Tuesday, 30 November 2021 00:00

ሕወሓት የገባበት የሞት ቀጠና እና የአሜሪካ ተለዋዋጭ ስልት

Written by  -ደረጀ ይመር-
Rate this item
(0 votes)

 ሕወሓት  የገባበት  ወጥመድ
በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደርና የአፍሪቃ ጉዳዮች ስቴት ሴክረታሪ ሆነው ያገለገሉት ቲቦር ናዥ ከቢቢሲ ጋር በነበራቸው ቆይታ፣ አሸባሪው ሕወሓት እያደረገ ያለውን መስፋፋት ቁልጭ አድርገው አስቀምጠዋል፡፡
#ሕወሓት ከዋናው ደጀን በጣም ርቋል፡፡ ልክ የሂትለር ጦር ራሺያ ውስጥ ገብቶ እንደቀለጠው ሁሉ፣ድርጅቱ ተመሳሳይ እጣፈንታ እንደሚገጠምው አያጠራጠርም፤ ይህ እንደ አፍጋኒስታን ያለ ምንም ተኩስ ልውውጥ ከተሞችን በቀላሉ የምትቆጣጠርበት ሀገር አይደለም፤; ብለዋል፡፡
የአማራ ክልል የልዩ ኃይል ዋና አዛዥ ብርጋዴር ጄነራል ተፈራ ማሞ ከአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን ጋር ባደረጉት ቆይታ፣ የቲቦር ናዥን ሐሳብን የሚያጠናክር አስተያየታቸውን አጋርተዋል፡፡
ሕወሓት ከተሞችን እያወደመና እየዘረፈ፣ ከደጀኑ ርቆ በአማራ ክልል ግዛት ውስጥ ተቀርቅሯል፤ ይኽ ደግሞ የሽብር ቡድኑን የማፍረክረክ ሥራን በጣም ያቀለዋል፤ ብለዋል፡፡
የጥፋት ቡድኑ በሕዝብ ማእበልና ግርግር ወደ አማራ ክልል ግዛት ዘልቆ ለመግባት የቻለው፤ ከመንግሥት ወገን በነበረው ዝንጉነት ነው፡፡ የድርጅቱን አውዳሚነት የሚመጠን በቂ ዝግጅት ባለመደረጉ የተነሳ፣ የጥፋት ኃይሉ ያደረሰውን መጠነ ሰፊ ጥቃት ገና በእንጭጩ ማቆም ሳይቻል ቀርቷል፡፡
የጥፋት ቡድኑን የማዳን ዘመቻ
አብዛኞቹ የፖለቲካ ታዛቢዎች እንደሚስማሙበት ከሆነ፣ ለምእራባዊያን ያልተገባ ጫና ልጓም ማበጀት የሚቻለው  ሽብርተኛው ደርጅት ዳግም  በማያንሰራራበት ደረጃ አከርካሪው ሲሰበር ብቻ ነው፡፡
በኢትዮጵያ ወቅታዊ የፖለቲካ ትኩሳት ዙሪያ፣ ጥልቅ ትንታኔዎችን በማቅረብ የሚታወቀው ቦርከና የተባለው ታዋቂ ደረገጽ፣ በኤዲቶሪያል አቋሙ ባንጸባረቀው ጽሑፍ፤ የአሜሪካንን ቅይጥ ጣልቃገብነት ለመከላከል ሕወሓትን በማያዳግም ሁኔታ መደምሰስ ከጥያቄ ውስጥ የሚወድቅ እንዳልሆነ ጠቁሟል፡፡
የቲፋይ ግሎባሉ ተንታኝ አክሻይ ናራንጅ በበኩሉ፣ አሜሪካ በኢትዮጵያ ላይ እያራመደች ያለውን አቋም በአጭሩ እንዲህ ይገልጸዋል፡-
 #ኢትዮጵያን ለማፈራረስ ጥቃት የከፈተውን ሕወሓት ከአሜሪካ በስተቀር በግልጽ ለመደገፍ የደፈረ ሀገር የለም፡፡ የአሜሪካ ጥብቅ ወዳጅ የሆነችው የተባበሩት ኢምሬት እንኳን ድጋፏን እየለገሰች ያለችው ለማእከላዊው መንግሥት ነው፡፡ የባይደን አስተዳደር ሕወሓትን አጥብቆ የፈለገው አሻንጉሊት መንግሥት በማስቀመጥ፣ ቀጠናው ላይ ያለውን ብሔራዊ ጥቅም ለማስጠበቅ በማሰብ ነው፤; ብሏል፡፡በርግጥም የተንታኙን ሐሳብ ውሃ የሚቋጥር እንደሆነ ለማረጋገጥ፣ መሬት ላይ ያለውን እውነታ ጥቂት መመርመር በቂ ነው፡፡
አሜሪካ ከኢትዮጵያ ጋር ስትራቴጂካዊ አጋርነት የፈጠሩትን ሌሎች ኃያላን ሀገራትን በመግፋት፣ ተላላኪ መንግሥትን ሥልጣን ላይ ማስቀመጥ ተቀዳሚ አላማ ያደረገ  የውጭ ጉዳይ ፖሊሲን እንደምትከተል፣ የሕወሓት የሥልጣን ዘመን ምስክር ይሆናል
ኢትዮጵያ የፓን አፍሪቃ ንቅናቄና ጸረ ቅኝ ግዛት ተጋድሎ ቀንዲል እንደሆነች ይታወቃል፡፡ በዚህም ምክንያት ምእራባዊያን ከኢትዮጵያ የሚነሳ ማንኛውም እሳቤን በጥንቃቄ እንደሚመለከቱት ጉዳዩን በቅርበት የሚከታተሉ ባለሙያዎች ይጠቁማሉ፡፡ ልእለ ኃያሏ ሀገርም ብትሆን ራሷን የቻለች፣ ለሌሎች አፍሪቃ ሀገራት ተምሳሌት የምትሆን ኢትዮጵያን መመልከት አትፈልግም፡፡
አሜሪካ ኢትዮጵያን በተመለከተ የምትከተለው የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ፣ ከትላንቱ የሚቀዳ ነው፡፡ ከዚህ ቀደም፣  ሕወሓትን ለሥልጣን ያበቃችበትን የጥፋት መንገድ፣ አሁንም መድገም እንደምትፈልግ፣ የቀንዱ ልዩ ልኡክ ጄፍሪ ፍሊትማን እስካሁን ያደረጉት የዲፕሎማቲክ መገለባበጥ፣ በገሀድ ይነግረናል፡፡
የወታደራዊ ጣልቃ ገብነት አዝማሚያ
የአሜሪካ ቁልፍ ወታደራዊ ባለሥልጣናት፣ ከያዝነው ወር መባቻ ጀምሮ የኢትዮጵያ ፖለቲካዊ ምስቅልቅልን በተመለከተ፣ እያስተላለፉት ያለው መልእክት ትኩረት የሚስብ ሆኗል፡፡  
የቀድሞው የሰሜን አትላንቲክ የጦር ቃልኪዳን ድርጅት ወይም ኔቶ ኮማንደር፣  ጀምስ ስታርድቪስ ቡሉምበርግ በተባለው ታዋቂ ድረገጽ ላይ ከሳምንታት በፊት ያጋሩት ጽሑፍ፣ ምናልባትም በነጩ ቤተ መንግሥት እየተሸረበ ያለውን ሴራ ሹክ የሚል ነው፤ይላሉ - ጉዳዩን በቅርበት የሚከታታሉ የፖለቲካ ታዛቢዎች፡፡
የስታርድቪስ የጽሐፉ ማጠንጠኛ፣ የኢትዮጵያን ፖለቲካዊ ምስቅልቅል የሰላም አስከባሪ ጦር በማሰማራት መፍታት እንደሚቻል ያትታል፡፡
“ለግጭቱ እልባት ለመስጠት የተባበሩት መንግሥታት በመሪነት በሚያሰማራው የሰላም አስከባሪ ጦር ላይ አሜሪካ ንቁ ተሳታፊ መሆን አለባት፡፡  ለዚህ ደግሞ በቀጠናው ያለው የአሜሪካ ወታደራዊ ካምፕ የሰላም ማስከበሩን ሒደት በመምራት ረገድ ትልቅ ሚና ይጫወታል” ብለዋል፡፡
ጅቡቲ ላይ ያለው የአሜሪካ ወታደራዊ ማዘዣ ጣቢያ ዋና አዛዥ ዊሊያም ዛና ከቢቢሲ ጋር በነበራቸው ቆይታ፣ የጦር አመራሩን ሐሳብ የበለጠ የሚያጠናክር ፍንጭ ሰጥተዋል፡፡
“በኢትዮጵያ የሚከሰት ማንኛውም ችግር፣ በቀጠናው ላይ የሚኖረው ተጽእኖ ከፍተኛ ነው፡፡ ኢትዮጵያ በውስጥ ችግሯ ስትጠመድ፣ ግብጽና ሱዳን በሕዳሴ ግድብ ላይ ያላቸውን ጥቅም በወታደራዊ ሃይል ለማስጠበቅ መጣራቸው አይቀርም፡፡ ይኼ ደግሞ ለቀንዱ ጂኦፖለቲካ አደገኛ ነው፡፡ በዚህም የተነሳ፣ በኢትዮጵያ የሚፈጠረውን ማንኛውንም ነገር በንቃት እየተከታተልን ነው፤” ሲሉ ተናግረዋል፡፡
የባይደን አስተዳደር፣ የተኩሰ አቅም ስምምነት ላይ የሙጢኝ ያለው፣ ለሕወሓት እስትንፋስ ለመቀጠል ነው፡፡ የተክሱ አቅም ስምምነት አላማ፣ የአሜሪካን ጦር ፋታውን ተጠቅሞ፣ በኢትዮጵያ ውስጥ የሚገባበት ዕድልን ለማግኘት ነው፡፡ ይኽ ደግሞ፤ ሕወሓትን ለማጠከር ተጨማሪ አማራጭ መሆኑ አይቀርም፤  ብሏል - ሳንቢር ሲናህ የተባለው ጸሃፊ፡፡
 አሜሪካ ይህን አማራጭ የመጠቀሟ ዕድል በጣም የጠበበ ይመስላል፡፡ ምክንያቱም፤ ከዚህ ቀደም በባእድ ሀገር ጦሯን አስገብታ ያተረፈችው ውርደትን እና ከፍተኛ የሆነ የመዋለ ንዋይ ኪሳራን ነው፡፡ ልእለ ኃያሏ ሀገር፣በቀንዱ ላይ ያላትን ብሔራዊ ጥቅም በወታደራዊ ጣልቃ ገብነት ለማሰከበር ከወሰነች፤ ልክ እንደከዚህ ቀደሙ ሁለንተናዊ ኪሳራ ሊያጋጥማት እንደሚችል እሙን ነው፡፡
 ከጥቂት ዐሥርተዓመታት በፊት ጦሯን ወደ ሱማሌ ግዛት አስገብታ የደረሰባት ሽንፈት በዚህ ረገድ ተጠቃሽ ይሆናል፡፡ ሀገሪቱ ሕወሓትን ቀና ለማድረግ ወታደራዊ ጣልቃ ገብነትን ምርጫዋ ካደረገች፣ ቅኝ ገዢዎችን አሳፍሮ የመመለስ ልምድ ያላት ኢትዮጵያ፣ የማይረሳ  ትምህርት ልትሰጣት ትችላለች፡፡
የቀጠናው ውስብስብ ጂኦ ፖለቲካ፣ ልእለ ኃያሏ ሀገር፣ ኢትዮጵያን በጦር ማንበርከክ የሚያስችል ምቹ ከባቢ የለውም፤ ከዚህ ይልቅ፤ እስከ መጨረሻው በተለያየ ማእቀፍ የሚመነዘር ማእቀብ በመጣል፤ ፍላጎትን ለማንጸባርቅ ብዙ ርቀት መሄዷ አይቀርም፡፡
ኃያሏ ሀገር አሁን አሁን የአቋም እጥፋት እያንጸባረቀች እንደሆነ ምልክቶች መታየት ጀምረዋል፡፡ የቀንዱ ልዩ ልኡክ ፊልትማን፣ ሕወሓትን አስመልክተው ባሳለፍነው ሳምንት በኬኒያ የሰጡት መግለጫ፣ለአቋም ለውጡ ማሳያ መሆን ይችላል፡፡
ማሰሪያ
የአሜሪካንንም ሆነ የምእራባዊያንን ጫና ለማለዘብ መፍትሄው ያለው በወታደራዊ ድል ላይ ነው፡፡ ሕወሓት እየተጎተተ ሰሜን ሸዋ ድረስ ለመዝለቅ የቻለው፣ እየተከተለ ባለው ተለዋዋጭ የትግል ስልት ነው፡፡ አጥፊው ቡድን ሕዝባዊ ማእበልን፣ መደበኛ ውጊያን፣ የከተማ ሽብርና የደፈጣ ጥቃትን ቀላቅሎ ይጠቀማል፡፡
ለአብነት ደሴን ለመቆጣጠር በከተማው ውስጥ መሽጎ የነበረው የጥፋት ቡድኑ ክንፍ ድርሻው የጎላ እንደነበር ከዐይን እማኞች ለማወቅ ተችሏል፡፡ ይኽም ለመዲናዋ ትምህርት ሆኖ ከወትሮው ለየት ያለ የጸጥታ ሥራ በመሥራት፣ የሽብር ቡድኑ የዘረጋቸውን የኅቡዕ ሕዋሶችን መረብ መበጣጠስ ተጀምሯል፡፡ መንግሥት ሕወሓት ይዞት የመጣውን ጸጉረ ልውጥ የትግል ስልት በውል ተረድቶ፣ የማክሸፊያውን ስትራቴጂ ገቢራዊ ማድረግ የጀመረው ዘግይቶ ነው፡፡
በአጠቃላይ በሀገራችን ኅልውና ላይ ከውስጥም ሆነ ከውጪ  የተጋረጠውን አደጋ በጊዜ ለማስወገድ፤ የሽብር ቡድኑን የመደምሰስ ሥራ በአፋጣኝ መከወን ይኖርበታል፡፡

Read 7596 times