Monday, 06 December 2021 00:00

“ኢትዮጵያ እጆችዋን ወደ እኛ ትዘረጋለች!”

Written by  ነፃነት አምሳሉ
Rate this item
(0 votes)

  "--ነገሩ የምርጫ ጉዳይ አይደለም፡፡ የመወሰን ግዴታ ነው፡፡ ያም ሃቅ በዚህ አጣብቂኝ መሀል ኢትዮጵያ እጆችዋን ወደ እኛ ዘርግታለች፡፡ ዛሬ ሴረኛው ከሀቀኛው÷ እውነተኛው ዜጋ ከአስመሳዩ÷ ገብሱ ከገለባ የሚለይበት የታሪክ ምእራፍ ላይ ደርሰናል፡፡ ሀገርን ማዳን የወቅቱ ጥያቄ ሆኗል፡፡--"
           
             ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ በጫካ የተሸፈነውን ነፋሻማውን የምኒልክ ቤተ መንግስት ለቀው በረሃ ከገቡ ሰነባበቱ፡፡ እንደ ሀገር ነፍስ ውጭ ነፍስ ግቢ ላይ ነን፡፡ ገመዶች ሁሉ ተወጥረው ከርረዋል፡፡ ፍርሃት ከብቦናል፡፡ ድንጋጤ ወድቆብናል፡፡ ስንራመድ ዙርያችንን መጠራጠር ጀምረናል፡፡ የገዛ ጥላችን ከአካላችን ይልቅ ገዝፎ ሲታየን እንደ ድንቢጥ በርግገናል፡፡ በሰሜኑ የሀገራችን ክፍል የተቀሰቀሰው ጦርነት ዳፋው ድሆ ድሆ ደጃችን እንደ ጎረምሳ ያፏጭብናል፡፡
ኃይል እንጂ ማስተዋል የጎደላቸው ኃያላን ሀገራትም በሀገራችን ላይ ለመዶለት የጽዋ ማህበር ከመሰረቱ ሰነባብተዋል፡፡ የጥጋብ ግስታቸውን ሲያቀረሹብን፣ ነውርና ይሉኝታቸውን በጠራራ ፀሐይ ጥለውታል፡፡ እንደ  ልጅነታችን ዘመን የቤት ስራ ሳንሰራ ቀርተን ክፍል ስንገባ እንደሚቀጣን አስተማሪ፣ የፖለቲካ ልምጫቸውን ዘርግተው፣ “እጃችሁን ዘርጉ” እያሉ እንድንሽቆጠቆጥና “አይለምደንም! የዛሬን ማሩን” እንድንላቸው ይፈልጋሉ፡፡ የፖለቲካ የአየር በአየር ነጋዴዎችም በማይገደዱበት ጨረታ ውርርዱን አጧጡፈውታል፡፡  
የሴራ ደላሎች “ከአሜሪካ ጋር መጣላት ከአለት ጋር መጋጨት ነውና ሰጥ ለጥ ብላችሁ አሜሪካ ሺ ዓመት ትንገስ!” በሉ እያሉን፣ ሽንፈታችንን እንደ ቅድሚያ ክፍያ እንድንሰጣቸው ደጅ ይጠኑናል፡፡ የአሜሪካ የአዲስ አበባው ኤምባሲም አንዱን አንብበን ሳንጨርስ፣ ሌላ አዲስ መግለጫ እያወጣ “ኢትዮጵያ የምስራቅ አፍሪካ ሶርያ ልትሆን ነው፤ አዲስ አበባም ተከባለች; እያለ፣ የሌሎች ሀገራት ዲፕሎማቶች ኢትዮጵያን ለቀው እንዲወጡ ይወተውታል፡፡ አንዱ ሰበር ዜናቸው ሌላኛውን እየሰበረ፣ የሽብር ወሬን ይነዙብናል፡፡
ምንጣፍ ዘርግተን÷ ቄጤማ ጎዝጉዘን÷ ርችት ተኩሰን÷ ፈንድሻ በትነን አሜሪካንንና ተባባሪዎቻቸውን “በርስዎ መጀን” ባለማለታችን ከአፍሪካ የልማትና የእድገት ትብብር በቀይ እስክሪብቶ ሰርዘውናል፡፡ የባለስልጣኖቻችንን  እንቅስቃሴ አግደዋል፡፡ የፌዴራሊስት ኃይሎች ህብረት የሚባል ዘጠኝ ፓርቲዎችን ሰብስበው፣ የእንግዴ መንግስት ሊልኩልን፣ የማሸጊያ ካርቶኖችን አዘጋጅተዋል፡፡ መንግስት ያለምንም ቅድመ ሁኔት ከህወሓት ጋር ይደራደር ብለው የፍቅር ሰባኪ ሆነውብናል፡፡ በእርዳታ መኪኖች እህል ውስጥ የጦር መሳርያና የመገናኛ እቃዎችን እያቀበሉ፣ የነደደው እሳት ላይ ቤንዚን አርከፍክፈዋል፡፡ ይህ ገርሞን ሳያበቃም በሶማሊያ የአሜሪካ  አምባሳደር በሆኑት ያማማቶ በኩል፣ እነ ፕሮፌሰር ይስሃቅና ዶ/ር እሌኒ ገብረመድኅንን “የአበባየሆሽ” የፊት መስመር ጨፋሪ አድርገው፣ የሽግግር መንግስት ሊያቋቁሙ ተንኮል ጎንጉነዋል፡፡
ወዲህ ደግሞ የሀገራችን መንግስት በቢሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ ለጦርነቱ አውሎ ላልታሰበ እዳ ተዳርጓል፡፡ የበጀት ማስተካከያ ወደ ማድረግም ገብቷል፡፡ የተያዙ ግዙፍ ፕሮጀክቶች ሲታጠፉ አይተናል፡፡
በዚህ አጣብቂኝ መሀል አንድ ሃቅ በራችንን ያንኳኳል፡፡ ነገሩ የምርጫ ጉዳይ አይደለም፡፡ የመወሰን ግዴታ ነው፡፡ ያም ሃቅ በዚህ አጣብቂኝ መሀል ኢትዮጵያ እጆችዋን ወደ እኛ ዘርግታለች፡፡ ዛሬ ሴረኛው ከሀቀኛው÷ እውነተኛው ዜጋ ከአስመሳዩ÷ ገብሱ ከገለባ የሚለይበት የታሪክ ምእራፍ ላይ ደርሰናል፡፡ ሀገርን ማዳን የወቅቱ ጥያቄ ሆኗል፡፡ አሁን ከኃያላኑና ከጀሌዎቻቸው ጋር የእጅ በእጅ የጨበጣ ውጊያ ላይ ገብተናል፡፡
በርግጥ የገንዘብ ድሆች ነን፡፡ ብንሆንም ግን ድህነትን አስቀምጡልኝ ብሎ እንደ አደራ እቃ የሰጠን የለም፡፡ እኛም ከድህነት ጋር እንደ አዲስ ፍቅረኛ ተሟሙቀን የምንተኛበት ምክንያት የለንም፡፡ ስለሆነም ድህነትን በስራ ለማስወገድ ወገባችንን ማጥበቅ የሚገባን ወቅት ላይ ነን፡፡ ከአሁኑ ጦርነት ማገገም የምንችለውም ከሁሉ አስቀድሞ ራሳችንን መመገብ ስንችል ነው፡፡ ስለሆነም የአርሶአደሩን አቅም በዘመናዊ መሳሪዎች ብቻ ሳይሆን በሰለጠነ የአመራረት ስልት ማበልጸግ ለነገ የምናሳድረው የቤት ስራ አይሆንም፡፡ በጦርነቱ የተጎዱ ክልሎችን መልሶ ለማልማትና የተፈናቀሉ ዜጎቻችንን ለማቋቋም ያለ ቀስቃሽ የምንንቀሳቀስበት ጊዜ ላይ ነን፡፡
በሌላ በኩል፤ በመንግስት ተቋም ውስጥ ያሉ ተቀጣሪዎች ላባቸውን ጠብ አድርገው እንዲሰሩ የሚጠበቅበት÷ አምራች ፋብሪካዎች የገበያ ክፍተት እንዳይፈጠር የሚተጉበት፤ የግሉ ዘርፍ ለኢኮኖሚው መነቃቃት ቀን ከሌት የሚሰሩበት÷ ነጋዴዎች ምርት በመደበቅ ሳይሆን ለገበያ በማቅረብ ለኑሮ መረጋጋት የበኩላቸውን አስተዋጽኦ ማድረግ፣ ተገቢውን የግብር ግዴታ በሃቀኝነት መክፈልና በግርግሩ ለመጠቀም በመሬት ወረራና በህገወጥ ተግባር ላይ የሚሰማሩትን ደግሞ ለህግ ማቅረብ ጠረጴዛ ላይ የተቀመጡ የቤት ስራዎቻችን ናቸው፡፡
የሃይማኖት ተቋማት መንፈሳዊ ልእልናን በማንበር አማኞቻቸውን የሚገሩበት÷ የኪነጥበብ ባለሙያዎች ጋኑን ለመደገፍ ጠጠራቸውን የሚያዋጡበት÷ የዘመኑን የሚዲያ ትግል መታገል የሚችሉትም በቴሌቪዥን በጋዜጣ በሬዲዮና በማህበራዊ ሚዲያ አውደ ውጊያ ላይ ተሳትፈው የኢትዮጵያን ድምጽ የሚያሰሙበት÷ ምሁራን መሬት ጠብ የሚል የመፍትሄ ሃሳብ እያቀረቡ ለሁለንተናዊ ትንሳኤ የመውጫ በሮችን የሚያሳዩበት÷ በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን የነገ ልቅሶ ደራሽ ከመሆን ይልቅ የዛሬ ፈጥኖ ደራሽ ሆነው ለውጭ ምንዛሪ መገኘት እጃቸውን የሚዘረጉበት÷ የወጥቶ አደር ሰራዊታችንን ሞራል መገንባት ብሎም አካባቢያችንን በንቃት መጠበቅ የወቅቱ አንገብጋቢ አጀንዳችን ነው፡፡
ሀገራችን ኢትዮጵያ ድረሱልኝ ስትል የእናቴ ቀሚስ ጠለፈኝ ማለት ውለታቢስነት ነው፡፡ የመዳኛ መንገዳችንም ኢትዮጵያዊ አንድነት ነው! ኢትዮጵያ የነፃነት እርጥባን ተመጽውታ ወይም አኮፋዳ ይዛ ከኃያላኑ መሶብ የህልውና ዳረጎት ለምና አታውቅም፡፡ እልቂታችንን ለመመልከት አጉሊ መነፅር ሰክተው ያደፈጡትን ኃይሎች ማሳፈር የምንችለው በብዝሃነታችን ደምቀን አንድነታችንን ስናጠናክር ነው፡፡
ኢትዮጵያ ሀገራችን አፍ አውጥታ ከዚህ መከራ እንድናወጣት በብዙ ጥያቄዎች ተወጥራ እጆችዋን ወደ እኛ ዘርግታለች፡፡ “አለንልሽ” እንበላት!


Read 1590 times