Print this page
Saturday, 11 December 2021 13:59

ጉዞ ወደ ካሜሮን 33ኛው የአፍሪካ

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(0 votes)

 • 500 ደጋፊዎችን በጋራ ለመውሰድ ታቅዷል፤ ለአንድ ተጓዥ የ10 ቀናት ቆይታ 68,223 ብር
           • 25 ጋዜጠኞች በነፃ የሚጓዙ ይሆናል
           • “የኢትዮጵያን ገጽታ ለዓለም ህዝብ በተቻለ መልኩ ማሳየት እንችላለን።” ሲሳይ አድርሴ
           • ከ100 በላይ ኢትዮጵያውያን ለተሳትፎ ከመላው አውሮፓ ተሰባስበዋል
           • ለተደራጁ የደጋፊ ማህበራት ጥሪ ቀርቧል


          ሲሳይ አድርሴ  ተወልዶ ያደገው በአራት ኪሎ ስጋ መደዳ በሚባል ሰፈር  ነው። ስርዓት ባለው ቤተሰብ ውስጥ ስራን ባህል አድርጎ አድጓል። ባለትዳርና የልጆች አባት ሆኖ እስኪመጣ ድረስ ብዙ  የሕይወት ተሞክሮዎችን  አሳልፏል።  ከስፖርት ጋር በተያያዘ በተለይም በእግር ኳስ ብዙ ልምዶችን አካብቷል። በአውሮፓ የኢትዮጵያውያን የስፖርትና ባህል ፌስቲቫል ላይ የረጅም ዓመት ተሳትፎ አለው። በአገር ውስጥም ከተለያዩ ክለቦች ጋር በገቢ ማሰባሰብ እና ሌሎች ዝግጅቶች ላይ ሰርቷል። በቅርቡ ደግሞ የአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫን  “ሲቲ ካፕን” አዘጋጅቶ ነበር። በ2012 ዓ.ም ላይ ሰላም የገና ባዛርን በ38.4 ሚሊዮን ብር በጨረታ አሸንፎ በማዘጋጀት በኤግዚቢሽን ማዕከል ለ24 ቀናት ማካሄድ ችሏል። ከ428 በልዩ ነጋዴዎች የተሳተፉበትና ከ500 ጎብኝዎችን ያገኘ ነበር። በአገር ውስጥ ከግልና ከመንግስት ኩባንያዎች ጋር በመተባበር የተለያዩ ሁነቶችን አዘጋጅቷል።
በአሁኑ ወቅት በሲሳይ አድርሴ ፕሮሞሽን ዋና ስራ አስፈጻሚ የሆነው ሲሳይ በሁሉም ስራዎቹ በጎፈቃደኝነቱን የሚያበዛ ታታሪ ሰራተኛ ነው።
 በሳምንቱ አጋማሽ ላይ በሸራተን አዲስ በተሰጠ መግለጫ ሲሳይ አድርሴ ፕሮሞሽን ከኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ጋር በመተባበር የደጋፊዎች የአፍሪካ ዋንጫ ጉዞን እንዳዘጋጁ አስታውቀዋል። የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በ33ኛው የአፍሪካ ዋንጫ የሚሳተፍ የሚታወቅ ሲሆን 500 ደጋፊዎችና 25 ጋዜጠኞችን ወደ ካሜሮን በጋራ ለመውሰድ በተያዘ እቅድ ነው። ይህን አስመልክቶ ስፖርት አድማስ ከሲሳይ አድርሴ ጋር ልዩ ቃለ ምልልስ አድርጓል።

          ባለፉት 2 ዓመታት  በኮሮና ወረርሽኝ ሳቢያ በሀገር አቀፍ ደረጃ ብዙ ሁነቶች አይካሄዱም ነበር። በፕሮሞሽን ኩባንያህ በዚህ ወቅት የነበረው ልምድ ምን ይመስላል?
በመስቀል አደባባይ የ6ኛው አገራዊ ምርጫ የመዝጊያ ፕሮግራምን አዘጋጅተን ነበር። አደባባዩ ከተመረቀ  ከሁለት ቀናት በኋላ በኮንሰርት የታጀበውን ታላቅ ሁነት ሰርተናል። ከጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ጋር በመሆን በቢጂአይ ኢትዮጵያ ድጋፍ  በስፖርት አካዳሚ  ተሰባስበው ለነበሩ የጤና ባለሙያዎች በበጎ ፈቃደኝነት የአዲስ አመት ዋዜማ ልዩ ዝግጅትም አሰናድተናል። የምሰራበትን ፕሮሞሽን ኩባንያ በስሜ ከሰየምኩ በኋላ በተለይ ብዙ ሀገር አቀፍ  እና ዓለም አቀፍ ስራዎችን እያከናወንን ነው።
ወደ ካሜሮን 33ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ደጋፊዎችና ጋዜጠኞችን ይዞ ለመጓዝ መነሻው ሐሳብ እዴት ተፈጠረ?
የካሜሮን ጉዞ መነሻው በመጀመሪያ በ2013 በደቡብ አፍሪካ የነበረው ተሞክሮ ነው። ከዚያም ባሻገር በአውሮፓ  በኢትዮጵያውያን በሚዘጋጀው የስፖርትና የባህል  ፌስቲቫል ላይ ባለፉት 4 ዓመታት ተሳትፎ ነበረን። በኢትዮጵያ ያሉ ክለቦችና ተጨዋቾቻቸው  ቢያንስ ከ100  ተጓዦችን በየዓመቱ እየወሰድን ተሳትፎ አድርገናል። የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ለ33ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ካለፈ በኋላ  ከኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ተደውሎ የአቀባበል ስነስርዓቱን አዘጋጅ የሚል ሃሳብ ቀረበልን። ብሔራዊ ቡድኑ አገሩ ሊገባና የአቀባበል ስነስርዓቱ ሊደረግለት የቀሩት ስምንት ሰዓታት ብቻ ናቸው። የፌዴሬሽኑ ስራ አስፈጻሚዎች በኮትዲቫር ስለነበሩ፤አንተ የምትችለውን አድርግ ብለው ሃላፊነት ሰጡኝ። በመጀመሪያ ብሔራዊ ቡድኑን በከተማዋ ዋና ዋና ጎዳናዎች ለማዘዋወር መኪና አዘጋጀን። ከተለያዩ ድርጅቶች ጋር ባለን የቆየ ትስስር ድንገተኛ ሁነቶችን ለማስተናበር አልተቸገርንም። ብሔራዊ ቡድኑ ሐሙስ ጠዋት ሊገባ ረቡዕ  ሌሊቱን ሙሉ የተለያዩ የብራንድንግና የህትመት ስራዎችን አከናወንን።ብሔራዊ ቡድኑን የምናጓጉዝበት መኪና በደንብ አስውበን ተዘጋጀን። በዚህ መሰረት ነው አቀባበሉን በአማረ ሁኔታ የሰራነው። በሲቲ ቱር ክፍት  መኪናው  ከብሔራዊ ቡድኑ ጋር በከተማው ዋና ዋና ጎዳናዎች ስንሽከረከር ጉዞውን  በነደፍኩት ካርታ እየመራሁ ስለነበር። በየመንገዱ ህዝቡ  ለብሔራዊ ቡድኑ ያሳየው ደስታና ክብር አገላለፅ ስሜቴን ነበር የነካው። በሄድንበት ቦታ ሁሉ የነበረው ስሜት ልዩ ነበር። ዘመኑ ያመጣውን ክፉ የመለያየት መንፈስ ሕዝቡ ረስቶ አንድነቱን ነበር ያሳየን። የአቀባበል ስነ-ስርዓቱ መዝጊያ የነበረው የእራት ምሽት በጁፒተር ሆቴል ሲካሄድ  ከፌዴሬሽን ኃላፊዎቹ ጋር ተመካከርን። ከ3 ወራት በፊት ማለት ነው። ጉዞ ወደ ካሜሮን ያልነውን  ፕሮጀክት በጋራ ለመስራትም ተስማማን።
የፌዴሬሽን ኃላፊዎች ደጋፊዎችና ጋዜጠኞችን ወደ ካሜሮን ለመውሰድ ሙሉ ኃላፊነቱን ከሰጡን በኋላ  መጀመሪያ ያደረግኩት በካሜሮን ከሚገኙ ሰዎች ጋር ግንኙነት መፍጠር ነው። በጉዞው ላይ የሚያስፈልጉትን ሁኔታዎች ለማሟላት ወደ ካሜሮን ተጉዘንም የተሟላ ጥናት አድርገናል። ከ500 በላይ ኢትዮጵያውያን  በአንድነት አስተባብረን ጉዞ የምናደርግበትን ዕቅድ አዘጋጅተናል። ዋናው አላማችን በካሜሮን ለ10 ቀናት  በሚኖረን ቆይታ የሀገራችንን ገፅታ ለዓለም ህዝብ  በተሻለ መልኩ ማሳየት የምንችልበት ዕድል ለመፍጠር ነው። ደጋፊዎች በአፍሪካ ዋንጫው በአንድ ቦታ እንዲያርፉ፣ በአንድነት እንዲጓዙ እና በተመሳሳይ አለባበስ እንዲንቀሳቀሱ አስበናል። የክለብ ደጋፊዎች ደግሞ የየክለቦቻቸውን ቀለም እዲያስተዋውቁ በልዩነት ውስጥ አንድነት  አለን የሚለውን መልዕክት እንዲያስተላልፉም እናደርጋለን።   መአቀቦች ሁላችንም ከፍተኛ ድምጽ ባላቸው የከበሮ ጨዋታዎች በብዛት በሚነፉ ጥሩንባዎች እንዲሁም በተጠኑ የድጋፍ ዝማሬዎች በስታድዮም ውስጥ፤ ከስታዲዮም ውጪና በጉዞ ላይ የብሔራዊ ቡድኑን የአፍካ ዋንጫ ተሳትፎ ልዩ ድምቀት እንዲኖረው እንፈልጋለን።  
በአፍሪካ ዋንጫ አዘጋጇ ካሜሮን ካለው የኢትዮጵያውያን ማህበረሰብ አባላት ጋር ምን  እየሰራችሁ ነው?
በካሜሮን ኢትዮጵያን የሚወክለው ኤምባሲ የሚገኘው በጋና ሲሆን በዚያ ያሉት የኤምባሲ አባላት፤ በተባበሩት መንግስታት ሌሎች ዓለማቀፍ ተቋማት የሚሰሩ ኢትዮጵያውያን በአንድ ላይ ተሰብስበውና ልዩ ዝግጅት አድርገው የአፍሪካ ዋንጫውን ይሳተፋሉ። በአጠቃላይ በካሜሮንና በአቅራቢያ ከሚገኙ የምዕራብ አፍሪካ  የኢትዮጵያ ማህበረሰብ አባላት ጋር በቅርበት እየሰራን ነው። በሳምንቱ መጨረሻ ላይ ወደ ያውንዴ  ተጉዘን በምናደርገው ውይይት ብዙ ነገሮች ይመቻቻሉ።
ወደ ካሜሮን ለሚደረገው የአፍሪካ ዋንጫ ጉዞ ለአንድ ተጓዥ ባዘጋጃችሁት ፓኬጅ ምን ያህል ክፍያ ትጠይቃላችሁ?  55,255 ብር ወጪ ይጠይቃል። አጠቃላይ የጉዞ መርሐ ግብሩን  በዝርዝር ብትገልፀው?
መጀመሪያ ላይ ያዘጋጀነው ፓኬጅ  ከአንድ ተጓዥ 55, 255 ብር ክፍያ የሚጠይቅ ነበር። ከሰሞኑ ድንገት በተፈጠረው የኢኮኖሚ ጫና ምክንያት በክፍያው ላይ ማሻሻያ ማድረግ ግድ ሆኖብናል። ለአንድ ተጓዥ የ10 ቀናት ቆይታ የምንጠይቀው ክፍያም 68,223 ብር ሆኗል። ክፍያው ወደ ካሜሮን የአየር በረራ የደርሶ መልስ ትኬቶች፤ ለ10 ቀናት ምግብ (ቁርስ ፣ ምሳ እራት)፤ መጓጓዣና የስታዲዮም መግቢያ ትኬቶችን ይሸፍናል። ከአፍሪካ ዋንጫ ውጭም በካሜሮን ውስጥ የሚገኙ ታሪካዊ ስፍራዎችና የቱሪዝም መስህቦችን የ3 ቀናት መርሃ ግብር በማዘጋጀት በአንድ ላይ በመጎብኘት ኢትዮጵያን እናስተዋውቃታለን። ባወጣነው ፕሮግራም ከመስቀል አደባባይ ልዩ  ሽኝት ለብሔራዊ ቡድኑ እና ለሚጓዙት ደጋፊዎች ይደረጋል። ካሜሮን ስንገባ ደግሞ እዚያ በሚገኙ አስተባባሪዎች ልዩ አቀባበል ይጠብቀናል። ለከውጠየቱ በኋላ ወደ ኢትዮጵያ ስንመለስ ልዩ አቀባበል ይዘጋጃል።
በዚህ አጋጣሚ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን በሙሉ ኃላፊነት እድንሰራ እድሉን ሰጥቶናል። የባህል  ቱሪዝም ሚኒስትር ለምናደርገው ጉዞ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ ትልቅ ድጋፍ እያደረገ መሆኑንም ማመስገን እፈልጋለሁ።
25 ጋዜጠኞችን ከደጋፊዎች ጋር በነፃ ይዞ ለመሄድ ስንወስን ድምፃችን የሆኑ የመገናኛ ብዙሃንን እንዴት እናሳትፋቸው ብለን ነው። ወጭያቸው በስፖንሰርሽፕ አድራጊ ድርጅቶች ይሸፈንላቸዋል። በካሜሮን የሚኖረንን ቆይታ በሙሉ ትኩረት እንዲሰሩበት እንፈልጋለን።
ብሔራዊ ቡድናችን አሁን ባለው አቋም ጥሩ ደረጃ ላይ ነው። ከምድቡ ያልፋል የሚል ዕምነት አለን።  ይህንንም ዋልያዎቹ ከምድባቸው አልፈው ቆይታችን የሚራዘም ከሆነ ከስፖንሰሮች ጋር ተመካረን በምግብና በማረፊያ የሚገጥሙትን ተጨማሪ ወጭዎች መሸፈን በሚቻልበት ሁኔታ እንሰራለን።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በምድቡ በሚያደርጋው ጨዋታዎች ሁሉም ደጋፊ ተመሳሳይ  ቲሸርት ለብሶ ስታድዮም እንዲገባ  አቅደናል። የመጀመሪያ ቀን አረንጓዴ፣ ሁለተኛ ቀን ቢጫ በሶስተኛው ቀን ቀይ  የለበሱ ደጋፊዎች በተጠኑ ዝማሬዎችና የሞዛይክ ትርኢት እንዲያሳዩ ነው።  በስታዲዮም ውስጥና ከስታድየም ውጭ የኢትዮጵያ በሚፈጥሩት ድባብ በቀጥታ የቴሌቪዥን ስርጭት ላይ ትኩረት እንዲያገኙና  ዓለም እንዲያያቸው እንፈልጋለን።
ከአፍሪካ ዋንጫ አዘጋጇ ካሜሮን ጋር በአንድ ምድብ ውስጥ መገኘታችን ትልቅ እድል ነው። በስታድየም ለ10 ቀናት በምናደርገው ቆይታ በስታድዮም ውስጥና ከስታድየም ውጭ ለምናደርጋቸው ተግባራት ዕቅድ አውጥተናል።
በአዲስ አበባ የሚገኘው ካሜሮን ኤምባሲ ምን አይነት ትብብር እያደረጉላችሁ ነው?
የካሜሮን ኤምባሲ የዲፕሎማቶች የተሟላ ትብብር እያደረጉልን ነው።  በእኛ ስር የተመዘገበ አንድም ደጋፊ ወደ ኤምባሲው ሄዶ የሚጉላላበት ሁኔታ የለም። በኮቪድ-19 ተጓዦች መከተል  ያለባቸውን መመሪያ ገልጸውልናል። ወደ ካሜሮን የሚያቀኑት ደጋፊዎች በሚያደርጉት ምዝገባ 2 ጉርድ ፎቶግራፎች ፓስፖርትና ሌሎች መረጃዎችን ካቀረቡ በሙሉ ፈቃድ እናስተናግዳቸዋለን። የካሜሮን ኤምባሲ ሁሉንም ክፍያ በዶላር እንድንፈጽም ጠይቀውናል። በአፍሪካ ዋንጫ ወቅት ደጋፊዎች ከጨዋታ በፊት የሚያደርጓቸውን የኮቪድ-19 የፒሲአር ምርመራዎች በጋራ ሆነው በሚያርፉበት ቦታ እንዲያገኙ እየተነጋገርን ነው።
ምዝገባችሁን ህዳር 28 ከጀመራችሁ በኋላ ምን የተለየ ነገር ተፈጥሯል?
በእቅዳችን መሰረት 500 ደጋፊዎችንና 25 ጋዜጠኞችን ወደ ካሜሮን ይዞ ለመጓዝ ነው። በየአቅጣጫው ከሚመጣው የተሳትፎ  ፍላጎት  አንጻር  ምዝገባውን በአጭር ጊዜ እንደምንጨርስ እያስዋልን ነው። የመጀመሪያውን ጋዜጣዊ መግለጫ ከሰጠን በኋላ በተለይ በለንደን የሚገኙ የኢትዮጵያ  ማህበረሰብ አባላት በአውሮፓ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንን በማስተባበር ለተሳትፎ ከሚያደርጉት እንቅስቃሴ ጋር ተባብረን እየሰራን ነው። ይህን አስመልክቶ ከቱሪዝም ሚንስትር ጋር ውይይት ጀምረናል። የኢትዮጵያ መንግሥት በቅርቡ ከ1 ሚሊዮን በላይ የኢትዮጵያ ዲያስፖራዎች ሀገራቸውን እዲጎበኙ ጥሪ ማቅረቡ ይታወሳል። በመላው አውሮፓ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን በአፍሪካ ዋንጫ ጉዞአችን ላይ ተሳትፎ በማድረግ ለዚህ የመንግስት ጥሪ ፈጣን ምላሽ ሰጥተዋል። ለስፖርቱ ፍቅር ያላቸው ከ100 በላይ ኢትዮጵያውያን በመላው አውሮፓ ተሰባስበው ወደ ኢትዮጵያ በመምጣት አብረን ወደ አፍሪካ ዋንጫ ልንጓዝ አስበናል።
በኢትዮጵያ ከሚንቀሳቀሱ የተለያዩ የደጋፊ ማህበራት ጋር ያላችሁ ግንኙነት ምን ይመስላል?
በዚህ አጋጣሚ በተለያየ መልኩ ለተደራጁ የደጋፊዎች ማህበራት መልዕክት እንዲተላለፍልኝ እፈልጋለሁ። የኢትዮጵያ እግር ኳስ ደጋፊዎች ማህበር፣ ዋልያ ፋንስ፣ ከክለቦች ጋር በተያያዘ በሊግ ካምፓኒው ጋር የሚሰሩ የክለብ ደጋፊዎች፣ የየክለቦችን የደጋፊ ማህበራት… ሌሎችንም በአፍካ ዋንጫ ጉዞ ላይ ኑ አብረን እንስራ ብዬ ጥሪ አቀርባለሁ። ከሁሉም የደጋፊ ማህበራት ጋር ውይይት ለማድረግ ከሰኞ ጀምሮ በራችን ክፍት ነው። አድራሻችን አዲስ አበባ ቦሌ መድኃኔዓለም ቤተክርስቲን ብርሃኔ አደሬ አፍሪካ ሞል ቢሮ ቁጥር M011 ነው። እንደ አገር ለሁሉም ደጋፊዎች ያለኝ መልዕክት በጋራ መስራት እንደሚያስፈልገን ነው። ሀገራችሁን ከፊታችሁ አስቀድማችሁ ያላችሁን ልዩነት ትታችሁ  ወደ ካሜሮን የአፍሪካ ዋንጫ  አብረን እንጓዝ። ድርጅታችን ከሁላችሁም ጋር ግልጽ ውይይት ማድረግ ይፈልጋል። ለሁላችንም አንድ ብሔራዊ ቡድን ነው ያለን፤ አብረን እንስራ ስል መልዕክቴን አስተላልፋለሁ።

Read 1164 times