Saturday, 27 November 2021 13:34

የእነ ፕ/ር ኤፍሬም ይስሃቅን ሴራ ያጋለጡት ጄፍ ፒርስ ምን ይላሉ?

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(3 votes)

   “አሁንም መሰል ሴራዎችን ማጋለጤን እቀጥላለሁ”
                           
          የቀድሞ የሃገር ሽማግሌዎች መማክርት አመራር በነበሩት ፕ/ር ኤፍሬም ይስሃቅ የተመራውንና የቀድሞ የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ዋና ሥራ አስፈጻሚ እሌኒ ገ/መድህንን (ዶ/ር) ጨምሮ ዘጠኝ ሰዎች የተሳተፉበትን ምስጢራዊ ውይይት ያጋለጡት የታሪክ ተመራማሪውና ጋዜጠኛው ጄፍ ፒርስ፤ አሁንም የኢትዮጵያን ህልውና ለመገዳደር የሚደረግን ስውር ደባ ማጋለጣቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ገልጸዋል።
ታዋቂው የታሪክ ተመራማሪ፣ ጋዜጠኛና ደራሲ ጄፍ ፒርስ በኢትዮጵያ አንድነት ጉዳይ ላይ አጥብቀው ከሚከራከሩና ለኢትዮጵያ ጥቅሞች ጥብቅና ከቆሙ ታዋቂ የውጭ ሃገር ዜጎች አንዱ ናቸው።
ከዳያስፖራ ቲቪ ጌራ ሾው ጋር ቆይታ ያደረጉት ካናዳዊ ምሁር ጄፍ ፒርስ፤ ግለሰቦቹ በሚስጥር ያደረጉት ውይይት፣ በዲሞክራሲያዊ መንገድ የተመረጠውን ጠ/ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አህመድ እንዴት ከስልጣን ማስወገድ እንደሚቻልና ቀጣይ የሽግግር መንግስት በሚመሰረትበት ሁኔታ ላይ ያተኮረ መሆኑን አስረድተዋል።
“ሰዎቹ የአዲስ አበባው መንግስት በመውደቅ  ላይ መሆኑን ነው የሚያስቡት” የሚሉት የታሪክ ምሁሩ፤  በውይይቱ ተሳታፊ የነበሩት  በኢትዮጵያ የቀድሞ የአሜሪካ አምባሳደር ዶናልድ ያማማቶ በዚህ ሴራ ውስጥ መሳተፋቸው በቀላሉ የማይታይ መሆኑን ይገልጻሉ።
ሰዎቹ ሲነጋገሩ የነበረው የዐቢይን መንግስት በሃይል አስወግዶ እንዴት የሽግግር መንግስት ማቋቋም ይቻላል በሚለው ጉዳይ ላይ መሆኑን የሚያስረዱት ጄፍ ፒርስ፤ በዚህ ውይይት ውስጥ ከቀናት በፊት “ቤቴ እንዴት ይፈተሻል፤ ዶ/ር ብለው ሊጠሩኝ እንኳ አይፈልጉም” ሲሉ ቅሬታቸውን በትዊተር ገጻቸው የገለፁት ዶ/ር እሌኒ ገ/መድህን መሳተፋቸው  ብዙዎችን እንዳስገረመ እርሳቸውም በሁኔታው መገረማቸውን ተናግረዋል።
“በቪድዮው አምባሳደር ብርሃነ ገ/ክርስቶስ የዐቢይ ቀዳሚ እቅድ ትግራይን ማፍረስ ነው ሲሉ ሰምቻለሁ። ይሄን የዐቢይን እቅድ እሳቸው እንዴት አወቁ? ማን ነገራቸው?” ሲሉ የሚጠይቁት የታሪክ ተመራማሪውና ደራሲው ጄፍ ፒርስ፤ ለኔ የገባኝ እነዚህ ሰዎች ምን ያህል የአለማቀፉን ማህበረሰብና ዲፕሎማቶችን እያጭበረበሩ እንዳለ ነው ብለዋል።
በዚህ የተሳሳተ መረጃቸው ያማማቶ ሳይቀሩ የትግራይ ሃይል በአዲስ አበባ ዙሪያ  ነው ያለው የሚለውን ማመናቸውን ጄፍ በቃለ-ምልልሳቸው በአግራሞት ይጠቅሳሉ።
“አሁን የእነዚህ ሰዎች ሴራ ተደርሶበታል፣ ሙሉ የቪዲዮ የምስል ድምጽ ሁሉም መረጃ አለን ይሄን ሃቅ እንዴት አድርገው ነው የሚያስተባብሉት፣ ኢትዮጵያውያን በጣም ብልሆች ናቸው፤ ይሄን መረጃ በአግባቡ ይጠቀሙበታል ብዬ አምናለሁ” ብለዋል ጄፍ ፒርስ።በዚህ ከ2 ሰዓት በላይ በተደረገ የዘጠኝ ሰዎች ውይይት ላይ አወያዩ ፕ/ር ኤፍሬም ይስሃቅ፣ እሌኒ ገ/መድህን (ዶ/ር)፣ ኩለኒ ጃለታ፣ ብርሃነ ገ/ክርስቶስ፣ አምባሳደር በቀለ ገለታ፣ ፕ/ር ጥላሁን በየነ፣ አምባሳደር ዶናድ ያማማቶ ተሳታፊ ሆነዋል።

Read 7876 times