Saturday, 11 December 2021 13:35

በአማፂው የህወኃት ሃይሎች መዓት የወረደባት ጭና

Written by  ናፍቆት ዩሴፍ
Rate this item
(0 votes)


            አማፂው የህወኃት ሀይል ጎንደርን ለመውረርና ለመቆጣጠር ሲያልም አቆራርጦ የመጣው በዳባት ወረዳ ጭና ቀበሌ በኩል ነበር፡፡ ነሐሴ 24 ቀን 2013 ዓ.ም ሌሊት 10 ሰዓት ላይ ያልታሰበ አደጋ በጭና ነዋሪዎች ላይ ተከሰተ፡፡ የአሸባሪው ሀይል ወታደሮች የከባድ መሳሪያ እሩምታ ማውረድ ጀመሩ፡፡ ህዝቡ በድንጋጤ ማቄን  ጨርቄን ሳይል፣ ህፃናት አዛውንቱን በጨለማ እየጎተተ ሽሽት ጀመረ።  መሸሽ ያልቻለው በአሸባሪው ሃይሎች ታፈነ። ታይቶና ተሰምቶ የማያውቅ ግድያና ዝርፊያ መፈጸሙን በህይወት የተረፉ የጭና ነዋሪዎች  ይናገራሉ። አንድ ሰው እስከ 7 የሚደርሱ የቤተሰብ አባላቱ በአሸባሪው ሃይሎች ተገድለውበታል። እርሻው ወድሞበታል። ቤት ንብረቱ ተዘርፎበታል። በመጨረሻም፤ በመከላከያ ሰራዊት በፋኖ፣ በልዩ ሀይልና በሚሊሻ ተቀጥቅጦ አብዛኛው ሞቶ፣ የቀረው ቁስለኛ ሆኖ በአምስተኛው ቀን ከአካባቢው  ተጠራርጎ ወጥቷል። ነገር ግን አካባቢው ነዋሪ ላይ ልብ  የሚያደማ ግፍ፣ ለወሬ የማይመች በደል ፈጽሞባቸዋል።የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ ናፍቆት ዮሴፍ ሰሞኑን ወደ ሰሜን ጎንደር ዞን ዳባት ወረዳ ጭና ቀበሌ ተጉዛ፣ ከሞት የተረፉ ጥቂት የቀበሌው ነዋሪዎችን አነጋግራለች። እነሆ ከአንደበታቸው፡-


            “ብዙዎቹን ጎረቤቶቼን ገድለዋቸው ነው የሄዱት”


       እማሆይ ጣይቱ ጌጡ እባላለሁ። እድሜዬ 81 ዓመት ይሆነኛል። ጧሪ የሌለኝ አቅመ ደካማ ነኝ፡፡ ባለቤቴም ልጆቼም በተለያየ ጊዜ ሞተውብኛል፡፡ አንዷ ልጄ አዲስ አበባ ናት፤ ትክክለኛ አድራሻዋን አላውቅም። እዚሁ ጭና ነው ነዋሪነቴ፡፡ ያለችኝን መሬት እያሳረስኩ፣ እራሴም እየቆፈርኩ በሰላም እኖር ነበር፡፡ ነሀሴ መጨረሻ አካባቢ በጭና ቀበሌ የወረደው መዓት፣ ታይቶም ተሰምቶም አይታወቅም፡፡ ያ ሁሉ የጥይትና የከባድ መሳሪያ በላያችን ላይ ሲወርድ፣ እኔም ከአካባቢው ሰው ጋር መሬት እየቧጠጥኩ ስወድቅ፣ ሰው እጄን እየጎተተኝ፣ ወደ  ውቅን ከተማ ደረስኩ፡፡ ከሳምንት በኋላ ወጥተዋል ተባልን። ወደ መንደራችን ስንመጣ የሆነውን ምኑን ልንገርሽ፡፡
እኔ እውነቴን ነው ሰዎቹ ሰው አልመሰሉኝም። ያልተፈጨውን ጤፍ ከዱቄት ጋር እየደባለቁ ገንፎ ሰርተውታል፡፡ ገንፎ መስራቱንስ ይሁን፣ በግቢው እንጨት ሞልቶ አራቱን መቋሚያዬን ምርኩዜን፣ ወገብ ወገቡን ቆርጠው፣ የገንፎ መስሪያ አድርገውታል፡፡ በደካማ አቅሜ ቆፍሬ የዘራሁት ድንች ደርሶ ነበር፤ የበሉትን በልተው ሌላውን ቆፍረው ሰው እንዳይጠቀምበት ጭፍጭፍ አድርገውታል። መቋሚያዬን ሰብረው ያለ ምርኩዝ፣ ንብረቴን አውድመው ያለ ቀለብ፣ ቤቴን አውድመው ያለ ማረፊያ አስቀርተውኛል። እግዚአብሔር ይፍረደኝ። (ለቅሶ)
እኔ በዚህ እድሜዬ ተሯሩጬ ቤት አልሰራ፤ ቀድሞም ኑሮዬ በችግር የተሞላ ነው፡፡ ጎረቤቶቼን ስሩልኝ አበድሩኝ እንዳልል ብዙዎቹን ገድለዋቸው ነው የሄዱት (ለቅሶ….)። ያልተሰራ ያልተደረገ ነገር የለም። እዚሁ ቀርተው ያዩ ሲነግሩኝ፤ ድንች ቆፍረው አውጥተው፣ አፈሩን ጠረግ ጠረግ አድርገው ጥሬውን ነው  የሚቆረጥሙት፡፡
ኧረ ልጄ ተይኝ፤ ለወሬም አይመች፣ አሁንም መንግስት ትንሽ ዱቄትም ዘይትም ልብስም እየሠጠን ለነፍስ ማቆያ እያገኘን ነው። አዝመራችን መቼም አንደኛውን ወድሟል፡፡ በዚህ ሁኔታ ነው ያለነው፡፡

___________________


                  “እኔ ላይ የወረደው በረዶ እንኳን ለኔ ለእግዜሩም ከባድ ነው”

          ወ/ሮ ሙሉቀን አማረ እባላለሁ። ሌሊት በተኛንበት ከባድ መሳሪያው ሲተኮስ እኔ ጨቅላ አራት ልጆቼን አንጠልጥዬ፣ በሆዴ ፅንስ ይዤ እየወደቅኩ እየተነሳሁ ወጣሁ። ሌሎቹ ቤተሰቦቼ ታፈኑ፡፡ ለአምስት ቀን ውጊያው ቀጠለ። እኛም ወቅን ከተማ ሄደን ወደቅን፤ ልብስ የለ ምን የለ፡፡ ሌላው ቤተሰቤ ምን እንደሆነ ምን እንደደረሰበት ማወቅ አልተቻለም፡፡ ብቻ የሰሩትን ግፍ ለመናገር ይከብዳል፡፡ ከሳምንት በኋላ ስንመለስ ባሌ፣ ትልቁ ልጄ፣ አባቴ፣ ሁለቱ የባሌ ወንድሞች አጎቴና የአክስቴ ባል… ይህ ሁሉ ቤተሰብ ጭጭ ብሎ ጠበቀኝ (ለቅሶ…)። አራት ህጻናት ልጆች አሉኝ። እንደገና በሆዴ ፅንስ አለ። አባቴን፣ ባሌን፣ ደጋፊ ልጄን ቤት ንብረቴን አጥቻለሁ፤ በምድር ላይ ቀረኝ የምለው የለም። እነዚህ ጨቅላ፤ አሳዝነውኝ እንጂ ራሴን ለማጥፋት  ብዙ ጊዜ ፈተና ውስጥ ገብቻለሁ፡፡ አሁን እዚህ የሬሳው ሽታ፣ቅዠቱ፣አጠቃላይ የተደረገው በምድር ለመኖር የሚያስመኝ አይደለም። ተመልከቺ፤ የተረፉት ልጆቼ የተረፉት የአካባቢው ጨቅላ ልጆች በጥይት ቀላህ ነው የሚጫወቱት፤ አባታቸው ወንድማቸው፣ አጎታቸው ሌላው ቤተሰባቸው በተገደለበት የጥይት ቀላህ፡፡ አሁን ይሄ መኖር ያስመኛል… እስኪ ንገሪኝ?! (ለቀሶ..) እኔ ሰማዩ በላዬ ተደፍቶ፣ ጨለማ ውጦኝ ልቤ ተሰብሮ ነው ያለሁት። ቆሜ መሄዴም በፈጣሪ ታምር ነው። (ለቅሶ)….

_________________________

                “ቄስ ባሌን በታቦቱ በመስቀሉ እያለ እየተማጸናቸው ገደሉብኝ”

            ወ/ሮ ደስታ ሰጠኝ እባላለሁ። ቀኑ ማክሰኞ ሌሊት ነው፤ መዓት የወረደበት እለት። ባለቤቴ ቄስና የተክለ ሃይማኖት ቤተ ክርስቲያን ገበዝ፣ ስሙም ቄስ ጥፍጥ ባዜ ይባላል፡፡
ማክሰኞ ሌሊት 10 ሰዓት ከገቡ ጀምሮ “ይህን  ቁሉ፤ ይህን ጋግሩ” ሲሉን ሰነበቱ፡፡ እኔም የሚቆላውን እየቆላሁ፣ የሚጋገረውን እየጋገርኩ እነሱን መቀለብ ያዝን፡፡ ባለቤቴም እንጨት እየፈለጠ ሁሉን እያቀረበ፣ የእነሱ አገልጋይ ሆነን ቆየን። “እኛ ቄስና ገበሬ አንነካም” እያሉ ሲያሰሩን ሰነበቱ፡፡ ከዚያ አርብ ማታ “የታቦት ቤቱን ቁልፍ አምጣ” አሉት። “በታቦት አምላክ በመስቀሉ ይዣችኋለ፤ ተውኝ” እያላቸው በጥይት ደብድበው ገደሉት። እኛ በቆጡም በማገሩም ተሸጉጠን ተረፍን፡፡ ባለቤቴ እንደነገርኩሽ ገበዝ (የታቦት ቤት ሃላፊ) ስለነበር የቤተ ክርስቲያኑ ሁሉ ቁልፍ እሱ ጋር ነው የነበረው፡፡ በኪሱ 40 ሺ ብር እና ያንን ሁሉ ቁልፍ እንደያዘ ገድለው ቁልፉንና ብሩን ይዘው ሄዱ፡፡
አሁን እኔ ከስድስት ልጆቼ ጋር ሜዳ ላይ ወድቄያለሁ፡፡ አንዱ ልጄ አባቱን ሲገድሉት አይቶ ቅርጫት ውስጥ ገብቶ በሶስተኛው ቀኑ ነው የተገኘው። የ20 ዓመትና የ11ኛ ክፍል ልጄ ነው። ባለቤቴን አርብ ሌሊት ገድለውት እሁድ ተቀበረ።  መስቀል የማያፍሩ፤ ታቦት የማይከብዳቸው ጨካኞች ናቸው፡፡
…ቤቱን በዶማ ቆፍረው ዘርፈው እንዳይሆን አድርገውብኝ ነው የሄዱት። መጥቼ እቤት እንዳልገባ ብቸኝነቱ ፍርሃቱ ገደለኝ። አሁን ስድስት ልጅ ይዤ ውቅን ከተማ ጠባብ ቤት ውስጥ ወድቄ ነው ያለሁት፡፡
ለጊዜው መንግስትም ባለጠጋም እየደጎመን እንጂ ከየት አምጥቼ በቤት ኪራይ እቀጥላለሁ ብለሽ ነው። ከብቶቻችንን… በግ ፍየል አርደው በልተው፣ የቀረውን ገድለው፤ የተረፍነው እንዳናገግም አድርገው ነው የሄዱት። ቤቴ ውስጥ ከብት አርደው ሽታው ቆሻሻው አያስገባም። ቤቱ አሸበረኝ፤ ልጆቼም እየቃዡ ያወደሙትን ቤት አፅድቼ እንዳልገባ ተቸገርኩኝ፡፡

_________________________

                     “ቀፎአችን ነው ቆሞ የሚሄደው፤ ተሰብረናል”


              ደስታው ትኩ እባላለሁ። ቦዛ የሚባለው አካባቢ እያሉ ሰው ስላልነኩ፣ እኛንም አይነኩንም ብለን ነው የተበለጥነው፡፡ በእነዚህ ክፉ አውሬዎች ከግራ ቀኝ ያሉኝን ሁለት ታላቅ ወንድሞቼን፣ የእህቴን ባል፣ የወንድሜን የልጅ ልጅ፣ በአጠቃላይ ስድስት ቤተሰቤን ተነጥቄያለሁ። ሲተኮስ ባለቤቴም የልጅ ማዘያ አንቀልባ እንኳ ሳትይዝ ጨቅሎቹን (ህጻናቱን) ይዛ ወጣች፤ እኔም ወጣሁ፡፡ ሄደን ውቅን የሚባል ከተማ ፈስሰን፣ እስከ ቅዳሜ ድረስ ጦርነቱ ቀጠለ። ከዚያም ወጡ፡፡  ቅዳሜ ተመልሼ ብመጣ ወንድሞቼ ቤተሰቤ አልቀው ከብቶቼ ንብረቴ ወድሞ ጠበቀኝ፡፡ እንዲህ አይነት መከራ ሲወድቅ የሞተን አቃባሪ አስተዛዛኝ ያገኘ ሰው ምንኛ የታደለ ነው፡፡ ሁላችንም ባለ መከራ ባለ ሀዘን ሆንን፤ማን ማንን ያጥናና? ሁሉም የራሱን ቤተሰብ እሬሳ ወደ ማንሳት ወደ ቀብር ሄደ፡፡ እኔ የወንድሞቼን ሬሳ ማን ያናሳኝ?! ቀን ጨለመብኝ፡፡ እንደገና ሁለት የወንድሞቼ ልጆች ከጎንደር መጥተው ነው ያናሱኝ፡፡ የሚገርምሽ ልብሳችንን ሙልጭ  አድርገው ወስደው ለከፈን የሚሆን ጨርቅ እንኳን አጣን፡፡ እንደገና እንደምንም ሁለት ጋቢ ወድቆ አግኝቼ አንዱን ለሁለት እየቀደድን ነው እንደነገሩ የሸፈናቸው እኛው ሀዘንተኞቹ መቃብር ቆፍረን፣ እኛው ቀብረን፣ ይሄው ቀፎ ሆነን ቆመን እንሄዳለን።
እስካሁን ውቅን ከተማ ነበርን፡፡ ዛሬ ተሰብስበን ያገኘሽን እስከ መቼ ባድማችንን ትተን እንከራተታለን ብለን ገና ቤት ጠርገን እየገባን ነው፡፡ መቼም ይመስገነው እኛ የተረፍነው ተርፈናል። ወገኖቻችን አልቀዋል። ንብረታችን ተዘርፏል። የሚበላ ነገር፣ በሬ ላም፣ በግ ፍየል የሚባል ሙልጭ አድርገው በልተው የተረፈውን ጭነው፣ ሁሉን አፍርሰው ነው የሄዱት፡፡ ይሄው መንግስት ለነፍሳችን ማቆያ ትንሽ ትንሽ ነገር እየጣልን ህጻናት ይዘን አለን፡፡ አዝመራው ውስጥ ሬሳ ወድቆ ወድቆ አሞራና ጅብ እየጎተተው፣ ሄደን ለመሰብሰብ ሽታውም ድንጋጤውም አላስቀረበንም። እህላችን ሜዳ በላው።
እንዴት አድርገን እንሰብስበው?! ሰዎቹ አረመኔ ናቸው፤ ጨካኞች ናቸው፡፡ ከዚህ በኋላ ተረጋግተን ልጆቻችንን ቦታ ቦታ አስይዘን ሄደን መግጠም እንጂ ከእንግዲህ ያዝኑልናል ብለን ተስፋ የለንም፡፡ የአሁኑም የሆነው ሳናስበው ሳንዘጋጅ ነው፡፡
______________________

                     “ወንድሜንና የእህቴን ልጅ ገድለውብኛል”

          አቶ ሙቀት ባዜ እባላለሁ። ማክሰኞ ሌሊት ሲገቡ እኔ ቤተሰቤን ይዤ ወጣሁ፡፡ አንዱ ቄስ ወንድሜ፣ አይነ ስውር አባታችንንና ደካማ እናታችንን ጥዬ አልሄደም ብሎ ታፈነ። እናትና አባቴ ተረፉ ነገር ግን ወንድሜና የእህቴ ልጅ ተገደሉ፡፡ ቤት ንብረት የተረፈ ነገር የለም፡፡ እኛ ነፍሳችን መቼም ተርፏል፡፡ መንግስትም አልረሳንም፤ አጥጋቢም ባይሆን ትንሽ ትንሽ እየሠጠን አለን፡፡ መሬታችንን ብታይው ጉድብ (ምሽግ) ለመስራት ተቆፍሮ አዝመራችን ወደመ፡፡ ያንን የቆፈሩትን ጉድብ ሬሳቸውን መቅበሪያ አደረጉት፡፡ ምሽግ የቆፈሩበትና ሬሳ የቀበሩበት መሬት ገና እሸት መያዝ የጀመረ ነበር፤ በዚህ ሰዓት ቢሰበሰብ እንኳን እኛን ሌላውን የሚመግብ አዝመራ ነበረው፡፡
በሁሉም ቦታ የእነሱ ሬሳ ወድቆ ወድቆ ሰብላችን ጠቅላላ በሬሳ ብዛት ተበከለ፡፡ ሄደን ማረም ሲደርስም መሰብሰብ አልቻልንም። አካባቢው ሽታው ለበሽታ ዳረገን፡፡ እኛ ላይ የደረሰው መዓት ታይቶም ተሰምቶም አያውቅም፡፡
ሌላው አንዲት የአሸባሪው ሴት ወታደር “እዚህ አካባቢ የጦር መሳሪያ ተቀብሯል፤ ቆፍሩ” ብላ መሳሪያ ፍለጋ የተቆፈረው መሬታችን፣ ገና እሸት የያዘ መሬት ነው መና የቀረው፡፡ ወይ መሳሪያው አልተገኘ ወይ እህላችን አልተረፈ መሬቱ ብላሽ ሆኖ ነው የቀረው። አሁን አካባቢው ቅዠቱ ሽታው ፍርሃቱ ተረጋግተን እንድንቀመጥ አላደረገንም፡፡ የወረደብን መዓት ልባችንን ሰብሮት፤ ወንድሞቻችንን ልጆቻችንን በነዚህ አረመኔዎች ተነጥቀን፤ ንብረታችንን አጥተን ተወልደን ያደግንበትን ባድማ ፈርተን በሰቀቀን ውስጥ ነው ያለነው፡፡
_________________________

              “ቤተሰቤንና ጎረቤቶቼን በጥይት ቆልተው ጨረሷቸው

           ወ/ሮ ተስፋነሽ ታከለ እባላለሁ። እኔ ከተፈጠርኩ እንዲህ ዓይነት መከራ ሰው ላይ ሲወድቅ አይቼ አላውቅም፡፡ በሰላም ሰላም እደሩ ተባብለን በተኛንበት በላያችን የጥይት እሳት ማዝነብ ጀመሩ፡፡ ባለቤቴን ልጄን፣የልጅ ልጄን፣ የባለቤቴን ወንድሞች፣ ጎረቤቶቼን፣ የጎረቤቶቼን ልጆች በጥይት ቆልተው ጨረሷቸው፡፡ ምን እንደምል ግራ ገብቶኛል፡፡ ከዚህ በኋላ ኑሮዬ እንዴት እንደሚቀጥልም አላውቅም፡፡ ምኑን እናገረዋለሁ፡፡ እኔ ለምን እንደተረፍኩም አላውቅም ልጄ፡፡ በረዶ ነው ያዘነቡብኝ። ቀንና ሌሊት በማልቀስ ይሄው አለሁ፡፡ ባዶዬን ቀረሁ፡፡ አሁን ሶስት ትንንሽ ልጆቼ ቀርተዋል፡፡ አንድ ልጅ በርሃ ውስጥ አለ- የቀን ስራ እየሰራ። ሌሎች ልጆቼም አዲስ አበባ አሉ፡፡ እዚህ ያለነው መቼም ከኔና ከህፃኖቹ በስተቀር የተረፈ የለም፡፡ ምን አጠፋን፣ምን በደልን፣ይሄ ሁሉ መከራና እልቂት ለእኛ ለምን አስፈለገ? በሰላም እያረስን ልጅ እያሳደግን ከመኖር ውጪ የምናውቀው ነገር የለም፡፡ ገብተው ጨረሱን። መንግስት ይፍረደን፣ፈጣሪ ይፍረደን፣ እንባችን ፈስሶ አይቅር፡፡ ልባችን ተሰብሯል፣ ጨለማና ሀዘን ውጦናል፤ የምንጽናናበት አንድም የቀረን ነገር የለም፡፡ እኔ በበኩሌ አለኝ የምለውን ሁሉ ወስደውብኛል፡፡ ከዚህ በላይ መናገር አልችልም፡፡ አዕምሮዬ ተዛብቷል፤ እንቅልፍም የለኝ፤ እሳት በውስጤ ታቅፌ ነው ያለሁት፡፡



______________________________




                  “በመጦሪያዬ ባለቤቴንና ልጄን ገድለውብኝ ብቻዬን ነኝ”


              ወ/ሮ የህዝብ ዓለም ጫኔ እባላለሁ። መከራም አይነት አለው፡፡ የጭና ቀበሌ ህዝብ ላይ የደረሰው መከራ ታይቶ ተሰምቶ አይታወቅም፡፡ አንዳችን ላይ የደረሰ ቢሆን አንዱ አንዱን ይደግፋል ያጥናናል፡፡ የአኛ እኮ ለንግግርም አይመችም። ወይ ከቤተሰቦቻችን ወይ ከቤት ንብረታችን ወይ ከአዝመራችን የቀረ የለም በቃ ሙልጭ ብሎ ባዶ መቅረት ነው የተረፈን። ፈጣሪ እኛንስ ለምን አብሮ አልወሰደንም እላለሁ፡፡ አሁን እኛ አለን ነው የሚባለው ልጄን በግና ፍየል ከብቶች እየነዳ በዱር ነው በጥይት ደብድበው የደፉት። እሱን ገድለው 12 ፍየል ስድስት በግ ወሰዱ። እሱን ከሚገድሉት በግና ፍየሉን ወስደው ቢተውት ምን ነበር?!
ልጄ ጥላሁን ንጉሴን ደፉት፡፡ ጭካኔያቸው ሰው ናቸው ለማለት አያስደፍርም፡፡ ባለቤቴ ንጉሴ ወንድይራድ ታፍኖ በደካማ አቅሙ ተገደለ፡፡ ቤቴ መፈንጫቸው ነበር፡፡ ዶሮ እንቁላል የተቦካ ሊጥ አልቀራቸውም። ከብቶችን ቤት ውስጥ ነው አርደው የበሉት፡፡ የድንች ማሳዬ ጥሩ ምርት ይዞ ነበር፡፡ በልብስ ማጠቢያ ሳፋ እየሞሉ ነው ቆርጥመው የጨረሱት፣ የተረፈውንም ጭፍጭፍ አድርገው አውድመዋል፡፡ የእነሱ በደል ብዙ ነው ሬሳቸው በየማሳችን ወድቆ አካባቢ በከሉብን፡፡
አሁን አንዱ ልጄ በዚህ የተነሳ ታማሚ ሆነ፤ እህል አይበላ፣በግድ ሲቀምስ ወደ ላይ ወደ ታች እያጣደፈው በሽተኛ ሆኗል፡፡ እንግዲህ ተመልከቺ፤ባሌንና ልጄን አጣሁ፤ ጎረቤቶቼ አለቁ፣ አዝመራችን በዱር ቀረ፤ ቤት ንብረታችን ወደመ፡፡
በምኑ እንጥናና? በምን እንጠገን? በእርግጥ መንግስትና የአዲስ አበባ ሰው ውሎ ይግባ፤ ለጊዜው ጦም እንዳናድር አድርጎናል። እንዴት ብለን ወደ ቀድሞው ኑሮአችን እንመለስ?! ሀዘን የበላን ያልታደልን ነን´ኮ! የኔ ልጅ፤ የደረሰብንን እያየሽው ምኑን ከምኑ ልንገርሽ፡፡ አንቺን እግዚአብሔር ይስጥሽ፣እንዲህ አይነት መከራ በዘር ማንዘርሽ አይድረስ፡፡ ጠያቂ አትጪ። የአዲስ አበባ ሰው ውሎ ይግባ፡፡



Read 2437 times