰፊ ተቃውሞ እየቀረበበት የሚገኘው ሲኤንኤን፤ የሠላም ኖቤል ተሸላሚው ጠ/ሚኒስትር፣ ዜጎች ወደ ጦር ግንባር  እንዲከተሉት ጥሪ አቅርቧል በሚል ንዑስ ርዕስ ባጠናቀረው ዘገባው፣ ጠ/ሚኒስትሩን በመከተልም የኦሎምፒክ ባለድሉ አትሌት ሃይሌ ገ/ስላሴና ሌላኛው አትሌት ፈይሳ ሌሊሳ ወደ ጦር ግንባር ለማቅናት መወሰናቸውን  ጠቁሟል፡፡
ተጨማሪ ማብራሪያ ከመንግስት ኮሚኒኬሽን ቢሮ ለማግኘት ያደረገው ጥረት እንዳልተሳካለት የገለፀው ሲኤን ኤን፤ በአዲስ አበባ ከተማ አካባቢያቸውን ለመጠበቅ 147 ሺህ ሰዎች መሰልጠናቸውንም በዘገባው አመልክቷል፡፡
“የኢትዮጵያው ዐቢይ አህመድ፡- ወደ ጦር ግንባር ያመራው የሠላም ኖቤል ተሸላሚ” በሚል ርዕስ ሰፊ ዘገባ ያቀረበው ሌላኛው የተዛቡ መረጃዎችን በማቅረብ የሚወቀሰው ቢቢሲ፤ በሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነቱን ያስጀመሩት ጠ/ሚኒስትሩ መሆናቸውንና ይህም በሃገር ውስጥም ሆነ በአለማቀፍ ደረጃ የነበራቸውን የለውጥ ሃዋርያነት  ክብርና ዝና እንዳጠፋባቸው ዘግቧል።
ከእውነታው ባፈነገጠው በዚህ የቢቢሲ ዘገባ፤ ጠ/ሚኒስትሩ የሃገሪቱ ግማሽ ያህል የተቃዋሚ ፓርቲዎች ባልተሳተፉበት የውሸት ምርጫ ስልጣናቸውን ማፅናት እንደቻሉ፣ በበአለ  ሲመቱ ወቅትም በርካታ የአፍሪካ ሃገራት መሪዎች ስለመገኘታቸው፣ ነገር ግን በወቅቱ በሃገሪቱ ያለውን ክፍፍል ለመሸፈን ያለመ ስነ-ስርዓት መካሄዱን አትቷል፡፡
“ጠ/ሚኒስትሩ የሰላም ኖቤል ሽልማት አሸናፊ በሆኑ ማግስት የጦር አዝማች መሆናቸውም ከሠላም እሴቶች በተቃራኒ የቆሙ መሆናቸውን ያሳያል” ይላል-  የቢቢሲ የተዛባ ዘገባ፡፡ለህወኃት ግልፅ ውግንና ከሚያሳዩ ዓለማቀፍ መገናኛ  ብዙኃን አንዱ የሆነውና በኢትዮጵያ መንግስት ማስጠንቀቂያ የተሰጠው ሮይተርስ የዜና ተቋም በበኩሉ፤ ከሲኤንኤን ጋር ተመሳሳይ ይዘት ያለው ዘገባና ትንታኔ አስነብቧል። ጠ/ሚኒስትሩ የሠላም ኖቤል ተሸላሚ ሆነው ሣለ ጦርነትን በአካል መምራታቸውን ይጠቅሳል-በዘገባው፡፡የጠ/ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አህመድ በቀጥታ ወደ ጦር ግንባር መዝመትና የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊትና ህዝባዊ ሃይሉ በጦርነት ድል እየቀናው መሆኑ እየተገለፀ ባለበት በዚህ ወቅት የአሜሪካ መንግስትና የተባበሩት መንግስታት ድርጅት፤ በአስቸኳይ ጦርነቱ እንዲቆም ማሳሰባቸውንም ከትናንት በስቲያ ጀምሮ እኒሁ መገናኛ ብዙኃን እየዘገቡት ይገኛሉ፡፡ይህ በእንዲህ እንዳለ የኤርትራ መንግስት የጠ/ሚኒስትር ዐቢይ አህመድን ወደ ጦር ግንባር መዝመት ያጣጣለውን የአሜሪካ መንግስት ክፉኛ ተችቷል፡፡

Read 1300 times