Tuesday, 07 December 2021 05:10

የጎንደር ዩኒቨርስቲ በህልውና ዘመቻው

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(0 votes)

  “ጦርነቱ ጠቅላይ ሚኒስትሩን ሳልሳዊ ምንሊክ ሊያሰኝ የሚችል ትልቅ አጋጣሚ ነው”
        “በህልውና ዘመቻው ኢትዮጵያውን እያደረጉት ያለው ርብርብ የሚደንቅ ነው”

          የጎንደር ዩኒቨርሲቲ በህልውና ዘመቻው ዘርፈ ብዙ ምላሽ እየሰጠ ይገኛል። ከዚህም በተጨማሪ በዩኒቨርስቲው ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ የክብር ዶክትሬት ዲግሪ ያገኙትን ዶ/ር ኢሌኒ ዘውዴ ገ/መድህንን የክብር ዶክትሬት ዲግሪ መሰረዙን ተከትሎ መነጋገሪያ ሆኖ ሰንብቷል። የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ ናፍቆት ዮሴፍ ከጎንደር ዩኒቨርስቲ ፕሬዚዳንት አስራት አፀደወይን (ዶ/ር) ጋር በህልውና ዘመቻው፣ ዩኒቨርስቲው በሰረዘው የክብር ዶክትሬት ዲግሪና በተያያዥ ወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ ሰፋ ያለ ቃለ ምልልስ አድርጋለች፡- እነሆ

        በአገሪቱ  ወቅታዊ ሁኔታ ዩኒቨርስቲያችሁ ዘርፈ ብዙ እንቅስቃሴዎች እያደረገ እንደሆነ ይደመጣል:: እስኪ ዋና ዋና የሚሏቸውን ያብራሩልኝ?
አገሪቱ ያለችበት ወቅታዊ ሁኔታ እጅግ አስቸጋሪ በመሆኑ እንደ ቀደምትና ትልቅ ተቋም ዘርፈ ብዙ ምላሽ ይጠብቅብናል። አሁን በዋናነት ያተኮርነው የማህበረሰብ አገልግሎት ላይ ነው።
ከማህበረሰብ አገልግሎቱ አንዱ የአርሶ አደሩን ምርት መሰብሰብ ነው። በተለይ ለህልውና ዘመቻው የዘመቱ አርሶ አደሮችን ሰብል የመሰብሰቡ ስራ በስፋት እየተሰራ ይገኛል። ከዚህ በተጨማሪ በጦርነቱ ከተለያዩ አካባቢዎች የተፈናቀሉ ወገኖችን የዩኒቨርስቲው ማህበረሰብ ከግሉ እያዋጣና ከማህበረሰቡ እያሰባሰበ፣ እነዚህን ተፈናቃዮች በመደገፍ ከፍተኛ ስራ እየሰራ ነው የሚገኘው።
በተለያዩ አካባቢዎች በመንቀሳቀስም ማህበረቡን የማንቃትና የማደራጀት ሥራም እየሰራን ነው ያለነው። አሁን በትክክል ይህ ያህል ነው ባልልም፣ በትንሹ ከ100 በላይ የዩኒቨርስቲያችን ሰራተኞች ማለትም መምህራን፣ ሰራተኞች፣ የጤና ባለሙያዎች ግንባር ዘምተው እየተዋጉ ይገኛሉ። ህብረተሰቡን በማንቃና በማደራጀት በኩል በተለያዩ አካባቢዎች የተሰማሩት የዩኒቨርስቲያችን ሰራተኞች ከ300 በላይ ናቸው።
እንደሚታወቀው የጎንደር ዩኒቨርስቲ የአስተዳደር ሰራተኛው፣ መምህራን፣ የሆስፒታል ሰራተኞች ተደምረው ወደ 11 ሺህ ስታፍ ነው ያለው። ከዚህ ቁጥር መካከል ከ4 ሺህ በላይ የሆነው የሆስፒታሉና የጤና ሳይንስ ኮሌጁ ሰራተኛ ነው። ይሄ ስታፍ አሁንም መደበኛ ሥራውን በቋሚነትና በትጋት እየሰራ ነው ያለው። መደበኛ ህክምናው አለ፣ በወቅታዊ ጉዳዩ ለህክምና የሚመጣው አለ፣ ታካሚን የመንከባከብ ስራውም ጥራቱን በጠበቀ መልኩ ቀጥሏል። የህክምና ተማሪዎችም ከግቢ አልወጡም፤ እየተማሩም ህሙማን እና በጦርነቱ የተጎዱትን በመንከባከብ ከፍተኛ እገዛ እያደረጉም ይገኛሉ። በአጠቃላይ በወቅቱ የሀገራችን ችግር ዩኒቨርስቲያችን ዘርፈ ብዙ ምላሽ እየሰጠ ይገኛል።
ከተናጠል ተኩስ አቁሙ በኋላ በሰሜን ጎንደር አካባቢ ዳባት ደባርቅና ጭና አካባቢ አሸባሪው ሃይል ብዙ ሰብአዊና ቁሳዊ ኪሳራ ማድረሱ ይታወቃል። የዩኒቨርስቲያችሁ ሆስፒታል በከተማው ብቸኛው እንደመሆኑ ቆስሎ የመጣውን በርካታ ሰው የማከሙን ጫና እንዴት ተወጣችሁት?
እንዳልሽው ጭና አካባቢ በነበረው ውጊያ ላይ ይህ አጥፊ ቡድን ከፍተኛ የሆነ ሰብአዊም ቁሳዊም ጉዳት አድርሶ ነው የሄደው። በጦርነቱ ሲሸነፍ ሲቪሉ አርሶ አደር ላይ ከፍተኛ በቀል  ነው የፈጸመው። ከብቶቻቸውን አርዷል፣ ገድሏል፣ ሌላውን ሀብት ንብረታቸውን አውድሟል። ከዚያ በከፋ መልኩ ከአንድ ቤተሰብ ሶስትና አራት ሰው እስከ መግደል የደረሰ ግፍና ጭካኔ ፈጽሟል። በአጠቃላይ የሰው ልጅ ይፈጽመዋል ተብሎ የማይታሰብ ከፍተኛ ጭካኔ የተሞላበት አፀያፊ ድርጊት ነው የፈጸሙት። ከግድያውና ከንብረት ውድመቱ በተጨማሪ የቻሉትን  ያህል ዝርፊያ ፈጽመው ህፃናትና ሴቶችን ደፍረው በምድር ላይ አለ የተባለውን ሁሉ ወንጀልና ጥፋት ሰርተው ነው የሄዱት። ይሄ እጅግ የሚያሳዝን ነው። እንግዲህ ሆስፒታሉ በጎንደር ከተማ ብቻ ሳይሆን በአካባቢውም ብቸኛ ሆስፒታል ነው ለማለት እችላለሁ። በቅርብ ይገኛል የሚባለው ዳባት ሆፒታልም አዲስና በርካታ መሰረተ ልማቶች ያልተሟሉለት ነው። ስለዚህ አብዛኛው ጫና ሆስፒታላችን ላይ ነው የወደቀው። ይህንን ጫና ለመቋቋም ቀደም ሲል በ1983 ዓ.ም ከነበረው ጦርነት የተወሰደ ልምድ አለ። በወቅቱ ከነበሩ ታሪኩን ከሚያውቁ ሰዎች ጠይቀን የነበረውን ሂደት አይተን ነበርና በዚያን ዘመን ቆርቆሮ በቆርቆሮ ቤት ተሰርቶ ነበር ህክምና የሚካሄደው። ያም ሆኖ ከፍተኛ ጫና  እንደነበር ሲነግሩን፣ እኛስ ከዚያ ምን እንማራለን በሚል በ2013 ጥቅምት 24 ጦርነቱ ከተጀመረ አንስቶ  እንደ አንድ ትልቅ ዩኒቨርስቲ እንደገናም እንደ አንድ የማስተማሪያ ሆስፒታል ምን ይጠበቅብናል ብለን ከጥቅምት 25 ቀን (ጦርነቱ በተጀመረ ማግስት) ጀምሮ ነው ዝግጅት የጀመርነው። ለዚህ ሊያገለግሉ የሚችሉ የህክምና መሳሪያዎች ማዘጋጀት፣ መድሃኒቶች እንዲመጡ የማድረግና ለማገገሚያ የሚሆኑ ክፍሎችን የማዘጋጀት ሥራ ስንሰራን ቆየን።  ያው ጦርነት እንደመሆኑ አብዛኛው ጉዳት ከአጥንት ስብራት ጉዳት ጋር የተያያዘ ነው። ህክምናው ከተደረገላቸው በኋላ ለማገገም ብዙ ጊዜ ይወስዳል። ለዚህ ደግሞ ማገገሚያ ክፍል ያስፈልጋል። ይህን የማገገሚያ ስፍራ ማዘጋጀት አንዱና ትልቁ ሥራ ነበር። የተለያዩ ቦታዎችን ፈለግን አየን፤ ግን የተሻለ ሆኖ ያገኘነው ግንባታው ያልተጠናቀቀ ህንፃ ነበረን። እሱን የመብራት፣ የውሃ፣ የመታጠቢያ ክፍሎች፣ የውሃ ማጠራቀሚያ ጋን የለውም ነበር። ይህንን በሁለትና በሶስት ቀናት ውስጥ ከተቋራጩ ጋር  ተነጋግረን እንዲያልቅ በማድረግ አዘጋጀን። ይህም በወቅቱ የነበረውን ያንን ትልቅ ጫና ለመቋቋም ረድቶናል። አጠቃላይ ቅድመ ዝግጅቱ ነው ሊፈጠር ከሚችለው ችግርና ጫና የታደገን። እንግዲህ  የወገን ጦር ቁስለኛ ብቻ አይደለም የሚመጣው፡፡ በጠላትነት ሲወጋንም የነበረው ሲመጣም የህክምና ስነ-ምግባሩ በሚያዘው መንገድ ያለ አድልኦ አክመን ወጥተዋል። በጭና ጦርነት ግን በአብዛኛው ስናክም የነበረው አርሶ አደሩን ነው። ቀደም ብዬ እንዳልኩት ጭና አካባቢ አጥፊው ሃይል ሲሸነፍ ብዙ ጉዳት ያደረሰው ንፁሃን ላይ ስለነበር ነው። ከወገን ጦር በላይ ንፁሃኑ ተጎድተው ወደ ሆስፒታላችን በብዛት መጥተዋል ጫናው በቀላሉ የሚገለጽ አይደለም። እኛ የጠላት ጦር ተመትቶ ሲመጣ ያለ አድልኦ እያከምን እነሱ ምግብና መጠጥ ሲቀርብላቸው በመጠራጠር “ቀምሳችሁ ስጡን” ሁሉ ይሉ ነበር። ምክንያቱም የላካቸው ቡድን “አማራ ጠላት ነው አጥፉት” ብሎ ነው።  በአጠቃላይ በሆስፒታላችን  ላይ ወድቆ የነበረውን ጫና ለማገዝ ከዩኒቨርስቲያችን ማህበረሰብ በተጨማሪ የጎንደር ከተማ ወጣቶች፤ ታካሚ ከቦታ ቦታ በማንቀሳቀስ፣ በማጠብ፣ በማብላትና በማጠጣት፣ የታካሚ ፀጉር በማስተካከል ጭምር ከፍተኛ አገልግሎት ሲሰጡ ነበር። ጫናው ቀላል አልነበረም። ነገር ግን በከተማው ህዝብ፣ በከተማ አስተዳደሩ፣ በዩኒቨርስቲያችን ማህበረሰብ፣ በሀገር ውስጥም በውጪም ባሉ ወገኖች ድጋፍ አገልግሎት ሳናጓድል እዚህ ደርሰናል። በዚሁ አጋጣሚ ሁሉንም በዩኒቨርስቲውና በራሴ ስም ላመሰግናቸው እወዳለሁ።
ሌላው ዩኒቨርስቲያችሁ በወልቃይት፣ በደቡብና ሰሜን ጎንደር ህውሃት ያደረሰውን የዘርጭፍጨፋና አጠቃላይ የሀብት ውድመት በተመለከተ ጥናት አስጠንታችሁ ማጠናቀቃችሁን ሰምቻለሁ ከዚህ ቀደምም በማይካድራ የደረሰውን የዘር ተኮር ጭፍጨፋ ሰርታችሁ ለሰብአዊ መብት ኮሚሽን መስጠታችሁንም አስታውሳለሁ። እስኪ ያብራሩልኝ?
እንግዲህ ጥናቱ ከህግ ማስከበርና ከህልውና ዘመቻው ቀደም ብሎ በተለይ በወልቃይት ህዝብ ላይ የተሰራው አጠቃላይ አሻጥር ምን ይመስላል? ባለፉት 40 ዓመታት ህወኃት በወልቃይት ህዝብ ላይ የሰራው ኢኮኖሚያዊ፣የጤና የህዝብ ምጥጥን (ዲሞግራፊ) አሻጥር ምን እንደሚመስል ተጠንቷል፡፡ ህወኃት ሀገሪቱን ሙሉ በሙሉ ከመቆጣጠሩ በፊትም ቀደም ብሎ የያዘው አካባቢ እንደመሆኑ አሻጥሩ የሚጀምረው ከዘመነ መንግስታቸው በፊት ከደደቢት ነው፡፡ ወልቃይትን ወደ ራሳቸው የማካለል እቅዳቸውን ለማሳካት ብዙ አሻጥር ተሰርቷል፡፡ በጤና በትምህረት የአካባቢው ህዝብ እንዳይጠቀም በማድረግ ሲያደርሱት የነበረው በደል ሁሉ በዚህ ጥናት ተካትቷል፡፡ ከዚያ በተጨማሪ በሀገራችን በጣም  አሰቃቂ የሚባለው የዘር ጭፍጨፋ  በማይካድራ ላይ መድረሱ በጥናቱ ተካትቷል፡፡ ከ1 ሺህ 600 በላይ የሆኑ ወገኖች በአጥፊው ቡድን ስለመገደላቸው በማስረጃ የተረጋገጠ ነው፡፡ የአካል ጉዳት የደረሰባቸው በርካታ ወገኖች አሉ፡፡ እነዚህን ወገኖች ዩኒቨርስቲያችን በተለያየ መንገድ እያገዘ ይገኛል፡፡ ወላጆቻቸውን ያጡ ህፃናትም አሉ። በአጠቃላይ በአካባቢው የደረሰውን አሰቃቂ ነገር ስንመለከት፤ ከእነዚህ ሰዎች ጋር በእርግጥስ አብረን ኖረናል ወይ? ይሄ ሁሉ ጭካኔና አረመኔነትስ ከየት መጣ ስንል ጠይቀናል፡፡ ይህንን በሀገራችን ታሪክ ላይ ጥቁር ነጥብ ጥሎ ያለፈ ድርጊት፣ ጥናቱ ተጠናቅቆ አልቆ ወደ እንግሊዝኛ እየተተረጎመ ነው፡፡ ተተርጉሞ ሲጠናቀቅ ይህን እኩይ ተግባር አለም እንዲያውቀው እናደርጋለን፡፡ ከዚህ ቀደም በተቆራረጠ መልኩ ለሚዲያም ለሰብአዊ መብት ኮሚሽንም እንዲደርስ አድርገናል፡፡
በሌላ በኩል ደግሞ በነፋስ መውጫ መስመር ገብተው እንዲወጡ ከተደረገና ከተሸነፉ በኋላ የደረሰውን መከራና ግፍም አስጠንተናል፡፡ በዚህም ሥፍራ የተፈፀመው ከማይካድራው ጋር ተመሳሳይ ነው፡፡
መጠኑ ይለያያል እንጂ የደረሰው ውድመትና ጉዳት እጅግ የሚያሳዝን ነው፤ ሴቶች ተደፍረዋል ተገድለዋል፡፡ ብዙ ሀብትና ንብረት ወድሟል፤ ብዙ መሰረተ ልማትም ተዘርፏል፤ የሆስፒታል የታካሚ ታሪክ ሳይቀር አቃጥለዋል። የተማሪ ሮስተር እንዲቃጠል አድርገዋል፡፡ ይሄ አይን ያወጣ ክፋት እንጂ የሚጠቅማቸው አይደለም፡፡ ግን ደግሞ የታካሚ ታሪክ መጥፋት ታካሚዎችን እንደሚጎዳ ያውቃሉ፡፡ የላብራቶሪና የህክምና መሳሪያዎችን መዝረፋቸው ሳያንስ የታካሚን ታሪክ ማቃጠል ምን የሚሉት ድርጊት እንደሆነም አይገባኝም፡፡ ይሄ የእነሱን የከፋ ስብዕና የሚያሳይ ነው፡፡ በጭና በኩልም እንዲሁ በተመሳሳይ ከደባርቅ ዩኒቨርስቲ ጋር በመሆን ተጠንቷል፡፡ እነዚህ ሶስቱም ማለትም በጭናና በንፋስ መውጫ፣ በወልቃይት ከ40 ዓመት በፊት ጀምሮ የተሰራው አሻጥርና የማይካድራው የዘር ጭፍጨፋ ተጠንተው ተጠናቅቀው ወደ እንግሊዝኛ እየተተረጎሙ ይገኛሉ። ይህ ሲጠናቀቅ ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ  እንዲያውቀው  የሚደረግ ይሆናል፡
ከማህበረሰብ አገልግሎቱ፣ከህክምናውና ከጥናቱ በተጨማሪ ለህልውና ዘመቻው ገንዘብ በማሰባሰቡም በኩል አስተዋፅኦችሁ ከፍተኛ እንደሆነ ይነገራል፡፡ ባለፈው እሁድ በሸራተን አዲስ ሆቴል የጎንደር ከተማ አስተዳደር ባዘጋጀው የገቢ ማሰባሰቢያ ፕሮግራም ላይ ድጋፍ አድርጋችኋል አይደል?
እንግዲህ በዚህ የህግ ማስከበርና የህልውና ዘመቻ እንዲሁም ቀደም ሲል በነበረው የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ እጅግ የመተዛዘንና የመደጋገፍ ሁኔታ የታየበት ጊዜ ነው።  ኮሮና በገባበት ሰዓት በሀገር ውስጥም ከሀገር ውጪም በርካታ ወገኖች ይህንን ወረርሽኝ ለመከላከል የሚያስችሉ ግብአቶችን፣የህክምና መሳሪያዎችንም ሆነ አስፈላጊ ነገሮችን በመላክ ከፍተኛ ርብርብ አድርገዋል። አሁንም በህልውና ዘመቻው በተመሳሳይ ቀደም ሲል አይተነው ከምናውቀው በላይ ትብበር የተደረገበት ከፍተኛ ፍቅር የተገለፀበትና እዚህም ላለነው ትልቅ የሞራል ልዕልና እንድናገኝ ያስቻለ ድጋፍ ነው የተደረገው። አሁንም ጭምር ከፍተኛ የህክምና መሳሪያዎች፣ በርካታ መድሃኒቶች አልባሳት እየተላከልን ነው ያለው፡፡ ይህ ደግሞ አሁን መንግስት ካለበት ጫና አኳያ ቀላል የማይባል እገዛ ነው፡፡ ከዚህ አኳያ ተወላጁም፣ እዚህ ጎንደር ሲሰራ የነበረውም፣ እና በተለያየ መንገድ በራሱ ተነሳሽነት ከሚያግዘው በተጨማሪ፣ እንደዚህ ዓይነት የገቢ ማስገኛ መርሃ ግብሮችን ማመቻቸት ደግሞ ከእኛ የሚጠበቅ ነው፡፡ ባለፈው እሁድ አዲስ አበባ በሸራተን ሆቴል የተካሄደው ፕሮግራምም፣ በጎንደር ከተማ አስተዳደር አነሳሽነት፣ አዲስ አበባ ላይ የሚገኙ ተወላጆ፣ ተቆርቋሪዎችና ከእኛ ዩኒቨርስቲ ጋር በመተባበር ነው የተዘጋጀው። በዚህ መርሃ ግብር ላይ በርካታ ወገኖች ተገኝተዋል፤ የተሰበሰበውም ቀላል የሚባል ገንዘብ አይደለም፡፡
እቅዱ ከ100 ሚ ብር በላይ ለማሰባሰብ ነበር ስንት ተገኘ?
ወደ 164 ሚ ብር ቃል ተገብቷል፡፡ ይህ ገንዘብ የሚውለው ለህልውና ዘመቻው ብቻ ሳይሆን በርካታ ወገኖች የተፈናቀሉ አሉ፡፡ ከሀብት ንብረታቸውና ከቀያቸው ተፈናቅለው በችግር ላይ ላሉትም ይውላል፡፡ ገጎንደር ዩኒቨርስቲም 5.ሚ ብር ለመደገፍ ቃል ገብቷል ቀሪው ስራ ቃል የተገባውን ገንዘብ በአፋጣኝ ሰብስቦ  ለአላማው ማዋል ነው፡፡ ርብርቡ በጣም የሚያስደስት ነው፡፡ ህዝቡ በኑሮ ውድነት በተለያዩ ወጪዎች እየተሰቃየም ቢሆን የ1 ወር ደሞዝ ሳይቀር የሰጠ አለ። ይህን ስንመለከት ህዝቡ እውነትም የህልውና ዘመቻ እውነትም ኢትዮጵያን የማስቀጠል ጉዳይ መሆኑን መረዳቱን ያሳየናል፤ እጅግ አበረታች ነው፡፡ ከጎንደርና አካባቢው ተወላጆችና ተቋማት ባለፈ እንደነዋቻሞ ዩኒቨርስቲ፣ሀዋሳ ዩኒቨርስቲና የተለያዩ ዩኒቨርስቲዎችም አጋርነታቸውን እያሳዩ ይገኛሉ፤ ቃል ያልገቡትም ቢሆኑ ከድህረ ጦርነት በኋላ ያለው ማህበራዊ ጫና ከፍተኛ ስለሚሆን ርብርቡ መቀጠል አለበት ብዬ አምናለሁ፡፡
እንደ አንድ ምሁርም ይሁን አንድ ትልቅ ዩኒቨርስቲን እንደሚመራ ሀላፊ አሁን የገባንበትን የህልውና ጦርነት፣የጠቅላይ ሚኒስትሩን ወደ ግንባር መዝመትና የጦር ሀይሉን መምራት እንዴት ነው የሚገልጹት?
እንግዲህ ጦርነቱ በግልጽ እንደሚታየው መነሻው ከህወኃት ቡድን ይሁን እንጂ ከጀርባው በርካታ ሀያላን መንግስታትና ሀገራት እንዳሉበት የተገነዘብንበት ጦርነት ነው። ስለዚህ አሁን የገባንበት ጦርነት ውስጣዊ ብቻ ሳይሆን ውጫዊም ነው። የቅኝ ግዛት መልኩን ቀይሮ  ኒዮኮሊያኒስቶች ተባብረው የመጡበት ጦርነት ነው፡፡ በእኔ እይታ ጦርነቱ ከአድዋ ጦርነት የሚስተካከል  ነው። በአድዋ ጦርነት የጣሊያን ወራሪ ሀይል መጣ፣ ከውስጥ ባንዳዎችን ተጠቀመ አልሆነለትም፤ ተሸንፎ ወጣ፤ አሁንም በተመሳሳይ እነዚህን ባንዳዎች (ህወኃትን) መሳሪያ በማድረግ፣ ጦርነቱ ከውጭ ሀይሎች ጋር እየተካሄደ ያለ ነው፡፡ እነ ሱዳን፣ ግብጽ፣ አሜሪካና ሌሎች ምዕራብባውያን ጦርነቱን በስነ ልቦና፣በተሳሳተ መረጃ፣ ለአሸባሪው ቡድን የስለላ እና ቴክኖሎጂ ድጋፍ በመስጠት ዘመቻ የተከፈተብን ወቅት ነው፡፡ ለዚህ ነው ጦርነቱ ከአድዋ ጦርነት ያልተናነሰ ነው የምለው፡፡ ይህን ጦርነት በድል መወጣታችንን ከአድዋ ድልም በላይ በደማቁ ልናከብረው የሚገባ ነው፡፡ መሪውም ሳልሳዊ ምንሊክ ሊባሉ የሚችሉበት ትልቅ አጋጣሚ ነው ብዬ ነው የምወስደው፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትራችን በአሁኑ ወቅት ጦሩን በግንባር እየመሩ  ትልቅ ተጋድሎ እያደረጉ ነው፡፡ ቀላል የማይባል ታሪክ ነው፡፡ አሁን ላይ በውጭ ሚዲያዎችም እንደምንሰማው ለስልጣን ብሎ ሳይሆን ለሀገሩና ለህዝቡ ክብር የቆመ መሪ ስለመሆኑ እየዘገቡ ነው የሚገኘው፡፡ በአጠቃላይ አሁን ያለንበት የህልውና ጦርነት፣ ሀገርና ትውልድ የማስቀጠልና ያለማስቀጠል ጦርነት ስለሆነ በድል መወጣት ምንም አማራጭ የሌለው ጉዳይ ነው፡፡ ደግሞም እንወጣዋለን፤ እናሸንፋለን። ኢትዮጵያዊያን እያደረጉት ያለው ርብርምም በጣም የሚደነቅ ነው፡፡ አንዳንድ ጊዜ ክፉ ነገር ሲገጥመን ወደ ጥሩ አጋጣሚም መቀየር ጥሩ ነው፡፡ ይህ ጦርነት ሲመጣ እስከዛሬ የተሰራብን መከፋፈል፣ የጎሪጥ መተያየትና እርስ በእርስ መጠራጠር ተወግዶ ኢትዮጵያዊያን ሁሉ ለህልውና በአንድ ላይ የቆምንበት ትልቅ አጋጣሚ ተፈጥሯል፡፡ ከጦርነቱም መጠናቀቅ በኋላ አሁን የቆምንበትን አንድነት አጠናክረን ማስቀጠል የሚጠብቀን የቤት ስራችን ይሆናል፡፡
ሌላውና ዋናው ጉዳይ የጎንደር ዩኒቨርስቲ በ2005 ዓ.ም በዩኒቨርስቲው የመጀመሪያውን የክብር ዶክትሬት ዲግሪ ለዶ/ር እሌኒ ዘውዴ ገብረ መድህን መስጠቱ ይታወቃል። ህዳር 21 ቀን 2014 ዓ.ም ግን ከግለሰቧ ይህንን የክብር ዶክትሬት ዲግሪ መቀማቱን ተከትሎ መነጋገሪያ ሆኗል። የክብር ዶክትሬቱን ስትሰርዙ የጠቀሳችሁት የከፍተኛ ትምህርት አዋጅም አለ። እስኪ ለግንዛቤ የክብር ዶክትሬት ዲግሪ አሰጣጥ ምን ይመስላል የሚለውን ይንገሩኝ?
የክብር ዶክትሬት የሚሰጠው ለተቋም፣ለሀገር ወይም ደግሞ አንድ ሰው ለአለማቀፉ ማህበረሰብ በሙያው ለሚያበረክተው የላቀ አስተዋፅኦ ነው፡፡ ይህ  የክብር ድግሪ አንድ ሰው በተሰማራበት ዘርፍ ማህበረሰቡን ሊጠቅም የሚችል ሙያዊ አስተዋፅኦ ሲያበረክት ነው የሚሰጠው፡፡ የአሰጣጥ ሒደቱም የዩኒቨርስቲው ሴኔት እጩዎችን የሚያቀርቡ አካላት ይሰማል፡ እነዚህ የተሰየሙ ቋሚ ኮሚቴዎች ከሁሉም ኮሌጆችና የተለያዩ አካላት ጥቆማዎችን ይቀበሉና ካቀረቡት ጥቆማዎች ውስጥ ሚዛን ሊደፋ የሚችል ከበቂ ማስረጃ ጋር ለዩኒቨርስቲው ሴኔት ያቀርባሉ፡፡ ሴኔቱ ደግሞ የቀረበውን ዕጩ መርምሮ ያጸድቃል ሂደቱ ይሄን ይመስላል፡፡ የዩኒቨርስቲው መተዳደሪያ ደንብ አለው “ዩኒቨርስቲ ሴኔት ሌጂስትሌሽን” የምንለው ይሄ ትልቁ የዩኒቨርስቲ መተዳደሪያ ደንባችን ነው፡፡ ከዚያም በተጨማሪ እንደ ሀገር የከፍተኛ ትምህርት ተቋም አዋጅ 1152/ 2011 የሚባል፣ አሁን እየተጠቀምንበት ያለ አዋጅ ነው፡፡ በዚህ አዋጅ በተሰጠን ስልጣን መሰረት ነው የምናከናውንው፡፡ ይህ አዋጅ ዩኒቨርስቲዎች ሊያከናውኗቸው የሚገቡ ዝርዝር ሁኔታዎች የተቀመጠበትና በሚኒስትሮች ምክር ቤት የወጣ አዋጅ ነው፡፡ ከተሰጡን ዝርዝር ተግበራት አንደኛው “የዩኒቨርስቲ ሴኔት፣ ዩኒቨርስቲው የሚሠጠውን ዲግሪ ይሰጣል ወይም ይሰርዛል የሚል ነው፡፡
ዩኒቨርስቲያችሁ የዶ/ር እሌኒን የክብር ዶክትሬት ዲግሪ መሰረዝን አስመልክቶ ባወጣው መግለጫ፤ “የክብር ዶክትሬት ዲግሪ የሚሰጠው ቀደም ሲል ለሰራው አስተዋፅኦ ብቻ ሳይሆን ወደፊትም ለሚያበረክተው አስተዋፅኦ ጭምር ነው” ይላል። ከዚህ አንጻር ዶ/ር እሌኒ የክብር ዶክትሬት ዲግሪያቸውን የተቀሙበትን ሁኔታና በዚሁ ጉዳይ አለም አቀፍ ተሞክሮዎችን አብረን ብናነሳስ?
 ጥሩ ጥያቄ ነው። እንዲህ የክብር ዶክትሬት አሰጣጥ ከሞላ ጎደል ዓለማቀፋዊ ነው። ብዙ መሰረታዊ የሆነ ልዩነት ሊኖረው አይችልም።
ወደ ዶ/ር እሌኒ ጉዳይ ስንመጣ  እንደተባለው በ2005 ዓ.ም ለሀገራችን ኢኮኖሚ በተለይ የአርሶ አደሩን ህይወትና የውጭ ምንዛሬን በማሳደግ ላበረከቱት አስተዋጽኦ፣ ዩኒቨርስቲው ቀደም ሲል በጠቀስኩት ሂደት አልፎ የተሰጠ የክብር ዶክትሬት ነው፡፡ ይህን የክብር ዶክትሬት የተቀበለ ሰው ቢያንስ ከዚህ ቀደም ሲሰራቸው የነበሩትን ማህበረሰባዊ አገልግሎት መጠበቅ አለበት፡፡ የክብር ዶክትሬቱ በመጨመሩ ደግሞ የበለጠ ተበረታትቶ አገርና ህዝብን እንዲያገለግል ታስቦ የሚሰጥ ነው፡፡ ስለዚህ ላለፈው እውቅና ነው፡፡ ይህን ያገኘ ሰው የበለጠ ትጋት ይጠበቅበታል እንጂ ወደ ኋላ ተመልሶ ማህበረሰቡንና አገርን የሚጎዳ ድርጊት ላይ መሳተፍ አይጠበቅበትም ማለት ነው። ከዚህ አኳያ  ዶ/ር እሌኒ በድብቅ በተካሄደውና የሰላምና ልማት ማዕከል የተባለው ድርጅት  ባዘጋጀው የበይነ መረብ ስብሰባ ላይ የተናገሩት ነገር አለ። ይህ ከተሰማ ጊዜ ጀምሮ ዩኒቨርስቲያችን እንደ አንድ ባለድርሻ አካል ጉዳዩን በጥልቀት ሲመረምረው ቆይቷል፡፡ በህግ ያለውን አንድምታ የሚያጣሩ ባለሙያዎች መድበን የንግግሩ ይዘት ምን ይመስላል? የሚለውን ባለሙያ ጭምር እንዲታይ ስናደርግ ከቆየን በኋላ ህዳር 21 ቀን ባደረግነው ውይይት የተመደበው አጥኚ ቡድን የንግግሩን ሂደትና ይዘት ካዳመጠ በኋላ በዋናነት የዩኒቨርስቲው እሴቶች የምንላቸውና በዩኒቨርስቲው የልማት እቅድ ላይ የተዘረዘሩ አሉ፡፡ ለምሳሌ አንደኛው “ፕሮፌሽናሊዝም” (ለሙያ ታማኝ መሆን) የሚል ነው። ይሔ አንደኛውና ትልቅ ቦታ ያለው እሴት ነው። ከዚህ አንጻር ዶ/ር እሌኒ በድብቅ ባደረጉት ንግግር፣ በሙያቸው ታማኝ ሆነው አልተገኙም፡፡ እሳቸው በድብቅ በተደረገው መድረክ ላይ መሳተፍ አልነበረባቸውም- ለሀገር ለወገን ብለው መስራት ስለሚጠበቅባቸው፡፡ ሁለተኛው ነገር፤ አንድ አይነት አስተሳሰብ ካላቸው አካላት ጋር ነው ሲሳተፉ የተገኙት፡፡  ያ ማለት አድልአዊነት ፈፅዋል ማለት ነው፡፡ ሁሉም እዛ ላይ ሲያንጸባርቁ የነበሩት ህወኃትን የሚደግፍና በሀገር ላይ ችግር እየፈጠረ ያለን ቡድን ስለመደገፍ፣ ከዚያ ድህረ ዶ/ር ዐቢይ ስለሚመጣው ኢኪኖሚና ተያያዥ ጉዳዮች ነው ግለሰቧ ሲናገሩ የነበሩት፡፡ ስለዚህ ሙያዊ ግዴታቸውን አልተወጡም አድልአዊነት አለ፡፡ ያንጸባረቁትም ሀሳብ ሀገርንና ህዝብን የሚጠቅም አይደለም፡፡ የኢትዮጵያን ህዝብ ፍላጎትም የሚያንጸባርቅ አልነበረም ወይም ደግሞ የህዝብ ውክልና አልነበረውም የሚለውን አረጋግጠናል፡፡ ይህ ለህዝብ የሚጠቅም ካልሆነ ደግሞ፣ ተቋማችን ሰምቶ ድ ላይ ሴኔቱ ደረሰ፡፡ በዚህም ምክንያት ለግለሰቧ ሰጥተነው የነበረውን ዲግሪ እንዲሰረዝ አድርገናል፡፡ ይህን ስናደርግ የክብር ዶክትሬት መስጠት የተለመደና ቀደም ያለ ታሪክ አለው፡፡ የመጀመሪያውን ዶክትሬት ዲግሪ አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ይመስለኛል የጀመረው፡፡ ከዚያ ቀጥሎ እኛን ጨምሮ ብዙ ዩኒቨርስቲዎች እየሠጡ ይገኛሉ፡፡
ለእኛ ዶ/ር እሌኒ በዩኒቨርስቲያችን የ59 ዓመታት ታሪኩ ውስጥ የክብር ዶክትሬት የሰጣቸው የመጀመሪያ ሰው ነበሩ፡፡ እንዳለመታደል ሆኖ ከላይ በተገለፀው ምክንያት ተሰርዞባቸዋል ማለት ነው፡፡ ለሀገራችን ዲግሪን በመሰረዝ የመጀመሪያዎቹ ልንሆን እንችላለን ነገር ግን በሌላው ዓለም  የተለመደ ነው፡፡ ለምሳሌ የቀድሞ የአሜሪካ ፕሬዝዳንት የዶናልድ ትራምፕን የ2020ን ልናነሳ እንችላለን። ትራምፕ እስካሁን አምስት የክብር ዶክትሬት ነበሯቸው፤ ከአምስቱ የቀራቸው አንድ ብቻ ነው፡፡ ሌላው ተሰርዟል፡፡ እነዚህ የክብር ዶክትሬቶች የተነሱባቸው የምርጫ ውጤት ባለመቀበላቸው ደጋፊዎቻቸው አመፅ አስነስተው ብዙ ችግር ተፈጥሯል፡፡ በዚህ ምክንያት የዋሽንግተን ዩኒቨርስቲ የቬንሴሊቤኒያ ዩኒቨርስቲም እና ሌሎችም አንስተዋል፡፡ ትራምፕ የህዝብን ድምጽ ሊቀበሉ አልቻሉም የምርጫ ውጤትን አልተቀበሉም መነጠቅ አለባቸው ብለው ነው የቀሟቸው፡፡ አሁን አንድ ብቻ ነው የቀራቸው፡፡ ሌሎችም አሉ ኬኔት ዩኒቨርስቲና ሌሎች ዩኒቨርስቲዎች አርቲስት ቢል ኮስቢ ወደ 50 የክብር ዶክትሬት ዲግሪ ነበረው በፆታዊ ጥቃትና በአደንዛዥ ዕፅ ዝውውር ምክንያ ከ50ው 20 ው ተነስቷል፡፡ በርካታ ምሳሌዎችንም ማንሳት እንችላለን፡፡
በስተመጨረሻ የሚሉት  ነገር ካለ ዶ/ር …?
በመጨረሻ ማለት የምፈልገው በውጭም በሀገር ቤትም ለሚገኙ መላው የሀገራችን ህዝቦች የገጠመንን አገራዊ ሁኔታ ውስጣዊ፣ ብቻና ቀላል አድርገው እንዳያዩና ይህን ለመወጣት የሁሉም ርብርብ እንደሚያስፈልግ መግለጽ     እወዳለሁ፡፡ የሁላችንም ሚና አስፈላጊና የማይተካካ በመሆኑ ለሀገራችን ህልውና ሁላችንም እናስፈልጋለን። የጦርነቱ ግንባር ብዙ ነው፡፡ በቀጥታ ግንባር ላይ ያለው ውጊያ አለ፣ ከድህረ ጦርነቱ በኋላ ልንሸፍናቸውና ልንጠግናቸው የሚገቡ በርካታ ቀዳዳዎች አሉ፡፡ ለሰራዊቱ ስንቅ በማዘጋጀት፣የዘማች አርሶ አደሮችን ሰብል በመሰብሰብ በጦርነቱ የደከመውን ኢኮኖሚ እንዲያገግም በማድረግ ሁሉም መረባረብ አለበት፡፡ በዚህ አጋጣሚ ዲያስፖራው ማህበረሰብ ሊመሰገን ይገባል- እያደረጉ ላሉት አለም አቀፍ  ዲፕሎማሲያዊ ተፅዕኖ፣ የገንዘብና የቁሳቁስ ድጋፍ። ይህ ተጠናክሮ መቀጠል አለበት፡፡ ይህንን ርብርብ ካደረግን ጦርነቱን በአጭሩ ቋጭተን፣ ወደ ልማታችን መመለስ እንችላለን፡፡



Read 1449 times