Saturday, 27 November 2021 15:05

የእውነት መልኮች

Written by  -አፀደ ኪዳኔ (ቶማስ)-
Rate this item
(1 Vote)

ለጋ የልጅነት ፍኖት ላይ የሚንከላወሱ ንፁህ የትውስታ ብሌኖች አሉ : ከልቦና የማይነጥቡ የምንጊዜም ለጣቂ ዳራ - በየዳናችን የሚከተሉን፣ በትላንት ብልቃጥ ውስጥ የተቀመጡ ግራጫማ ዛሬዎች ይመስላሉ። እነዚህን የብልቃጥ ውስጥ ነቁጥ ጉብታዎች በዛሬው የኑረት ንብርብር ቸል ልላቸው ታተርኩ። ወጣትነቴ ደረስኩ ሲል ፣ ሪዝ ጉንጬ ላይ እንዳቆጠቆጠ፣ ዓይኖች ከየሰዉ ልብ ልጥለቅ ብለው ሲማስኑ - እምነት አሰናሳይ ያ የልጅነት ልቤን በቂልነቱ ገፋሁት። ጸሊም እልፍ የእውቀት ንጥር ቃረምኩ። ሂድ ወዳሉኝ መንገድ ሁሉ ስመላለስ አልታከትኩም። ስህተት የሚሉትን መሰል ጥያፌያቸውን እንደ ራሳቸው አነወርኩ። በማይጎድል የእውቀታቸው ድንኳን ውስጥ ያልባተ ኅልዮት እንደ ደመና ከበቡኝ። ደስታ ከተንተራሰበት ናህይ ትራስ ላይ ጠቅልዬ ወደማይታይበት በኣት ሸሽግኹ።
በራሴ ውስጥ እልፍ ማንነቶች አሉ።
አዕምሮዬ ቅጠል ላይ የከተቡ ብዕሮች ብዙ ናቸው።
[ ት ላ ን ት ]
ተመሳሳይ መንገዶች አሉን። ቋንቋችን አንድ ነው። በማህበረሰብ ቅንፍ ውስጥ ስለተሰባሰብን . . . የአኗኗር ቀኖና ተረቆልን የምንጓዝ ነን። ቅቡል ማንነት አለኝ - እንደዉነቱ። ጥሩ ስራ ስለምሰራና ጠንከር ብዬ በመማሬ ባንሾካሹክም ድምፄ ፀርሐ አርያም ድረስ የሚሰማ ነው። ከስራቸው ያደኩ ነኝ። የተለየ ነገር የለኝም (በእርግጥ ሊኖረኝም ይችላል)። በማህበረሰብ አንቀልባ ታዝዬ አድጌያለሁና ፣ እነሱ እኔ - እኔ እነሱ ነኝ።
(እንደ ባዕድ ብቀላቅልም እራሴን )
.. . ያለ ዘመድ የወጣሁት ግዙፍ ተራራ አለ። እናቴን ሳጣ የአስራ ስድስት አመት ልጅ ነበርኩ። ጠባብ የቀበሌ ቤት ውስጥ ብቻዬን ነበር የቀረሁት። በዚያች ለጋ አቅሚት የቀን ስራ መጋተር ነበረብኝ።
. . . ያቆዩኝ በፍቅር የተፈተሉ እናታዊ ዘሃዎች ናቸው። ጥዑም ትውስቶች። መንፈሷ የህይወቴ ወጋግራ ነበር። በዚህም ጠንክሬ ተማርኩ። የድህነትን ግድግዳ በተባ ስለት ቦርቡሬ እንደምንም ሾለኩ።
ቸል ያሉኝ ሰዎች አዳንቀው ተቀበሉኝ። በህይወቴ ውስጥ ዘልቀው ወጣትነቴ ላይ የእውቀታቸውን ልጓም አበጁ።
ከእናቴ ቀጥሎ በማህበረሰብ ጉያ ውስጥ አደርኩ።
“አየህ አሁን አድገሃል፣ እራስህን ችለሃል በዚያ ላይ ጥሩ ቀለም ቀስመህም አይደል? . . “ ብዙ ብዙ ዘበዘቡ. . .
በእኔ ልብ ውስጥ እራሳቸውን ተከሉ ... ስኬቴን ስኬታቸው አደረጉ። እኔ እነሱ - እነሱ እኔ ሆንን።
 2
[ ዛ ሬ ]
ስመላለስ አየዋለሁ። ወደ ስራ ስሄድ ከዚያች ድንጋዩ ላይ ሆኖ ይፅፋል። . . . ሰዓቴን ስለሚያውቅ ያደረ ስካር ያጨናበሰው ትንንሽ ዓይኑን እያንከራተተ ይማትረኛል። ጠይም መልክ አለው። የፊቱ አጥንቶች አግጥጠው ወትተዋል። ጥልቅ ከሆነ ጉድጓዳቸው የሚንቀዋለሉ ዓይኖቹ ማንንም በጥርጣሬ ይመለከታሉ። መንገድ ደርዝ ላይ በጭቃ የተለሰነች ጠባብ አንድ ክፍል ቤት አለችው። እንዴት መች እና በምን ሁኔታ እንደመጣ ለሰፈሬው ግልፅ አይደለም። ደጋግሞ እንደሚለው የሚኖረው በአጎቱ ቤት ነው (ከሞቱ ቆይተው ነበር)። ይህ ደግሞ ማንንም የማይመለከት አብሶ መንደሬው የማያገባው ጉዳይ ነው - እሱ እንደሚለው።
ታዲያ ዕለት ዕለት ይጠጣል። ሲሰክር ንጉሱን እንደረገመ ነው። “ያ ከይሲ ሽማግሌ መሰሪ ነው” ይላል። “ወዝ አደሩን የበዘበዘ። ቢሮክራሲውን በዘሩና በሃይማኖቱ የሞላ ! ደሞ. . .” ምላሱ እየተሳሰረ “ህጉም... መሬቱ..ም... ህዝ..ቡም ...የንጉሱ ነው ሲል የማያፍር. . . “
ወታደራዊ መንግስት ሁሌም  በክብር ስሙ ይጠራል።
“ምንም ከኩሎ የቀጥቃጭ ጎሳ የዘር ሃረጉ ቢመዘዝም አንቀጥቅጦሃል። ትክዳለህ? መንጌን የተካ ወንድ አለ? ሽንታም ሁላ እናቅሃለን!”
ይሄን መሰል ንግግሮች ያስደምጣል። ከአልጋዬ ላይ ሆኜ ምናልባት መፅሃፌን ይዤ በጥቂቱ ፈገግ እላለሁ።
ተኮላ ጭር ያለችው መንደር ላይ ትንሽ የጩኸት ቅመም ይጨምራል።
  ***
« አንተ! » ድንገት ደርሼ . . .
«እንደ ወፍ በሰማይ መብረር ጀመርክ እንዴ ? እንዴት አላየውህም? ገብርኤልን! በቃ አንተም ሌላን ሰው መምሰል ጀምረኻል »
«ይሄ ድፍርስ ዓይንህ ያያል ለመሆኑ? » ጀርባውን መታ አድርጌ እንደማቀፍ ያዝኩት።
«እንዲህ ስታቃልደኝ ደስ ይለኛል ፤ ገብርኤልን! ከምትሰጠኝ ቅራቅምቦ ገንዘብህ የበለጠ ማለቴ ነው። አየህ ቆሻሻ ሰለሆንኩ ወይ እብድ ነገር ስለምመስል ሰው እርቆኛል። እህል ብቻ አይደለም እቅፍም ይርባል። እንዲህ ጀርባዬን እየመታ የሚቃለደኝ፣ እንዳንተ የሚያቅፉኝ ለምን ጠፉ? ምናልባት እግዜሩ አትጠጉት ብሎ ይሆናል። የእሱ ነገር ምን ይታወቅል. . ግራ ሲሉት ቀኝ፣ ቀኝ ሲሉት ግራ ነው »
ደጋግሞ ከሚናገረው ይሄን መሰል ንግግር ውስጥ ወና ልቡን አያለሁ። አንዳች የማላውቀው ስሜት ይወረኛል። ሰቆቃው የማንም ነው። የሁሉም ልብ እንጉርጉሮ እዚህ ሰው የኑረት ግርጌ ላይ ተፅፏል። እያደባ ቀን የሚጠብቅ። እግዜርን ለመርገም ያኮበኮበ ምላስ . . .
ከስራ ስመለስ ቀን የፃፋቸው ሰብስቦ ሲያቃጥል አያለሁ። ሁሌም እንደዛ ያደርግ ነበር። አንድ ዕለት አንድ ፅሁፉን ከማቃጠሉ በፊት ደርሼ ተቀበልኩትና ማንበብ ጀመርኩ። የእጅ ፅሁፉ ቅልብጭ ያለ ነው።
«ጠይም መስታወት»  ይላል የፅሁፉ ርዕሱ... ማንበቤን ቀጠልኩ።
“የደራሲው ብዕር  በአድርባይነት ቀለም ተሞልቷል። እንደ እስስት አካባቢን መምሰል በህቡዕ የተከተበ የጠቢቦች መርህ ነው”
ፀሃይ ልትጠልቅ ፍም አሎሎ  መስላ ትጓዛለች። ሰማይ በደም የተነከረ የሚመስል ገላዋን ዓለም መድረክ ላይ  እያሳየች ነገም የዛሬ ክፋይ መሆኑን ታበስራለች። ሰዎች የጨረቃ መውጣትን እንደ ተዓምር ይጠብቃሉ። ከዋክብትን እንደ ትንግርት አጀብ እያሉ የሚያዩ ሰዎች መቆሚያ አጥተው ተንከራተዋል።
 እዚያ መንገድ ዳር አንድ ሽማግሌ ይናገራሉ...የለበሱት  ዘባተሎ...የዓይኖቻቸው  መቅላት. .. የፀጉራቸው መሸበት፣ እግዜር ሰዎችን ሰርቶ  ሲጨርስ  በተረፈው ቅንጥብጣቢ  ግብዓት የፈጠራቸው ይመስላል... እግዜር ከሰውም ሰው እንደመረጠ ያሳብቃል - የኚህ  ሰው አፈጣጠር። እንዲህም ሆኖ መናገሩን አላቆሙም...
“ይሄን ሁሉ ንገሯቸው። እግዜር ዓለምን  እረስቷል። እግዜር ሰዎችን እረስቷል። ዓለም ቁርሷ የሃሰት አፈር፣ ምሳዋ የሞት  ድንጋይ ሆኗል። የዓለም  ሰዎች እንባቸውን የሚያብስ አንዳችም ሰው ፣ አንዳችም አማልክት አጥተዋል። ሃዘናቸውን አንዴ እንኳን የሚቃኝ የለም። እውነት እውነት እላችኋለሁ ግልፅ ተነጋግሮ ባይገፋፋም   ሁሉም ተጠላልቷል። አደባባይ አይውጣ እንጂ ሁሉም ተናንቆ ሽንገላ ላይ ነው...ሸንጎ አይቁም እንጂ ሁሉም የእግዜር ተበዳይ  ይመስላል።  ይሄን ሁሉ ንገሯቸው። የፍቅርን ሳር ይዞ የሚመርቅ አባት መጥፋቱን ንገሯቸው። ልጅ ሳይወለድ ተረግሞ በሽልነቱ መክኗል። ጎረምሶቻችሁ ሃቅን አያውቁም። ስሜት የሚወስዳቸው፣ ቁጭት የሚመልሳቸው ናቸው። እውነት እውነት እላችኋለሁ መኖራችሁ ለአንድ የተራበ ህፃን ዳቦ አይሆንም። ጥበባችሁ ለአንዲት ብርድ ላንገላታት እንስት ሙቀት አይገዛም። እውቀታችሁ  ልጇን በሞት ተነጥቃ ብቻዋን ለቀረች እናት ማፅናኛ ቃላት የለውም። ብዙ ብትመስሉም ምንም ናችሁ። አንቱ ተብላችሁ ጨቅላ  ናችሁ። ልብ አድርጉልኝ... ሰባኪው ህዝብን ከማስተማር ደላይ ቃላት ተጠቅሞ ሆዱን መሙላት ቀሎታል። የደራሲው ብዕር በአድር ባይነት ቀለም ተሞልቷል። እንደ እስስት አካባቢን መምሰል በህቡዕ የተከተበ  የጠቢቦች መርህ ነው  “
“ በእኔ ላይ ከመሳቃችሁ በፊት  ለራሳችሁ አልቅሱ...ለህይወታችሁ አልቅሱ...ለሞት እያሸበሸባችሁ ዘምሩ። ሞት መዳኛ ትንፋሽ ነው። የዚህችን እርካሽ ዓለም ጦር መከለያ ጋሻ ሞት አይደለችምን “
ከኚህ ሽማግሌ አፍ የሚወጡት ቃላት ከእርግማን የከፉ፣ ከተዓምር የረቀቁ ናቸው። ሰዎች ግን እያይዋቸው በሳቅ ይፈርሳሉ...ጅል ሽማግሌ መሆናቸውን ይናገራሉ።  እብደታቸው  እስካሁ እንዴት እንዳልተሻላቸው  ይጠያየቃሉ።
“ንገሯቸው... ዓለም ቅጠል ላይ የተፃፈው የኑፋቄ ታሪክ መሆኑን፣ ሰዎች እራሳቸውን እንደ ጣዖት እንደሚያመልኩ...አምልከውም ለራሳቸው የበደል ደም እንደሚገብሩ...መሆንም የሚጀመረው እራስን ከመምሰል እንደሆነ ንገሯቸው... ንገሯቸው ያንን የግፍ ትርክት...ያንን ሰይጣንን የመምሰል ሁነት አንድ በአንድ ንገሯቸው።
ይህቺ ዓለም ጠይም መስታወት መሆኗን አልሰሙም...እግዜርም ቂም እንደሚይዝ ፣ ያልወደደውን እንደሚቀጣ አልሰሙም። እዚህቺ ቆሻሻ መቀመጫዬ ላይ ሆኜ ለነዚህ ሰው ለተባሉ ተንቀሳቃሽ ጉዑዛን እንደማነባ... እንባዬም ምድር ላይ እንደሚፈስ ንገሯቸው። ሁሉም ነገር የተፈጠረው ከመፈጠሩ አስቀድሞ መሆኑን ንገሯቸው። ሰዎች የሙታንን ጩኸት አልሰሙም...ንገሯቸው ለእነዚያ ደካሞች...መውደቅያዬን ላላዩ፣ የልቤን እልፍኝ ላልቃኙ...ሰም እና ወርቅ ንግግራቸው ሲፈተሽ ባዶ አቁማዳ ስለመሆኑ... እውነትም እንደ ጀንበር እንደምትጠልቅ ...ቀን ሲጎል ያመኑት  እንደሚከዳ...የወደዱት እንደሚርቅ ንገሯቸው... ሃይማኖት የደካሞች በኣት መሆኑን ንገሯቸው....”
ሰዎች ይሳሳቃሉ።  ሽማግሌው መናገሩን ቀጥለዋል...
“ንገሯቸው ለእነዚያ ደካሞች ...ተመሳሳይ እንቅፋት ሁለት ጊዜ እንደመታቸው...የፍቅር አዝመራቸውን የማስመሰል ተባይ  እንደበላው ንገሯቸው። ክህደት የሚጀምረው ከልብ መሆኑን አልሰሙምና ንገሯቸው። የህይወትን  ነገ አስቀድሞ የሚያይ የፍቅር ነቢይ ማጣታቸውን አያውቁም። ልክፍት ነው። የህይወት ልክፍት። ለዕለት ኑሯችሁ ስታዳክሩ፣ ለዕለት ጉርሳችሁ ስትለፉ የነፍሳችሁን  ሃሴት እንዳጣችሁ እወቁት።  ትልማችሁ ቅዠት መሆኑን ተመልከቱ። ህልማችሁም ከጨለማ ውጪ የሚያሳያችሁ አንዳችም ነገር የለም። አንዲትም  ተስፋ አላይባችሁም። ተስፋችሁ መክኗል። የምታምኑት እግዜር ሳይቀር ክዷችኋል። አታውቁትም...ዓለምን  መመልከቻ ዓይናችሁ ታውሯል። አታውቁትም... ማምለጫ እንዳጣች አይጥ የዘበት ወጥመድ ውስጥ መግባታችሁን አታውቁትም...አንድ በአንድ ንገሯቸው...የእነሱ የድሎት ኑሮ ለእኔ የህይወት ቅራሪ መሆኑን፣ የእነሱ ልጅ የመውለድ ፀጋ እርግማኔ ስለመሆኑ ንገሯቸው። በዘመድ አዝማድ፣ በቀዬ መንደር፣ በተወልድኩበት ሃገር - እንደማልታጠር ንገሯቸው። ዓለም ሃገሬ መሆኑን አያውቁም። ምድር እናቴ መሆኗን አልሰሙም። ስለዚህ ንገሯቸው...ሃሳባቸው ግልብ መሆኑ፣ ዓይናቸው ከአፍንጫቸው አርቆ  እንደማያይ፣ ጆሯቸውም ከዕለት ፀሎታቸው ውጪ ሌላ እንደማይሰማ ንገሯቸው። ...”
ህመም ሲሰማቸው በላስቲክ ወደ ተከለለ ማደሪያቸው ገቡ። መቆም አቃታቸው። ዓይናቸውን መግለጥ እንደከበዳቸው ደም በአፋቸው ይወጣ ጀመር... አካላቸው አልታዘዛቸውም...
በመጨረሻም የዘለዓለም እንቅልፍ አንቀላፉ።  ከመሞታቸው በፊት እንዲህ ይሉ ነበር :
“ንገሯቸው” ...
ከዘመናት በዃላ እግዜርን ሲወቅሱ  በቁጣው መብረቅ የሞቱ አንድ ሽማግሌ እንደነበሩ የዓለም የተረት ድርሳን መዘገበ።
ፅሁፉ እንዲህ ባለ አሳዛኝ ታሪክ  ያልቃል። በእርግጥም ጥሩ ይፅፋል።  
...በእጁ ሃይላንድ ሙሉ አረቄውን ይዟል። ዳር እንደታዛቢ በታላቅ አርምሞ የሚንፎለፎለውን ጢስ ይመለከታል። ፅሁፉ ጥሩ ስለሆነ  ለምን እንደሚያቃጥላቸው ጠየኩት።
«ልታቃጥለው ከሆነ ለምን ትፅፋለህ»
« አይ ዮሲ» በጥያቄዬ የተሰላቸ ይመስል ነበር «በብዙ የህይወት ውጣ ውረዶች አልፌያለሁ። `ምልህ ፣ የደርግ ወታደር ነበርኩ። አየህ ሻዕቢያን ስታገል የኖርኩ ነኝ። ብዙ ሰዎች በሳንጃ ሆድ እቃቸው ተዘንጥሎ ሲወድቁ አይቼ እንዳላየሁ ማለፍ ነበረብኝ። የደርግ ወታደር የጨበጣ ውጊያ እንደማይችል ታውቃለህ? አንዳንዴም ብዙዎች በጥይት ተመተው ሲያጣጥሩ፣ ግደሉኝ ብለው ሲማፀኑ ምናምን ልታይ ትችላለህ . . . ምልህ ጓድህን ተኩሰህ ልትገድል የምትችልበት አጋጣሚ ሊፈጠር ይችላል። ደባሪ ነገር ነው። በህይወት አስቀያሚና አሰቃቂ ፍኖት ላይ ስትራመድ አይነት. . . ትውስታ ይሰቅዝሃል። የሚወነጥል ሃዘን ታቅፈህ ታዘግማለህ።
ታድያ ይህን መሰል ታሪክ ጆሮ የሚፈልግ አይመስልህም። አየህ ፣ ብዕርና ወረቀት ሲገናኙ ጥሩ ጆሮ ያበጃሉ። የሚነፋፋህን ደስታ ሆነ ሃዘን ወደዚህ ጆሮ እያሰገርህ ለመተንፈስ ትሞክራለህ። ስትነበብ የጆሮህ ከረጢት ከአንዱ ጭንቅላት ግርጌ ተለጥፏል ማለት ነው። አብዛኛው ጊዜ ያሳለፍኩትን እፅፋለሁ። ዳራዬ ቁጭት ነው። ሃዘን የቀበተተው የምንጊዜም የሙሾ አምድ ነው። ታዲያ የከተብኩትን ዳር ሆኜ ሳነድ ቁጭቴም አብሮ የተቃጠለ ይመስለኛል። ከእሳቱ በኋላ ሃዘኔ አመድ እንዲወልድ እጠብቃለሁ። በእንዲህ አይነት ነገር የሚደሰቱ ጥቂቶች ይመስሉኛል። »
ጠፍጣፋ ድንጋይ ላይ አጠገቡ ቁጭ አልኩ። በሃይላንድ የያዘውን አረቄ ተቀበልኩት።
«ተው ያምሃል»
«አንተን አያምህም» ከፍቼው ጥቂት ተጎነጨው። ጉሮሮዬን እየቧጠጠ ሲወርድ ይሰማኛል።
«ደስ የሚል»
«አሳደግንህ የሚሉህ መንደሬዎች ደሞ ካዩህ ጉድ ይፈላል። ተነስ ዮሴፍ »
«ተዋቸው ባክህ» አልኩት።
ወደ ውስጥ እንድገባ በእጁ ምልክት ሰጠኝ። ቤቱ ጠባብ ፣ በጭስ የታመቀ ክፍል ነው። መሬት ላይ የተንጋለለ ፍራሽ ይታያል።አንድ የመመገቢያ ሳህን መሬት ላይ ወድቋል። የበዙ ዕቃዎች አልነበሩም።
ፍራሹ ላይ ቁጭ አልኩ። አረቄ ሊጨምር ለስላሳ ጠርሙስ ይዞ ወጣ። ጭርታው ያስፈራ ነበር። አንድ ፎቶግራፍ ከጫማዬ ስር ውድቋል። አንስቼ ፍራሹ ላይ አስቀመጥኩት። ልብ ብዬ ያላጤንኩት ግን የማውቀው አይነት ይመስላል። አቅርቤ በደንብ አየሁት። ወጣት ተኮላ የጅንስ ጃኬት ለብሶ አንዲት ጉብል አቅፏል።
ገረመኝ። እጄን አፌ ላይ ጫንኩ። ይህቺ ጉብል  እናቴ ነበረች።
በደመ- ነፍስ  ወጣሁ። ግርታ ሰቅዞኝ ነበር። ቤቴ እስክደርስ እራሴን መቆጣጠር አልቻልኩም። እናቴ የእኔ የምታላቸው ዕቃዎች የምታስቀምጥበትን ሳጥን ገለባብጬ በረበርኩ። ተመሳሳይ ፎቶ ተቀምጦ ነበር።
ተኮላ?????
ከዚህች ክስተት በኋላ ተኮላን አላየሁትም። ምናልባት ልጄ ብሎ ይጠራኝ ዘንድ ድፍረት አልነበረውም።
ሌላ ሰው መምሰል ነበረበት። ምክንያቱን ሊያስረዳኝ አልፈለገም። በገባው ወይ በማይገባው መንገድ ሃዘኔታዬን ቃርሟል። እቅፌን በእጅ አዙር ሰርቋል። የሚያሳዝን ሌባ ነበር። አሳዛኝ አባትም ጭምር።
ባገኘው እንደ በፊቱ አቅፈው ይሆን?
አላውቅም!
ምናልባት እሸሸዉ ይሆናል።
ምናልባት ከፊቱ እገበዝ ይሆናል።
የእውነት መልኳ ብዙ ነው።


Read 681 times