Print this page
Saturday, 04 December 2021 13:28

“የኦፌኮ የሽግግር መንግሥት መግለጫ እኔንም አስደንግጦኛል”

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(1 Vote)

    ኦፌኮ በአንድ ሰው የበላይነት የሚዘወር ፓርቲ ነው
       እኔ ለህወኃት ምንም ዓይነት ሩህሩህ ልብ የለኝም
       እኛ የመገንጠል ጥያቄ ከኦነግ ጋር ተጋርተን አናውቅም

       ባለፈው ሰሞን የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ (ኦፌኮ)፤ የሽግግር መንግስት እንዲመሰረት የሚጠይቅ መግለጫ አውጥቶ ነበር። መግለጫው አንዳንድ የፓርቲው አመራሮች ሳያውቁት የወጣ መሆኑም እየተገለጸ ነው። “መግለጫው ከእኔ እውቅና ውጪ የወጣ ወቅቱን ያልጠበቀ፣ ኦፌኮም እንደ ፓርቲ አቋም ያልያዘበት ነው” ይላሉ፤ የኦፌኮ ም/ሊቀ መንበር አቶ ገብሩ ገ/ማርያም። በዚህ አወዛጋቢ መግለጫና ተያያዥ ወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ የኦፌኮ ም/ሊቀ መንበር አቶ ገብሩ ገ/ማርያም፣ ከአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ አለማየሁ አንበሴ ጋር ተከታዩን ቃለ ምልልስ  አድርገዋል።



            ኦፌኮ ከሰሞኑ በድጋሚ የሽግግር መንግስት እንዲቋቋም የሚጠይቅ መግለጫ አውጥቷል። መንግስት ደግሞ የሽግግር መንግስት የመመሥረት እንቅስቃሴ የሚያራምዱ አካላት ላይ እርምጃ እወስዳለሁ ብሏል። ይሄን መግለጫ ፓርቲያችሁ በዚህ ወቅት  እንዴት ሊያወጣ ቻለ?
ይሄን መግለጫ እኔ አላውቀውም። መግለጫው የወጣው እኔ አዳማ ለስብሰባ በሄድኩበት ወቅት ነው። ስለ መግለጫው እንደ ምክትል ሊቀ መንበርነቴ ምንም የማውቀው ነገር የለም። ልክ መግለጫው እንደወጣ በጣም ነው የደነገጥኩት። ከአዳማ እንደመጣሁ ከምክትል ሊቀ መናብርቱ አንዱ የሆኑትን አቶ ሙላቱ ገመቹን ነበር  ለማናገር የሞከርኩት። ነገር ግን የሰጠኝ መልስ አጥጋቢ አልነበረም። ምንም መልስ አላገኘሁም ብል ይቀላል።
መግለጫውን ማን ነው ያወጣው? መግለጫ የሚወጣው በሥራ አስፈጻሚ ውሳኔ አይደለም? እርስዎ የስራ  አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል አይደሉም እንዴ?
እኔ አዳማ  ከመሄዴ በፊት ባለው ረቡዕ ነበር የታሰበው። ነገር ግን ለእሁድ አሸጋገሩት። በወቅቱ እኔ አዳማ ስለነበርኩ እኔ በሌለሁበት ነበር ስብሰባው የተካሄደው ማለት ነው። የሆነው ሆኖ እንዲህ ያለ መግለጫ ሲወጣ  የድርጅቱ ሊቀ መንበር መኖር ነበረበት ወይም ማዕከላዊ ኮሚቴ አሊያም ሁሉንም ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ መጥራት ያስፈልጋል። ቢያንስ ሁለት ምክትል ሊቀ መናብርት ነው ያለነው። እንደው የፈለገውን ያህል አንገብጋቢ ቢሆን እንኳ ለሌላ ጊዜ ማድረግ ይቻል ነበር። ይህ እኮ ቀላል ነገር አይደለም። የሽግግር መንግስት የሚጠይቅ መግለጫና አቋም ነው። በዚህ ወቅት እንዲህ ያለ ነገር ፈጽሞ የሚመከር አይደለም። ጊዜውንና ሁኔታውን ያገናዘበ አይደለም። ሃገር በውጥረት ላይ ባለችበት ጊዜ እንዲህ ያለ መግለጫ ማውጣቱስ ለምን ተፈልጎ ነው? እንደውም  አንዱ አባላችን "ተው ይሄ ነገር ይቆይ” ብሏቸው እንደነበር፤ ነገር ግን ሳይሰሙት ተጣድፈው መግለጫውን እንዳወጡት ነው የነገረኝ። እንዳጋጣሚ ሆኖ መግለጫው በወጣ ማግስት ደግሞ መንግስት እንዲህ አይነት ነገር በህግ ያስጠይቃል የሚል መመሪያ ነው ያስተላለፈው። ሲጀመር አሁን የሽግግር መንግስት ለማቋቋም ምንም ተጨባጭ ምክንያት የለም።
የኛ ትልቁ ጥያቄ የነበረው ተፋላሚ ሃይሎች ጦርነቱን አቁመው፣ በጠረጴዛ ዙሪያ ይደራደሩ የሚል ነው። ድርድር ነው ጦርነቱን ሊያስቀር የሚችለው። ጦርነት እየተካሄደ የሚደረግ ድርድር ጦርነቱን ይቋጫል። በርካታ የዓለም ጦርነቶች መጨረሻ ላይ የቆሙት በድርድር ነው፡፡ ይሄ ነው እኛ የነበረን አቋም። የሽግግር መንግስት ግን በዚህን ወቅት ፈጽሞ የሚታሰብ አይደለም። ይሄን የፈለገ አሜሪካን  ሃገር  አስታራቂ ነኝ ሲሉ ከነበሩት ከእነ ፕ/ር ኤፍሬም ጋር መቀላቀል ነው ያለበት። ከዚያ በመለስ ግን ይህቺ ሀገር እንዲህ ያለ አውዳሚ ጦርነት ውስጥ እያለች እንዴት ነው  የሽግግር መንግስት ተብሎ የሚጠየቀው? እንዴት ቢታሰብ ነው? ከዚህ ይልቅ ብሄራዊ ውይይት፣ ድርድር ነው መጠየቅ ያለበት። መንግስትም በዚህ ጉዳይ ነው ቁርጠኛ አቋም መያዝ ያለበት።
በመግለጫው በግልጽ የሽግግር መንግስቱ የሚቋቋምበትን ሂደትና የሽግግር መንግስቱን መልክና ቅርጽ ጭምር እንደ ፍኖተ ካርታ የሚያስቀምጥ ነው፡፡ በፓርቲያችሁ ውስጥ  ከዚህ ቀደም እንዲህ ያለ መግለጫ  ለማውጣት የሚያስችል ምክክር ተደርጓል?
አልተደረገም። ፕ/ር መረራ ወደ ውጪ ሳይሄድ በፊት አንድ ያቀረብኩት ሃሳብ ነበር። ይኸውም፤ እስኪ መጀመሪያ ባለፉት ሁለት አመታት ያከናወናቸውን ተግባራት እንገምግምና ከዚያ በኋላ የዚህን ሃገር ፖለቲካ ሁኔታ አገናዝበን አንድ ጠቃሚ ሰነድ እናውጣ ብያቸው ነበር። ፕ/ር መረራ ሃሳቡን ተቀብሎ “በሁለት ሳምንት ጊዜ ውስጥ ሁላችሁም አንዳንድ ነጥቦች ይዛችሁ ኑ” አለና ወደ ስዊዘርላንድ ሄደ። ከዚያ በኋላ  በዚህ ዓይነት ጉዳይ ላይ ተወያይተን አናውቅም። ሌላው በመግለጫው የገረመኝ፣ ዋና ዋና ባለድርሻ አካላት የሚሳተፉበት የሽግግር መንግስት ይላል፡፡ እንዴ! እነማን ናቸው እነዚህ ዋና ዋና አካላት? ዋና ዋና አካላትን መለያ መስፈርቱ ምንድን ነው? እነማን ናቸው የዚህ የሽግግር መንግስት መሪ ተዋንያን?
እንዴት እርስዎ ም/ሊቀመንበሩ ሳያውቁ ፍኖተ ካርታ የሚያስቀምጥ መግለጫ ሊወጣ ይችላል?
አሳፋሪው ነገር እሱ ነው። እኔ አስቀድሞ እንዲህ ያለ መግለጫ ሊወጣ መሆኑን ባውቅ ኖሮ፣ የአዳማውን ስብሰባ እሰርዝና ቢያንስ በመግለጫው ላይ የሃሳብ ልዩነቴን አስቀምጥ  ነበር። የፖለቲካ አሻጥር ነው የሚመስለው፡፡ እውነቱን ለመናገር እዚያ ውስጥ ካሉ የስራ አስፈጻሚዎች በልምድ እበልጣለሁ። ይሄን የመሰለ መግለጫ እንዲወጣ የምፈቅድበት ምክንያት አይኖረኝም፤ የፖለቲካ ልምዴም አይፈቅድልኝም።
ሊቀ መንበሩ ፕሮፌሰር መረራስ ይሄን መግለጫ ያውቁት ይሆን?
እንደምገምተው ከሱ እውቅና ውጪ ይሄ መግለጫ የወጣ አይመስለኝም።
ኦፌኮ አሁን በምን ሁኔታ ላይ ነው ያለው? ማንስ ነው የሚመራው?
እውነቱን ለመናገር ኦፌኮ ድሮም  የአንድ ሰው ፓርቲ ነው። ፕ/ር መረራ ከተናገረ ሁሉም ነገር ያለ ተቃውሞ ይፈጸማል። ሌላው ከአስተያየት ያለፈ ድርሻ የለውም። አሁንም በአንድ ሰው የበላይነት የሚዘወር ፓርቲ ነው።
እርስዎ በፓርቲው አካሄድና የመግለጫ አወጣጥ ላይ ከፕ/ር መረራ ጋር አይነጋገሩም?
ሁለት ጊዜ ከሱ ጋር ለመነጋገር ጠይቄ አልተቻለም። አንዱ “ወደ  ምርጫ ያልገባሁት ኦነግ ስላልገባ ነው" ያለውን በተመለከተ ነበር። እንዴ! እኛ  ኦነግ ጫካ ሆኖ ምርጫ ስንሳተፍ የቆየን ነን እኮ። ለምንድን ነው #ኦነግ ስላልገባ ነው” ያልገባሁት ያለው? የትኛው ኦነግ ነው ምርጫ ያልገባው? በቀጄላ የሚመራው ነው? በዳውድ ኢብሳ የሚመራው ኦነግ ነው? ወይስ ኦነግ ሸኔ ነው? ለየትኛው ኦነግ ብለን ነው ምርጫ ያልገባነው? ይሄን ልጠይቀው እፈልግ ነበር።
እኛ የምንታወቅበት ዓለምም የኢትዮጵያ ህዝብም ተቀብሎት ድጋፍ የሚሰጠን የራሳችን አካሄድ ስለነበረን ነው። ይሄ አካሄድ ደግሞ ግልጽ ነበር። እኛ የመገንጠልን ጥያቄ ከኦነግ ጋር ተጋርተን አናውቅም። እኔም እዚህ ፓርቲ ውስጥ የገባሁት የኦሮሞ ችግር በኢትዮጵያ ማዕቀፍ ውስጥ ከሌሎች ብሄር ብሄረሰቦች ጋር ሊፈታ ይችላል የሚለውን አቋም ስለማምን ነው። ይሄን አቋም ከተውን እኔ እዚህ ፓርቲ ውስጥ የለሁም ብያቸው ነበር። ዛሬም የድርጅቴ የኦፌኮ ፕሮግራም፣ የኔም እምነት ይህ ነው። እገሌ የሚባል ፓርቲ ምርጫ አልገባም ተብሎ እንዴት እንደዚህ ያለ ውሳኔ ይወሰናል? ማን ነው ደግሞ ኦነግ ስላልገባ እኛ ምርጫ መግባት የለብንም ብሎ የወሰነው?
ፓርቲው እርስዎ እንዳሉት በአንድ ሰው  የሚዘወር ከሆነ እናንተ እንዴት ዝምታን መረጣችሁ? እንዴት ይህን መታገል አልቻላችሁም?
ይሄ የራሱ ብዙ ታሪክ አለው።  በኛ ስብሰባዎች ላይ ብዙ ጊዜ ፕሮፌሰሩ ከተናገሩ፣ “እርሳቸው እንዳሉት” የሚባል ነገር አለ። የፖለቲካ እውቀታችንም ይለያያል። በብዙ ልፋት የተመሰረተ ፓርቲ ነው። እያንዳንዱ እንቅስቃሴን በጥንቃቄ ለመያዝ ሲባል ብዙ ነገሮች ይተላለፋሉ። እኔ ሁሌ ትክክል ባልመሰለኝ ጉዳይ ላይ የሃሳብ ልዩነቴን አስመዘግባለሁ።
አሁን ባለው የኢትዮጵያ ተጨባጭ ፖለቲካዊ ሁኔታ እርስዎ ከሊቀ መንበሩ ጋር ግልጽ ልዩነት አለዎት?
አዎ አለኝ። ይሄ መግለጫ ካለ ፕ/ር መረራ እውቅና አልወጣም። ይሄን የመሰለውን መግለጫ እኔ በመጀመሪያ አይቼው ቢሆን ኖሮ በፍጹም አልስማማም ነበር።
በቀጣይ ታዲያ እርስዎ በኦፌኮ ውስጥ ምን ሚና ነው የሚኖረዎት?
አሁን እኔ የምጠብቀው የፓርቲውን መሪ ወደ ሃገር ቤት መመለስ ነው። ከዚያ በኋላ  ተነጋግረን የኦፌኮ አካሄድ የማይቃና ከሆነ፣ የራሴን ውሳኔዎች እወስናለሁ ማለት ነው።
እርስዎ ይሄን መግለጫ በግልጽ እየተቃወሙት ነው?
አዎ፤ ይሄ የኔ ብቻ ሳይሆን የፓርቲዬም አቋም አይደለም። የሽግግር መንግስት የሚል አቋም የለኝም። እንዲህ አይነት ውይይትም በድርጅታችን አላካሄድንም። ድርጅቱም አቋም አልያዘበትም። ይሄ መንግስት አሁን በስልጣን ላይ ነው ያለው። ይህን መንግስት እንዴት እበጠብጣለሁ ብለህ ትነሳለህ? እንዴት በዚህ ወቅት የሽግግር መንግስት ይታሰባል ነው ጥያቄዬ፡፡ እንዴት አንድ ፓርቲ፣ የሽግግር መንግስት ፍኖተ ካርታ ያወጣል? ይሄ ትልቅ ስህተት ነው።
ኦፌኮ አሁን ባለው የሃገሪቱ ሁኔታ ላይ ምን አቋም ነው ያለው?
ምንም ግልጽ አቋም የለውም። እንዲሁ የተወነባበደ ነው አቋሙ። ወይ ከእነዛ ጋር ቆሜያለሁ አይልም ወይ ከዚህ መንግስት ጋር ቆሜያለሁ አይልም፡፡ መንገዱ የጠፋብን  ነው የሚመስለው።
እርስዎ በግልዎትስ…..?
እኔ በግሌ ስብሰባ ላይ ያልኩትን አቋም ነው ያፀናሁት። ለህወሃት ምንም አይነት ሩህሩህ ልብ የለኝም። የጠላቴ ጠላት ወዳጄ ነው የሚል አካሄድ እኔ ጋር አይሰራም። እኔ አሁንም የምለው፣ ጦርነቱ እየተካሄደ መደራደር ይበጃል ነው። ዘላቂ ሰላም ሊመጣ የሚችለው በዚህ  መንገድ ነው።
የኦነግ ሸኔን ከህወሓት ጋር ማበር በተመለከተ እርስዎ ምን ይላሉ?
እኔ ስለሸኔ  ብዙም አላውቅም። እኔ የማውቀው አቶ ሌንጮ ለታን ነው። ህዳር ወር 1983 ናይሮቢ ላይ አግኝቼው ነበር፤ ያኔ አሁን ያሉት ችግሮች እንደሚመጡ ነግሬው ነበር። እነሱ ያወጡት የኦሮሞ ነጻነት ማረጋገጫ አካሄድ፣ ከሁሉም ብሄር ብሄረሰብ ጋር ሊያጋጭ እንደሚችል በወቅቱ ነግሬዋለሁ።
በኢትዮጵያ ማዕቀፍ ውስጥ ሆነን ነው ማግኘት ያለብንን ማግኘት ያለብን ብዬው ነበር። አሁን እነዚህ ዋና ዋና የኦነግ አንጋፋ መሪዎች ከዚህ መንግስት ጋር ናቸው። እና አሁን ጫካ ውስጥ ያሉት ምን ፈልገው ነው? እኔ ለእነዚህ ልጆች የምመክረው ቢኖር፤ ወደ አገር ውስጥ ገብተው በሰላም መታገላቸውን እንዲቀጥሉ ነው፡፡ ለኦሮሞ ህዝብ የሚበጀው ይኼ ነው። የኦሮሞ  ህዝብ ስንት ዓመት ነው በሰቆቃ ውስጥ  የሚኖረው? ዛሬም ህዝቡ በዚህ ምክንያት እየተጨፈጨፈ ነው። ለዚህ መፍትሔው  ወደ ሰላም መስመር ገብቶ ቁጭ ብሎ መነጋገር ነው፡፡ ዛሬ ጠመንጃ በማንሳት የሚደረግ እንቅስቃሴ፣ ማዕከላዊ መንግስቱን ከማስቸገር በቀር ዘላቂ መፍትሄ አያመጣም። እኔም ሆነ የኔ ድርጅት አሁንም የምናምነው፣ የኦሮሞ ህዝብ ጥያቄ፣ በኢትዮጵያ ማዕቀፍ ውስጥ መፍትሄ ሊያገኝ እንደሚችል  ነው።
ህወሓትና ሸኔ የመጣመራቸው ጉዳይስ?
እኔ አስቀድሜ እንዳልኩት ለወያኔ ምንም አይነት የሃዘኔታ ልብ የለኝም።
 ማንም አካል “ከወያኔ ጋር መጥቼ ለኦሮሞ እጠቅመዋለሁ” ቢለኝ መቼም አይገባኝም። ጥፍራቸውን ከነቀለ፣ ብልታቸው ላይ የውሃ ኮዳ ካንጠለጠለ፣  እናትን የልጇ አስክሬን ላይ አስቀምጦ ከተዛባበተ ወያኔ ጋር ዛሬ አብረን እንሰራለን ማለት ለኔ ትልቅ ስድብ ነው ። እኛ´ኮ ነን ይሄን መከራ የታገልነው። ፕ/ር መረራ በታሰረ ጊዜኮ አሜሪካ ነበርኩ፡፡
ልጄ “ተው አትሂድ” እያለችኝ ነው  “የያዝኩት ትግል ነው” ብዬ በወቅቱ የተመለስኩት። ፊት ለፊት‘ኮ ነው ወያኔን ስንታገለው የነበረው። ወያኔንና ተግባሩን እኛ ጠንቅቀን እናውቃለን። ስለዚህ ከወያኔ ጋር ማበር ማለት ለኔ ሞት ነው።

Read 5951 times