Print this page
Tuesday, 14 December 2021 00:00

በመላው አለም 293 ጋዜጠኞች በእስር ላይ ይገኛሉ

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

  ባለፈው አመት 24 ጋዜጠኞች ተገድለዋል

           በመላው አለም የተለያዩ አገራት በእስር ላይ የሚገኙ ጋዜጠኞች  ቁጥር በታሪክ እጅግ ከፍተኛ በመሆን 293 ላይ መድረሱንና በፈረንጆች አመት 2021 በመላው አለም 108 ጋዜጠኞች ለእስር መዳረጋቸውን፣ ከ24 በላይ የሚሆኑ ደግሞ ከሙያቸው ጋር በቀጥታ በተያያዘ መገደላቸውን አለማቀፉ የጋዜጠኞች መብት ተሟጋች ሲፒጄ ሰሞኑን ባወጣው አመታዊ ሪፖርቱ አስታውቋል፡፡
ላለፉት ስድስት ተከታታይ አመታት ባወጣቸው ሪፖርቶች የታሰሩ ጋዜጠኞች ቁጥር ከአመት ወደ አመት አዲስ ክብረ ወሰን በማስመዝገብ እያደገ መምጣቱን ያስታወሰው ተቋሙ፤ 50 ጋዜጠኞችን ያሰረችው ቻይና በአመቱ በርካታ ቁጥር ያላቸውን ጋዜጠኞች በማሰር ከአለማችን አገራት በቀዳሚነት እንደተቀመጠች አመልክቷል፡፡
ቻይና ባለፉት ሁለት ተከታታይ አመታትም ቀንደኛ የአለማችን አሳሪ በመሆን በ1ኛ ደረጃ ላይ እንደነበረች ያስታወሰው ሪፖርቱ፣ ማይንማር 26፣ ግብጽ 25፣ ቬትናም 23 እንዲሁም ቤላሩስ 19 ጋዜጠኞችን በማሰር እንደ ቅደም ተከተላቸው እስከ አምስተኛ ያለውን ደረጃ መያዛቸውንም ያሳያል፡፡
በአሁኑ ሰዓት በመላው አለም በእስር ላይ ከሚገኙ 293 ጋዜጠኞች መካከል 40 ያህሉ ሴቶች መሆናቸውን የገለጸው ተቋሙ፤ የጋዜጠኞችን እስርና ግድያ አስመልክቶ በየአመቱ አለማቀፍ ሪፖርት ማውጣት ከጀመረበት እ.ኤ.አ 1992 አንስቶ እስካለፈው ወር መጀመሪያ በድምሩ ቢያንስ 1 ሺህ 440 ያህል የአለማችን ጋዜጠኞች መገደላቸውን ማረጋገጡንም አስታውሷል፡፡


Read 2668 times
Administrator

Latest from Administrator