Saturday, 27 November 2021 14:25

ዲዛይነር ደስታ ደጀኔ

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

  የ79 ዓመቷ የዕድሜ ባለጸጋ ወ/ሮ ደስታ ደጀኔ አቦዬ ከግማሽ ክ/ዘመን በላይ የሚሆን ጊዜያቸውን ያሳለፉት በልጅነት ዕድሜያቸው በተማረኩበት የባህል አልባሳት ዲዛይን ሥራ ላይ ነው፡፡ በታዳጊነት ዘመናቸው ትምህርታቸውን አቋርጠው በጀመሩት በዚህ ሙያ በአገር አቀፍና በዓለማቀፍ ደረጃ  ትላልቅ ሽልማቶችና ዕውቅና አግኝተውበታል፡፡ ወ/ሮ ደስታ ለታዋቂ ግለሰቦች፣አርቲስቶችና ሞዴሎች አልባሳትን ዲዛይን እያደረጉ ሲሰሩ ኖረዋል፡፡ በዚህም የላቀ ስኬትን ተቀዳጅተዋል፡፡ በአሁኑ ሰዓትም የወ/ሮ ደስታን ሥራ ተረክበው በመስራት ላይ የሚገኙት ልጆቻቸው ናቸው፡፡ የአዲስ አድማስ ጋዜጣ ስለ ወ/ሮ ደስታ የእድሜ ዘመን ሙያና ሥራ ከልጃቸው ናኦሚ አባይ ጋር ተከታዩን ቃለ ምልልስ አድርጓል፡፡ እነሆ፡-


                     #ባህላዊውን ከዘመናዊው ማዋደድ ያስፈልጋል;


            እስቲ ራስዎትን ያስተዋውቁን--?
ናኦሚ አባይ እባላለሁ፡፡ የወ/ሮ ደስታ ደጀኔ ስድስተኛ  ልጅ ነኝ፡፡ በአሁን ሰዓት የእናታችንን ስራ ተረክቤ በመስራት ላይ እገኛለሁ፡፡
 በዚህ አጋጣሚም የእናታችንን የወ/ሮ ደስታ ደጀኔን ታሪክ እንድናሳውቅ እድሉን ስለሰጣችሁን በጣም እናመሰግናለን፡፡
የወ/ሮ ደስታ ትውልድና ዕድገት ምን ይመስላል?
ዲዛይነር ደስታ ደጀኔ የተወለደችው በ1935 ዓ.ም በአዲስ አበባ ንፋስ ስልክ አካባቢ ነው፡፡ እድሜዋ ለትምህርት ሲደርስ እቴጌ መነን ትምህርት ቤት ብትገባም፣ ትምህርት ቤቱ ከመኖሪያቸው ይርቅ ስለነበር በአቅራቢያ ወደሚገኘው የቀድሞው በየነ መርዕድ፣ በአሁኑ ዕድገት በህብረት ትምህርት ቤት ገብታ፣ እስከ ስምንተኛ ክፍል ድረስ መማር  ችላለች፡፡
ከስምንተኛ ክፍል በኋላስ ለምን አልቀጠሉም…?
መማር ትችል ነበር፤ ግን በውስጧ ከፍተኛ የሆነ የልብስ ስፌት ፍቅር ስለነበር እሱን ለማሳካት ብላ ወላጆቿ ሳያውቁ ነው ትምህርቷን ያቋረጠችው፡፡ በወቅቱ  ወላጆቿ ትምህርት ማቋረጧን ሲያውቁ በጣም ከባድ ፈተናዎችን ነው ያሳለፈችው፤ ግን ያው ዓላማ ስለነበራት ዛሬ የደረሰችበት ቦታ ላይ ለመድረስ በቅታለች፡፡
ትምህርት ካቋረጡ በኋላ ወዴት አመሩ?
ትምህርቷን በማቋረጥ በቀጥታ ወደ ዲዛይን ትምህርት ቤት ነው ያመራችው፡፡ ያኔ አንዲት ከጣሊያን ሀገር በልብስ ዲዛይን ተምረው የመጡ ኢትዮጵያዊት የከፈቱት ‹‹ሳባ የልብስ ስፌት ትምህርት ቤት›› ገብታ ሥልጠና ጀመረች፡፡ በ1958 በልብስ ስፌትና ቅድ በዲፕሎም ተመረቀች፡፡ በስልጠና ወቅት ባሳየችው ልዩ ብቃትም በዛው ተቋም ውስጥ በማስተማር ቀጠለች፡፡ ማስተማሩን እንዳቆመች የራሷን ትንሽ የንግድ ቦታ በመክፈት ጨርቆችን ከውጭ አገር በማስመጣት ዘመናዊ ልብሶችን እንድትሰራላቸው ለሚጠይቋት መሥራት ጀመረች፡፡ መኖሪያ ቤቷ በጣም ሰፊ ስለነበር ስራዋን ወደዛ በመውሰድ ለረዥም ጊዜ እዛ መስራት ቻለች፡፡ በወቅቱ ትሰራ የነበረው የሚዜ ልብሶች፣ የእራት ልብሶችና የሙሽራ ልብሶችን ነበር፡፡  
ደንበኞችን እንዴት ነበር የሚያፈሩት? ማስታወቂያ የሚያስነግሩበት የተለየ መንገድ ነበራቸው?
ምንም የማስተዋወቂያ መንገዶችን አትጠቀምም ነበር፤ አሁንም አትጠቀምም፤ ልብሱ እራሱ ይመሰክራል የምትለው እምነት አላት፡፡ ‹‹የት ነው ያሰራሽው›› እየተባባሉ ደንበኞቿ ናቸው የሚያስተዋውቁላት፤ ስራውን የሚያመጡትም እነሱ ናቸው፡፡
በልጅነታቸው  ወደ ልብስ ስፌት የሳባቸው ምን ነበር ? እንደ አርአያ የሚያዩት ሰው ነበር?
ሁሌም ስትናገር እንደምንሰማት ወደ ስፌቱ እየተሳበች የመጣችው፣ የእናቷን ወይንም የእኛን አያት የሰርግ ልብስ፣ (ልባልማሱሪ ይባላል) የሀበሻ ቀሚስ ነው፤ ከላይ ካባ አለው፡፡ እሱን በፎቶግራፍ ማየት ከጀመረችበት ጊዜ አንስቶ  እንደሆነ ትናገራለች፡፡
ከቤተሰቡ ውስጥ በዚህ ሙያ ላይ የተሰማራ ሰው ነበር ?
የእናታችን ወ/ሮ ደስታ አያት፣ በንግስተ ነገስታት ዘውዲቱ ዘመን፣ የንጉሳዊያን ቤተሰብ አልባሳትን ይሸምኑ ነበር፡፡
ከ90 ዓመታት በላይ ያስቆጠረ የባህል ልብስ እንዳለ ሰምቻለሁ…
አዎ 90 ዓመታትን ያስቆጠረ ልብስ አለ፤ ጥንድ ድርብ ይባላል፡፡ የአያቷ ነው፤ ወደዚህ ስራ መግባቷን ሲያይ በስጦታ መልክ የሰጣት… ድሩም ማጉም በእጅ ነው የተሰራው፤ ምንም አይነት ማሽን አልነካውም… አሁን ላይ እንዲያውም ብዙ ደንበኞቿ ይህን ዓይነት ልብስ  እያዘዟት ትሰራለች፡፡
እንደማየው የቤት ቁሳቁሶችም  በጥበብ ተውበዋል---
ማስጌጥ በጣም ነው የምትወደው፤ስለዚህ የተለያዩ መንገዶችን በመጠቀም ሁሉም ነገር በጥበብ እንዲያጌጥ በማድረግ አብሮ የሚሰራበትን መንገድ በመፍጠር ታስውባቸዋለች፡፡ እንደምታይው አብዛኞቹን ቁሳቁሶች በጥበብ አስጊጣቸዋለች፡፡
በ1977 በኢትዮጵያ ተከስቶ በነበረው ከፍተኛ የድርቅና የረሃብ አደጋ የዕርዳታ እጃቸውን ዘርግተው ለነበሩ የሰሜን አሜሪካና የአውሮፓ ሀገራት ምስጋና ለማቅረብ በተዘጋጀውና እስካሁንም ድረስ በብዙ ሰው ልብ ውስጥ በቀረው የ‹‹ህዝብ ለህዝብ የሙዚቃ ትርዒት›› ላይ የመሳተፍ እድል አግኝተው ነበር ---
አዎ፤ በወቅቱ ከባህልና ቱሪዝም አቶ አያልነህ ሙላት ናቸው፣ ሥራውን ይዘውላት የመጡት፡፡ ሥራው እንዲሰራላቸው ብዙ ቦታ አወዳድረው ነበር፤ ‹ሳምፕል› እንዲሰራላቸው ግን ሳያገኙ ቀሩና ወደሷ ጋ ይዘውት ሲመጡ በሳምንት ጊዜ ውስጥ ሰርታ አሳየቻቸው፡፡ ሳምፕሉም አሸነፈና ወደ ስራው እንድትገባ ዕድሉን አገኘች፡፡ ብዙ ቦታ ሳምፕል ሲያሰሩ ጊዜ ወስዶባቸው ስለነበር ስራውን ለመጨረስ የተሰጣት ጊዜ በጣም አጭር ነበር፤ ስለዚህ ብዙ ሰው ቀጥራ ነው የ14 ብሔሮችን ወደ 140 ልብሶች በ15 ቀናት ውስጥ  ሠርታ ያስረከበችው፤ ሙሉ የባህል ልብሱን ከእነ ጌጣጌጡ ማለት ነው፡፡
በወቅቱ የየብሔሩን አለባበስ እንዴት ነበር የሚያውቁት?
የየብሄሩ ትክክለኛ ሳምፕል ቀርቦላት ነበር፤ በዛ መሰረት ትንሽ አዘምናው ነው የሰራቸው፡፡ ጌጣጌጡን በመስራት ደግሞ አሁን ባህር ማዶ የምትገኘው እህታችን ሰናይት አባይ ታግዛት ነበር፡፡ በወቅቱም ከባህልና ቱሪዝም የምስጋና የምስክር ወረቀት ተበርክቶላታል፡፡
በኮንሶ ባህላዊ አለባበስ በዓለማቀፍ ደረጃ ተሸልመዋል አይደል?
አዎ ከ15 ዓመት በፊት ግሪክ አቴንስ ውስጥ በሚስ ቱሪዝም አማካኝነት የ32 አገራት አልባሳት ይቀርብ ነበር፡፡ እዛ ተጋብዛ ሄዳ በኢትዮጵያ  የኮንሶ ባህላዊ አለባበስ አሸናፊ ሆኖ ተመርጦ ሽልማት ተቀብላለች፡፡
ስመጥር ከሆኑ አለምአቀፍ ሞዴሎች ጋር የመስራት እድል ማግኘታቸውንም ሰምተናል--
እውነት ነው፡፡ ከፈረንሳይ አገር የመጣች ማጋሊን የምትባል የተለያዩ ሞዴሎችን በማሰልጠን በተለያዩ ጊዜያት ደስታ ዲሞድ በማለት የፋሽን ትርዒት አዘጋጅተዋል፡፡ በወቅቱ ከሰለጠኑ ሞዴሎች መካከል ሊያ ከበደ.. ሳራ መሀመድ ይገኙበታል፡፡ ሊያ ከበደ እንዲያውም የመጀመሪያዋ ሞዴል ናት፡፡ ብዙ ሞዴሎች በኛ ቤት ውስጥ የእናታችንን ልብስ እያስተዋወቁና እየሰለጠኑ ዛሬ ትልልቅ ደረጃ ላይ ደርሰዋል፡፡
ለአርቲስቶችና ለተዋንያን እንዲሁም ለታዋቂ ሰዎች ብዙ አልባሳትን ሰርተዋል ...
በጣም ለብዙ የአገራችን ታዋቂ ሰዎችና አርቲስቶች ሰርታለች፡፡
 ለምሳሌ አስቴር አወቀ ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ኢትዮጵያ ስትመጣ የለበሰችውንና ሸራተን ባዘጋጀችው የሙዚቃ ኮንሰርት ላይ ለሚያጅቧት ተወዛዋዦች በሙሉ እኛ ነን የሰራነው፡፡ ለኢትዮጵያ ሚሊኒየም የተለበሱት አልባሳት በተለይም የወ/ሮ አዜብ መስፍን፣ አርቲስት ሙሉዓለም ታደሰ.. በብሔራዊ ቴአትር ‹‹ዋዜማ›› በሚል ተተርጉሞ በቀረበው የዊልያም ሼክስፒር ተውኔት ላይ ለተሳተፉ ተዋንያን አልባሳት የሰራችው እሷ ናት፡፡ እንዲሁም  የሰርከስ ኢትዮጵያ፣ የሰርከስ ጅማ፣ የሰርከስ ትግራይን አልባሳትም ሰርታለች፡፡ ይሄ በጣም ከብዙ በጥቂቱ ነው፡፡
የተለያዩ የአልባሳት አውደርዕይም አዘጋጅተዋል አይደል?
በግሏም በጋራም በጣም ብዙ ሥራዎችን አቅርባለች፡፡ ለምሳሌ በአዲስ አበባ ሂልተንና ሸራተን ሆቴሎች፣ ኤግዚብሽን አዳራሽ፣ ንግድ ምክር ቤት … የኦሮሚያ ቴሌቶን የባህል አልባሳት እንዲሁም በጋራ ደግሞ አፍሪካን ሞዛይክ ከአና ጌታነህ ጋር በመሆን በአሜሪካ ኒውዮርክ፣ ማክዳ በዛብህና ሳራ መሀመድ ከተባሉ ታዋቂ የፋሽን አልባሳት ዲዛይነሮች ጋር በመሆን ዘመናዊ አልባሳትን ከባህላዊ ጋር በማዋሃድ በቡፌ ደላጋር ያቀረቡት እና በተለያዩ ኤምባሲዎች የተዘጋጁት መድረኮች መካከል ጥቂቶቹ ናቸው፡፡
ወ/ሮ ደስታ ያላቸውን ሙያ ለትውልድ ለማስተላለፍ ምን እየሰራችሁ ነው?
እናቴ አሁን ድረስ ውስጧ የማስተማር ፍላጎት አለ፡፡ እኔ እናቴና አንድ ወንድሜ ሆነን እንዲሁም ዳንኤል አባይ የሚባል ወንድማችን አሁን በሕይወት የለም በጋራ በመሆን መስቀል ፍላወር አካባቢ ደስታ ዲዛይን በሚል የዲዛይን ትምህርት ቤት ከፍተን፣ ብዙ ባለሙያዎችን አፍርተን ነበር ሆኖም በተለያዩ ምክንያቶች ትምህርት ቤቱ ለጊዜው ተዘግቷል፡፡ እንድ አምላክ ፈቃድ በድጋሚ ከፍተን ለማስተማር እቅድ አለን፡፡
ሴቶች ባህልን ለማስተዋወቅ ያላቸውን ሚና ለማበረታታት በሚል የ2014 ዓ.ም ‹‹አርአያ ሰው›› ተሸላሚ ሆነዋል ---
በዚህ አጋጣሚ የአርአያ ሰው ሽልማት አዘጋጅ የሆነውን ዲያቆን ፍሬውን በጣም ማመስገን እፈልጋለሁ የዘንድሮ ብቻ ሳይሆን የ2006 ዓ.ም የኢትዮጵያ የባህል አልባሳትን ለረጅም ዘመን በማዘጋጀት እንዲሁም ባህልንና ታሪክን በመጠበቅና በማስተላለፍ ላበረከቱት አስተዋጽኦ በሚል የ‹አርአያ ሰው›› የረጅም ዘመን ሽልማት አሸናፊ ሆና ተሸልማለች፡፡ ዘንድሮም ላደረገችው ባህልን የማስተዋወቅ ስራ ተሸላBAHELሚ ሆናለች፡፡ ለዛም እጅግ በጣም ደስተኞችና አመስጋኞች ነን፡፡

Read 1265 times