Tuesday, 07 December 2021 05:49

የሌሊት የእግር ጉዞ - የዕብደት ለዛዎች

Written by  ያዕቆብ ብርሃኑ
Rate this item
(0 votes)

   እኔ የውድቅት ሰው ነኝ፡፡ ሌሊቱን እወደዋለሁ፡፡ ሆኖም ከመሸታ ቤት ጋር ፈጽሞ ንክኪ የለኝም፡፡ ከ2002 - 2010 ዓ.ም በነበሩት ስምንት ዓመታት ብቻ በሳምንት ቢያንስ አንድ እኩለ ሌሊት፣ ከሌሊቱ ስምንት ሰዓት እየተነሳሁ፣ የአዲስ አበባን ተርፎ አደባባይ የተሰጣ ነውር ሳስስ አሳልፌያለሁ፡፡
ይሄም ሁሉ ሆኖ አሁንም ሲመሽ ግርርር ይለኛል... ጨለማን አልፈራም። በረጃጅም ሌሊቶች መሃል እየተሣከርኩ ለእግር ጉዞ ተመላልሻለሁ። እናስ ሲመሽ ስለ ምን እደናገራለሁ?
      
            የተፈጥሮን የልብ ምት፣ እስትንፋስ ጠንቅቀው የሚያውቁት አፍሪካዊ የማሳይ ጎሳዎች ‹‹ቀኑ ዓይኖች፣ ሌሊቱ ደግሞ ጀሮዎች አሉት›› ይላሉ፡፡ እውነትም ሌሊት ከዓይኖች ይልቅ ጆሮዎች ስል የሚሆኑበት ጊዜ ነው፡፡ አንዲት የቅጠል ኮሽታ በአዳኙም በታዳኙም ላይ ብርክ የመፍጠር አቅም አላት፡፡ በውድቅት ሕይወት በመስከን ውስጥ ጥርጣሬን ተሸክማ እንደ ዶሮ በአንድ ዓይን ያንቀላፋች ድንጉጥ ሆና ትቀበለናለች፡፡ እያንዳንዷ ንቅናቄ መደነቅና መበርገግን አዝላ በመንታ ስሜት ትስተናገዳለች፡፡ የትንኟ ሲርሲርታ ሳይቀር በዝታ ተባዝታ ጎልታ ትሰማለች፡፡ በሌሊት ለማጥመድም፣ ለማምለጥም ከዕይታ ይልቅ ማዳመጥ ይጠቅማል፡፡
እኔ የውድቅት ሰው ነኝ፡፡ ሌሊቱን እወደዋለሁ፡፡ ሆኖም ከመሸታ ቤት ጋር ፈጽሞ ንክኪ የለኝም፡፡ ከ2002 - 2010 ዓ.ም በነበሩት ስምንት ዓመታት ብቻ በሳምንት ቢያንስ አንድ እኩለ ሌሊት፣ ከሌሊቱ ስምንት ሰዓት እየተነሳሁ፣ የአዲስ አበባን ተርፎ አደባባይ የተሰጣ ነውር ሳስስ አሳልፌያለሁ፡፡ ይሄም ሁሉ ሆኖ አሁንም ሲመሽ ግርርር ይለኛል... ጨለማን አልፈራም። በረጃጅም ሌሊቶች መሃል እየተሣከርኩ ለእግር ጉዞ ተመላልሻለሁ። እናስ ሲመሽ ስለ ምን እደናገራለሁ?
ሌሊት በጨለማ ካፖርቱ ብዙ የሕይወት ውልብታዎችን የሚሸፍንብኝ ስለሚመስለኝ ይሆን? ምናልባት የሕይወት ዋነኛው ወዘናዋ ዘወትር አይለመዴ (ever strange) መሆኗ ይሆን? ሺህ ሌሊቶችን በመቅበዝበዝ ባሳልፍም ቅሉ ዛሬም እግር ጥሎኝ ለእግር ጉዞ ብቅ ካልኩ እንደ አዲስ እንግዳነት፣ መስገብገብና መበርገግ ይቆጣጠረኛል፡፡ ማንም ጨለማው ምን እንደያዘ ሊናገር አይችልም፡፡ ጨለማ ምንጊዜም የሚያጓጓ፣ በከፊል የሚያስፈራ ጥቂት በጥቂቱ የሚገለጥ አባባይ ኑባሬ ነው፡፡
ይህ ውል የለሽ የውድቅት መክለፍለፍ ግን የአብዛኞቹ ጠቢባን ልክፍት ነበረ/ነውም፡፡ ቻርለስ ዲከንስ በተለይ በእንቅልፍ እጦት (insomnia) ተጠቅቶ ሆስፒታል ከገባ በኋላ፣ ቤንጃሚን ፍራንክሊን በግለ-ታሪኩ “ቆሻሻ” ብሎ በጠራት የያኔዋ ለንደን ጎዳናዎች ሌሊቱን ሙሉ ይንሸራሸር ነበር፡፡
በአንድ ግልምጫ ብቻ የዓለምን የተውኔት አጻጻፍ ይትብሃል ምናልባት የሰው ልጆችን ዕጣፋንታ አረዳድ ጭምር እስከ ወዲያኛው ግራ እና ቀኝ ያጠናገረው ሳሙኤል ባርክለይ ቤኬት ደግሞ በውድቅት ጉዞ አፍቃሪነቱ አቻ አልነበረውም፡፡ የሳሙኤል ቤኬት የሌሊት የጉዞ ጀብድ በርካታ ገጠመኞች አሉት፡፡ ስፍርቁጥር በሌላቸው ምሽቶች የፓሪስን ከተማ ከምዕራብ እስከ ምሥራቅ ጫፍ ሲያስሳት አንግቷል፡፡ በአብዛኞቹ ምሽቶች እንደርሱው የሌሊት ምናኔ ወዳጁ የስዊዝ ተወላጅ ሰዓሊና ቀራጺ አልቤርቶ ጂያኮሞቲ ጋር ይገናኛሉ፡፡ የሆነ ቅያስ ላይ እስኪነጣጠሉ የማያልቅ የሚመስለው ክርክራቸው ይቀጥላል፡፡ ቤኬት ጥቂት የማይባሉ እንደርሱው ጨለማ ለባሽ አድናቂዎቹ በውድቅት እያጠመዱ መጻሕፍቱ ላይ እንዳስፈረሙት ተጽፎ አንብቤያለሁ፡፡
እ.ኤ.አ በጥር 7 1938 ሌሊት ግን አስደንጋጭ ነገር ተከሰተ፡፡ ሳሙኤል ቤኬት እንደተለመደው በውድቅት ሲንሸራሸር አንድ ሰው ድንገት ተጠግቶ በጩቤ ደረቱ ላይ ወጋው፡፡ ለበርካታ ወራት ሆስፒታል ተኝቶ ከሞት አፋፍ ዳነ፡፡ ሲያገግም ወህኒ ቤት ወርዶ ይህ ከእርሱ ጋር ምንም ዓይነት ግንኙነት የሌለው ሰው ስለምን ሊያጠቃው እንደሻተ ጠየቀ፡፡ ያገኘው መልስ አስገራሚና ለሕይወት ዘበትነት (Absurd) አረዳዱ መጉላት ሌላ መገለጥ የጨመረለት ሆነ፡፡ ቃል በቃል ይህችው ናት፡- ‹‹አላውቅም ጌታዬ፡፡ ይቅርታ አድርግልኝ!››
የቱንም ያህል በቢላ ጠርዝ ላይ እንደ መራመድ ያለ አደገኛ ሰዓት ቢሆን ሌሊት ምንጊዜም ግርማ ሞገስን የተላበሰ የጊዜ ክፋይ ነው፡፡ ሌሊት ... ክቡድ የጊዜ ጥላ፣ ጭፍርግ የፅልመት በርኖስ፣ ጥልቅ የብቸኝነት አዘቅት፣ የአስፈሪነት ግርማ፣ የነፍሳት ሲርሲርታ፣ የስክነት ጥግ፣ የጥቁር ብርሃን ንብርብር፣ የዝምታ ርቱዑ ልሣን፣ በቅጠል ኮሽታ መላ ሰውነትን የሚያርድ አቻ አገዛዝ... ዝምታ፣ ፀጥታ፣ ጭጭታ ... ሌሊት...
እነሆ አሁን ውድቅት ሆኗል፡፡ እንደተለመደው የማላውቀውን ጥሪ ተከትዬ፣ የእኔን ነገር ሁሉ የተፈጥሮ መዳፎች ላይ ጥዬ ሁሉንም ልታዘብ ወጥቻለሁ፡፡ መሄድ እወዳለሁ፡፡ ዘወትር በሌሊትም፣ በአመሻሽም ለእግር ጉዞ ከቤቴ ስወጣ ወደየት እንደምሄድ እንኳ አላውቅም፡፡ ደመነፍሴ ወደ መራኝ መራመድ ብቻ ነው፡፡ ደመነፍሴን ለዓመታት አሰልጥኜዋለሁና አምነዋለሁ፡፡ እንዳሻኝ ርቄ እንዳልጓዝ ኑሮው እግር ተወርች ቢጠፈንገኝም እሄዳለሁ፡፡ ሕይወት እንደሁ ኒውዮርክም ሆነ ኒውዴልሂ ወይ ባሌ ተራሮች ያው ሕይወት ነች፡፡ በዥጉርጉር ገጽዋ የተሞላች፤ ዘወትር አይተዋት፣ ኖረዋት፣ ቀምሰው ዳስሰዋት ግን ሁልጊዜ እንግዳ፡፡ አዎ መሄድ እወዳለሁ... አዳዲስ አካባቢ ማሰስማ አብሾ የጠጣሁ ያህል ያቅበጠብጠኛል፡፡ ለምን ጭንቁስ ያለ ጎስቋላ ሰፈር አይሆንም፡፡ አዲስ ከሆነ ምናቤን ያጥበረብረዋል፡፡ ተራራ? እሱማ ይለያል! ከወራት በፊት በዚህችው ጋዜጣ በአንድ መጣጥፌ ላይ እንዳተትኹት ተራሮችን መውጣት በእግዜር ችሎት ላይ እንደመታደም ያለ ሌላ ፍጹም መደነቅን ይፈጥራል፡፡
በኦሮሚፋ እንዲህ የሚል አባባል አለ፡- ‹‹Chisura dhabachuu waya, tauera dhabachuu waya, dhabachuura demuu waya- ከመተኛት መቀመጥ፣ ከመቀመጥ መቆም፣ ከመቆም መራመድ ይሻላል›› የሚል፡፡ ቃርሜ ነውና ቁቤው ላይ ብሳሳት አይግረምህ፡፡ አየህ ያለፍንበት የሃምሣ ዓመታት ስሪት እኛን ለእኛ በዐድ አድርጎ ከኦሮምኛ ይልቅ ፈረንሳይኛ መጥቀስ እንዲቀለኝ አስገድዶኛል፡፡ ይሄ ግን እውነት ነው፡፡ የሚጽፍ፣ የሚስል፣ የሚዘፍን፣ የሚደንስ ወይም ሌላ ማንኛውም ከያኒ የሚጠበበው በእርምጃው ልክ ነው፡፡ ካልተራመደ መጠበቡ የሆነ ስንኩል፣ ነፍስን ለመንዘር ትንፋሽ የሚያጥረው በድን መሆኑ አይቀርም፡፡ እርምጃው የሌሊት ከሆነ ደግሞ መገለጡ ተዓምር ነው፡፡ ምክንያቱም ሌሊቱ ደመነፍስ ስል የሚሆንብት ክፍለጊዜ ስለሆነ... በእስልምና የተቀደሰው ወር የመጨረሻው ሣምንት፣ ከጎዶሎዎቹ ዕለታት በአንደኛው፣ ለፍጥረታት ሁሉ የምትገለጠውን የቀድር ሌሊት (laylat-ul-qadr) ታውቃለህ? ካላወቅህ ቀርቶብሃልና ሼካዎችን ተወዳጅ፡፡ ይህችን ሌሊት ለይተህ አውቀህ ባለማቋረጥ ስትጸልይ ካነጋህ፣ የ83 ዓመታት ያህል ዋጋ ይከፈልሃል፡፡ አየህ ሌሊቱ መለኮት ወደ ፍጡሩ ጆሮዎቹን የሚያቃናበት ጊዜ ነው ማለት ነው፡፡ ልባዊ በሆነ መሻት ከተከናወነ ምንም ነገር ጸሎት ነው ምህላ፡፡ ምንም ነገር! የሌሊት የእግር ጉዞም ቢሆን! ... የሌሊት የእግር ጉዞ በዓለም ላይ ካሉት አስደሳች ነገሮች ሁሉ የበለጠው መሆኑን እንዴት ላስረዳችሁ ይቻለኛል?
በሕልውና ለሚቀዝፍ ሁሉ የሚሰራ አንድ በጣም ጠቃሚ ነገር አውቃለሁ፡፡ እሱም ነውር የሌለበት መመኘት፣ መፈለግ (desire) ነው፡፡ ሌላውን ሁሉ ተፈጥሮ እንደ ፍጥርጥሯ እንድታረገው መዳፏ ላይ ጥዬ እኔ ምኞቴን ብቻ ተከትዬ ፍለጋዬን እኳትናለሁ፡፡ በተፈጥሮ ንፁህ ይሁንታ ከመጣ ሞት እንኳ ማምለጫ (escaping route)፣ ወይ ደግሞ መባረክ እንጂ ቅጣት ሊሆን አይችልም፡፡ ከተፈጥሮ ጋር የሚናበብ እሱ ከእግዜሩ ጋር እየተመሳጠረ እንደሆነ አስባለሁ፡፡ ምክንያቱም ተፈጥሮ እና እግዜሩን ልትነጥላቸው አትችልም፡፡
በውድቅቱ ሌሊት እርምጃዬን ቀጥያለሁ፡፡ እነሆ በዚህ ድቅድቅ ጨለማ በቀኑ ክፍለ ጊዜ በሙሉ ኃይሏ የምታምባርቀው አዲስ አበባ በአንፃራዊነት ጸጥታ መላበሷን አየሁ፡፡ በለጋዋ ጨረቃ የልጃገረድ የሚመስል ተሽኮርሟሚ ጨዋታ እየተመሰጥኩ ጥቂት እንደተጓዝኩ ግን ድንገት በጎዳናው ላይ ትኩረት የሚሰርቅ ትዕይንት ተመለከትኩ፡፡ ከመጋቢ መንገድ ወጥቶ ዋናውን ጎዳና የተከተለ አንድ ብዙ ዓይነት ኮተቶች የተሸከመ እብድ ጮክ ብሎ እያወራ ከፊቴ ቀደመኝ፡፡ የሚለውን ለመስማት ብጣጣርም አልተሳካልኝም፡፡ በእኔ እምነት የዚህ ከንቱ ዓለም ምሥጢር በከፊል የተገለፀላቸው እብዶች ናቸው፡፡ ‹‹a grain of madness is what is best in art.›› እንዲል ቫን ጎግ።
ይህ ሰው እጆቹን እያወናጨፈ ጥቂት እንደተጓዘ ከተሸከማቸው እንቶ ፈንቶዎች መካከል የተጣጠፈች አንዲት ወረቀት እንደ ዘበት ወደ መሬት ወደቀች፡፡ ልብ ሳይላት ዝም ብሎ ጉዞውን ቀጠለ። ስደርስባት በግድየለሽነት አንስቼ እጥፋቷን ገልጬ ተመለከትኳት... ፈፅሞ ያልጠበኩትን አስገራሚ ፍልስፍናዊ ወጎችን አጭቃ አገኘኋት፡፡ እነሆኝ አንብቧት…
  ***
“ከማበዴ በፊት ያው እንደ እናንተ እብድ ነበርኩ፡፡ እኔም እናንተም እኮ እብዶች ነን፡፡ ልዩነቱ እብደታችንን በቅጡ አውቀን መተወኑ ላይ ብቻ ነው፡፡ ከማበዴ በፊት እንደ እናንተ እንደ እያንዳንዳችሁ ነበርኩ፡፡ መንጋ… ሂድ ሲሉኝ የሚሄድ ቁም ሲሉኝ የምቆም፡፡ የዘለዓለምን ድሪቶ የምጥፍ አንድ ደቃቅ ፍጡር… የልማድ እስረኛ፡፡ ሰው ወደዚህ ምድር በተፈጥሮ ይሁኝታ ሲመጣ ሌጣው ነበር። እናንተ ግን አባቶቻችሁ ያወረሷችሁን የዘለዓለምን ደበሎ ድሪታችሁን ያለ ውዴታው ታሸክምታላችሁ፡፡ ከዚያ ወዲያ ሠው እንደ ሠው ሳይሆን እንደ እናንተ ይሆናል፡፡ እንደ እናንተ ሙስሊም፣ ወይም እንደ እናንተ ክርስቲያን… ከምንም ውጪ እንዲሆን አትፈቅዱለትማ፡፡ እንደ እናንተ ኢትዮጵያዊ ወይም እንደ እናንተ አሜሪካዊ፤ እንደ እናንተ ሀብታም ወይም እንደ እናንተ መናጢ ድሃ… ኤዲያ ሠው ከዚህ ውጪ የሕይወት ቅኝት የለውም ማለት ነው?
“እንዳልኳችሁ ነው፡፡ ከማበዴ በፊት እኔ እንደ እናንተ እንደ እያንዳንዳችሁ ነበርኩ፡፡ በሚያዳልጠው ህዋ ላይ ሞትን ዘወትር የምሸሽ ፈሪ ፍጥረት፤ ለእናንተ ጣዖታት ሱባኤ የምይዝ፣ ለእናንተ አማልክት መስዋዕት የማቀርብ ድንጉጥ... እንደ እናንተ ህሊናን የሚያክል ትልቅ እግዚአብሔርን እያታለልኩ ከደመና በላይ በምናብ ለሰቀልኩት እግዜር የለበጣዬን የማጎበድድ፣ የሞራል ዝቅጠቴን እንደ ሥልጣኔ የምቆጥር ግልብ ነበርኩ፡፡ ነገርኳችሁ በቃ… ከማበዴ በፊት እንደ እናንተ እንደ እያንዳንዳችሁ ነበርኩ፡፡ በተዘፈነበት የምጨፍር፣ በተለቀሰበት የማለቅስ፣ ጮኽ ብዬ የምስቅ ተራ ሰው… ለነገሩ ከእናንተ የወጣ ሰው እንደ እናንተ ከመሆን ውጪ ሌላ ምን ዕጣ አለው? አትፈቅዱለትማ! …
“ዕብደቱ ሲጀማምረኝስ ምን ሆንኩ? ለእናንተ እንዲገባችሁ እንጂ ዕብደት ማለቴ ነገርዬው ያው ተምሰልስሎት ቢጤ ነው፡፡ መጀመሪያ ቤተሰቦቼን ተውኩ፡፡ በመቀጠል የእናንተን የእያንዳንዳችሁን አስተሳሰብ ናቅኩ፡፡ እግዜራችሁም አላስፈለገኝም፡፡ በመጨረሻስ? በመጨረሻማ የማይቀረው ዕጣዬን ራሴ መካድ ሆነ፡፡ በፍለጋ ህይወት ትልቁ መገለጥ እኮ ይሄ ነው፡፡ እንዳልኳችሁ ከማበዴ በፊት እንደ እናንተ እንደ እያንዳንዳችሁ ለማዳ እንስሳ ሆኜ ከቤት ወደ ስራ ከስራ ወደ ቤት መመላለስ የማይሰለቸኝ፣ መንጋዬን የምከተል ነበርኩ፡፡ አሁን ይሄ ታሪክ ተቀየረ፡፡
“እንዲያውም የአበድኩ ሰሞን እግዚአብሔርን መንገድ ላይ አግኝቼው ነበር መሰለኝ፡፡ ላናግረው ስል ተሰወረብኝ፡፡ እብዶችን ይፈራል ልበል? ወይስ እሱም በራሱ መንገድ አብዷል? መቼም ያላበደ አምላክ ይህችን የተቀዣበረች ዓለም ሊፈጥር አይችልም፡፡
ያበድኩት ሰሞን መጀመሪያ የተገለፀልኝ እውነት ግን የእናንተ የእያንዳንዳችሁ ሕይወት ጥቂትም ለዛ ያገኘው ስለ አምላክ ባላችሁ ቀቢጸ ተስፋ ላይ መሆኑ ነው፡፡ እውነትስ ይህ ምስኪን ጉስቁል ህዝብ እግዚአብሔር የለም ቢሉት በቅፅበት ገበያ መሀል የጣሏት ጥንቸል ሆኖ መጠለያ ሊያጣ አይደለምን? ለነገሩ እኔም እናንተም እንሸሻለን፡፡
 ልዩነቱ የመሸሻ መጠለያችን ብቻ ነው፡፡ እኔ ወደ ምንምነት አዘቅት... እናንተ ደግሞ ወደ እምነት ቀቢፀ ተስፋ … እኔ በነቃ እናንተ ባንቀላፋ ደመነፍስ...
“ካበድኩ በኋላ በዓለም መሀል እያለሁ ከዓለም ተነጥያለሁ፡፡ ግን የቱንም ያህል ብሸሽ ላመልጣችሁ አልቻልኩም፡፡ እንደ ጥላዬ በየሄድኩበት ትከተሉኛላችሁ፡፡
ለነገሩ ታስፈልጉኛላችሁ፡፡ ሀኪሞች መድሀኒቶቻቸውን በአይጦች እንደሚሞክሩ እንደዚያ እኔም በእናንተ ጎስቋላ ሕይወት መመራመሩን ወድጀዋለሁ፡፡ በነገራችን ላይ በዓለም ላይ እንደ ሁሉም እንድሆን ቢፈቀድልኝ የእናንተን እግዜር ግን መሆን አልፈልግም፡፡ ውዳሴና ምስጋናን አምርሬ እጠላቸዋለሁ፡፡ አስቡት እስቲ ወፈ ሰማይ መላእክት እግሬ ስር ጠብ እርግፍ ጧ ፍርጥ እያሉ ሲሰግዱልኝ ማየት እንዴት ያስጠላል? ለነገሩ የእናንተ እግዜር እና የምድር ነገስታት አንድ ናቸው፡፡ የሚገዙላቸውን ይወዳሉ፡፡ የሚያምፁትን በሰይፍ ይቀጣሉ፡፡ አለቀ፡፡ ትናንት ጣዖታቱ ሀውልቶች ነበሩ፡፡ ዛሬ ጣዖታቱ ከደመና በላይ ናቸው፡፡
“እኔ ለእናንተ አብጃለሁ፡፡ እናንተ ለእኔ ሙልጭ ያላችሁ እብዶች ናችሁ፡፡ በዚህ መሀል እውነት የለም፡፡
ለነገሩ እውነት አለ ከምል ሰይጣን አለ ብል ይቀለኛል፡፡ ይሄ የምርምሬ ግኝት ነው፡፡ ተብሰልሳይ ሰው ወታደር ቢሆን ጥይቱ ጥያቄው ነው፡፡ በተምሰልስሎት ውስጥ ጥያቄዎች አያልቁም መልሶችም አይነጥፉም፡፡ ሆኖም ሁሉም መረዳት፣ ሁሉም አስተውሎት የጥርጣሬ፣ የምናልባት ብቻ ነው፡፡
አሁን ሙሉ ለሙሉ አብጃለሁ፡፡ በምንም ለምንም የማልጓጓ፣ በምንም ለምንም የማልፈራ፣ በምንም ለምንም የማልደነግጥ… ሆኛለሁ፡፡ እንደ እናንተ የጊዜ ቅጣት እና በረከት ለእኔም ይደርሰኛል፡፡ ውርጩ ያወረዛኛል፡፡ ዝናቡ ያበሰብሰኛል፡፡ ፀሐዩ ያቃጥለኛል፡፡ አሁን ረሃብን ረስቸዋለሁ፣ ማፍቀር ተዘንግቶኛል፣ መጥላትም ተረስቶኛል፡፡ ...እናስ ዓለምን አላሸነፍኳትም ትላላችሁ? በምን ታታልለኛለች?”
                    ***
እንደ ዘበት በተጣለችው ወረቀት ላይ የተጻፈው ነገር ያነበባችሁትን ይመስላል፡፡ ቆይ ግን ከመጋቢው መንገድ ወጥቶ ዋናውን አስፓልት ሲቀላቀል ያየሁት የመሠለኝ ዕብድ የእኔ ጥላ ሳይሆን ይቀራል? ስለዚህ ወድቆ የተገኘ ወረቀት አለመኖሩንም ደርሰንበታል። እናም የፃፍነው እኛ ነን። ያበደውስ? እኛው?
ከአዘጋጁ- ፀሐፊውን በኢ-ሜል አድራሻቸው፡ This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it. ማግኘት ይቻላል፡፡

Read 637 times