Tuesday, 07 December 2021 05:36

አንተ፣እናቴ እና እኔ

Written by  ነቢዩ ተካልኝ
Rate this item
(6 votes)

    ዛሬ
ጋሼ… ይኸው ለዓመታት ውስጤን ስቆፍር አለሁ። አንተን ፍለጋ ነፍሴ እንደባከነች ሃያ ስንት ደመራ ተለኮሰ? የጮርቃ ትዝታዬን ሙዳይ ከፍቼ፣ ከደገኛ ዘመናት ቀለማም ህልሞቼ ውስጥ እፈልግሃለሁ። ግን… አላገኝህም።
ያኔ!
አዲሲቷ ፀሃይ የእለቱን ብርሃን ልትገላገል ስታምጥ ሰማዩ ሰፊ ዝርግ ፊቱ ላይ የደም ዓይነርግብ ለጥፎ ብርማ ገጽታውን ሸሸገ። ያኔ የደጃችን በር ተንኳኳ… ፊቶች! በጥቁር፣ ግራጫ፣ አመድማ ጥለቶች ውስጥ የተሸሸጉ ዓይኖች… ሞት ያረገዙ… ጥቁር ብርሃን የሚረጩ ቀዝቃዛ አይኖች ጠባቧን ሳሎናችንን ወረሯት። በቅዠት ከታፈነው እንቅልፋችን መንጭቀው፣ የማያባራ የቀን ቅዠት  ውስጥ ዘፈቁን… ሞትህን አረዱን… በዚያ ቅጽበት… በዚ ቅጽበት እናቴ ስትሞት አየኋት… የቁም ሞቷ ቁልቁል ሲደፍቃት ‘ህእ!` ብላ… ደም የሚያዘንብ ´ነፍሷን´ ይዛ ሸብረክ አለች… ሸብረክ! የዘላለም ርዝማኔ ያለው ለሚመስል ቅጽበት ሸብረክ! ኔ መኖር አቆመች፤ ብርሃን የሚረጭ ጸዳሏ አመዳይ ለበሰ። ያኔ የእናትነት ንፁህ ፍቅር የሚንፎለፎልበት ውብ ገጽታዋ፣ ዳግም ላይገለጥ ተሰወረ።
´ህእ?´ ሸብረክ! እናቴ በዓይኔ ስር የቁም ሞቷን ጨለጠችው። ሞቷን ሁላችንም አየነው፤ እኔ፣ እህቶቼ።
ኋላ ዘላለማዊ ከሚመስለው ቅጽበት ውስጥ፣ አመድማ ፊቷ ላይ አመድማ ፈገግታ ተለጥፏል። ጥርሶቿ ተገለጡ። ደነገጥን! ሙት ፈገግ ሲል አይተን አናውቅምና ክፉኛ ደነገጥን!
ከዚያ ሳቅ!! ካካካካካካ… ካካካካካካ በድንጋጤ ´የጨው አምድ´ የሚያደርግ ሳቅ! በፊትም፣ በኋላም ተሰምቶ የማያውቅ ሳቅ! አካካካካ! ግን… ሳቅ?
የሳቅና  የለቅሶ ልዩነት እስኪምታታብን ግራ ተጋባን። እንዴት ያስፈራል? በዚያ ጥልቅ ዝምታ ውስጥ ድንገት በየአቅጣጫው የሚወረወር የሳቅ ፍንጣሪ! እንዬ በዚያ የሳቅ ፍንጣሪ  እርሟን አወጣች። አንተ ህልሟ፣ አንተ ሕልውናዋ፣ አንተ የመኖር ትርጉሟ፣ አንተ የነገ ተስፋዋ፣ አንተ ዓለሟ፣ አንተ ልጇ ስትሄድ… እንዲህ በሳቅ ፍንጣሪ ተንጠላጥላ ተከተለችው። ከዚያ ወዲህ እናቴ ኖራ አታውቅም…
የዋይታ ድምጽ  በራማ ተሰማ፤ ራሄል ለልጆቿ ምርር ብላ አለቀሰች፤ መጽናናትም አልወደደችም…
ዛሬ
ጋሼ! አንተን ብቻ ሳይሆን እናቴንም እፈልጋታለሁ። ሞትህ የነጠቀኝን  እናቴን ስፈልግ ምንኛ በጽልመቴ ዳከርኩ? ምንና በአመድማ እሷነቷ ውስጥ ተመላለስኩ? ግን የለችም። እኒያ በልጅነት ደማቅ ህልሞቼ ውስጥ የሚመላለሱ የብርሃን ጨረሮቿ ቆፈን የያዛ ነፍሴን እንዲያሞቋት እሻለሁ። ግን አልተሳካልኝም። ሁሌም የሚያፍነኝ በግራጫ ገጽታዋ የሚበን ግራጫ ፈገግታዋ! ይህ ነው ነፍሴን ትን የሚላት እውነት።
ያኔ!
ሞትህን ሲያረዱን፣ አንዳች የሰላ ጎራዴ በልቤ እንደተሰነቀረ ሁሉ እንደ እናቴ ´ህእ!´ ብዬ… ባልሸበረክም፣ ትንሽቱ ልቤ መግቢያ ጠፍቷት በሰውነቴ ውስጥ ተራወጠች። ይህ መራራ እውነት እንዳትሰማ ማደሪያዋን ትታ መሸሸጊያ እንዳጣች ሁሉ በመላ ሰውነቴ ተወራጨች። ከዚያም ላብ፣ ከሁለመናዬ የሚፈልቅ ላብ ወይም ሁለመናዬ አይን እንደሆነ ሁሉ… ከየቆዳዬ ቀዳዳ የሚፈልቅ እምባ? ወርዶ ወርዶ የማያባራ! የሚያየኝ የለም… ዓይኖች ሁሉ በእናቴ ላይ እንደ አልቅእህት ተጣብቀዋል። በእኔ ውስጠት ደግሞ ዶፍ ይጥላል… ቆዳዬ ይህን ወስዶ አዠ።
በእድሜ ልዩነታችንና ተራርቀን በመኖራችን ሳቢያ መልክህን እንኳ በውል ባላውቀው… በውስጤ አንዳች የተስፋ ገመድ ሲበጠስ ተሰማኝ። ትምክህቴ! ጧ! ከአንተ የተቆራኘ የተስፋ ገመዴ ጧ!
የኋላ ኋላ ምራቅ ዋጥ አድርጌ ክፉና ደጉን መለየት ስጀምር በሕይወቴ ውስጥ አንተን፣ አንድ ወንድሜን ማጣት ምንኛ የክፉ እጦት፣ ምንኛ ክፉ በደል መሆኑ እየተገለጠልኝ መጣ። በህይወት መደነቃቀፌ ውስጥ አንተ ብትኖር አልኩ፤ የኑሮ እንቆቅልሽ ሊበርቅብኝ ምክርህን ናፈቅኩ፤ በማጥ ውስጥ ስዳክር ምርኩዝ ፈለግኩኝ፤ ስወድቅ አፈፍ አድርገው በሁለቱ እግሬ የሚያቆሙኝ ጠንካራ እጆችህን ሻትኩ። እና… የሞትህ አረዛዘሙ! በእያንዳንዷ የሕይወቴ ቅጽበት ለመውደቅ በመነሳቴ  በሽንፈት በድሌ ውስጥ… ያንተን መኖር ስሻ… አንተ ግን  አልነበርክም… እና ሞትህን መሪር መርዶ ስንት ሺህ ጊዜ ለራሴ አረዳሁት! ስሻህ ባላገኘሁህ ወቅት ሁሉ የሞትህ እርግጠኛነት ልቤን ደጋግሞ በስለቱ ሸቀሸቃት።
ያኔ!
ማለፍህን ሲዘፍኑልን! በእንባችሁ እየተቃጠላችሁ ኑሩ አሉን። እሽሽሽ! ዝም! ጭጭ! በሉ አሉን። እህህን ነፈጉን… እዬዬን ነፈጉን! የሚንተከተክ፣ የሚገነፍል እንባችን ውስጣችንን አነፈረን.. የታፈነው ጩኸታችን፣ የተገደበ እንባችን ሁለመናችንን እንደለበለበን ይኸው እስከዛሬ ውስጠታችንን እንደሰነጣጠቀው አብሮን አለ። ይኸው እስከዛሬ በፍል የእንባችን ባህር ውስጥ እንደተደፈቅን አለን።
ያኔ!
እናቴ ከቁም ሞቷ ድንገት ባንና “ ማየት አለብኝ!” አለች። “ልጄ የወደቀበትን፤ ልጄ ባረር የተቃጠለበትን ቦታ ማየት አለብኝ” አለች። በድን ገላዋን እየጎተተች ወደ ሸገር አቀናች… ወደ ሞትህ ከተማ አሰሰች… ጉጡን፣ ስርጓጉጡን፣ ቄራውን፣ የሙታኑን መንደር፣ የደቦ ቀብሩን ሰፈር… አልሆነላትም። ጮኸች… “ቢያንስ ወስጄ የምቀብረውን አንዳች ነገር ስጡኝ” አለች። “ባረር የተቃጠለ ከናቴራውን በደም ´የደመቀ´ ሸሚዙን… ጠልፎ የጣለውን የጫማውን ማሰሪያ ስጡኝ! እባካችሁ የምቀብረውን ስጡኝ!” አለች። ተሳለቁባት! እናቴ ላይ ተዘባበቱባት… በድኗን እየጎተተች የወጣች… ጻረ መንፈሷን እየጎተተች ተመለሰች። ከዚያ በኋላ በረዥም ዝምታዋ ውስጥ ተዘፈቀች። በማቋ ውስጥ ተንሸራታ ገብታ ጠፋች።
ያኔ! ጋሼ የወደቅክበት  ባይታወቅ፣ በልቤ ላይ ረዥም ሐውልት ተክዮልሃለሁ። በሐውልቱም ስር እንዲህ ይላል፡ “ለሰው ልጅ ፍቅር ላለፈው ሰው ላልታወቀው ጀግና።” ሆኖም ዛሬም አንደፈለግሁህ አለሁ! ግን አሁን አንድ እውነት በርቶልኛል።
የት እንደምፈልግህ አውቃለሁ። የት እንደማገኝህም አውቃለሁ። የማገኝህ… አንተን ወንድም ጋሼን፣ ጀግናዬን የማገኝህ በልጅነቴ ሕልም ውስጥ ሳይሆን በጽናትህ፣ በጥንካሬህ፣ በአይበገሬነትህ፣ የሚንተገተግ የሰው ልጅ ፍቅርህ ውስጥ ነው። እና አንተ ያልተዜመልህ፣ ቅኔ ያልተዘረፈልህ ጀግናዬ ሆይ! ያን ካድማስ አድማስ የተዘረጋ የሠወ ልጅ ፍቅርህን ከተቃጠልኩት የፅናት የጥንካሬህን ዳና ተከትዬ  ከተጓዝኩኝ በእርግጠኝነት አገኝሃለሁ። ከራስ መውረድ አዙሪት ተላቅቄ መደዴ ፍላጎቴን አድቤ ሰው ለሚባለው ፍጡር ከኖርኩኝ… ያኔ ያንተ ትንሳኤ ይሆናል። ያኔ ከወደቅክበት ከዚያ ከማታወቅ ስፍራ ቨአፈርህን አራግፈህ ትነሳለህ.. ያኔ እናቴ ተንሸራትታ ከገባችበት  ማቋ ውስጥ በብርሃን ደምቃ ብቅ ትላለች። ያኔ የሷም ትንሳኤ ይናሆል። ያኔ ያንድም ሦስትም ሞታችን፣ ባንድም ሦስትም ትንሳኤያችን ድል ይሆናል። ያንተ የናቴና የኔ።
ያኔ!
የነገ ፀሎቴ… በሀሳብ ልዩነታችን ሳቢያ ደም እንዳንራጭ፣ ሕይወት እንዳንነጠቅ፣ ለቃታ የፈጠኑ ጣቶች ሳይሆን በሰው ልጅ ፍቅር የሚቃጠሉ ብሩህ ልቦችን ስጠን ነው። አሜን!
ለወንድሜ ለመለስ ተካልኝ እና ለሰው ልጅ ፍቅር ላለፉ ሰው ያላወቃቸው ጀግኖች።
ከታናሽ ወንድሙ ነቢዩ፣ ሚያዚያ፣ 1999 ዓ.ም
(ምንጭ፡- “ዳቦ 60 ደራስያን” ከሚለው መድብል የተወሰደ)


Read 1341 times