Saturday, 11 December 2021 14:09

ተረቴን መልሱ፣ ከረከሰ አፌን በዳቦ አብሱ!

Written by 
Rate this item
(2 votes)

    ....... “ተረት በእነ - እከሌ ዘመን ቀረ!” እያልኩ ያላየሁትን ዘመን በማዳነቅ ቁጭት መቀስቀስ አማረኝ።
ታዲያ ቢያምረኝ ምን አለበት ወገን? ሀቅ ሀቁን እንነጋገር ከተባለ ተረት እየተነገረው የሚተኛ ህፃን ነው እንግዲህ አድጎ ባለስልጣን ሲሆን በየፓርላማው ላይ አንዳች እንደዋጠ ዘንዶ “ዧ” ብሎ ተጋድሞ ስብሰባ የሚረብሸው። የአንዳንዱ አስተኛኘትና ደንብርሮ አነቃቅ፣ መንግስት በልዩነት ለፕሮቶኮል የፈቀደው እስኪመስልህ ያስገርምሃል።
ስለዚህ ወላጆች ተረት ስትነግሯቸው ልጆቻችሁ ተረቶቻችሁን ጨርሰው፣ ከተረቱ  የተረዱትን  ነግረዋችሁ ሲጨርሱ ይተኙ።   ወይም ተረት ይቅር !
ስንቱን አስተምሮና አፀፅቶ ከጉድ ያወጣ ተረት፣ ዛሬ በኛ ዘመን ህፃናት ማስተኛ እንቅልፍ መድሃኒት ይሁን ? ወይ ነዶ አለ ገራዶ! (ውሸቴን ነው አላለም)
አንዳንዴ ከጓደኞችህ ጋር ሆነህ አንዳች ነገር እያወጋህ ወይም አንድ መስሪያ ቤት ተገኝተህ የሆነ ነገር እያስረዳህ ስትናገር “ባክህ ተረት ተረትህን ተውና ነገሩን አስረዳኝ! “ይሉሃል።  ምን እያሉህ መሰለህ? "እንቅልፌን ታመጣውና ከስራዬ (ከውሎዬ) ታስተጓጉለኛለህ"  ማለታቸው ነው።
ዛሬ በእድሜ ዘመኔ ተረት እንደ እንቅልፍ አስወሳጅ ሻርፕ፣ በሁሉም የከንፈር መዳፍ በሚጎተትበት ሰዓት "ነፃ አውጪ ነኝ!" እያሉ ነፋስ እንደሰበሰበው የቅጠል ክምር ተከምረው፣ ሰላማችንን ከሚነሱን ድርጅቶች ውስጥ አንድ ስለ ተረት ነፃ አውጪ የሆነ ተቋም በማጣታችን እጅግ ያሳዝናል።
ዛሬም የአባት የአያቶቻችን ተረት ያቃረን እንቅልፍ ፍራቻ ይሆን? ለማለት እልና፣ ነገን ባለማሰብ እንደጠገበ ሰነፍ ለጥ ብላ የተኛች ሀገሬን እያሰብኩ፣ “አበስኩ” እላለሁ፤ እናንተ ከፈለጋችሁ “ገበርኩን” ጨምሩ።
እናም እንደ መሸጋገሪያ ለተረት ነፃ አውጪነት ሳይሆን እንዲሁ ለመተዛዘን አንድ ተረት ልንገራችሁ።
በየተረቱ መሀል እንቅልፍ እንዳይወስደን የሚፈነዳ ቦንብ እስክፈጥር እንዳትተኙ ለማለት ያህል ነው።
መልካም እንቅልፍ! ማነው መልካም ንባብ!
ተረት.... ተረት
የመሰረት በሉ እንጂ! (ግን መሰረት ማናት? ሆሆሆሆሆ)
....... ወይ ነዶ! ... (ርዕሱ ነው። ማሪያምን!)
....በድሮ ዘመን በአንድ ማህበረሰብ ውስጥ የሚኖሩ አዋቂዎች ነበሩ። እነዚህ አዋቂያን፣ ከአባት አያታቸው የወረሱትን ጥበብ እየተመራመሩ፣ በአንዲት ትንሽዬ መንደር በማሳለፋቸው፣ ራቅ ካሉ ወዳጆቻቸው ጋር ሳይቀር የሚታወቁና የሚወደዱ ነበሩ።
ከእለታት በአንዱ ቀን ካሉበት መንደር እጅግ ራቅ ወደ ምትል መንደር በአስቸኳይ መልዕክት መላክ አስፈለጋቸው። መልዕክቱንም በፍጥነት እንዲደርሳቸው በማሰብ፣ ከማህበረሰቡ ውስጥ አንድ ጠንካራ ወታደር መርጠው ጠሩት። አደራቸውንም ሲያስረዱት፤
“ዋናው መንደር የስምንት ቀናት መንደር ናት። ከቻልክ በሰባት ቀን ከግማሽ ጨርሳት። አለበለዚያ ግን ከስምንት ቀን በላይ ከቆየህ ወራሪ ጠላት መንደራቸው ይገባና እንደተለመደው ወንዶችና ህፃናትን ገድሎ፤ ሴቶችን ደፍሮ፤ ንብረት ዘርፎ ይሄዳል። ይህ አይነት ወረራ በሀያ ዓመት አንዴ የሚሆን ቢሆንም አቆጣጠሩ እጅግ አደናጋሪና ግራ አጋቢ ነው። እነሱም ባለፈው አመት ይመጣሉ ብለው ጠብቀው ነበርና ሳይመጡ ቀሩ። አቆጣጠሩን ተሳስተዋል። ሃያኛው የመሰላቸው አምና አስራ ዘጠኝ ነበር። ዋናው መንደር ከመድረስህ በፊት መሀል ላይ አንዲት መንደር ታገኛለህ፤ እዛች መንደር ውስጥ ቀላሉን የአቋራጭ መንገድ የሚያሳዩህ ሽማግሌዎች አሉ። እነሱ አቋራጩን ያሳዩሀል፤ በፍጥነት ከአደጋው ታደጋቸው፤ አደራ አደራ ...” እያሉ ወታደሩ እንዲዘገጃጅ በጥድፊያ ውስጥ ሸኙት።
ወታደሩ ማልዶ ከመንደሩ ወጥቶ አለእረፍት ተጉዞ፣ በአራተኛው ቀን አመሻሽ ላይ ልክ ጀምበር ማዘቅዘቅ እንደጀመረች፣ በዛች መሀል ላይ ታገኛታለህ በተባለችው  መንደር ገባ። ወደ መንደሯ ሲገባ ወታደሩ ባልለመደው ሁኔታ ጭር ብላ አገኛት። በመንደሯ የሚገኙ ቤቶችም በርና መስኮታቸው ተከርችሞ በፅማዌ ሸማ ተጀቡነዋል።
ይህ ግራ ያጋባው ወታደር ሰውነቱ በድካም በመዛሉ፣ የመንደሯ እምብርት ላይ የሚገኘውን ግዙፍ ዋርካ ደገፍ ብሎ ሁኔታውን ለማጣራት አረፍ አለ። ሆኖም ግን አንድም በመንደሯ የሚዘዋወር ሰው በአይኑ ያልገባው ወታደር ግራ እንደተጋባ፣ ደራሽ ድካምና እንቅልፍ ተባብረው ደገፍ ባለበት ያንኮራፋ ጀመር።
ወታደሩ ቀኑን ሙሉ ባሳለፈው ጉዞ በተጫጫነው ታላቅ ድካም ጭልጥ አድርጎ ያስቀረው እንቅልፍ፣ ነግቶም የመንደሯ ነዋሪዎች ከእንቅልፋቸው ያን ዋርካቸው ስር ያረፈውን ወታደር አይተው ዝም አላሉም።
የተኛን ከእንቅልፍ መቀስቀስ ባህላቸው የማይፈቀደው እኚህ ማህበረሰቦች፣ ወታደሩ በተኛበት መጠነኛ ዳስ ሰርተው የሚለበስ ነገር አልብሰው እስኪነቃ ጠበቁት። ወታደሩ ግን በህልሟ ለምለም ሰርዶ እየጋጠች መንቃት እንዳልፈለገች ህልመኛ ላም፣ ለጥ ብሎ መነሳት ገደፈ።
የመንደሯ ነዋሪዎችም የምሽት ጀምበር ከማዘቅዘቋ ቀደም ብለው የመተኛት ልምድና የንጋት ጀምበር ሳትወጣ የመንቃት ባህል ስለነበራቸው፣ ልክ ጀምበር በምስራቅ የአድማስ ሰቀላ ስር ደም መስላ ከመታየቷ በፊት እያንጎላጀጀ በሚነዳቸው የእንቅልፍ እረኛቸው እየተነዱ፣ ወደ አልጋቸው ግርግም አዘገሙ።  
ልክ የመንደሬው ሰው ከገዛ እንቅልፉ ጋር ሰምና እሳት ሆኖ ለጉድ ሲንበለበል፣ ጀምበሯ ጠልቃ ምድር በፅልመት የብርሃን ጠላት ስትወረር፣ ወታደሩ አንድ ሌትና አንድ ቀን ካሸለበበት ነቃ። ሲነቃ ምድሩ በፅልመት የብርሃን ጠላት ከመወረሩም ባሻገር ያላወቀው ሰው ዳስ ዘርግቶ ኩታ አልብሶ መኝታውን ስላመቻቸለት በልቡ እያመሰገነ፣ የተኛው አንድ ሌትና ቀኑ እንቅልፍ፣ የአንድ ሰዓት ያህል ስለቀለለበት የጀመረውን እንቅልፍ ቀጥሎበት ተኛ።
በነጋታው የመንደሩ ሰው ከእንቅልፉ ሲነቃ፣ ወታደሩ ከባለፈው ሌሊት በተሻለ ቦታና ሁኔታ ላይ ተመቻችቶ በመተኛቱ፣ እፎይታ በነገሰበት ጥልቅ የእንቅልፍ ሰረገላ ላይ ተሳፍሮ ፍም ውስጥ የወደቀ ቅቤ ሆኗል። እንደተለመደውም ባህላቸው የተኛን መቀስቀስ ነውር ስለሆነባቸው፣ ምግቡን ከጎኑ አስቀምጠው ሲጠብቁት መሸና ወደ ማረፊያቸው አቀኑ።
እንደተለመደው ወታደሩ በውድቅት ሲነቃ፣ ለቀናት ያሳሰረው የድካም ሰንሰለት ተበጣጥሶ ወድቆ ስለነበረ፣ ድጋሚ ሳይተኛ እስከ ንጋት ጠበቃቸው። የመንደሩ ነዋሪዎችም ሲነቁ ወታደሩን በአጀብ እየተመለከቱት እንዴትና ለምን እንደመጣ ጠየቁት። ወታደሩም ከመንደሩ ሽማግሌዎች የተቀበለውን አደራ ሙሉ በሙሉ አስረድቷቸው እንዳበቃ፣ ለምን ያህል ቀናት እንደተኛ ጠየቃቸው፡፡ እነሱም ለሁለት ቀናት እንደተኛ ሲነግሩት “ ዋናዋ መንደር የስምንት ቀናት መንገድ ናት። ከቻልክ በሰባት ቀናት ከግማሽ ጨርሳት። አለበለዚያ ከስምንት ቀናት በላይ ከቆየህ ወራሪ ጠላት መንደራቸው ይገባና እንደተለመደው ወንዶችና ህፃናትን ገድሎ፤ ሴቶችን ደፍሮ፤ ንብረት ዘርፎ ይሄዳል።" ያሉት የሽማግሌዎቹ ንግግር ትዝ ብሎት በድንጋጤ ደርቆ ቀረ።
****
ዘውትር በሰማዋት ቁጥር ሆድ ሆዴን የምትበላኝ አንዲት አባባል አለች።
“ሳይነቁ ነቅተን ሲነቁ ተኛን!”  የምትል። እውነት ነው!! ማንም ሳይነቃ ከአለም ሀገራት ቀደም ብለን ነቅተን፣ አሁን ጨምባሳዋ አለም ከተኛችበት ስትነቃ፣ ማሸለባችን የአደባባይ ሚስጥር ሆኗል።
ለረጅም ዘመናት ሀገራችን ልክ እንደ ወታደሩና የመንደሯ ነዋሪዎች የመንቃትና የመተኛት አዙሪት
ውስጥ ወድቃ ነበር። ወይም ወድቃለች። ሀገር ከጀግኖቿ እኩል ልትነቃ አልቻለችም። ጀግና ሲያልፍ ህዝብ፤ ህዝብ ሲያሸልብ ጀግና እየነቃ አሳራችንን አይተናል።
በታሪክ ዳራዎቻችን ዳስ ውስጥም ከአፄ ቴዎድሮስ ዘመነ - መንግስት ጀምሮ አሁን እስከአለንበት የጉዞ ወሰን ሀገርና ጀግኖቿ እየተፈራረቁ የሚነቁና የሚያሸልቡበትን ሽሚያ በስፋት እየተመለከትን እንደሆነ እገምታለሁ። እንደ አብነትም ሁለት በታሪካችን የጉዞ መስመር ውስጥ ታይተው የከሰሙ እውነታዎችን በትዝታ መልክ እንመልከት፡፡ እነሆ፦ አፄ ቴዎድሮስ ፪ኛ በ፲፰፵፯ /1847 / ዓ.ም የንግስና መንበሩን ከጨበጡበት ጊዜ አንስቶ እስከ አሁን ድረስ ፈተና የሆነብንን የአንድ ኢትዮጵያን ፅንሰ-ሀሳብ ይዘው ሲመጡ ህዝብ /ትውልድ/ ተኝቶ፣ የነቃ ጀግና ብቻውን ሲንጎማለል ከረመ።
አፄው ቴዎድሮስም ሀሳቡን ሊረዱለት ባልቻሉ የሀገሩ ህዝቦች መካከል ሽሉን ተሸክሞ አዋላጅ ፍለጋ እድሜ ዘመኑን ቢባዝንም፣ አንድም በጄ ብሎ የተቀበለው በማጣቱ፣ ያሰበው የግዙፍ ሀሳብ ፅንሰት ተጨናግፎ ቀረ።
እሳቸውም አይደለም ኢትዮጵያን አፍሪካን የሚያበለፅግና ሰርክ በመሪር ክንዱ ከሚያላጋት የድህነት አዘቅት ጎትቶ ሊያወጣት የሚችለውን ሀሳብ ታቅፈው፣ የገዛ ድንበራቸውን ተሻግሮ ሊወጋቸው ለመጣው የኢንግሊዝ ጦር እጅ አልሰጥም ብለው፣ በራሳቸው ሽጉጥ ራሳቸውን አጠፉ። በተኛ ትውልድ መካከል መንቃት ፈተና የሆነባቸው አፄ ቴዎድሮስ፣ ከሞቱ ወዲህ ቀጣይ በመጣው ትውልድ ምላስ ላይ ብቻ እየተዘከሩ፣ ግብራቸው ተረስቶ፣ ዛሬም ድረስ ስማቸው ከፍ ብሏል።
በመቀጠልና በሁለተኛነት ትልቅ ቅዠት ውስጥ ተዘፍቀው በነበሩት ቀዳማዊ አፄ ኃይለ ስላሴ ዘመን፣ ህዝቡ የተገላቢጦሽ ነቅቶ ጀግና መሪዋ ተኝቶ ነበር። ይህም የህዝብ ንቃት ጣሊያን በድጋሚ ሀገሪቱን ለመውረር ጦሩን ሰብቆ በመጣ ወቅት ንጉሱ በእርዳታ ሰበብ ሀገር ለቀው ሲጠፉ፤ በላይን የመሰለ የቁርጥ ቀን ልጅ ንጉስ ይዘዘኝ ሳይል፣ ለሀገሩ ዘብ ቆሞ፤ ስንቱን ጣሊያን እንደፈጀ ለማወቅ ዞር ብሎ ታሪክ ማጥናት በቂ ይመስለኛል።
በላይ የወንዶች ቁና ለሺህ ሰራዊት ያልደነገጠ እቶን፣ የተኛውን ተፈሪን ትቶ፣ ከነቃው ህዝብ ጋር ነቅቶ የሀገሩን ክብር ቢያስጠብቅም፣ እንቅልፋሞቹ ሸልመው እንሹምህ ሲሉት አሻፈረኝ ባላቸው ማግስት በሀኬታቸው ገመድ ተብትበው የጣሊያን ታንክ ያልመለሰውን ጀግና፣ እንደ ተፈሪ አንገት የሰለለች ቀጭን ሲባጎ የኒሻኑ ማሳረጊያ ሆነች።
የሆነው ቢሆንም ከእግዜር መቀባትን እንደ ሁለት ብር ባዝሊን መቀባት ያቀለሉት እኚህ ሰው፣ በተራ የመንደር ውሪ “ሌባ !” እየተባሉ ከስልጣን ተባረው  መገደላቸው ይታወቃል።
(ማሳሰቢያ) በአፄው ዘመነ - መንግስት የህዝብ ንቃተ - ህሊና ከፍ ያለ በነበረበት ወቅት፣ ከህዝብ መካከል የወጡ እልፍ ጀግኖች እንደነበሩ ማስታወስ ያሻል። ሆኖም የጀግኖቹ መምጣት እረፍት የነሳቸው አፄው፣ መጨረሻቸውን የአፈር ፅዋ ድግስ አድርገውታል።
መቀስቀስን በጠላ እንቅልፋም መሪ የጠፉትን የሀገሬን ጀግኖች ሳስብ፣ ልክ እንደ በላይ የእርግማን ምንዳ ዛሬም የሚያዞረን አዙሪት መች ጥሎን እንደሚጠፋ እያሰብኩ፣ ማን አስደግሞብን ነው እላለሁ። ጣሊያኖች ናቸው እንግሊዞች ? ወይስ ደርቡሾች ናቸው በመሬታችን ውስጥ መተት ቀብረውብን የሄዱት ? ማለት ያምረኛል።
ብር ማዋጣትን እንደከዳ ወዳጅ እርግፍ ባናደርግ ኖሮ፣ አዋጡና በጣሊያን ወይም በእንግሊዝ ፤ በሱዳን ወይም በቱርክ ገጠሮች ውስጥ ጠንቋይ እየፈለግኩ ሀገርና ጀግኖቿ እኩል እንዳይነቁ ያስቀበሩብንን መተት አስፈታ ነበር። ከዚህ ቀደም ባዋጣችሁት ገንዘብ ስንቱ ጉድ እንደሰራችሁ ስለምታውቁ "በብራችን በየገጠሩ እየዞረ ልጃገረድ (ድንግል) ሊፈልግበት ነው።” ማለታችሁ አይቀርም።
እናንተ ብቻ አዋጡ እንጂ እኔ ሁለቱንም መፈለግ አውቅበታለሁ። ከጠንቋዩ ጓሮ ልጃገረዷን አገኝ ይሆናል። ማን ያውቃል? ማንም!
ወደ ጉዳያችን እንግባና ሀገር ከጀግኖቿ እኩል እንዳትነቃ የሆነችበትን ሰበብ ሳስብ የሚመጣልኝ ይሄ ነው።
የኛ ህዝብ በመሪው፣ በሀይማኖት አባቱ፣ በፖለቲካውና በጋዜጠኛው ብሎም የህዝብ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ላይ ባሉ አባሎች ጭምር በተለያዩ ጊዜ ተሸውዷል። ተታሏል። ህዝቡን ሜዳ ላይ እንደተገኘ ፈረስ በእውነት ስም ለሀሰት እየጋለቡት ልቦናውን ሰልበውታል።
ልጅ ሆኜ ካነበብኳቸው የተረት ታሪኮች ውስጥ አሁን ድረስ በጉልምስናዬ ይሁን በጉርምስናዬ ባላውቅም የማትዘነጋኝ ሀሳብ አለች።
ልጁ እረኛ ነው። ሲበዛ ቀልድ ወዳድ ነው። ያልሆነን ነገር ሆነ ብሎ ሰው ሲደነግጥ በድንጋጤ ውስጥ ባለው መረበሽ ይዝናናል። አንድ ወቅት በመንደሩ ውስጥ በጎቹን እየጠበቀ ድንገት “ኡኡኡኡ በጎቼን ተኩላ በላብኝ! አትርፉልኝ ኡ-ኡ-ኡ-ኡ" አለ የመንደሩ ሰው አካፋ፣ ዶማ፣ ዘነዘና፣ ጭልፋ፣ ማንቆርቆሪያና ሊጎርሰው ያለውን ጉርሻ (ይህቺ እንኳን የኔ ጭማሪ ናት!) አንከርፍፎ በደረስንለት ውክቢያ እየተንጋጋ መጣ።
እረኛው ሁኔታቸውን ባየ ጊዜ ልቡ ፍርስ እስክትል ድረስ በሳቅ አውካካ። የመንደሩ ነዋሪዎችም ተበሳጭተው እየተሳደቡና እየተራገሙ ወደየ ቤቶቻቸው ገቡ። እንዲሁም በሌላኛው ቀን እንደተለመደው "ኡኡኡኡ ተኩላ በጎቼን በላብኝ፤ ድረሱልኝ! ድረሱልኝ" እያለ ጮኸ።
እንደተለመደውም፣ የመንደሩ ነዋሪዎች እየተንጋጉ ሲወጡ፣ እሱ እንደ ከዚህ ቀደሙ አመጣጣቸውን እየተመለከተ እንደለመደው መስኩ ላይ እየተንከባለለ በሳቅ መንፈር ጀመረ። ነዋሪዎቹም በሁኔታው እየተበሳጩና እየተራገሙ ወደ ቤታቸው ገቡ።
ለሶስተኛ ጊዜም እንደዚሁ የተለመደውን ተግባር ፈፅሞ የሰፈሩ ሰዎች የያዙትን ይዘው ሲወጡ እንደለመደው እየተራገሙ ወደ ቤታቸው አዘገሙ።
ከእለታት በአንዱ ቀን ግን እውነተኛ የተኩላ መንጋ መጥቶ፣ መስኩ ላይ የፈሰሱት በጎች ላይ መስፈር ሲጀምሩ፣ እረኛው እውነተኛ ጩኸቱን ጮኸ። የሰማው ግን አልነበረም።
የመንደሩ ሰው በሞላ “የአንተ መጫወቻ አይደለንም" ብሎ ሰምቶ እንዳልሰማ ዝም አለ።
የእኛም ህዝብ የገጠመው ይህ አይነት ጨዋታ ነው።
ቀልዱ ሸፍጡ እና ሴራው እየበዛ በመምጣቱ፣ እውነተኛው ደወል የትኛው እንደሆነ መለየት አቃተን።
ዘላለም አለሙን ቀልድና ፌዝ፤ ማስመሰልና ውሸትን መርህ ያደረጉ እረኞቻችን ተሳስተው እውነት እንዳይወጣቸው የቀልዳቸው፣ የሀሰታቸው፣ የፌዛቸው ክብደት ሚዛን ደፍቷል።
ማንም ሊፈርድብን አይችልም።
እኛን ሆኖ ያፈረ፣ አንገት የደፋ እና የተሳቀቀ ካልሆነ ማንም አይረዳንም።
ቀልዳቸው የድንጋጤ ካባችንን ገፎ፣ የቸልታ ካባ አልብሶናል።
የመንሰፍሰፍ ሸማችንን ነጥቆ የተስፋ መቁረጥ ጋቢን አልብሶናል። ሲጠሩን ያልሰማነው ፤ ያታልሉናል ብለን ነው። ሀገሬ ሀገሬ ሲሉን ዝም ያልናቸው ጋልበውን ሲያበቁ፣ የትም የጣሉን ስላሉ ነው።
እረኞቻችን በእምነት እንዳንነሳ ሰብረው ጥለውናል። እንደ ማሳሰቢያ ራሳችንን ከሀሰተኛ እረኞች ጥሪ መታደግ ካልቻልን፣ እጣ ፈንታችን አሳሳቢ ይመስለኛል። ምናልባት አንድ ቀን የእውነተኛ የእረኛ ድምፅ ይሰማንና የመንደሩ ነዋሪዎች ቸልታ ተወግዶ፣ በጎቻችንን ከተኩላ መንጋ እንታደጋቸዋለን ብዬ አስባለሁ።
ሀሰተኛ፣ ፌዘኛና መሰሪ እረኞችም በቸልታችን ስውር ምሬት ተማረው ሄደው ፤ አዲስ ልባም ፣ ታታሪና ፈሪሀ እግዚአብሔርን የተላበሱ እረኞች እናገኝ ይሆናል።
እናም እንደ መሰናበቻ ሀገር እንደ ሀገር የምኞት ቀንዲሏ ላይ የተግባር ሻማዎች ተለኩሰው፣ ትንሳኤዋ በወገግታ እንዲታይ፣ ሀገር ስትነቃ የሚያልፍ ጀግና ፤ ጀግናዋ ሲነቃ የምታሸልብ ሀገር እንዳትኖር የእኩል ንቂያ ደወል በጋራ መስማትን ያሻል።
አንድ ላይ መንቃት የህልም ያህል ቢከብደንም፣ አምናለሁ አንድ ቀን ይሆናል።
በተባበረ ክንድ ሀገራችንን ከፍ የምናደርግበት ጊዜ ሩቅ አይሆንም።
.........................../////............................
ተረቴን መልሱ፣ ከረከሰ አፌን በዳቦ አብሱ!

Read 1495 times