Tuesday, 14 December 2021 00:00

የመቀሌው የመልስ ጉዞ!!

Written by  አያሌው አስረስ
Rate this item
(0 votes)

 "ትሕነግ በአፋርና በአማራ፣ በተለይ ደግሞ በገባበት የአማራ አካባቢ ሁሉ ጦሩ ንብረት እንዲዘርፍ፣ መዝረፍ ያልቻለውን እንዲያወድም፣ ከጥቅም ውጪ እንዲያደርግ፣ ሴቶችን እንዲደፍር፣ ተቋማትን እንዲያፈራርስ መመሪያ ሰጥቶ በፈጸመው ወንጀል ሁሉ መጠየቅ እንዳለበት መዘንጋት አይገባም፡፡--"
           
           ባለፉት ሁለት ሳምንታት የአገርን ህልውና ለማስከበር እየተካሄደ ባለው ጦርነት ከፍተኛ ለውጥ ታይቷል፤ እሰይ የሚያሰኙም ድሎች ተመዝግበዋል። አዲስ አበባ ለመግባት ምን ቀረን ያለው ትሕነግ፤ ከደብረ ሲና ከመሐልሜዳ፣ ከከምሴና ከሌሎችም አካባቢዎች እየተመታ ወደ ኋላው እንዲመለስ ተደርጓል። ደሴና ኮምቦልቻን፣ መሐል ሜዳን፣ ጋሸናን፣ ላሊበላን፣ ሀይቅን  ቢስትማን እንዲለቅ ተገድዷል። “ሚሌ ወይም ሞት” በማለት ለወረራ ቢመጣም፣ ተደጋጋሚ ሽንፈት ደርሶበት ካሳጊታን ብቻ ሳይሆን ባቲንም ለቅቋል።
ጉልበታቸውን፣ እውቀታቸውን ፣ አካላቸውንና ሕይወታቸውን መስዋዕት አድርገው ይህን ድል ላስገኙ ለየአካባቢው መረጃ ሰጪ  ገበሬዎች፣  ለአማራና አፋር ልዩ ሃይልና ሚሊሽያ እንዲሁም ለአማራ ፋኖዎች ያለኝን አክብሮት ከልብ እገልጻለሁ። ለእነሱ ብቻ አይደለም፣ ራሳቸው ወደ ዘመቻው ገብተው የጦርነቱን ሂደት ለለወጡት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ፣ “እኛስ” ብለው ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጎን ወደ ጦር ሜዳ ለገቡት አቶ ክርስቲያን ታደለ፣ እንደ የሱፍ ኢብራሂም፣ እንደ ሻለቃ አትሌት ኃይሌ ገብረ ሥላሴ፣  እንደ ታማኝ በየነ፣ እንደ አቶ ንአምን  ዘለቀ፣ እንደ  አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ ያሉትንም አመሰግናለሁ። ምስጋናዬና አክብሮቴ በዚህ አይቆምም። እንደ አቶ ወርቁ አይተነውና እንደ አቶ በላይነህ ክንዴ ያሉ ባለሃብቶችንም ይጨምራል። ክብር ለእናንተ ይሁን።
ጦርነቱ አሸባሪውን ትሕነግ ከአማራና አፋር ክልል በማስወጣትና ወደ ትግራይ እንዲመለስ በማድረግ መቆም የለበትም። ትግራይም የትሕነግ ርስተ ጉልት ከመሆን መጽዳት አለባት። የትግራይ መሬት ለትሕነግ እንደተፈለፈለባት ሁሉ መቀበሪያውም መሆን አለባት።
ትሕነግ በአፋርና በአማራ፣ በተለይ ደግሞ በገባበት የአማራ አካባቢ ሁሉ ጦሩ ንብረት እንዲዘርፍ፣ መዝረፍ ያልቻለውን እንዲያወድም፣ ከጥቅም ውጪ እንዲያደርግ፣ ሴቶችን እንዲደፍር፣ ተቋማትን እንዲያፈራርስ  መመሪያ ሰጥቶ በፈጸመው ወንጀል ሁሉ መጠየቅ እንዳለበት መዘንጋት አይገባም፡፡
አሸባሪው ትሕነግና አመራሩ በአማራና በአፋር  ሕዝብ ላይ የከፋ በደል እንዲደርስ የመንግስትና የግለሰቦች ንብረት እንዲዘረፍ፣ ወደ ትግራይ እንዲጫን፣ መጫን ያልቻለውን እንዲያወድም ያደረገው፣ የትግራይን ሕዝብ ከአማራና ከአፋር ሕዝብ ጋር ደም አቃብቶ ወገን በማሳጣት መደበቂያው ለማድረግ አስቦ በመሆኑ፣ ይህ  እድል ፈጽሞ  ሊሰጠው አይገባም።
ትህነግ ራሱ በሸረበው ሴራ ከማዕከላዊው መንግስት ተገፍቶ እንዲወጣ እንደተረገው ሁሉ ከትግራይ ህዝብ ልብ ውስጥም ተነቅሎ እንዲወጣ መደረግ አለበት። በአማራም ሆነ በአፋር ክልል ለወንጀል ሥራ ያሰማራው ሰራዊቱ የፈጸመውን እያንዳንዱን ድርጊት ለትግራይ ህዝብ ማጋለጥና በህዝቡ እንዲጠየቅም ማድረግ  ያስፈልጋል።
በትሕነግ ዘንድ ንብረት መዝረፍና ወደ ትግራይ መጫን አዲስ ነገር አይደለም። በዚህ ዓመት ያመጣው አዲሱ ጉዳይ መውሰድ የማይችለውን ንብረት ጥቅም ላይ እንዳይውል አስቦና ይሁነኝ ብሎ መሰባበርና ማበላሸት ነው። ሊጠገን እንዳይችል አድርጎ ያፈረሰውንና ያደቀቀውን ንብረት መመለስ ባይቻል እንኳን፣ መቀሌ የጫነውን ንብረት  ከተደበቀበት ወይ ከተከማቸበት ቦታ አውጥቶ ለባለቤቱ  መመለስ ያስፈልጋል። ይህ የመከላከያ ኃይሉና የፌደራል መንግስት አንድ ስራ መሆን አለበት።
መንግሥት ወደ መቀሌ የሚያደርገው ቀጣይ ጉዞ  ከቀደመው ስህተቱ የተማረበት መሆን አለበት። የተደላደለ  ሰላማዊ ሁኔታ እስኪፈጠር ድረስ የክልሉ አስተዳደር በቀጥታ በማዕከላዊ መንግሥት በወታደራዊ አስተዳደር ሥር (ኮማንድ ፖስት) የሚመራ መሆን  ይኖርበታል። የክልልና የዞን፣ የወረዳና ከተማ አስተዳደሮች በሚታመኑ የመከላከያ አባላት እጅ መያዝ አለበት። ይህ ደግሞ በጦርነት በተሸነፉ አካባቢዎች በዓለም ዙሪያ ሲፈጸም የኖረ በመሆኑ፣ በትግራይ እንደ አዲስ አሰራር  ሊቆጠር አይችልም።
በአውሮፓ በአሜሪካና በአፍሪካ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን ባደረጉት ተከታታይ ሰላማዊ ሰልፍና ዘመቻዎች፣ በኢትዮጵያ መንግስት ላይ የሚደረጉ የውጭ ተፅዕኖዎች እየቀነሱ መጥተዋል፡፡ ይህ ተስፋ ሰጪ ነው። ቢሆንም አሁንም መዘነጋት  አይገባም፡፡
አሸባሪውን ትህነግን በዓለም አቀፍም ሆነ በሀገር አቀፍ ደረጃ በፕሮፓጋንዳ መምታት የሚቻለው እሱ የፈጠረውን ወሬ በማስተባበል ሳይሆን፣ የሱን ደረቅ ወንጀሎች ወደ አደባባይ በማውጣት ዓለም እንዲያያቸውና እንዲነጋገርባቸው  በማድረግ ነው። በዚህ ረገድ የመንግስት የግንኙነት ቢሮ (ኮምኒኬሽን) ከምንጊዜውም የበለጠ ታጥቆ ሊነሳ ይገባል። ዓለም አቀፍ የመገናኛ ብዙኃንን ነጻ ወደወጡ አካባቢዎች በመውሰድ የጅምላ መቃብሮችን እንዲመለከቱ፣ በደል የተፈጸመባቸውን ሰዎች እንዲያነጋግሩ ማድረግ፣ የተዘረፉና የወደሙ ተቋማትን  ማስጎብኘት አለበት።
የፕሮፓጋንዳ ዘመቻ ለተከፈተበት መንግሥት ጥብቅና የመቆም ኃላፊነት የተሰጠው የመንግሥት ኮምኒኬሽን ቢሮ፣ መንግሥትን ሊያገለግልና ሊጠቅም የሚችለው ቀድሞ መረጃዎችን ወደ ሕዝብ ሲያደርስና የተዛቡ ታሪኮችን ሲያጋልጥ ብቻ መሆኑን ለአፍታ መዘንጋት የለበትም። እውነትን ቀድሞ መናገር ፈጥሮ የሚዋሽን ከመከላከል በላይ የቀለለ ሥራ መሆኑን መረዳት ተገቢ ነው።
ክብር አገር ሰው በምትፈልግበት ሰዓት ሰው ሆነው ለቆሙላት ሁሉ!!

Read 7538 times