Saturday, 11 December 2021 13:57

ሰውየው፤ “መሬት ላይ ሆኜ ልውጋህ ዛፍ ላይ ወጥቼ? ቢሉት ዛፍ ላይ ወጥተህ! አለ፤ ለምን ቢባል፤ እስከዛ ድረስ እቆያለሁ አለ” አሉ፡፡

Written by 
Rate this item
(6 votes)

     የሀገራችን ፈላስፋና የታሪክ ምሁር እጓለ ገብረ ዮሀንስ  “የከፍተኛ ትምህርት ዘይቤ፡፡” ብለው በጻፉት መፅሐፍት ውስጥ የሚከተለው ግጥም ይገኛል፡-
ወጣቶች አነሱ ግንባራቸውን፤ ሊጠይቁ እኛን
“ታውቁት እንደሆነ እስኪ ንገሩን”
ባቀበቱ ዙሪያ መንገድ ይኖርን?፤
ቪርጂልዮ መለሰ እንዲህም አላቸው-
“መስሏችሁ ይሆናል እኛ የምናውቀው
ምንገደኞች ነን እኛም እንደናንተው
ትንሽ ቀድም አልንይ የደረስን አሁን ነው
መንገዳችን ሌላ፤ የባሰ ከናንተው
(ቀጥ ያለ አቀበት እንቅፋት የመላው)
እንግዲህስ መውጣት ለእኛ መቅለሉ ነው፡፡
               ዳንቴ(መካነ ንስሐ፤መዝሙር ፪)
በዚሁ መፅሀፋቸው ውስጥ “የስልጣኔ ዘይቤ” በሚል ርዕስ በጻፉት ምዕራፍ ውስጥ፣ ሰው በብዙ ስቃዮች መካከል ሲላጋ፣ሲንገላታ፣ሲንከራተት ስለመኖሩ ለማስረዳት የሚከተለውን የግሪክ ትምህርት “የፕሮሚሴቭስ ተረት” ብለው አስቀምጠውባታል፡፡ እኛም እንደሚከተለው ለርዕሰ አንቀጻችን ፋና - ወጊ አድርገነዋል፡፡
ፕሮሚሴቭስ በከፊል አምላክ በከፊል ሰው የሆነ ህላዌ ነበረ፡፡ በከፊል አምላክ እንደመሆኑ፣ አስራ ሁለቱ የግሪክ አማልክት በኦሊምቦስ ተራራ ሆነው ስለ ሰውና ስለዓለም አስተዳደር ሲመሰክሩ ይሰሙ ነበር፡፡ በከፊል ሰው እንደመሆኑ ደግሞ፣ የሰው ሥቃይና መከራ በጣም ያሳዝነውና ይፀፅተው ነበር፡፡ ሰው፤ ቤት ንብረት ሳይኖረው በበረሃ፣ በጫካ፣ በዱር በገደል በዋሻ፣ በቁር በሃሩር እንዲኖር ተፈርዶበት ነበር፡፡ ይህ መሆኑን አማልክት መክረው፣ ዘክረው፣ ለሰው የእውቀት ምንጭ የሆነውን ብርሃንን የሰጡት እንደሆን፤ ከዕለታት በአንድ ቀን ሰጪነታቸውን ክዶ፣በእነሱ ላይ በመነሳት የሚያምጽ መሆኑን በመረዳት፣ ብርሃንን ከሰዎች ደብቀው፣ (ሰዎች) ከማይደርሱበት ቦታ መሰወራቸው አስፈላጊ ነው ብለው ወሰኑ፡፡ በዚህ ምክንያት ሰዎች በጭለማና የእርሱ ተከታይ በሆኑ ችግሮች ስር ሲሰቃዩ ይኖራሉ፡፡
 ይህ የሰዎች መራራ እድል፣ ወገናቸው በሚሆን በፕሮሚሴቭስ ላይ ርህራሄ አሳድሮበት፤ ብርሃንን፣ አማልክት አርቀው ከደበቁበት ሰርቆ፣ለሰዎች ወስዶ ሰጠ፡፡ ያን ግዜ ማናቸውም ነገር በግልጽ ሆኖ ታያቸው፡፡
በብርሀን ምክንያት  ጥበብና ማናቸውም የዕውቀት ስልት  ስለተገለፀላቸው፣ ራሳቸውን በገዛ ራሳቸው ዘዴ ለማስተዳደር ጀመሩ፡፡ ፕሮሚሴቭስን ግን ለሰዎች ብርሃንን ሰጥቶ በጎ በመስራቱ አማልክት ቀንተው በብርቱ ስቃይ ይቀጣ ዘንድ አዳኝ ከማይደርስበት ገደል ላይ ከቋጥኝ ድንጋይ ጋር በሰንሰለት ተቆራኝቶ አሞራ ለዘለአለም እንዲበተበተው ፈረዱበት፡፡
ከላይ የሆነው ፕሮሚሴቭስ የሰውን እድል ለማሻሻል የሚታገሉት የእውቀት ሰዎች፣ የመምህራንና የሊቃውንት ውሳኔ ነው፡፡ እሱ ብርሃንን አማልክት ከደበቁበት ቦታ ወስዶ ለሰው እንዳበረከተ ሁሉ፣ የእውቀት ሰዎችንም፤ እውቀት በመለኮታዊ ምሦውርነት ከሰው ተደብቃ ስትኖር ሳለ በብዙ ትግል አግኝተው፣ ከገዛ ራሳቸው አስርጸው የወገኖቻቸውን እድል ለማሻሻል ያበረክታሉ፡፡
ዋጋቸውም ሌላ ሳይሆን ስቃይ፣መከራ ነው፡፡ ለምሳሌ ያህል ሶክራቲስ በመርዝ ተገድሏል፡፡ ጆርዳኖ ቡርኖ የጧፍ ቀሚስ ተጎናፅፎ በእሳት ተቃጥሏል፡፡ እነዚህ ሰዎች እንደ ጧፍ መብራት ማለት ናቸው፡፡ እራሳቸው ነደው ተቃጥለው ያልቃሉ፡፡ ለሌሎች ግን ብርሃን ይሰጣሉ፡፡ የፕሮሚሴቭስ ምሳሌ አንድ ትልቅ ህግ ጉልህ አድርጎ ያሳያል፡፡ ይህም “ዕውቀት በስቃይ የሚገኝ ነው”(Learn through  suffering) የሚለው ነው፡፡
እንግዲህ ከመነሻችን እንዳየነው ዳንቴ ፈላስፋው እንዳለው፤ ሁላችንም መንገደኞች ነን። በሀገራችን፣አዲሶች አሮጌዎቹን መንገድ ሲጠይቁ “አሁን እናንተ የሆናችሁትን እኛም አንድ ቀን ነበርን፤” ብለው መመለሳቸው የተለመደ ነገር ነው፡፡ ቀረብ ብለን ስንመረምረው የምናስተውለው፤ የኋለኞች ከፊተኞች አለመማራቸውን ነው፡፡ ሲዳክሩ ውሎ የድሮው ቦታ መቀመጥ ነው፡፡ Back to Square one እንዲል መፅሐፉ፡፡ እንደገና ወደ መሀይምነት፣ እንደገና ወደ ድንቆርና፣እንደገና ወደ ጦርነት፣ እንደገና ወደ መልሶ መገንባት መሄድ መርገምት ነው፡፡ ቢያንስ ከትናንት የተሻለ፣ ስልጡን ስህተት መስራት የአባት ነው፡፡ አንድ የሀገራችን ምሁር “የሰሜኑ የሀገራችን ክፍል ችግር፣መንኳኳት የማይለየው በር ነው” እንዳለው ነው፡፡
እንደ እውነቱ ከሆነ “ሳያስቡት የጀመሩት ቀረርቶ ለመመለስ ያስቸግራል” እንደተባለው፣ የማይቆም ችግር ውስጥ ከመግባት መታቀብ ይገባናል፡፡ ምሁራን፣ንቁና  ስር ነቀል አስተሳሰብ ያላቸው ዜጎች በስሜት ከመነዳት መቆጠብ አለባቸው፡፡ የሀገር ጉዳይ እንደ ትኩሳት “በላብ ያልፍልሃል” የሚባል ነገር አይደለም፡፡ ስክነት፤ቆም ብሎ ማሰብ እና ጥበብ (wisdom) ሊኖረን ግድ ነው፡፡ ጠብ ውስጥ ከገቡ በኋላ ፉርሽ ባትሉኝ ማለት አይቻልም፡፡ ስለዚህ የእውር የድንብር ጉዞ አንሂድ፡፡ “ጅብ በአጥንት የተገደገደ ቤት አለ ቢሉት ወዴት ነው ሳይል ሮጦ ገደል ገብቶ ሞተ” እንዳይሆን እንጠንቀቅ፡፡
ነጋድራስ ገብረ ሕይወት ባይከዳኝ እንዳስቀመጡት፤ “በእያንዳንዱ መንግስት የሚያድሩ ብዙ ልዩ ልዩ ነገዶች ይኖሩ ይሆናል፡፡ መንግስት አንዱን ነገድ አጥቅቶ ሌላውን ነገድ  ለመጥቀም ስራው አይደለም፡፡ አስተካክለን ካሰብን ዘንድ መንግስት መቆሙ ለህዝቡ ሁሉ ጥቅም ነው፡፡ ህዝቡን ሁሉ በትክክል ለመጥቀም ካላሰበ መንግስት በዙፋኑ ሊቆም አይችልም፡፡ ለአንዱ ነገድ ወይም ለጥቂት ሰዎች ብቻ ማድላት ለመንግስት የሚገባ ስራው አይደለም”፡፡ (የመንግስትና የህዝብ አስተዳደር)  
ከላይ የጠቀስናቸው ፀሀፊ ስለደንብ ሲያስረዱንም፤ “እውቀት ላላቸው ህዝቦች ደግ የሆነው ደንብ፣ እውቀት ለሌላቸው ህዝቦች ትልቅ ጉዳት ይሆንባቸዋል፡፡….” ይሉናል፡፡ ዞሮ ዞሮ ምንግዜም ለውጥ እንዲኖር መገኘት አለበት፡፡ ጊዜን የገዛና በአግባቡ የተጠቀመ የብርሃን ወዳጅ ነው፡፡ ጊዜን ያልገዛ፤ “የቸኮለች አፍስሳ ለቀመች” አባዜ ላይ ይወድቃል፡፡ ሰውየው፤ “መሬት ላይ ሆኜ ልውጋህ፣ዛፍ ላይ ወጥቼ? ቢሉት ዛፍ ላይ ወጥተህ አለ፡፡ ለምን ቢባል፤እስከዚያው ድረስ እቆያለሁ አለ” የተባለው የሚገልጽልን ይሄንኑ ነው፡፡ በጊዜ እናስብ፣በጊዜ እንስራ ለውጥን ማሸነፍም ሆነ መሸነፍ የሚገኘው ከጊዜ ጋር ባለን አቅም ነውና  ጥናቱን ይስጠን፡፡




__________________________

Read 12556 times