Saturday, 11 December 2021 00:00

የኢትዮጵያ ፖለቲካ ከየት ወዴት?

Written by 
Rate this item
(0 votes)

     በአንጋፋው ፖለቲከኛና ምሁር እይታ

          የዛሬ እንግዳችን ፕ/ር አድማሱ ገበየሁ ናቸው፡፡ ፕ/ር አድማሱ ገበየሁ የቀድሞ አንጋፋ ፖለቲከኛ ምሁርና ተመራማሪ ናቸው፡፡ ለ16 ዓመታት በዩኒቨርስቲ መምህርነት፤ ከ25 ዓመታት በላይ በሃገር አቀፍ አህጉር አቀፍና አለማቀፍ ደረጃ በውሃ ሃብት ምህንድስና መምህርና አጥኚ ሆነው እያገለገሉ ይገኛሉ፡፡
በፖለቲካ ተሣትፎአቸው የቀድሞ ኢዴአፓ- መድህን ፕሬዝዳንት፣ በ1997 ደግሞ የቅንጅት ለአንድነትና ለዲሞክራሲ ፓርቲ ም/ሊቀ መንበር ሆነው መርተዋል። በተለይ የቅንጅት ም/ሊቀ መንበር በነበሩ ወቅት በቅንጅት ፅ/ቤት የሚከናወኑ ወሳኝ ተግባራትን ሲመሩ እንደነበር ይነገርላቸዋል። ከፖለቲካ ተሣትፎአቸው በመለስ ደግሞ በበርካታ ሲቪል ማህበራት አመራርነት አገልግለዋል፡፡ ከእነዚህ ውስጥ የኢትዮጵያ ሠብአዊ መብቶች ጉባኤ (ኢሠመጉ) የስራ አስፈጻሚ አባል በመሆን ያበረከቱት የጎላ ድርሻ ተጠቃሽ ነው፡፡ በሌላ በኩል በኢትዮጵያ ሲቪል መሀንዲሶች ማህበርና የወሎ ልማትና ተራድኦ ማህበር የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል እንዲሁም በኢትዮጵያ ዝናብና ውሃ  አጠቃቀም ማህበር አደራጅ ኮሚቴ ሊቀመንበር በመሆን ያገለገሉበትም ይጠቀሳል፡፡
በመምህርነትና ተመራማሪነት ደግሞ በአንጋፋው አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ፣በአርባ ምንጭ ዩኒቨርስቲ፣ በተለይም በሙያቸው የውሃ ምህንድስና ትምህርትን በኢትዮጵያ ካጎለበቱት አንጋፋ ምሁራን በቀዳሚነት ከሚጠቀሱት መካከል ናቸው፡፡
እኚህ የቀድሞ ፖለቲከኛና ምሁር በአሁኑ ወቅትም በጡረታ እድሜ ላይ ሆነው እሳቸውም  ቤተሰባቸውም ለአያሌ ዓመታት መቀመጫቸውን ባደረጉበት ስዊድን ሃገር በሚገኘው ስቶኮልም  ሮያል ኢንስቲቲዩት ኦፍ ቴክኖሎጂ እና ሌሎች አለማቀፍ ዩኒቨርስቲዎች ውስጥ  በማስተማር ስራ ላይ ይገኛሉ፡፡
አንጋፋው ፖለቲከኛ መምህርና ተመራማሪ ፕ/ር አድማሱ ገበየሁ ከሶስት ዓመታት በፊት ኢትዮጵያም  ሆነች  ኢትዮጵያውያን ሊመሩበት ይበጃል ያሉትን የፖለቲካ ፍኖተ ካርታ የሚያመለክት “መግባባት፡- ፖለቲካዊ እኩልነት ለሁሉም ኢትዮጵያውያን” የተሰኘ መፅሐፍ አበርክተው ነበር፡፡ ረጅም የፖለቲካ ተሳትፎ ያላቸው ፕ/ር አድማሱ ገበየሁ፤ አሁን በአዛውንትነት እድሜ ላይ ሆነው ሃገር እንዴት ከፖለቲካዊ ችግሮች ትውጣ የሚለው የዕለት ተዕለት ጭንቀታቸው እንደሆነ ይናገራሉ፡፡
እኒሁ አንጋፋ ፖለቲከኛና ምሁር ከህይወት ልምዳቸው ከምርምርና ጥናታቸው እየጨለፉ ለሃገር ይበጃል ያሉትን መፍትሔ  ለአዲስ አድማስ ጋዜጣ አጋርተዋል፡፡ ጋዜጠኛ አለማየሁ አንበሴ ከፕ/ር አድማሱ ገበየሁ ጋር ያደረገው ቃለ ምልልስ እንደሚከተለው ተጠናቅሯል፡፡ መልካም ንባብ፡-


           ለበርካታ ዓመታት ከፖለቲካው መድረክ ገለል ብለው ቆይተዋል፡፡ ለምንድነው  ከፖለቲካው አካባቢ የጠፉት?
ከ1997 ዓ.ም በኋላ በሃገራችን የፖለቲካ እንቅስቃሴ ለማድረግ አመቺ ሁኔታ አልነበረም፡፡ አብዛኞቹ የቅንጅት አመራሮች እስር ቤት ነበሩ፡፡ ከእስር ቤት ውጪ የነበርነውም የፖለቲካ ሜዳው ወደ መዘጋት ሲደርስና አደጋዎች እያንዣበቡ ሲመጡ፣ እዚህ ሃገር ለመኖር አዳጋች ስለነበር፣ እኔም ባለቤቴም ለመሰደድ ተገደናል። በወቅቱ እኔ  ቀደም ብሎ የማውቀውና የተማርኩበት በተለይም ፒኤችዲ ዲግሪዬን ያገኘሁበት ሃገር ስዊድን ነበር፡፡ ለልጆቼም ለኔም የሚመቸው ሃገር ስዊድን ነው ብለን ወደዚያው አቀናን፡፡ ስዊድን ከገባን በኋላ ብዙዎች እንደሚሉት ውጪ ሆኖ የፖለቲካ ትግል መታገል አልቻልንም፡፡ በኔ እምነት አንድ የፖለቲካ እንቅስቃሴን የሚመራ ሠው በቅርበት ከሌለ፣ ከባህር የወጣ አሳ ነው የሚሆነው፡፡ ትግሉም ድሉም ሃገር ቤት ነው መሆን ያለበት፡፡ እኔ ውጪ ሆኜ በማይሆን ነገር መመፃደቅ አልፈለግሁም፡፡ በወቅቱ እኔ ከባህር የወጣ አሣ ሆኛለሁ፡፡
ከፓርቲ ፖለቲካ ነው ወይስ ከማንኛውም የፖለቲካ እንቅስቃሴ ነው የወጡት?
እዚህ ሆኜ በኢትዮጵያ ውስጥ የዲሞክራሲያዊ ስርዓትን እውን ለማድረግ ነበር የምታገለው ይህን ግን የግድ የፖለቲካ ፓርቲ በመምራት ብቻ አይደለም የምታከናውነው፡፡ በሲቪል ማህበረሰብ መሪነት ሊሆን ይችላል፡፡ ይሄም ቢሆን እዚሁ ሃገር ቤት መሆን አለበት፡፡  በግልም ሊሆን  ይችላል፡፡ በግል በሚሠራበት ጊዜ በተለያየ መንገድ መታገል ይቻላል፡፡ እኔ ያደረግሁት ምንድን ነው? መጀመሪያ በራሴ የእስከዛሬ አካሄድ ላይ ጥያቄ ነው ያነሳሁት። እስካሁን ድረስ በፖለቲካ ፓርቲ አባልነት ከዚያም አልፎ በአመራርነት፣በሲቪል ማህበረሰብ እንቅስቃሴ ውስጥ  በመሪነት ስሳተፍ ቆይቻለሁ፡፡ ለመሆኑ የማደርጋቸው ነገሮች በሙሉ ትክክል ነበሩ ወይስ ስህተት ነበረባቸው? የሚለውን ጥያቄ ለማንሳትና በዚህ ላይ ምርመራ ለማድረግ እድል አገኘሁ፡፡ ይሄን በማደርግበት ጊዜ አንዳንድ ሃሳቦች ቀደም ብሎም ነበሩ። ለምሳሌ በፈረንጆች 2000 ዓ.ም ላይ ለንደን ውስጥ ሆኜ የተለያዩ መፃህፍት ቤቶች ውስጥ እየተዟዟርኩ ስመለከት፣ አንድ ቀልቤን የሳበው መፅሐፍ አገኘሁ። በሳንድያጎ ስቴት ዩኒቨርስቲ የፖለቲካል ሳይንስ ትምህርት ክፍል ሃላፊና ተመራማሪ የሆነው አሜሪካዊ አረን ላንድፎርድ የፃፈው መፅሐፍ ነበር፡፡ ገና የመፅሐፉን  መግቢያ ገለጥ ገለጥ  ሳደርግ  ብዙ ጊዜ ጭንቅላቴ ውስጥ የሚመላለሱ ነገሮች አየሁኝና፣ ያንን መፅሐፍ ምንም ሳላቅማማ ገዛሁት፡፡ መኝታ ክፍሌ ውስጥ ሆኜ ሳነብ በመጀመሪያ ቀን እንቅልፍም አልወሰደኝም አነጋሁበት፡፡ በቃ ይሄን ነበር የምፈልገው፡፡ ከዚያ ጊዜ ጀምሮ አብዛኛዎቹን ጥያቄዎቼን ሊመልስልኝ የሚችል መሪ አገኘሁ ማለት ይቻላል፡፡ ያንን መፅሐፍ ካነበብኩ በኋላ በሃገራችን ውስጥ ሊሆን የሚገባው የዲሞክራሲያዊ አስተሳሰብ መመራት ያለበት በመግባባት (ኮንሰንሰስ) ሞዴል ነው ብዬ ወሰንኩ፡፡  ይሄን ሃሳብ ይዤ ወደ ሃገር ቤት ከተመለስኩ በኋላ በቅንጅት እንቅስቃሴም፣ በአጠቃላይ ባለኝም አስተሳሰብ በማራምደውም ፖለቲካ ውስጥ እንደው እንዳለ ባትገባበትም በተለያየ መልኩ በመግባባት ሞዴል ውስጥ ያሉ ሃሳቦች በቅንጅት ማኔፌስቶ ላይም አሉ። ሌሎችም ያዘጋጀኋቸው ፅሁፎች ውስጥ አሉ፡፡ በዚህ መንገድ የሃሳቡን ዘር በተለየ መንገድ  መትከል ጀምሬ ነበር፡፡ ከዚያም በኋላ ውጪ ሃገር መጥቼ ትንሽ ፋታ ሳገኝ ይሄ ሞዴል ለኔም በሁለንተናዬ ሠርጎ እንዲገባ የማድረግ እድል አገኘሁ፡፡
በሌላ በኩል ይሄን ሞዴል ይዤ የንፅፅር ጥናት ማድረግ ጀመርኩ፡፡ በአጠቃላይ በዲሞክራሲ ውስጥ ባሉ ሃገሮች ይሄን ሞዴል ማሰስ ጀመርኩ፤ እናም ያገኘሁት ውጤት ያመለከተኝ  የዓለም ዲሞክራሲዎች በሁለት ዋነኛ ጎራ የተሰለፉ መሆናቸውን ነው፡፡ አንደኛው የመግባባት ዲሞክራሲ ሲሆን ሌላኛው የአብላጫ ዲሞክራሲ ነው። የአብላጫ የሚባለው ባጭሩ ሲገለፅ፤ አሁንም በሃገራችን ውስጥ የሚንፀባረቀውና እንገነባዋለን እያልን የምንዳክርበት ነው። በአንፃሩ ደግሞ የመግባባት ዲሞክራሲ የተመጣጣኝ ውክልና ስርዓት ነው፡፡  የተመጣጣኝ የምርጫ ስርዓትን ተግባራዊ ከማድረግ ነው የመግባባት ዲሞክራሲ የሚጀምረው፡፡ በአብላጫ ምርጫ ስርዓት ግን ወደ መግባባት ዲሞክራሲ መግባት አይቻልም፡፡ እኔ 136 ሃገሮችን በንፅፅር ተመልክቻለሁ፤ ከእያንዳንዱ አገራት ልምዶችን አግኝቻለሁ፡፡
እርስዎ የመግባባት ዲሞክራሲን ሞዴል አስመልክቶ ዝርዝር የጥናት ውጤቶችን ያካተተ መፅሐፍ ከ3 ዓመት በፊት ፅፈዋል። ይህ መፅሐፍ ምን ያህል ለህብረተሰቡ ተደራሽ ሆኗል ማለት ይቻላል?
እኔ መፅሐፉን ስፅፍ ብዙ ነገሮች ግልፅ አልነበሩም፡፡ የማውቀው ነገር በወቅቱ  የኢትዮጵያ ህዝብ አምርሮ እየታገለ ነው። ከጊዜ ወደ ጊዜ ብሶቱ እያስተሳሰረው አንድ ላይ እያደረገው ነበር፡፡ በዚህ ላይ መንግስት የሚታለልለት ሰው እየቀነሰ፣ ትግሉ ወሣኝ ሁኔታ ላይ እንዳለ ይሰማኝ ነበር፡፡ ለውጥ እንደሚመጣ እርግጠኛ ነበርኩ፡፡ ይሄ ለውጥ ግን እስከዛሬ እንደ ነበሩት ለውጦች አልነበረም፡፡ እንዳይቀለበስ ሁሉም ሊሠራ ይገባ ነበር፡፡ ለውጡ ሲመጣ ችግር አልነበረውም፡፡ ከዚያስ? የሚለው ላይ  ትክክለኛ አቅጣጫ (ሮድማፕ) መነሻና መድረሻ ግቡን የምናገኝበት መሠላል ወለል ብሎ ሊታየን ይገባል፡፡ በዚሁ ጉዳይ ላይ በወቅቱ ራሴን እንደ ባለድርሻ  ማድረግ ነው የፈለግሁት፡፡ እኔ ጋ ያለው ሃሳብ ደግሞ መውጫው መንገድ መፅሐፍ ነበር። መፅሐፉን በአማርኛ መፃፍ እንዳለብኝ አመንኩ፡፡ መፅሃፉም ከባህላዊ እሴታችን ጋር የመግባባት ዲሞክራሲ እሴቶችን ያዛመደ ሆኖ እንዲዘጋጅ ያስፈልግ ነበር። እኛ የምንከተለው ተግባር ላይ ያለው የአብላጫ ዲሞክራሲ ስርዓት ከባህላችን ጋር ምንም ቁርኝት ያለው አይደለም፡፡ በአንጻሩ የመግባባት ዲሞክራሲ ግን  ከእርቅ ሽምግልና ስርዓታችን፣ በውይይት የጋራ መግባባት ላይ የመድረስ የማህበረሰባችን የቆየ እሴት ጋር ጥብቅ ቁርጠኝነት ያለው ሲሆን ተጋግዞና ተረዳድቶ እየተግባቡ መሄድ የሚያስችል ሆኖ ነው ያገኘሁት። በመግባባት ዲሞክራሲ ፓርቲዎች አብረው በጋራ በመግባባት ይሰራሉ፡፡ እንደ አብላጫ ድምጽ ስርዓት 51 በመቶ ያገኘው ሁሉንም ጠቅልሎ፣ 49 በመቶ ያገኘውን አርፈህ ተቀመጥ የሚልበት አይደለም፡፡ ሁሉም የየድርሻውን የሚያገኝበት ነው፡፡ በተለይ እንደኛ አይነት ብዝሃነት የበዛበት ሃገር ላይ  በልሙጥ አስተሳሰብ መሄድ የትም አያደርስም፡፡ ስለዚህ ለኛ የሚበጀው የመግባባት ዲሞክራሲ ነው፡፡ ይሄ እንዴት ይሆናል የሚለው ነው በመፅሐፉ በዝርዝር ለማቅረብ የተሞከረው፡፡
ይህ መፅሐፍ ወይም ሃሳቡ አሁን ሃገር እየመሩ ላሉ አካላት  ደርሷል  ብለው ያምናሉ?
ለተወሰኑ መድረሱን የማውቅበት መንገድ አለኝ፡፡ ግን እገሌ ጋር ሃሳቡ ደርሷል ብዬ ለይቼ ለማስቀመጥ አልችልም፡፡ መፅሐፉ ታትሞ በአዲስ አበባ ተሰራጭቷል፡፡ በኢ-ሜይል ደግሞ ከሁለት ሺህ በላይ ሰዎች በሶፍት ኮፒ እንዲደርሳቸው አድርጌያለሁ። ከዚህ በመለስ ግን የጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይን ተግባራት ስከታተል ሃሳቡ እንደደረሳቸው እንድገምት የሚያደርገኝ ነገር አለ፡፡ በተለይ ሴቶችን ወደ ስልጣን በማምጣት በኩል በተለያዩ ተቋማት ውስጥ ለውጥ ለማምጣት ያደረጉት ጥረት ካሰብኩት በላይ ሆኖ ነው ያገኘሁት፡፡ የእኔ መፅሐፍ ውስጥ የሴቶችና የወንዶች የፖለቲካ ሚና እኩል መሆን አለበት ይላል፡፡ ምክንያቱም እኛ የሳባ ልጆች ነን፤ የሴቶች የፖለቲካ ተሣትፎ ምን እንደሆነ በሚገባ እናውቃለን። ምናልባት ታሪካችንን ማስታወስ ብቻ ነው የሚጠበቅብን። ይሄን ማድረግ በባህላችን በልማዳችን የሚከብድ ነገር የለውም። አሁን በዶ/ር ዐቢይ ያሉ በጎ አመራሮች በሙሉ በተቋም ደረጃ በጠበቀ መሰረት ላይ መተከል አለባቸው፡፡ ለዚህ ደግሞ በመፅሐፉ ላይ ያመለከትኳቸው የጥናት ውጤት ሃሳቦች እንደ አንድ  አማራጭ ሆኖ  ሊቀርብ ይችላል፡፡ አሁንም አጥብቄ የማሳስበው በጎ እሳቤዎች በተቋሞች መገንባትና መፅናት ነው ያለባቸው፡፡ ሌላው የመግባባት ዲሞክራሲን እውን ለማድረግ ሃሳብ እንዳለ የምረዳበት፤ በቅርቡ ተቃዋሚ ፓርቲዎችም የስራ አስፈፃሚ አባል ሆነው በፖለቲካው እንዲሳተፉ የተደረገበት መንገድ ነው። ግን ይህም በህግና በተቋም የተመሰረተ አይደለም፡፡ በበጎ ፍቃድ የተደረገ ነው፡፡
ከእርስዎ ጋር ቃለ ምልልስ በምናደርግበት ወቅት ሃገራችን በጦርነት ላይ ናት፡፡ ይህ አይነቱ ጦርነት ደግሞ በየተወሰነ ዓመታት እየዞረ የሚመጣ ሆኖ እናገኘዋለን፡፡ ለምን ይሆን ከዚህ የጦርነት አዙሪት ታሪክ መላቀቅ ያልቻልነው? እርስዎ የሚያራምዱት የመግባባት ዲሞክራሲ ለዚህ ሁነኛ መፍትሔ ይኖረው ይሆን?
እንግዲህ እነዚህ ጦርነቶች በተለይ የድሮዎቹና የአሁኑ በባህሪያቸው የተለያዩ ናቸው፡፡ አብዛኛዎቹ ግጭቶች ግን ለስልጣን ሲባል የሚደረጉ፤ ስልጣን ከመያዝ ጋር የተያያዙ ናቸው፡፡ እነዚህ ለስልጣን ተብለው የሚፈጠሩ ግጭቶች በየጊዜያቸው አይነታቸውም ይዘታቸውም ይለያያል። እኛ ሃገር ስልጣን ለሁሉም ክፍት ነው። የአንድ ትውልድ ሃረግን ተከትሎ የመሄድ ዘለቄታዊ ልማድ የለውም። ተሞክሯል፤ ነገር ግን ብዙም አልተሳካም። በሃይማኖት የተለያዩ ወገኖች ስልጣን ለመያዝ ሞክረው ይዘዋል። የሃገራችን ስልጣን ዝም ብሎ አንዱ ወገን ብቻ ርስቱ አድርጎ የያዘው አይደለም። ለሁሉም ክፍት የሆነ ነው፡፡ ይህ መሆኑ ደግሞ ስልጣን ለመያዝ የሃይል አማራጮች ናቸው ጥቅም ላይ ሲውሉ የነበረው። ስልጣኑን ቶሎ ለመያዝ ጦርነቶች ይካሄዱ ነበር፡፡ ይሄ የዘመናት ታሪካችን ነው፡፡ አሁንም በዚህ አዙሪት ውስጥ መቆየታችንና በምርጫ መንግስት የመቀየር የዲሞክራሲ መሠረት ላይ አለመገኘታችን የሚቆጭ ነው፡፡ ሆኖም ግን ኢትዮጵያን ለማስተዳደር አንደኛው ሲፈጠር ጀምሮ ለዚያ የተቀባ፣ ሌላኛው ዝም ብሎ ተገዢ ሆኖ አለመለመዱ ትልቅ ነገር ነው። አሁንም የገባንበት ጦርነት ይሄው አዙሪት መቀጠሉን የሚያመለክት ነው፡፡ ነገር ግን አሁን በሌላ ጫፍ ሆኖ ጦርነቱን የሚያደርገው አካል 27 ዓመት ሙሉ ስልጣን ይዞ የተፈተነ፣ በታሪክ አጋጣሚ በህዝብ መገፋት ከስልጣኑ የተባረረ ነው፡፡ ይሄ ሃይል ከዚህ በኋላ በጦርነት አሸንፎ ስልጣን እይዛለሁ፤ ሌላውን ህዝብ እንደቀድሞ እመራለሁ ወይም ህዝቡ ይመራልኛል የሚል መተማመን የለውም። ይሄን ማድረግ እንደማይችል በሚገባ ያውቀዋል፡፡ ይሄ ጦርነት ከዚህ ቀደም በታሪካችን ካስተናገድናቸው ለስልጣን ተብለው ከሚደረጉ ጦርነቶች የተለየ ነው የምልበት አንዱ ምክንያት ይሄ ነው፡፡ ተሸናፊ እያሳደዱ መውጫ መግቢያ ማሳጣት የሚባል ነገር አልነበረም፡፡ አሁን ግን ያለው ከዚያ ፈጽሞ የተለየ ነው፡፡
ስለዚህ ይሄን ግጭት ከቀድሞዎቹ ጋር እናመሳስለው  ከተባለም ለስልጣን የሚደረግ መሆኑ ላይ ብቻ ነው፡፡

Read 744 times