Saturday, 11 December 2021 14:11

“ነውርን እንደ ወረደ” (አዲሱ ፋሽን)

Written by  አብዲ መሃመድ
Rate this item
(1 Vote)

በዚህ-ዓመት የመጽሐፍት ገበያውን በከፊል ተዟዙሬ ለማየት እንደሞከርኩት ጥቂት የማይባሉ “ወሲብ” እና “ጭን” ተኮር ሥራዎች በገፍ ተቀላቅለው በብላሽ ተነበዋል፡፡ ፍላጎት ያለ-ቅጥ መኖሩ አቅርቦቱን ማብዛቱ አያጠያይቅም፡፡ የቁጥር-ብዛታቸውን ያህል አይነታቸውም የተለያየ ነው፡፡ በተለይ አሁን-አሁን በዚህ ጉዳይ ላይ የሚጻፉ ድርሣናት፤ ፀሐፊዎቻቸው የወሲብ ገድላቸውን፣ የአስረሽ ምቺው ድላቸውን ብቻ ለይተው መተረክ እንደ-ፋሽን እየተለመደ፣ እየበረከተ መምጣቱ የአደባባይ ሚስጥር ከሆነ ሰነባብቷል፡፡ ከወሲብ የዘለለ ሕልም የሌለን ይመስል፡፡ አእምሮአችንን በዚህ ጠምደውና ሰንክለው የሚያደነዝዙን፣ ትውልዱን ከማነጽና ከመቅረጽ ይልቅ የበሸነና፣ የውስልትና ነፃነትን በይፋ የሚያውጁ፣ ነውርን እንደ የአዘቦት ግብር የሚያበረታቱ፣ የንፁህ እህቶቻችንን ጭን በማርከስ ሀሳብ የተበጃጁ፣ የቡና ቤት ጀብዱዎች፣ የማሳጅ ቤቶች ድብቅ ባዮግራፊዎች፣ የፔንሲዮን ዜና-መዋዕሎች፣ የገስት ሀውስ ዝክረ-ነገሮች፣ የፓርቲ ከበርቻቻ ፣ የናይት ክለብ መዛሞቻ…..ዛሬ-ዛሬ እግራችን በሚረግጥበት የንባብ ማዕከላት፣ ለሽያጭ በተዘረጉ መጽሐፍት መካከል ፣ ጎራ ባልንባቸው የንባብ መደብሮች ማየታችን የተለመደ ሆኗል፡፡ ኢትዮጵያዊ  ግልጽ ወሲባዊ ነውሮችን ዛሬ በመጽሐፍ ነገ ደግሞ በተንቀሳቃሽ ምስል (ቪዲዮ) የምናይበት ጊዜ ሩቅ እንዳልሆነ ለመተንበይ እምብዛም ወልይ መሆን አይጠይቅም፡፡ በመጽሐፍ ከተሰነዱልን (ከብዙ በጥቂቱ) ከቅርብ ጊዜዎቹ መርጬ ለዛሬ ሁለቱን ለመቃኘት እሞክራለሁ፡፡
በተለያዩ ግለሰቦች ተጽፈዋል፡፡ ዞሮ-ዞሮ ጭብጣቸው ተመሳሳይ ነው፡፡ በአምሳል ጥንድ - በቋንቋ ስድ መጽሐፍቶች፡፡ ዋሂዱ  “የጭን አበባ” ይሰኛል፤ አበባው ድንግልና መሆኑ ነው፡፡ መጽሐፉ የድንግልና ዝርዝር ሜኖ ይዟል፡፡ በዚህ ዓመት ጥቅምት ወር አካባቢ ለንባብ የበቃ የስርያ ማስታወሻ ነው፡፡ ዮኒ ማኛው በተባለ ግለሰብ  (ጤፉ የሰርገኛ ነው  የአቦልሴ) ጭን ሲያንቀጠቅጥ፣ በየስርቻው ከልጃገረድ ጋር ሲልመጠመጥ በጐለመሰ ብኩን ፀሐፊ የተደረሰ፡፡ በርግጥ መጽሐፉ ድርሰት አይደለም፡፡ የድርሰት ቁመናም-ናሙናም የለውም፡፡ የወሲብ ዛሩን፣ የስርቆሽ ሀራራውን ሊያጋባብን ያነጣጠረ፣ የዞረበት መዝገብ እንጂ፡፡ ይሄንን የዞረ-ድምር ስካር ለመፃፍ መነሻና ድፍረት የሆነው ስብሀት እንደሆነ በመግቢያው ላይ አስፍሯል፡፡ ፀሐፊው አንድ መቶ ሃምሳ ገጽ ሙሉ ጭን ያስቀጠቀጠባቸውን፣ ድንግልና የሰባበረባቸውን የደም ሪከርዶቹን ለመፃፍ ስብሃትን ከለላ ማድረጉ አንድም ከምግባር የራቀ ውርደት፣ ሁለትም  የስብሃት ልብወለዶችን ጭብጥ ካለመረዳት ድንቁርና  የመነጨ እብደት ነውና ምን ማድረግ ይቻላል? የነውሩን  ድህረ-ብልግና የስብሀትን “ናቹራሊዝም” አፃፃፍ በጭምብልነት ሲጠቀም የሚያስነብበን እንዲህ በማለት ነው፡፡… “ታላቁ ደራሲ ስብሃት ገ/እግዚያብሔር እርሱ የፈጠረው እያለ ምን አስፈጠረኝ እንዳለ፣ እኔ ከልቤ አንቅቼ በአይምሮዬ አሰላስዬ አንዲት  እንኳን አልፃፍኩም፤ እንዲሁ የኖርኩትን ፃፍኩ እንጂ፡፡ እውነትን ለማለዘብ እና ስነ-ጽሑፋዊ ውበት ለመስጠት አልታተርኩም ይልቁንም እንደ-ወረደ ሁነቱን ገለጽኩ እንጂ፡፡ ስለዚህ ይህ የኔ የወሲብ እውነተኛ ገድል ነው።" (ገጽ 2)
እንግዲህ በመግቢያው ይሄን ብሎ የጀመረ ፀሐፊ፣ ቀጥሎ ምን ሊጽፍ እንደሚችል ለመተንተን መሞከር አንባቢን አላዋቂ አድርጎ መቁጠር ይሆናል፡፡ ወይም ለቀባሪው ማርዳት፡፡ በአስራ አራት ንዑስ ርዕሶች ስር ያለ-ቅደም ተከተል የሸነሸናቸው ታሪኮቹ ተዘርዝረዋል፡፡ ከቅጠሉ ጀርባ፣ የእውቀትን ፍሬ አበላኋት፣ ሎቱ ስብሃት፣ ወሲብ በዜማ….እያለ ልቅ በሆነ ሁኔታ እንደ-ወረደ ይተርከዋል፡፡ በርግጥ ነፍሱን ይማረውና ጋሽ ስብሀትም ቢሆን ሣያለዝብ እንደ-ወረደ በማህረሰቡ በግልጽ የማይጠሩትን ሀራም ቃላት ሲጠራ፣ የማይፃፉትን እንደ-ልቡ ሲጽፍ የኖረ ደራሲ እንደሆነ እሙን ነው፡፡ ይሁንና የሥራዎቹ  ሙሉ ይዘትና ጭብጥ …. ጊዜ፣ ዘመን፣ የወጣትነት ትኩሳት፣ ፍቅርና ነፃነት የሚቀነቀንባቸው፣ አብዮት እና ለውጥ የሚደመጥባቸው …በሌላም በብዙ መልኩ የሚታዩና የሚተረጎሙ ናቸው እንጂ፤ በወሲብ ደረጃ ብቻ የሚፈረጁ የውቤ በረሃና የፈረንሳይ የወሲብ ገድል ብቻ አይደሉም፡፡ ሥራዎቹን ለመተንተንም የሞከሩ ደራሲያንም የማያስረግጡልን ይህንኑ እውነት ነው፡፡
ፀሐፊው ከ“ሀላል” ቃላት ታቅቦ በ“ሃራም” ቋንቋ ሙሉ ለሙሉ ከመጠበብ በላቀ የእውቁን ደራሲ ስም ማጠልሸትም ጭምር ድርብ ስህተት መስራቱን ለማጤን ተጋርዶበታል፡፡ ለዚህም ነው በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ በኢትዮጵያ ቋንቋዎችና ሥነ-ጽሁፍ ክፍል መምህር የሆኑት ደረጀ ገብሬ “ተግባራዊ የጽሕፈት መማሪያ” በተሰኘ መጽሐፋቸው ውስጥ በፀያፍ ቃላት ስለሚፃፉ ታሪኮች እንዲህ በማለት የሚነቅፉት… “በሕብረተሰቡ ልማድ ውስጥ በግልጽ፡- በአደባባይ የሚነገሩ እልፍ-አእላፍ ቃላት የመኖራቸውን ያህል ፍፁም ክልክል የሆኑና የማይጠሩ፡- የማይፃፉ “ነውር” (ሀራም) ቃላት አሉ፡፡ በጽሁፍ ውስጥ እነዚህን ቃላት ላለመጠቀም መሞከር የተገባ ነው፡፡ አንዳንድ የሰውነት ክፍሎች ፡- የአካላዊ ንኪኪዎች፡- የማህበራዊ ግንኙነቶች፡- የእንስሳ ስሞች በቀጥታ የማይጠሩ በመሆናቸው እዚህም በምሳሌነት ለማቅረብ ባሕል አግዷል፡፡; (ገጽ 16)
የየኔታ ደረጀ እውነታን ተላልፎ የሰውነት ክፍሎችን በልቅ ስድቦች አጭቆ፣ ልቅነትን እያበረታታ፣ ብልግናን እየደገፈ፣ ከጨዋነት በተፃራሪ በመቆም ባህላችን ያገዳቸውን ነውሮች በተቃራኒው ባላንጣ በመሆን የወሲብ ገድሉን ይዞ ብቅ ያለው ፀሐፊ ተስፋአብ ተሾመ ይባላል፡፡ “ክራራዊ ህይወት” በሚል ርዕስ፡፡ በተሰበረ የፍሬም መስታወት ውስጥ ጀርባዋ ላይ የክራር ንቅሳት ያላት ሴት ምስል የፊት ሽፋኑ ላይ በጉልህ ይታያል፡፡ መጽሐፉ አዙሪታም የወሲብ ንውዘቷን የምትተርከው ይህችው ናርዶስ የተባለች እንስት፣ እንደ-ክራር ነጋ-ጠባ የሚገረፍ የጭን መነባንቧን ነው፡፡ በገጽ 12 ላይ ኑሮዬ የክራር ነው ትላለች፡፡.. ሕይወቴ ክራራዊ ነው፡፡ የክራር ጅማት ሲመታ ድምጽን ይፈጥራል፡፡ በክራሩ መገረፍ የሚፈጠረው ድምጽ ቅኔ ይመስለኛል፡፡ የክራር ክር የሚያወጣው የለቅሶ ጩኸት፣ ለገራፊው ጆሮ ጣፋጭ ሙዚቃ የሆነውን ያህል የኔ ስቃይ ለሌሎች ጆሮ ጥዑም ሙዚቃ ሆኗል፡፡ ደግሞስ የተበጠሱ ክሮችን መልሶ ለመቋጠር ቢሞክር ትርጉም አልባ እንደሆነው ሁሉ የተበጠሱ የሕይወት ዜማ ክሮቼን መቀጠል ሣይቻለኝ ቀርቷል፡፡
ይህቺ ገፀ-ባሕሪ ከልጅነቷ ወሲባዊ ደስታና - እርካታ ቀምሳም - አጣጥማም የማታውቅ ተንከራታች ነች፡፡ በዚህም የበታችነት ስሜት ተጭኗት ለስነ-ልቦና መዛነፍ የተዳረገች። ማንነቷን ከወንዶች በምታገኘው ምላሽ የምትለካ ደካማ ሴት። ወንዶች እንደሚንቋት ስታስብ ህመም የሚወርሳት እቺ እንስት፤ የማነስ ስሜቷ የፈጠረባትን ርሀብ ወንድን በመደራረብ ታስታግሳለች፡፡ በወንድ ማደን መማሰኗ ውስጥ ግዳዮቿ የስጋ ዘመዶቿም ጭምር ናቸው፡፡ ከአክስቷ ልጅ ጀምሮ ሁሉን በማዳረስ፣ ከወላጅ አባቷም ጋር ለመፈጣጠምና ለመወስለት የማትመለስ አለሌ ሆና ተስላለች፡፡ ከዚህ በላይ መጽሃፉን ለመዳሰስ መግፋት ነውርና ጥፋታቸውን ማስተጋባትና እውቅናም መስጠት ይሆናል፡፡
ወሲብ የፍጡራን ሁሉ ተፈጥሯዊ ፀጋ ነው፡፡ ሰውን ከእንስሳ የሚለየው ወሲብ አይደለም፡፡ ነገር ግን ይህን ተፈጥሮ እንዴት መግዛትና ማስተዳደር እንዳለበት ማወቁ ነው የተለየ ችሎታው፡፡ ዛሬ-ዛሬ በስልጣኔ ስም ከእንስሳ ብሰን ማህበራዊ ዝቅጠት ውስጥ ወድቀናል፡፡ ወጣቶች ራሳችንን ከወሲብ ገርተን በማስገር በፍላጐት የተሞላውን ዓለም ለመገዳደርና እውቀትን የምንሻ የተሟላ ሰብዕና ያለን ትውልድ መሆን እንሻለን፡፡  ስለዚህ ስለ ግብረገብ፣ ራስን ስለ መግዛት፣ ከጭፍን ስሜት ይልቅ በሕሊና ስለ መመራት እሚያውሱ መጻሕፍት ያስፈልጉናል፡፡ እንዲህ ያሉ የበሸቀጡ … በታተሙበት ማግስት ገበያ  ላይ እንደ ቆሎ የሚሸጡ፣ ትውልድ አምካኝ መጽሐፎች እንዳይወጡ እሚይዝልን - እሚያግድልን አለሁ የሚለን አካል ያስፈልገናል፡፡
እዚያ ጋ አስተሳሰባችሁ ከጭን በታች የሆነባችሁ ታላላቆቻችን፣ ሲንግል የምትራጩ፣  የከረንቡላ ድንጋይ የምታጋጩ፣ በእድሜ ማምሻችሁ  የወሲብ ስካራችሁን  አትንገሩን፡፡ እኔ ከሞትኩ በሚል አጓጉል ገመና እየሰነዳችሁ ትውልዱን አትግደሉ፡፡
አዎ እኛ ግን ከሥነ-ምግባር ባሻገር ስንመዘን እዚህ ደርሰናል፡፡ ከዚህም ልቀናል፣ ነውርን በአደባባይ ሰብከናል፡፡ ነባር እሴታችን፣ኢትዮጵያዊ ጨዋነታችን የሙዝየም ቅሪት ብቻ ሆኖ ቀርቷል፡፡ ሀገር ለነገም የምናሻግራት አደራ መሆኗ ተዘንግቷል፡፡ ግዴለሽነታችን ትውልድ ሲያመክን ማሰብ ያስፈራናል፡፡ የግብር ይውጣ ድርጊታችን ትርምስ መልሶ ትውልድን ሲሰለቅጥ ታሪክ መላልሶ አሳይቶናል። ፍርስራሹ ልጆቻችን የመሆናቸውን መራራ ሀቅ መቀበል ይመረናል፡፡ ዞሮ-ዞሮ ለልጆቻችን እናስረክባታለን የምንላትን ሀገር የምንገነባው ለነዚህ ጥያቄዎች የምንሰጠውን ምላሽ ተገን ያደረገ ነው፡፡ በአንድ-ወቅት በእውቀቱ ስዩም   የዝሙት ቤቶች ያለ-ገደብ  መስፋፋታቸውን፣ እንደ-ወረርሽኝ መዛመታቸውን ታዝቦ በመነካት ውስጥ ሆኖ ከ“አሜን ባሻገር” ውስጥ ያሰፈረውን እዚህ መልሶ መድገም ግድ ይላል፡፡ … “ልብ በሚያሞቅ መልኩ ኢትዮጵያ ለዘላለም  ትኑር እንላለን እንጂ ኢትዮጵያን ለዘላለም ሊያኖራት የሚያስችል መሠረት ግን ሀገሪቱ ላይ የለም፡፡”


Read 485 times