Sunday, 12 December 2021 00:00

ጠላትነትና ክፋት ከአጠገብ ነው። መቀራረብ፣ ለወዳጅነትና ለፍቅር እንዲሆንስ?

Written by  ዮሃንስ ሰ
Rate this item
(0 votes)

አብዛኛው ወንጀል የሚፈፀመው፣ በቤተሰብና በሚተዋወቁ ሰዎች መካከል ነው። ባሏ የሚደበድባት ሚስት በሰው እጅ ከተገደለች፣ ወንጀለኛው ሌላ ሳይሆን ቧላ ሆኖ ይገኛል - 90 በመቶ ያህሉ።
በወጣቶች ወይም በህፃናት ላይ የሚፈፀም የፆታ ጥቃትም፣ ከሩቅ ሰው አይመጣም። ከመጣም ጥቂት ነው። ከጎረቤት ከባልደረባ፣ ከወዳጅ ከዘመድ ነው፤ ወራዳ ጥቃት የሚከሰተው፤ እዚያው ከቅርብ፣ ከአይን ስር አጠገብ።
ኮሙኒስት ፓርቲዎች፣ እጅጉን አብዝተው የሚጠሉት፣ አምሳያቸውን ነው። ከአጠገባቸው የሚገኝ ኮሙኒስት ፓርቲ ነው፤ ዋና ጠላታቸው። ከሌላ አገር ኮሙኒስት ፓርቲ ጋር፣ አለማቀፍ የአጋርነት ማህበር ይመሰርታሉ።
እዚያው አገር ውስጥ ግን፤ እርስ በርስ በጥላቻ ይጠማመዳሉ። በሴራና በጭካኔ ይጠፋፋሉ። እንደየ አቅማቸው፣ አንዱ በድብቅ ሌላኛው በግላጭ፣ ከተቻለ ረግጦ ለመጨፍለቅ፣ ካልሆነም ከርክሮ ለመጣል ይጣጣራሉ። “የአገር ጠላት” እና “ፀረ ሕዝብ”፣ “አምባገነን ገዢ” እና “አመፀኛ ወንበዴ” ብለው እየተወነጃጀሉ አገርን ያናውጣሉ። የደርግ ዘመን ተፋላሚዎችንና ያስከተሉትን የእልቂት ታሪክ መቃኘት ትችላላችሁ።
በብሔር ብሔረሰብ ተወላጅነት የተቧደነ ፓርቲ ወይም ድርጅት፣ በዚያው ብሔረሰብ ስም ሌላ ፓርቲ ከተመሰረተ፣ እንቅልፍ አይኖረውም። ደመኛ ጠላቴ ነው ይለዋል - ከሃዲ፣ ባንዳ፣ ሰርጎ ገብ፣ ተለጣፊ እያሉ እርስ በርስ ይጠፋፋሉ።
በሌላ ብሔረሰብ ስም፣ ወይም በሌላ ብሔር ታፔላ የሚቋቋም ፓርቲ ከመጣባቸውስ? እንደሁኔታው ነው። ራቅ ያለ ከሆነ፣ የጋራ ግንባር ያቋቁማሉ። ከአጠገብ በቅርብ ርቀት ከሆነ፣ በተቀናቃኝነትና በጠላትነት ይፈራረጃሉ።
መጠጋጋት መወጋጋት የሚሆነው ለምንድነው?
ርቀት በጨመረ ቁጥር በወዳጅነት የመነጋገር እድል ይጨምራል። በተጠጋጉ ቁጥር ደግሞ፣ የጠላትነት ሰበብ ይበራከታል። ሲቀራረቡ፣ ስድብና ውንጀላ ይጧጧፋል። የመጠፋፋት ዛቻና ፉከራ ይንቀለቀላል።
ዘመዳሞች በአንድ ግቢ መኖር ሲጀምሩ፣ አክስት አጎት ሲጎራበቱ፣ ፍቅር የሚበዛ ይመስላል። ግን፣ ብዙም አይቆይም። ፀብ ውስጥ ይገባሉ።
በሆነ ምክንያት ቅርርብ ከተፈጠረ፣ ጠላትነት ይወለዳል።
ከመቶ ሃምሳ አመት በፊት አስቡት። ስለ ቻይናም ሆነ ስለ ጃፓን፣ ስለ አሜሪካም ሆነ ስለኖርዌይ፣ ስለ ራሺያም ሆነ ስለ ብራዚል፣… ቅንጣት የጠላትነት ሰበብ ማግኘት ከባድ ነበር። በዝና ወይም በተረት፣ ከርቀት የወዳጅነት ስሜት ለመፍጠር ይቀልላል።
ከጎረቤት አገር ጋር ግን፣ ይብዛም ይነስ፣ ቢዘገይም ቢያሰልስም፣ ጠላትነትንና ጦርነትን የሚለኩስ አይጠፋም።
“የእገሌ ጎሳ” በሚል ስም የሚቧደኑ ሰዎች፣ ውቅያኖስ ተሻግረው፣ አገራትን አልፈው አይዘምቱም። አጠገባቸው በጠላትነት የፈረጇቸው “የእከሌ ጎሳ” ተወላጆች ላይ ይዘምታሉ፣ አድብተው ይዘርፋሉ፤ አሸምቀው ይገድላሉ።
በምንም ሰበብ ቢሆን፣ በዘረኝነትም ሆነ በጭፍን የሃይማኖት ሰበብ፣ በጭፍን የፖለቲካ ፕሮፖጋንዳም ሆነ በቲፎዞ ስሜት ለጥፋት የሚነሳ ሰው፣ ሩቅ መሄድ አያስፈልገውም።
ወንዝ ከመሻገሩ በፊት፣ እዚያ በሰፈሩ፣ በመንደሩ፣ በከተማው ውስጥ ነው፣ ዝርፊያና ግድያ የሚፈፅመው - አብዛኛው ወንጀለኛ። ኪስ ለማውለቅ፣ ቤት ለመሰርሰር፣ ሩቅ መንደር አይሄድም።
“ወንጀል የምፈፅመው በባዕድ ከተማ ላይ ነው” ብሎ ቃል አይገባም። መውጫ መግቢያውን በሚያውቀው መንደር፣ አጥሩንና ቅያሱን በለመደው ሰፈር ነው የሚሰማራው። እሱም ነው የሚመቸው።
ደግሞም፣ የአለማችን ፖሊሶች ዋና ስራ፣ ከማርስ ወይም ከሌላ ሩቅ ዓለም የሚመጡ ወንጀለኞችን ለመከላከል አይደለም። የዚህችው የአለማችን ወንጀለኞችን ለመግታት እንጂ። አገሬው፣ ህግና ፍርድቤት፣ ፖሊስና እስርቤት የሚያቋቁመው፣ “የውጭ አገር ዜጎች መጥተው ወንጀል ይፈፅማሉ? በሚል ፍርሃት አይደለም።
በየከተማው፣ ፖሊሶች የሚሰማሩት፣ ተላላፊ መንገደኞችና የዳር አገር ሰዎች ወንጀል እንዳይፈፅሙ በመስጋት አይደለም። የዚያው የከተማው ወንጀለኞች ናቸው፤ ዋና የነዋሪዎች ስጋት።
እውነትም፣ መጠጋጋት አደገኛ ይመስላል። አማን ለመሆን ርቀትን መጠበቅ ሳይሻል አይቀርም። ግን፣…
ተያይተው የማያውቁ ሰዎችን ሁሉ ከየአቅጣጫው እየጎተተ የሚያገናኝ ዘመን ሲመጣስ? እጅግ የተራራቁ አገራትን የሚያቀራርብ ነገር ሲመጣስ? ድንበርና ባህር የማይገድበው፣ ቦታና ጊዜ የማይበግረው፣ ሁሉን የሚያዳርስና የሚያገናኝ አንዳች ተዓምር ሲፈጥርስ?
የሚያቀራርብ ተዓምር፣ የሚያቃቅር መዓት እንዳይሆን።
ቴክኖሎጂ፣ መሳሪያ፣ መርከብ፣ አውሮፕላን፣ ንግድ፣ ሳተላይት፣ ሚሳየል? ፅሁፍ፣ ሬዲዮና ቴሌቪዢን፣ ስልክ፣ ሞባይልና ኢንተርኔት፣ ፍልስፍና፣ ሳይንስ፣ ትምህርት፣ ሃይማኖት?
እነዚህ ሁሉ፣ በአንድ ወይም በሌላ መንገድ፣ የጊዜና የቦታ ርቀትን ይሽራሉ። አጥር ይጥሳሉ፤ ግንብ ያፈርሳሉ።
ሰውን ያገናኛሉ፤ ሰውን ያነካካሉም።
የተራራቁ ሰዎችን ያቀራርባሉ። የማይደራረሱ ሰዎችንም ያገጣጥማሉ። ያጋጫሉ።
በአንድ በኩል፣ ሰውን የሚያገናኙ ተዓምሮች፤ ሲሳይ ያመጣሉ።
ለመነጋገር፣ ለመገበያየት፣ ለመተዋወቅ ያመቻሉ። የመግባባት፣ የመተባበር፣ የመዋደድ እድልን ይከፍታሉ።
በሌላ በኩል ደግሞ፤ ሰውን የሚያቀራርቡ ተዓምሮች፤ ከእርግማን አይተናነሱም። ለዚያውም፣ “መዓት ይምጣባችሁ” የሚል ክፉ እርግማን ይሆናሉ እንጂ። ለምን በሉ።
መቀራረብ ማለት፤ ሁልጊዜ መከባበር ማለት ላይሆን ይችላላ።
“አወቅኩሽ ናቅኩሽ፤ ቀረብኩህ ጠላሁህ” ማለት ይመጣላ። ከዚህ ውጭ፣ ሌላ አይነት ትውውቅና ቅርርብ የማይጥማቸው የማይታያቸው ሰዎች ሞልተዋል።
በመቀራረብ - በገበያና በጦር ሜዳ።
“መጣሁ፣ አየሁ፣ ገዛሁ” ብሎ የሚደሰት ገበያተኛ ይኖራል። ሌሎች ገበያተኞች በፊናቸው፣ እሱ ያመጣውን አይተው ገዝተዋል፤ ተደስተዋል።
አዎ፣ ያኛውን ሸቀጥ ከሌላኛው እቃ ያማርጣሉ። በዋጋ ይከራከራሉ። ቅሬታና ወቀሳም ሊኖር ይችላል - ለግብይት ሲገናኙ።
ነገር ግን፣ ሁሉም ሰው፣ አንዳች ጠቃሚና አስፈላጊ ነገር ለማግኘት ነው የሚገበያየው። ጠቅሞ ለመጥቀም ነው።
በዋጋ ይደራደራል። ግን፣ የግል የንብረት ባለቤትን ከማክበር የሚመነጭ ነው - የዋጋ ድርድር። በግዴታ የሚሆን አይደለም። ግብይት ማለት፣ የትብብር ቅርበት ነው።
የገበያተኛ ግንኙነት፣ አንዱ ተጠቃሚና ሌላኛው ተጎጂ ለመሆን አይደለም። መስዋዕትነት ሰጪና ተቀባይ አይሆኑም። ይጠቅመኛል ብሎ ይሸጣል፤ ይጠቅመኛል ብሎ ይገዛል። ይሄ መልካም ቅርርብ ነው - የገበያ ቅርበት። ድንበር ማወቃቸው ጠቀማቸው።
“የሰው ንብረት አትመኝ” የሚል የስነምግባር ድንበር አላቸው። “በራስህ ጥረት ንብረት አፍራ” የሚል ነው የስነምግባር መርሃቸው። “የግል ንብረት አክብር፤ አትስረቅ፤ አትዝረፍ” የሚል የህግ ድንበርም አላቸው። በእነዚህ መርሆች እስከተራመዱ ድረስ፣ እነዚህን ድንበሮች እስካልጣሱ ድረስ፣ ቅርርብ መልካም ነው። መጠጋጋት ማለት፣ መጋጨትና መጠፋፋት አይሆንባቸውም።
“ቀጥቅጬ ገዛሁ” የሚል ሲመጣስ?
“I came, I saw, I conquered.” ብሎ የለ ቄሳር! ወደ ሩቅ አገር የዘመተ አይምሰላችሁ። የራሱን ወታደሮች እየመራ፣ ወደ መኖሪያ ከተማው፤ ወደ ሮም በመዝመት ነው፤ የቄሳርነት ታሪኩን የጀመረው። ቄሳር፣ የግል ስሙ ቢሆንም፤ ከሱ በኋላ ግን፣ ቄሳርነት ወደ ንጉሥነት የተጠጋ የስልጣን ስያሜ ሆኗል።
ከ”ቄሳር” የባሱ ደግሞ አሉ። የጥንቶቹ የአሲርያ ጦረኛ ንጉሦች፣ “ገዛሁ” ከማለት ይልቅ፣ “ገደልኩ፤ ደመሰስኩ” ማለት ይቀናቸው ነበር።
ስንቱን በጎራዴ ስንቱን በጦር እንደገደሉ፤ ስንት ሰው እንደሰቀሉና እንዳቃጠሉ፣ የስንት ሰው እጅና እግር እንደቆረጡ፣ ስንት ሕፃናትና ሴቶችን በባርነት እንደሸጡ፣ ስንት ከተሞችን እንደበዘበዙና እንዳወደሙ፣ በጀግንነት ስሜት እየዘረዘሩ በሃውልት አስቀርፀው ያስተክሉ ነበር።
በዛሬዋ ኢራቅ፣ ከሁለት ሺ ዓመታት በፊት፣ በነነዌ፣ በኒምሩድና በባቢሎን የነገሡ ሃያል ጦረኞች እንደምሳሌ ይጠቀሳሉ። የቅርብ የቅርቡን በመበዝበዝ ነው የሚጀምሩት። ዙሪያቸውን በጦርነት ማስገበራቸው አይገርምም። የአንዳንዶቹ ዘመቻ፣ ግን “ከማሸነፍ” እና ከማስገበር ያለፈ ነው።
The exploits of the conquerors are recorded in the Royal Annals, as the following example shows:
I felled 3,000 of their fighting men with the sword. I carried off prisoners, possessions, oxen and cattle from them. I burnt many captives from them.
I captured many troops alive, I cut off some of their hands and arms; I cut off of others their noses, ears and extremities.
I gouged out the eyes of many troops. I made one pile of the living and one of heads.
I hung their heads on trees around the city. I burnt their adolescent boys and girls. I razed, destroyed, burnt and consumed the city. (Quoted in J. Oates, Babylon)
ለጭካኔ፣ ይሄን ሁሉ ፉከራ ቢጨመርበት፣ የሚያምርበት መስሏቸው ይሆን? በእርግጥ፣ ከዚያው ከባቢሎን ነው፣ ባለብዙ አንቀፅ የሕግ አዋጅ በሰው ልጅ ታሪክ የተፃፈው። የባቢሎን ሥም፣ ከስልጣኔ ታሪክ ጋር የተዛመደው አለምክንያት አይደለም።  
ለማንኛውም፣…
ሰዎች ሲቀራረቡ፣ ለገበያ ሊሆን ይችላል - ለመሸጥ ለመግዛት። ለግጭትና ለጭካኔም ይሆናል - ለጦርነት፣ ለመግዛት፣ ለማውደም።
ሰዎች ሲቀራረቡ ለመግባባት ለመማማር ሊሆን ይችላል። እንደ ኮሙኒስቶች፣ እርስበርስ ለመተላለቅ፣ እንደ አክራሪዎች ለመጠፋፋት ሊሆን ይችላል።
ሰዎች ሲቀራቡ ለወዳጅነትና ለጋብቻ ሊሆን ይችላል። ተቧድኖ ለመጨፋጨፍም ይሆናል።
ለንግግር ጊዜ አለው፤ ለዝምታም ጊዜ አለው።
እውነት፣ እውቀት፣ ሳይንስ… ከሰሜንም መጣ ከደቡብ፣ ከመሃልም ሆነ ከዳር አገር፣ ችግር የለውም። ጎረቤትም ሆነ መንገደኛ፣ ቤተሰብም ሆነ የባሕር ማዶ ሰው፣… ማንኛውንም ሰው ሊያግባባ የሚችል አስተሳሰብ ሲኖር፣… መቀራረብ ማለት መወጋገዝ አይሆንም። እንዲያውም፣ መግባባት፣ እውቀት ስልጣኔና ሕይወት ይለመልማል። ታዲያ በዘፈቀደ አይደለም። መንገዳቸውን ማወቅና ድንበራቸውን መጠበቅ አለባቸው - ለመግባባት።
“ለእውነት መታመን፣ ውሸትን አለመቀበል ነው” የስነ ምግባር መርሁና ድንበሩ። አእምሮ የግል መሆኑን ማመንና ማክበር፤ የአእምሮ ነፃነትን አለመጣስ ነው፤ የህግ መርሁና ድንበሩ።
እነዚህ መርሆችና ድንበሮች እስከተከበሩ ድረስ፣ የሰዎች ቅርበት፣ የብርሃን በረከት ይሆናል።
ሳይንቲስቶች፣ በብዙ ሃሳብ ሊለያዩ፣ ሊከራከሩ፣ ትችትና ወቀሳ ሊሰናዘሩ ይችላሉ። ነገር ግን፣ ሁለት ሦስት የፊዚክስ ጎራዎች፣ አራት አምስት ተቀናቃኝ የሂሳብ ቡድኖች ተደራጅተው፣ እርስበርስ ለመጠፋፋት ጦርነት አውጀው የሚዘምቱበት አጋጣሚ፣ ኢምንት ነው - ለዚያውም ካጋጠመ ነው።
የሳይንስ ትምህርት በመላው ዓለም የተስፋፋው፣ በጦርነት ዘመቻ አይደለም።
ሃይማኖት ግን ከዚህ ይለያል። ብዙ ጦርነት ብዙ እልቂትና ውድመት በየዘመኑ እየተደጋገመ፣ መከራ ታይቷል - በሃይማኖት ሰበብ።
አስገራሚው ነገር፣ በሃይማኖት ሰበብ የተካሄዱት እልፍ ፀቦችና ጦርነቶች የተፈጠሩት፣ በጣም ተቀራራቢ ተብለው በሚጠቀሱ የሃይማኖት አይነቶች ስም ነው። ተመሳሳይ ሃይማኖትን ለመስበክ በተቧደኑ ጎራዎች አማካኝነት ነው፣ የጥፋት ዘመቻ የሚታወጀው።
ብዙ ጊዜም፣ በአንድ ሃይማኖት ተከታይ አማኞች መካከል ነው፣ ፀብና መጠፋፋት የሚከሰተው።
አፍሪካን፣ አውሮፓን ወይም የአረብ አገራትን ተመለከቱ። ተቀራራቢ በሆኑት በአይሁድ፣ በክርስትናና በእስልምና ሃይማኖቶች ሰበብ ብዙ ፀብ ብዙ ጥፋት ተፈጥሯል። በቻይና ወይም በጃፓን የተስፋፉ የሃይማኖት አይነቶችን የሚያንቋሽሽና ሃይለኛ የጥላቻ ስሜት ለማራገብ የሚሞክርብን ሰባኪ ግን ብዙ የለም። ለምን? ሩቅ ናቸው። በቦታ ቅርባችን አይደሉም። በሃይማኖት አይነትም ከአጠገባችን አይደሉም።
ብንቀራረብስ? ያኔ፣ ያሰጋል። በሃይማኖት ዙሪያ መከራከር ይመጣል። የሃይማኖት ክርክር ደግሞ፣ መቋጫ የለውም።
በአንዳንድ ነገር ላይ፣ ርቀትን መጠበቅ ሰላም አለው። በአንዳንድ ነገር ላይ ዝምታ ይሻላል፤ ወርቅ ነውም ይባላል።
ፍቅርና ድንበሩ
የግል ሕይወትንና ድንበርን ማጥፋት፣ የፍቅር ምልክት ይመስላቸዋል - ብዙ ሰዎች። ፍቅር የሚኖረው ግን፣ የየራሳቸውን ድንበር የሚያውቁ የተለያዩ ሰዎች (ግለሰቦች) ሲኖሩ ነው።
የግል ሕይወትና ማንነት ጠፍቶ፣ ሁሉንም ነገር የጋራ ለማድረግ የሚሞክሩ ሰዎች፣ “ቤቴ ቤታችሁ፣ ጓዳዬ ጓዳችሁ፣ ሃሳቤ ሃሳባችሁ፣ ንብረቴ ንብረታችሁ” በማለት፣ ለጊዜው በፍቅር የከነፉ ይመስላቸዋል። ብዙም አይቆዩም። ከሌላው ሁሉ የከፋ ጥላቻና ፀብ ነው መጨረሻቸው - በጣም የመረረ።
የሰው ሕይወት፣ የግል ህይወት ነው። ይሄ ነው እውነታው። የግል ማንነት ነው የግንኙነት መነሻ።
የግል ሃላፊነትን መውሰድና የራስን ስብዕና መቅረጽ፤ እያንዳንዱን ሰው እንደየስራው ማድነቅና መራቅ ነው፤ የስነ ምግባር መርህና ድንበር።
የግል ህይወትንና ማንነትን ማክበር፤ እያንዳንዱን ሰው እንደየስራው መዳኘት ደግሞ፣ ህጋዊ የፍትህ ድንበርና መርህ ነው።
የግል ማንነትን አክብረው፣ የግል ድንበርን ለሚጠብቁ ሰዎች፣ ቅርበት፣ የወዳጅነትና የፍቅር እድል ይሆንላቸዋል።Read 3521 times