Monday, 06 December 2021 00:00

“አጥር ውስጥ የመቀመጥ ባህርይ የለኝም”

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

  የሰዓሊ ዳዊት አድነው የስዕል አውደ ርዕይ በማልታ ደሴት


          ሰዓሊ ዳዊት አድነው በማልታ ደሴት ስሊማ ከተማ “Paved Road” በሚል ርዕስ ያዘጋጀው የስዕል  አውደ ርዕይ ለ18 ቀናት ለዕይታ ቀርቧል፡፡ ስራዎቹ የአፍሪካን ዘመነኛ ስነ ጥበብ ማስተዋወቃቸውን የጠቆመው የአገሪቱ ታዋቂ ጋዜጣ “ታይምስ ኦፍ ማልታ”፤ አውድ ርዕይ ማልታ ኢትዮጵያ ውስጥ ኤምባሲዋን በከፈተችበት ወቅት መዘጋጀቱ የዲፕሎማሲ ትስስሩን ያጠናክረዋል ብሏል፡፡
በስሊማ ከተማ በቲንዬ ጎዳና በሚገኘው ክሪስቲን ኤክስ የሥነጥበብ  አዳራሽ ውስጥ በተከፈተው አውደ ርዕይ  ላይ የሰዓሊ ዳዊት 19 የስዕል ሥራዎች ለዕይታ በቅተዋል፡፡ አብዛኛዎቹ  ሥራዎች ኤግዚቢሽኑ በታየበት ሰሞን የተሸጡ ሲሆን የተቀሩት ስራዎች የጋለሪው ቋሚ ንብረት ሆነው ይቆያሉ ተብሏል።
 ሰዓሊ ዳዊት አድነው ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ አለ የስነጥበብና ዲዛይን ትምህርት ቤት በግራፊክስ ዲዛይን የተመረቀ ሲሆን  ባለፉት 20 ዓመታት በግሉና በቡድን ከ30 በላይ  የስዕል አውደ ርዕዮችን በኢትዮጵያ፤ ኡጋንዳና ፈረንሳይ ከተሞች አሳይቷል፡፡
ከቅርብ ዓመታት ወዲህ የአፍሪካ ሥነ ጥበብ በአውሮፓና አሜሪካ  ተፈላጊ እየሆነ መምጣቱን   በክሪስቲን ኤክስ አርት ጋለሪ የተዘጋጀው ጋዜጣዊ መግለጫ ይጠቁማል፡፡  በአፍሪካ በስነጥበብ ላይ የሚሰሩ ሙዚየሞችና ጋለሪዎች እየበዙ መምጣታቸውን ያወሳው መግለጫው፤ አፍሪካውያን የስነጥበብ ባለሙያዎች አውደርዕዮችን በአውሮፓና አሜሪካ ከተሞች በስፋት እያቀረቡ ናቸው ብሏል፡፡
አውደ ርዕዩ ስነጥበብ ድንበር የለሽ መሆኑን አስገንዝቦኛል ሲል ለአዲስ አድማስ የገለፀው ሰዓሊ ዳዊት፤ “ስዕል በአጠቃላይ የዓለም ቋንቋ… የዓለም መስመር… የዓለም ቀለም ነው፡፡ ማንኛውም ሰው የሚረዳው ጥበብ ነው፡፡ በየአገሩ በየጊዜው የራሱ መገለጫ ይኖረዋል፡፡›› ብሏል፡፡
ለረጅም ጊዜ በሙከራና ምርምር ውስጥ መቆየቱን ሠዓሊ  ዳዊት  ይናገራል፡፡ ‹‹ ነገሮችን እያፈረስኩ እየገነባሁ የምሄድ ሰው ነኝ፡፡ እምነቴ ነው፡፡ አንድ ነገር የእኔ ብዬ ተመስጬ ተደላድዬ አልቆይም፡፡ ይህም የምፈልገውን ጥርጊያ መንገድ እንዳገኝ የረዳኝ አስተሳሰብ ነው፡፡ ኢትዮጵያዊ  የመሆኔን ያህል የዓለምም ዜጋ ነኝ፤ ስዕል የዓለም ቋንቋ ነው፡፡ እዚህ ባለቤት እንዳለው ሁሉ  በሌላ የዓለም ክፍልም ባለቤት አለው፡፡ ›› በማለት ሰዓሊው አብራርቷል፡፡
 በማልታ ያቀረብኩት አውደ ርዕይ አጠገቤ ላሉት ሰዓሊዎች መነቃቃትን ይፈጥራል የሚለው ዳዊት፤ ከስዕሎቹ ጋር ተያይዘው የወጡ ዘገባዎችና ፅሁፎችም ትልቅ  ዋጋ ያላቸውና የኢትዮጵያ ስነጥበብን የሚያስተዋወቁ ናቸው  ብሏል፡፡
የአገሪቱ ታዋቂ ጋዜጣ  “ታይምስ ኦፍ ማልታ” የዳዊትን የማልታ አውደ ርዕይ በተመለከተ   “Introducing Contemporary African Art” በሚል ርእስ ባወጣው ሰፊ ዘገባ፤ የዳዊት ስዕሎችን ከፈረንሳዊው ታዋቂ ሰዓሊ ፖል ጎጊንን ስራዎች ጋር በማነፃጸርና በማመሳሰል ሰፊ ሃተታ አቅርቧል፡፡   በአውደ ርዕዩ ላይ የቀረቡት ስዕሎች በአፍሪካ፣ በእስያና በፈረንሳይ  እንዲሁም በፖሊኔዢያ ካለው አኗኗርና የስነጥበብ ሂደት ጋር የተጣጣሙ መሆናቸውንም ጋዜጣው አትቷል፡፡
በአውደ ርዕዩ  አዘጋጅ ክሪስቲን ኤክስ አርት ጋለሪ  የተዘጋጀው መግለጫ እንደሚያወሳው፤ ኤውዤን ሄንሪ ፖል ጎጊን በህይወት ዘመኑ የሚገባውን ያህል  አድናቆት  ባያገኝም፣ ከሞቱ በኋላ ግን የተለዩ ቀለማትና የራሱን የአሳሳል ዘይቤ  በመጠቀም ስሙ የሚነሳ ሆኗል። የሕይወቱን የመጨረሻ ጊዜያት፣ለ10 ዓመታት ያል  በፈረንሳይ ፖሊኔዥያ  ደሴት ማሳለፉም ተጠቅሷል፡፡
“ሰዓሊ ዳዊት ልክ እንደ ጎጊን ሁሉ ደማቅ ቀለማትን   ከመጠቀሙም በላይ በብዙ ቀለማት መካከል ህብር ለመፍጠር ይታትራል፡፡  የሥነ ጥበብ ሥራዎቹን በሞቃታማ መልክዓ ምድር ከሚበዙት አረንጓዴና ሰማያዊ ዕፅዋት ድባብ ጋር አዋህዶ ነው የሚሰራቸው፡፡ ልክ እንደ ፈረንሳዊው ሠዓሊ በአገሩ የተፈጥሮ ቀለማት  ስዕሎችን ማስዋብ ይችላል” ሲልም አብራርቷል- መግለጫው፡፡
ሰዓሊ ዳዊት  ለአውደ ርዕዩ በተዘጋጀው ካታሎግ ላይ “መነሻዬ ሁልጊዜ በንድፍ፣ በመልክና በቀለም ከምገነዘበው እንቅስቃሴ ነው” ሲል የፃፈ ሲሆን ከፈረንሳዊው ሰዓሊ ጋር ለንፅፅር  መቅረቡን አስመልክቶ ለአዲስ አድማስ ሲናገር፤ ‹‹ከፖል ጎጊን ጋር ሲያነፃፅሩኝ ጥያቄዎች ተፈጥረውበኛል፡፡ ከሚያውቁት ነገር ተነስተው ንፅፅር ውስጥ ገብተው ሊሆን ይችላል፡፡ እኔም ደግሞ በአስተማሪዎቼ በኩል ተዋውቄው ይሆናል፡፡ የእኔ ጥናት በኢትዮጵያ ውስጥ ከኦሞ ዳሰነች፤ ከሱርማ የተነሳ ሊሆን ይችላል፡፡ ከሃይቲ ጋር የሚያዛምድና የሚመሳሰል ሁኔታ ሊፈጠር ይችላል፡፡ እኔ በዘመኔ የምሰራ ሰዓሊ እንደመሆኔ ዓለምን በሚያዛምዳት ነገር ሰርቼ ልገኝ እችላለሁ፡፡ ንፅፅሩ ጥሩ ስሜት ነው የሰጠኝ፡፡ ከፈረንሳዊው ጋር በአንድ መፈረጃችንን በፀጋ ነው የምቀበለው፡፡ ዳዊትን ግን ባስቀመጡት ፍረጃ ውስጥ እንደማይጠብቃቸው ማረጋገጥ እፈልጋለሁ፡፡ እኔ በምርምርና ጥናት ውስጥ ያለሁ አርቲስት ነኝ፡፡ አጥር ውስጥ የመቀመጥ ባህርይ የለኝም፣፡፡ ነገ ከነገ ወዲያ ስዕሌ እየተንደረደረ ሌላ ምዕራፍ ውስጥ እንደሚገባ አውቃለሁ፡፡›› ብሏል፡፡
ሰዓሊ ዳዊት  አድነው በአሁኑ ወቅት ከሰባት አመታት በፊት ባቋቋመውና ፒያሳ ራስ መኮንን ድልድይ በሚገኘው ክታብ የተባለው ስቱድዮ ውስጥ  እየሰራ ይገኛል፡፡ ከነፃ አርት ቪሌጅ መስራች አባላት መካከል አንዱ ሲሆን  ቦታው በመንግስት የመሰረት ልማት ግንባታ ዉስጥ ሲገባ  ከሁለት ዓመታት በፊት በጎማ ቁጠባ ግቢ በተመሰረተው “ኦዳ መደመር አፍሪካ የስነጥበባት ስፍራ” በስራ አስኪያጅነት ከማገልገሉም በላይ በስፍራው ከነበሩ ሌሎች ከ9 በላይ አርቲስቶች ጋር በጊዜያዊ ስቱድዮው እየሰራና በስነጥበብ ስራውም ላይ የተለያዩ ምርምሮችን እያከናወነ ይገኛል፡፡


Read 641 times Last modified on Tuesday, 07 December 2021 06:20