Saturday, 27 November 2021 14:28

የኮንስትራክሽኑ ዘርፍ ባለሙያዎች ለህልውናው ዘመቻ የሚችሉትን ሁሉ ለማድረግ ወስኑ

Written by 
Rate this item
(0 votes)

 በኮንስትራክሽኑ ዘርፍ የተሰማሩ ባለሙያዎችና ተቋራጮች ለህልውና ዘመቻው የሚችሉትን ሁሉ ለማድረግና አገር ከገባችበት ጫና እንድትወጣ መስዋዕትነት ለመክፈል ቃል ገቡ። የዘርፉ ባለሙያዎችና ባለሃብቶች ይህን ውሳኔ ስተላለፉት ትናንትና ህዳር 17 ቀን 2013 ዓ.ም ስድስት ኪሎ በሚገኘው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ዲዛይንና ግንባታ ስራዎች ቢሮ በሚገኘው አዳራሽ የኮንስትራክሽን ስራ ተቋራጮች ማህበር ከአዲስ አበባ ዲዛይንና ግንባታ ስራዎች ቢሮ ጋር  በመተባበር ባዘጋጁት የውይይት መድረክ ነው።
ከሁለት ሳምንት በፊት በሸራተን አዲሰ ሆቴል በቢሮውና በማህበሩ ትብብር ለህልውና ዘመቻው በተዘጋጀ የገቢ ማሰባሰቢያ መርሃ ግብር ላይ ከ100 ሚ. በላይ መሰብሰብ መቻሉን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የዲዛይንና የግንባታ ስራዎች ቢሮ ሃላፊ ኢ/ር አያልነሽ ሀብተማሪያም ተናረዋል።ከዚህ በተጨማሪም ተቋረጮቹ  5 ሚ. 238 ሺህ ብር፣ 21 ገልባጭ መኪኖች፣ 8 ፒክአፕ መኪኖች፣ አይሱዙና አንድ ውሃ ቦቴ ለመስጠት ቃል የገቡ ሲሆን ተሽከርካሪዎቹ ዘመቻው እስኪጠናቀቅ አገልግሎት ላይ እንደሚውሉና 7 የማህበሩ አባላት ለመዝመት ፈቃደኛ መሆናቸውም በእለቱ ይፋ ሆኗል።የግንባታ ዘርፉ ለሀገር እድገት ወሳኝ ሚና የሚጫወት ዘርፍ መሆኑ ግልጽ እንደሆነ  የገለጹት ኢ/ር አያልነሽ ኢትዮጵያ ጡት ነካሽ በሆኑ ከሀዲ ልጆቿ ከውጪ ጠላቶቿ ጋር አብረው አጣብቂኝ ውስጥ ሲከትቷት ደግሞ የዘርፉ ተዋንያን ገንዘብ ከማዋጣት ባለፈ በግንባር ዘምቶ እስከመሰዋት፣ የስንቅና ትጥቅ ማመላለሻ መኪኖቻቸውን በመስጠትና በግንባር ለሀገር ክብር ደሙ እየፈሰሰ ላለው መከላከያ ሰራዊት ልዩ ሀይል፣ ፋኖና ሚሊሻ ደም በመለገስ ሀገራዊ ሃላፊነታችንን እንወጣለን ያሉ ሲሆን፣ በቀጣይ እኔን ጨምሮ 40 ያህል የቢሮው አመራሮች ወደ ግንባር ለመዝመት ዝግጅታችንን አጠናቀናል ብለዋል።
የዘለቀ ረዲ ደረጃ 1 እና 2 ኮንስትራክሽን ተቋራጭ ባለቤትና የህብር ኢትዮጵያ ፓርቲ አመራር ኢ/ር ዘለቀ ረዲ በውይይቱ መድረክ መክፈቻ ላይ ለታዳሚ የማነቃቂያ ንግግር ያደረጉ ሲሆን በገንዘብና በእውቀታቸው የህልውና ዘመቻውን ከመደገፍ ባሻገር በተለያዩ ግንባሮች እየተገኙ ሰራዊቱን ሲያነቃቁ እንደነበር አስታውሰው፣ በዚህ መድረክ ወደ ግንባር ለመዝመት ከሚወስኑ የሙያ አጋሮቻቸው ጋር እሳቸውም ሆነ ሰራተኞቻቸው እንደሚዘምቱና በደም ልገሳም እንደሚሳተፉ አስታውቀዋል።
የኮንስትራክሽን ተቋራጮች ማህበር ፕሬዚዳንት ኢ/ር ግርማ ሀብተማሪም ባደረጉት ንግግር አሸባሪው የትግራይ ወራሪ ሃይልና እነሱን አይዟችሁ በሚሉ ጥቂት ምዕራባዊያን ሀገራት በሀገራችን ኢትዮጵያ ላይ የተከፈተውን ጦርነትና በህልው ላይ የተቃጣባትን አደጋ ለመመከት መላ ኢትዮጵያዊያን በጠቅላይ ሚኒስትራችን ፊት አውራሪነት እየተፋለሙ ይገኛሉ ካሉ በኋላ፣ ሁላችንም በምናደርገው ርብርብና ትግል ኢትዮጵያ በድል አድራጊነት እንደምትወጣው ጽኑ እምነት አለኝ ብለዋል።
“እኛም የኮንስትራክሽን ስራ ተቋራጮች ይህ የህልውናውና ዘመቻ ከተጀመረ ጀምሮ በጦር ግንባር በመገኘት ለመከላከያና ለሌሎች ህዝባዊ ሰራዊቶች የሞራል ስንቅ ከመሆን ባለፈ አቅማችን የፈቀደውን የገንዘብና የሎጂስቲክ ድጋፎች ሁሉ እያደረግን እንገኛለን።”
ያሉ ሲሆን ይህም ድጋፍ በጦርነቱ ከቤት ንብረታቸው የተፈናቀሉ ወገኖች መርዳትት  በእጅጉ ያካተተ ስለመሆኑ በንግግራቸው ገልጸዋል።ኢ/ር ግርማ አክለውም ሀገራችን ኢትዮጵያ ላይ የህልውና ጦርነት የከፈተው የትህነግ ወራሪና ተባባሪዎቹ ኢትዮጵያዊያን ከ1983-2010 ዓ.ም መጋቢት ወር ድረስ ያሳለፍነውን የባርነት ዘመን ከከፍተኛ የቂምና የበቀል እርምጃዎቻው ጋር ድጋሚ ሊጭኑብን አሁንም በእብሪት መነሳታቸው ኢትዮጵያዊያን ከፍተኛ እልህና ቁጭት ውስጥ ከትቶናል ያሉ ሲሆን አሁን ያሉንን ማንኛውም አይነት መኪኖች፣ ደማችንንና ገንዘባችንን ከመለገስ ባለፈ በግንባር ከጠቅላይ ሚኒስትራችን ጎን ለመዝመት ዝግጁ ነን ብለዋል። ህልውናችን ተከብሮ ጦርነቱን በድል እስክናጠናቅቅ ማንኛውንም አይነት ድጋፍ አጠናክረን እንቀጥላለን ሲሉም አክለዋል የማህበሩ ፕሬዚዳንት ኢ/ር ግርማ ሀብተማርያም።ኢ/ር አያልነሽ በበኩላቸው እርሳቸው በሚመሩት መስሪያ ቤት ከ280 በላይ ሰራኞች እንዲሁም ከሌሎች ሁለት ተጠሪ ተቋማት ጋር በድምሩ ወደ 700 የሚጠጉ ሰራተኞች መኖራቸውን አስታውሰው ሁሉም የወር ደሞዙን ከመስጠት ጀምሮ ደም በመለገስና ግንባር በመዝመት ብዙ አስተዋጽኦ እያረጉ ሲሆን ይህ ቅዱስ ጦርነት እስከሚጠናቀቅ ድጋፉን አጠናክረን እንቀጥላለን ብለዋል። በቀጣይም በርካታ የኮንስትራክሽኑ ዘርፍ ተዋናዮች ቀይ መስቀል ግቢ ተገኝተው ደም እንደሚለግሱም ኢ/ር አያልነሽ ጨምረው ገልፀዋል።


Read 1276 times