Monday, 13 December 2021 00:00

ሁሌም በክፉ ሰዓት የምትከዳን አሜሪካ!!

Written by  (ካለፈው የቀጠለ) ጌትነት ደብሊው
Rate this item
(1 Vote)

ክፍል ፫
አሜሪካኖቹ ግን
ለምን እንዲህ ያደርጋሉ?
፩. በተለይ በነጭ የበላይነት የሚያምኑ፣ የኢትዮጵያ በብቸኛነት ቅኝ ያለመገዛት ታሪክ ያብከነከናቸውና
ባልተጻፈ ሕግ ለመጣው መሪ ሁሉ “ያራዳ ልጅ የእነሱን ነገር በጥንቃቄ ያዘው እ” እያሉ ይቀባበሉ ይሆን?
እላለሁ፡፡ በአንድ ወቅት የኢትዮጵያ ደራሲያን ማኅበር ሰብሳቢ አቶ ጌታቸው በለጠ፣ በአሐዱ ሬዲዮ ከጋዜጠኛ ጥበቡ በለጠ ጋር ቃለመጠይቅ ሲያደርጉ፤ “አሜሪካን ሀገር ስማር (ከውጭ ጉዳይ ፖሊሲ አማካሪና ባለስልጣናት ጋር ሳወራ) ‘ለመሆኑ ሀገራችሁ/አሜሪካ በኢትዮጵያ ላይ ያላት ግልጽ አቋም ምንድን ነው? እንዴት ነው ሀገሬን የምታይዋት?’ ብዬ በቁጭት ጠየኳቸው፤ እነሱም እጅግ የሚገርም ነገር ነገሩኝ፤ ያሉኝን ነገር ለጊዜው ማውጣት ጥሩ ስለማይሆን ይቆይ” ሲሉ ሰምቻቸው ነበር፡፡ አቶ ጌታቸው ግዴለዎትም ያውጡት፡፡ እኔ ከሞላ ጎደል ከላይ የጠቀስኩት ወይም ቀጥዬ ከማስቀምጠው ነጥብ ጋር እንደሚገናኝ እገምታለሁ፡፡ እናንተም ገምቱ እስቲ!
፪. አፍሪካን በማስተባበር ራሱን ወደቻለና በሁለት እግሩ የሚቆም አህጉርና ሕዝብ ለማድረግ የሚወጠንን የትኛውንም ፓን አፍሪካዊ እንቅስቃሴ ለመቀበል ይቸግራቸዋል፡፡ ይሄ ምክንያቱ ሁለት ነው፡፡ አንድም የነጭ የበላይነትን የማስጠበቅ ነው፤ አንድም አፍሪካ የጥሬ ሀብት /Raw Materials/ ምንጭ ስለሆነ አንጡራ ሀብቱን /Resource/ የመጠቀም መብት  የለውምና ነው፡፡ ይሄ ይበልጥ ልቤን ያሳምመዋል እንደውነቱ!
ሁለት ምክንያቶችን ባነሳ ያጠናክርልኛል። አንዱ በቻይናና አሜሪካ (ምዕራቡ) መካከል ያለው ግልጽ የወጣ የጥሬ ሀብት ሽሚያና ሽኩቻ ነው፡፡ ሁለተኛው በቅርቡ ያገኘሁትና ሀዋርድ ኒኮላስ በተባለ የምጣኔ ጠበብት ነጭ ሰው “Africa must be kept poor by any means” የሚል ንቀት ጭምር ያለበት ገለጻ አይቼ ሳላስበው እንባዬ እየወረደና እያልጎመጎምኩ ኖሮ፣ “ምነው ሰላም አይደለህም?” ሲለኝ ጎኔ የተቀመጠው ሰው እንደ ደነገጥኩ አስታውሳለሁ፡፡ እዚህ ላይ “Confessions of the Economic Hit Man” የሚል መጽሐፍ እና  ፋንታሁን ዋቄ የሚያደርጋቸውን ድንቅ ገለጻዎች መስማት ከላይ ያብከነከነኝን እውነት ይበልጥ ያጎላልናል፡፡ ታዲያ ከእኛ ጋር ምን ያገናኘዋል? ይገናኛል፣ ለምን መሰለህ? ዩጋንዳ፣ ኬንያ፣ ጋና፣ ግብጽ፣… ወዘተ አፍሪካውያንን ከሚያስተባብሩት በላይ ኢትዮጵያ በፉጨት ጠርታ የማሰባሰብና ማስተባበር ዳራዊ አቅሟ ከፍ ያለ ነው፡፡
የአፍሪካን ሀብት መቀራመት ስንል የተማረ የሰው ኃይልንም እንደሚጨምር ልብ ብላችሁልኛል አደለም?!
የየትኛውንም ሀገር ዜጋ የአዕምሮ ስብ መጠቀም መርህ ያደረጉት አሜሪካኖቹ፣ በሁለተኛው የዓለም ጦርነት
ጀርመናዊውን አ. አንስታይንና የአቶሚክ ቦምብ ቀመሩን ተጠቅመው ዓለምን እንዳስገበሩት በውል
ያውቃሉ፡፡ ያማልላሉ፣ ይወስዳሉ፣ ይከፍላሉ፣ ያድጋሉ፡፡ ለዚህ ደግሞ ማማ አፍሪካ በትንሽ ትንሽ ማማለያ
አተብ ተደርጋ የምትታለብ ጥገት ላም መሆኗን ከባሪያ ፍንገላው ጀምሮ በደንብ ያውቁታል፡፡ አንድ ምሳሌ
ብቻ መጥቀስ በቂ ነው፡፡ በBrain_Drain አማካኝነት ምሥኪኗ ማላዊ በዓመት ስልሳ ነርሶች አስመርቃ
መቶዎቹ ከሀገሯ ይወጣሉ ይባላል። ዋነኞቹ ተቀባዮች እመት አሜሪካና እንግሊዝ ናቸው። በቀዘቀዘው ሻያችን ጎሯሯችንን እያረጠብን እንዝለቅ እስቲ…
፫. ይህም ከቁ .፪ ጋር በተወሰነ መጠን  ይገናኛል፡፡ እሱም  የሰውነት ሀገር መሆኗ ነው። ኢትዮጵያውያን ሰውን በሰውነቱ ይቀበላሉ።  በኢትዮጵያ የእስልምና አመጣጥን ማየት ጠቃሚ ነው፡፡ በግል የማምነው
ኢትዮጵያውያን ፈላስፎች ጊዜያቸውን የሚያጠፉት ስለ ሰውነት ሲመራመሩ ነው። ይህም ቀጥታ ከሃይማኖት ጋር ይያያዛል። በአጠቃላይ ሃይማኖተኛ ሕዝብ ነው፡፡ እንደ አጋጣሚ ሆኖ ደግሞ ሁለቱ ዋነኞቹ Abrahamic Religion ናቸው፡፡ ሰው ማክበር፣ እግር ማጠብ፣ የተራበ ማጉረስ፣ መረዳዳት፣ አለመግደል፣ አለመዘሞት፣ አለመስከር፣ ተመሳሳይ ጾታ ግንኙነትን መጸየፍ፣ የሰው ልጅ እኩልነትን መቀበል፣ ነጻነትን…. የሚያስተምሩ፡፡ እና አሁን ይሄ ለምዕራቡ ዓለም ፈጣን “የእድገት” እና የመሰልቀጥ ግስጋሴ አደገኛ መሰናክልኮ ነው፡፡
፬. ጂኦፖለቲካዊ ሁነቶች፡፡ ከአክሱም ሥልጣኔ መዳክም ጀምሮ በቀይ ባህር አካባቢ ያለ ፖለቲካ በዐይነ
ቁራኛ የሚታይ ነው፡፡ ቀይ ባህርን መቆጣጠር ዓለምን መቆጣጠር ተደርጎ ጭምር እየተወሰደ ነው፡፡
በአናቱ ደግሞ የዓለም ግዙፍ መርከቦች መተረማመሻ መንገድ /Coridor/ እየሆነ መምጣቱ ግለቱን
ጨምሮታል፡፡ አሁንም እዚህ ውስጥ አንዲት ጣጠኛ ሀገር አለች፡፡ ኢትዮጵያ! ከመልክዓ ምድራዊ አቀማመጥ፤ እንግሊዝን፣ ፈረንሳይንና ጀርመንን በአንድ ላይ የሚበልጥ ቆዳ ስፋት፣ ሁሉን ማብቀል የሚችል ለም መሬት፣ የዛሬን አያድርገውና አንጻራዊ ሰላም፣ ሚጢጢዬ እድገት ነገር፣ ታሪክ፣ ባህል፣ ዕምነት፣…ምናምን ምናምን ያላት በአብዛኛው ወጣት የሆነ ፻፲፭ ሚሊዮን ሕዝብ ሀገር! ይችን በቀላሉ የምትለወጥ ሀገር መያዝ/መቆጣጠር ወደ ቀኝም ወደ ግራም ለመወንጨፍ፣ ወዲህም ሲሻቸው “እስቲ ጀግኒት ዝመቺ” ብሎ ለማዘዝ አዋጭ ስልት ነው፡፡ ታዲያ ጥገቷ መጋጡን ትጋጥ፣ እንዲያውም ሳትነሳ እንደተኛች ትንሽ ትንሽ ጣፋጭ ሣርም ጣል ይደረግላታል፣ ግን ከተፈቀደላት ማሠሪያ ርዝመት በላይ መንጠራራት አትችልም፣ ያስቀስፋል!
፭. ሕዳሴ ግድብ፡፡ እርግጥ ነው፣ ከላይ ባሉት አራት ሁነቶች ውስጥ ሊጠቃለል ይችል ነበር፡፡ ግን ያቺ
እጅጋየሁ “ዓባይ ወንዛ ወንዙ፣ ብዙ ነው መዘዙ” እንዳለችው፣ መዘዘኛውን_በረከት ለብቻ ማየቱ ጠቃሚ
መስሎ ይሰማኛል፡፡ ዓባይ ለሒሳብ (በተለይ ለGeometry) ማቆጥቆጥ ከፍተኛ አስተዋጽዖ ያለው ብሎም
ለግብጻውያን ሁሉ ነገራቸው የሆነ የሚበላም የሚጠጣም ሲሳይ ነው። እንግሊዞች የዚህን ወንዝ መነሻ
የመቆጣጠር ከፍተኛ ፍላጎት እንዳላቸው ይታወቃል፡፡ የእንግሊዝና አሜሪካን አብሮ አደግና ዘማችነት
እንጨምርበትና ከላይ የተጠቀሱ ሚዲያዎቻቸውን የት በቀልነት አስታውሰን ብቻ ማለፉ ከአሜሪካ
“በነገሮች ሁሉ እኔ ካላቦካሁት አይጣፍጥም” እና “የእርጎ ዝንብነት” ጠባይ ጋር ስንደምረው፣ አንድ ሌላ
ኢትዮጵያን ጥርስ ውስጥ የሚያስገባ “ነገር” ለመሆኑ ጥርጥር የለውም። ይህም ጉዳይ ለምን ብለን ካሰብን
“ደካማ ኢትዮጵያ ብሎም አፍሪካ” ከመፍጠር ጋር የሚያያዝ ለመሆኑ ጥርጥር የለውም፡፡ እዚያ ላይ
የግብጾችን መርህ አልባ ግንኙነት ስንጨምርበት፣ እዚያ ላይ በእስራኤል በኩል በመምጣትና በመሄድ
መካከል ሆኖ የሚዋልለውና መካከለኛው ምሥራቅንና አጠቃላይ አረቡን ዓለም ለመቆንጠጥ ግብጽን
እንደ እጅ ለመጠቀም ሰማይ መቧጠጥ የሚከጅለውን እውነት ስንጨምርበት፣ ምሥሉን የበለጠ የጠራ
ያደርግልናል፡፡
፮. የኢትዮጵያ የግዛት አንድነት። ከላይ ባሉት ነጠብጣቦች ውስጥ እንደ ምክንያት ብቻውን መጠቀስ
አለበት ብዬ ያሰበኩት ደግሞ የኢትዮጵያ ግዛት አንድነት ተጠብቆ እንዳይቆይ የመሻት ነው፡፡ የፕሮጀክቱ
መነሾ ቀደም ያለ ቢሆንም ጣሊያን ግን በወረቀት አስፍራ በግልጽ በመምጣቷ ዋነኛዋ መሠሪ ያሰኛታል፡፡
በኋላ እንግሊዝም ብትሆን ከሁለተኛው የጣሊያን ወረራ በኋላ የጀርባ ቅኝ ግዛት ሕልማቸው ከመከነ ዘንዳ
በሚል ይመስላል እነ ኮሎኔል ፒንክ በቦረና፣ ሐረርጌይና ሶማሌ እየተመላለሱ ይዘሩት ነበረው “መርዝ”
ፍላጎታቸውን በበቂ ያስረዳናል። እውነቱን ታሪክና ሊቃውንቱ የሚያወጡት እንደተጠበቀ ሆኖ “የጡት
ቆረጡ” ትርክት የጀመረው ከነኮሎኔል ፒንክና የወለጌዎቹ ጀርመን ሚሲዮናውያን ትርክት በኋላ ነው (እዚህ ያለ የሚያመረቅዝ ሕመም በደንብ መጠናትና መታከም አለበት ብለው ከሚያምኑት ወገን ነኝ)፡፡
ጊዜውም ብዙ የተራራቀ አደደለም። ነገሩ የጊዜም የመሪዎችም ጥበብ ታክሎበት ብዙ ሳይሳካላቸው
ቀረና ኖረ፡፡ ጅቡቲን ቀድመን ሰጥተናል፡፡ ኤርትራ ተገነጠለች፤ በዚህም በቅድሚያ ጣሊያን ቀጥሎ
እንግሊዞች (እርግጥ ነው በጅቡቲ በኩል ፈረንሳይ) በአንደኛነት የተደሰቱ ይመስለኛል፡፡ አንፋሽ አጎንባሹን
ለጊዜው አቆይተነው፡፡ ከዚህ በኋላ ይችን በኃይል ቅኝ ያልተገዛች ሀገር ብቸኛው መፍትሔ እንዲህ እየገነጣጠሉ እጅ፣ እግር፣… አልባ ማድረግ ጥሩ ስልት መስሎ ያገኙት እንደሆነ ይሰማኛል፡፡ በትምህርቱ በኩልም ሳይቸግር ጤፍ ብድር እንዲሉ፣ በቁና ሰፍረን አምጥተን የቃምነውን መርዝ ሳይረሳ፡፡ እንግዲህ አዋጭነቱን ትንሽ ቆዝሙበት፡፡ ይህ ጦስ በዚህ መቆም የሚችል፣ የሚያበቃም አይመስልም፡፡ በሌላው አካባቢ ሞክረው ሞክረው ያልተሳካላቸውን የመገንጠል (ገ ይላላል) ጥያቄ የፋስሽቱ ጣሊያንን የጨቋኝ ተጨቋኝ የተረጨ መርዝ ከስታሊናዊው የብሔር ፖለቲካ ጋር አጫፍሮ የሚጋልብ፣ መርሕ አልባ፣ የፖለቲካ ዜማና ጭሬ ላፍሰው ባይ ትሕነግ ጋር ግጥምጥም አሉ፤ ተዋደዱ፣ ተቃቀፉም፣ አብረው ፬ ኪሎ ገቡ፡፡ ዙሪያ ገባው በኢትዮጵያዊነት እሳት ታጥሮ ያስቸገራቸው እነ እንቶኔ፣ በትሕነግ በኩል የተሸነቆረ_ቀዳዳ አገኙና ወደ ትግራይ ማጮለቅ ጀመሩ። ያ (ትግራዋይ) ማኅበረሰብ ደግሞ ችግሩ ኢትዮጵያዊ_ብቻ_ሳይሆን_ራሱ_ኢትዮጵያ_ ሆኖ አገኙት፡፡ ምን ያድርጉ? መጀመሪያ የጨቋኝ ተጨቋኝ ትርክቱን ማጦዝ፣ አብዝቶ ማስከፋት፣ ብቸኛ ተጠቂነት እንዲሰማው ማድረግ፣... ይህን ዮሐንስ፣ አሉላ፣ ቴዎድሮስ፣ ምኒልክ፣ አባጅፋር፣ አክሱም፣ ላሊበላ፣ ... ኢትዮጵያ ምንትስ ቅብጥስ ይሉ ብሂል መጀመሪያ ከአፍ፣ ቀጥሎ ከግድግዳ፣ ከዚያ ከልቡና ሰሌዳ መፋቅ፣ በምትኩ ጭቆናና ሰማዕታት ብቻ! ማሠሪያው ሕግ ነውና ሕገ መንግስት ውስጥ “ጨዋታው ፈረሰ ዳቦው ተገመሰ” ብሎ የፉርሽ ጨዋታ መጫወት የሚያስችል አንቀጽ ማስገባት፡፡ ገባ!... እድሜ ይስጠንና እኛንም “ውሸታም” ለመባል ያብቃን፤ የሚሆነውን እናያለን እስቲ!
ለእኔ ግን አሁን ግብ ግቡ “እዚህ አካባቢ” ይመስለኛል፡፡ በነገራችን ላይ ትሕነግም’ኮ ምኒልክ ቤተ መንግስት የመግባት ሕልምም ትልምም አልነበራትም፡፡ እንዲያውም ጦሩ ከተከዜ ሲሻገር ከፍተኛ ማጉረምረምና መከፋፈል ተፈጥሮ በነኣይተ መለስ “ሁሉም ጭቁን ነው፤ ትግራይን ብቻ ሳይሆን ሁሉንም ነው ነጻ ማውጣት ያለብን” በሚል ነበልባላዊ ስብከት እንደገና ለምልሞ ነው ጦሩ ሸዋን የረገጠው፡፡ አደለም ወይ…?
፯. የዲፕሎማሲ ውድቀት ያመጣው ጣጣ፡፡ ከላይ የጠቃቀስናቸው ከሞላ ጎደል ውጫዊ፣ የዓላማ
እና/ወይም በሳይንስ ቋንቋ Uncontrolled Variables ልንላቸው እንችላለን። እስቲ ከእኛ አንጻር ወይም
Controlled Variable የሆነውን እንይ፡፡ ትንሽ ቀደም ባለው ጊዜ “እኛ ሀገርኮ ጋዜጠኝነትና ዘፋኝነት
በአቦሰጥ/ደምሴ ደማጤ አብሮ እንዳይሰደብብኝ በተፈጥሮ ችሎታ ቢባል/ ነው” ይባል ነበር፡፡ አሁን አሁን’ኳ ቢያንስ “አንዱ” ዘርፍ ከዚህ አባባል “በመጠኑም” ቢሆን እየተላቀቀ የመጣ ይመስለኛል፡፡ ለእኔ ግን ዲፕሎማት መሆንም ከላይኞቹ ጋር ቢደመርልኝ ወይም አቦሰጥ የምትለዋ “በግዴለሽነት የሚገኝ ልቅና” ከፈለጋችሁ “የጡረተኞች ጂም” ልንለው እንችላለን፡፡ ይህን የድፍረት ቃል /የምሬት መደምደሚያ/
እንድናገር  ያደረገኝን  አንድ  ምክንያት  ልጥቀስ፡፡
እግር ጥሎኝ በፖለቲካ አጋጣሚ /በሥራ አጋጣሚ እንደሚባለው መሆኑ ነው/ ተቀማጭነታቸውን በአዲስ
አበባ ያደረጉ አብዛኞቹን የውጭ ሀገር ዲፕሎማቶች በቡድንም በግልም የማግኘት እድሉ ነበረኝ፡፡ በነገራችን ላይ አብዛኞቹ ወጣቶች ናቸው፡፡ ታዲያ የሚያደርጉትን ነገር ከእኛዎቹ ጋር ሳነጻጽረው፣ የመምህርና ተማሪ ከፈለጋችሁ የሰማይና ምድር ያህል ነው፡፡ አንድ ቦታ እንዲሁ ስለሀገራችን ጉዳይ “ደጅ ጥናት” ሄደን በዚሁ በሰሜኑ ጦርነት ጉዳይ ሥረ መሠረቱን ጭምር እያወራን ሳለ እኛም ያለችንን ሀቅ አስረድተን ለሀገራችን “ቢያደርጉልን” የምንለውን ወረወርንና ተራውን ወሰዱ፡፡ ከወደ ጠረጴዛቸው በቀለማ ቀለም የተዥጎረጎረ ካርታ ሳቡና “ጦርነቱ አሁን እዚህ፣ እዚህ ነው ያለው፡፡ ይሄ ይሄ ተለቋል፣ ይሄ ተይዟል” እያሉ የሰፈር ስሞችን ጭምር እየጠሩ ተነተኑልን፡፡ ወዲህም የውጊያውን ጠባይ ነገሩን፡፡ ከጓደኛዬ ጋር ዐይን ለዐይን ተያየን፤ገርሞናል፡፡ ይህን ጦርነት እስከ ጥግ ተከታትየዋለሁ፣ በጭራሽ ግን አንድ ነጭ እንዲህ ያስረዳኛል ብዬ አላሰብኩም፡፡ ምኗም መሬት ጠብ አትልም፡፡
ምዕራቡ ዓለም (በተለይ አሜሪካኖቹ) በንግግር እንዲሁም ውትወታ/Lobby/ ያምናሉ፡፡ እንዴታ ኧረ
እንዲያውም ጨውም ላስ ያደርጉታል። በቀላል ምሣሌ ላስረዳ እፈልጋለሁ። Google የራሱ Algorithm አለው። እንዲያውም አንዳንዴ እንደ ሰው /Artificially/ ያደርገዋል፡፡ ለምሳሌ በአንድ አጋጣሚ ያየነው መልዕክት ወይም Video ሊሆን ይችላል፡፡ ከዚያ በኋላ ከጀርባ የማናየው ሰውዬ ያንንና ያን የመሰለ ይዘት ያላቸውን መልዕክቶች ፊታችን ላይ እያመጣ ገጭ ያደርግልናል፡፡ አያ GOOGLE ይህን ሰዋዊ ጠባዩን/Algorithm/ ከራሳቸው ከአሜሪካኖቹ የቀዳው ይመስለኛል፡፡ ደጋግመህ በጮክ፣ ደጋግመህ ባስረዳህ ቁጥር (አሁን አሁን መንከባለልም ተጨመረ መሰል፣ ለፈገግታ ነው) ተሰሚነት ይኖርሃል። የእኛዎቹን ኤሊቶች ከዚህ Algorithm ጋር ለማራመድ ራሱ ምዕተ ዓመት ይፈጃል። ክራቫት አስተካክሎ፣ ውድ ዶላር እየላፉ መጎለት ብቻ! ለምኑ? ይበቃናል፡፡ ወደ ምን ተሻለ? እንዝለቅ፡፡ ግን አንድ ነገር ብቻ እንበል። ለጊዜው ብዙ የማላብራራው ግን ሁልጊዜ የሚደንቀኝ ነገር አለ። እሱም ሃይማኖት ነው፡፡ እርግጥ ነው ከላይ ጠቅሸዋለሁ፡፡ ቢሆንም አንድ ጥያቄ ብቻ ጭሬ ልለፍ፡፡ ኤርትራ ከኢትዮጵያ ስትገነጠል /እንድትገነጠል/ ከፍተኛ ሚና የነበራት ሱዳን፣ ብድር በምድር ሆኖ ላሟ ደቡብ ሱዳን ጎጆ ስትወጣ፣ የእኔዋ ኢትዮጵያም ብድሯን” መልሳለች፡፡ የደቡብ ሱዳን መገንጠል ሃይማኖታዊ /የዕምነት ነገር እንዳለበት ስንቶቻችን እናውቅ ይሆን? ጉዳዩ ታዲያ አሜሪካ ደቡብ ሱዳንን ለማዳን ያን ያህል እንዳልተጋች ለምን ኢትዮጵያን ለማዳን አትተጋም?  ያውም ብሉይ ከሀዲስ እንደ ሰልሔ መልሔ ተዋውጦ በሚሰበክባት ሀገር፡፡ እህ ምን ትላለህ እንዲያውም ማጥፋት የሚፈልጉት እሱንኮ ነው፡፡ ቆይ በቃ ጥያቄ ብቻ ሆኖ ይለፍ ተወው፡፡ ሆ ሆ…
ምን_ተሻለ?
…ባህር ውስጥ ገብተን አላልቅ አለኮ፣ እንመለስበታለን፣ እንዲያውም ብንወያይበት! ሁሉ እላለሁ፡፡

Read 3202 times