Tuesday, 07 December 2021 05:50

እኔና እንጀራዬ

Written by 
Rate this item
(5 votes)

 እኔና እንጀራዬ

በኔ የሳር ጎጆ - አይቀኑ ቀንቶብኝ
የጣርያ ክዳኔን - አፋፍሶ ወስዶብኝ
የጓዳዬን ምስጢር - ለሰው ገለጠና
የስንት አሽሙረኛ .....................
ከንፈሩ ነከሰኝ ............................
ስሜን እንደ ሽንኩርት - ገሽልጦ ጣለና!
-*-
ዉሃ እንዳጣ ተክል - አወዛውዞት ግንዴን
ነቃቅሎ ሲጥለኝ - ቆርጦት ቅርንጫፌን
ቅጠሌን ሰብስቦ - ጥሎት ከምድጃ
አመድ አደረገኝ ..........................
ልፋቴን ቀርጥፎ - ይሄ የቀን ፍርጃ !
-*-
ድንገት ሳት ብሎት - ቀና ቢል አንገቴ
ኮርኳሚ ይበዛል - ተቀማጭ ከአናቴ !
እድል ያገኘ ለት - እግሬ ከመሄዱ
ሞቴን ለማፋጠን ..............
ጎድጓድ የሚቆፍር - አለ በመንገዱ!
-*-
ፊቴ ድንገት ወዝቶ - ጥርሴ የሳቀ ለት
ሰበር ዜና ሆኖ .....................
ሀዘን ይታወጃል - እኔ ባለሁበት !
ቆርፋዳ ጫማዬን - አልፎልኝ ባስቀባ
በግንቦት ፀሐይ ላይ ....................
ዶፍ ዝናብ ይጥላል - ክረምቱ ሳይገባ !
-*-
ሆዴን እየበደልኩ - አንድ ልብስ ብገዛ
እንደ ቅርስ ሰቅየው - ከግድግዳው ታዛ
በስስት እያየሁ - መስቀያው ላይ አድሮ
ለድግስ ያሰብኩት .................
አይጥ ይበላዋል - ግድግዳ ቆፍሮ !
-*-
ወር መሉ ለፍቼ - ልፋቴን ቋጥሬ
ደመወዜን ስቀበል - አንጀቴን አስሬ
ከየት መጣ ሳልል - ድንገት ያመኝና
መድሃኒት ስገዛ .....................
እጅ ባዶ ይቀራል - ተለይቶኝ ጤና !
-*-
እንዲህ ነው ነገሬ - የእለት ቀን ውሎዬ
ሁሌ ትግል ላይ ነን - እኔና እንጀራዬ!
-*-

Read 1404 times