Sunday, 12 December 2021 00:00

የአንዲት ምሽት ቁዘማ

Written by  ያዕቆብ ብርሃኑ
Rate this item
(1 Vote)

       "ኢትዮጵያዊ ከሆንክ አስራ አምስት መጻሕፍት ጽፈህ፣ ተርጉመህ በመጨረሻ እንኳን ልትቀናጣ መጻሕፍትን ገዝተህ ለማንበብ ትቸገራለህ፡፡ እንደተረሳ አልባሌ እቃ ትጣላለህ፡፡ ኢትዮጵያዊ ከሆንክና ዕድል ከቀናህ የሚደምቀው ሕይወትህ ሳይሆን ቀብርህ ብቻ ነው፡፡--"
           
            ጥንቅቅ ብለው የተሰሩ ነፍሰኛ ልብወለዶችና አጫጭር ልቦለዶች ለንባብ ቀዳሚ ምርጫዎቼ ናቸው፡፡ ከዚያ ቀጥሎ ለንባቤ የማነፈንፈው ትርክት ቢኖር ግለ ታሪክ… በየትኛውም ሀገር፣ ስለ ማንኛውም ዓይነት ሰው ይጻፍ ግለ ታሪክ ከሆነ የማንበብ ጉጉቴ ከፍ ያለ ነው፡፡ ከአምስት ዓመታት በፊት እንዲሁ ግለ ታሪኮችን ፍለጋ ስክለፈለፍ አብዲ መሐመድ - የወሊሶው የሳህለሥላሴ ብርሃነ ማርያምን ግለ ታሪክ ‹‹ፍኖተ ሕይወት›› እንደ ዘበት አቀበለኝ፡፡ ቀድሞውኑም ቢሆን ይበልጡኑ በትርጉም ሥራዎቻቸው አክብሮቴ ላቅ ያለ ስለነበር ግለ ታሪካቸውን ለማንበብ ጊዜ አላጠፋሁም፡፡
አንብቤ ስጨርስ ግን ከሕይወታቸው ጋር ተገምዳ ዘመናቸውን ሁሉ ያጨመተቻቸው አንዲት ፍሬ ሰበዝ፣ ባለ ሁለት ፊደል መጠሪያ፣ ‹ፊሉ› ስለሚሏት እንስት ተብከነከንኩ፡፡ ገና የዩንቨርሲቲ ኮሌጅ ተማሪ ሳሉ በዚህች የናዝሬት እስኩል ተማሪ ፍቅር ተነደፉ፡፡ ለማግባት ሽማግሌ ቢልኩም ትምህርቷን ሳትጨርስ ወይ ፍንክች ተባሉ። እያመነቱ ወደ ፈንሳይ ሀገር ለትምህርት አቀኑ፡፡ ፈረንሳይ ሀገር እያሉ የደረሳቸው ደብዳቤ ግን መርዶ ነጋሪ ሆነ፡፡ ልጅቷ አግብታለች፡፡ ከዚያ በኋላ የሆነው ሁሉማ ምኑ ይገለጻል፡፡ በባዕድ ሀገር ራሳቸውን ለማጥፋት ዳድቷቸው እንደነበርም ይነግሩናል፡፡ እኒህ ሰው እነሆ ሰማኒያ ሰባተኛ ዓመታቸውን ጀምረውታል። ግን ዘመናቸውን ሁሉ በመጻሕፍት እንደተከበቡ ነው፡፡ ማንበብ፣ መተርጎም፣ መጻፍ የመኖር ምክንያታቸው ይመስላል፡፡ ልጅም ሆነ ትዳር ኖሯቸው አያውቅም፡፡ በኢትዮጵያ ምድር በእንግሊዘኛ ቋንቋ ተጽፎ የታተመ የመጀመሪያው ልብወለድ የእርሳቸው ይመስለኛል፡፡
ከሁለት ዓመታት በፊት ቤታቸው ሄጄ ቃለ መጠይቅ ባደረግሁላቸው ጊዜ እንዲህ አሉኝ፡-
‹‹ከእንግሊዝ ኤምባሲ ተርጓሚነት ስራዬ በጡረታ ከወጣሁ እነሆ 27 ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡… ለእነዚህ ሁሉ ዓመታት ምንም የገቢ ምንጭም ሆነ ጡረታ የለኝም። ስራዬ ማንበብና መጻፍ ብቻ ነው። ቀደም ባለው ጊዜ አስር ብር ይዤ ብወጣ የምፈልጋቸውን ሁሉ መጻሕፍት ገዝቼ መግባት እችል ነበር፡፡ አሁን የመጻሕፍት አማካይ ዋጋ 200 ብር ሆኗል፡፡ ለእኔ የሚቻል አይደለም፡፡ ቢሆንም ወዳጆቼ መጻሕፍትን ያመጡልኛል፡፡ አሁን ሳምንቱን ሙሉ ከቤት እንኳን ሳልወጣ (ምንም ጠያቂ ሳይኖረኝ)  የማሳልፍበት ጊዜ ብዙ ነው… ››
ለሁለት ሰዓት ያህል የነበረንን ቆይታ ቋጭቼ መቅረጸ ድምጼን ይዤ ስወጣ እየመሸ ነበር፡፡ ያው እንደተለመደው…፣ ወደ እርሳቸው ቤት ስሄድ ያረጠበኝ እንዳልተገራ ፈረስ የሚደናበር ዝናብ የፈጠረብኝ ቅዝቃዜ፣ ጠልጣላ ነፍሴን በእንቅጥቅጥ እያርገፈገፋት ይገኛል፡፡ ጥሎብኝ ለዝናብና ለችግር ግንባር እንጂ ጀርባ መስጠት(ሽሽት) አልወድም፡፡
እነሆ እየመሸ ይገኛል፡፡ እድሜም እንደ ጀምበር…
የሆነ በቃላት አውጥቼ እንዲህ ነው ልለው ያልቻልኩት ስሜት ነፍሴን አስቆዝሟታል፡፡ በሕይወት ሀዲድ ላይ እኔ እና ሣህለሥላሴ በቅርብ ርቀት ተላልፈናል፡፡ ፊትና ኋላ ሆነን፡፡ ሆኖም መንገዳችን ብቻ ሳይሆን መዳረሻችንም ተመሳሳይ ይመስለኛል፡፡ መለየት፣ መሰናበት፣ ችላ መባል፣ ባዶነት፣ ከንቱነት፣ እንቶፈንቶ… በበኩሌ ልዩነቱ የሕይወት ዳናዎቹን በንቃት የመታዘብና ያለመታዘብ እንጂ የማንም ሰው ሕይወት ከዚህ የተለየ አይመስለኝም፡፡
ቢሆንም ሣህለሥላሴ ከአብዛኞቻችን የሚሻሉባቸው፣ ደብዛዛ የሕይወት መስመሮቻቸውን አድምቀው ያቀለሙባቸው በርካታ ጥበባዊ አሻራዎች አሏቸው፡፡ በስነጽሁፍ የኖቤል ሽልማት አሸናፊው J.M. Coetzee እንዲህ ይላል፤ ‹‹In a larger sense all writing is autobiography, everything that you write including criticism and fiction, writes you as  you write it.››
Samuel Butler በበኩሉ፤ ‹‹Every man’s work- whether it be literature or music or architecture or anything else- is always a portrait of himself.›› ብሏል፡፡ ሣህለ ሥላሴ በትርጉም ስራቸው ‹‹እምቢ ባዮች›› ያነበብኩት እንግዳ ገጸባህሪ፣  ‹‹ባልተርቢ›› ግልባጭ ናቸው ለማለት ባልደፍርም፣ ተመልካች የሌላቸው ክንፎቻቸውን ያሽሞነሞኑት ከአስራ ሦስቱም ስራዎቻቸው ባውጣጡዋቸው ላባዎቻቸው ይመስለኛል፡፡
ይሄን ጽሑፍ ከጻፍኩ ከሁለት ዓመታት በኋላ ዛሬ ረቡዕ ህዳር 29 ቀን 2014 ዓ.ም በድጋሚ ለጉብኝት ቤታቸው ተገኘሁ፡፡ (ጽሁፉ ከሁለት ዓመታት በፊት ተጽፎ ለዚህ ሣምንት ለአንባቢያን እንዲመች ተሻሽሎ የቀረበ መሆኑን አንባቢ እንዲረዳልኝ እፈልጋለሁ፡፡) እንዲያነቡ ሰጥቻቸው ስለነበሩት የአሰፋ ጫቦ ‹የትዝታ መንገድ› እና የእኔን ከዓመታት በፊት የወጣች ደፋር ሙከራ ‹ሠለስቱ ጣዖታት› አንስተው ሐሳባቸውን አካፈሉኝ፡፡ እንደተለመደው ቀኝ ቀኙን መናገርን መርጠዋል፡፡ ላመኑበት ነገር፣ ላልወደዱት መጽሐፍ ስሜታቸውን ለመናገር ማመንታት እንደሌለባቸው አውቃለሁ፡፡ ታዛ መጽሔት ላይ በተስተናገደ ከእኔ ጋር የነበራቸው ቃለ ምልልስ ላይ ይሄን አጫወቱኝ፡፡ በአብዮቱ ዘመን ያኔ የሁለት መጻሕፍት ዝነኛ ደራሲ የነበረውን በዓሉ ግርማን በአንድ ድግስ ላይ እንደ ድንገት አገኙት፡፡ በዓሉ ጋሽ ሣህለሥላሴን እንዳያቸው ነጠል ብሎ ሄዶ ሰላም ካላቸው በኋላ፣ ስለ መጻሕፍቱ አስተያየት ጠየቃቸው። ‹‹እኔ የወደድኩት ‹ከአድማስ ባሻገርን ነው፡፡ በየህሊና ደወል ለጋዜጠኝነትህ አድልተሃል›› መልሳቸው ነበር፡፡ ያው ደርዝ የለውም ዘገባ አስመሰልከው መሆኑ ነው፡፡ ምናልባት ይሄን መሰል ሀቀኛ አስተያየቶች ገፋፍተውት ይሆናል በዓሉ ‹የሕሊና ደወልን› ድጋሚ ወዝቶ፣ ‹ሀዲስ›ን እንዲያበስል መነሻ የሆነው፡፡
ብዙ ነገር አወጉኝ፡፡ የመጀመሪያው የጉራጊኛ ቋንቋ ልብወለዳቸው ‹የሽንጋ ቃያ›  ወደ ‹የሽንጋ መንደርነት› ተተርጉሞ በጋሽ ዘነበ ወላ እና ሌሎች ወዳጆቻው ትብብር ሙሉ ወጪው ተሸፍኖ ታትሞ ተመርቆላቸዋል፡፡ በአንድ አሳታሚ ፍላጎት መነሻነት ‹መከረኞቹ› እና ‹እምዩ› የትርጉም ሥራዎቻቸው ድጋሚ የሕትመት ብርሃን ደርሷቸዋል፡፡ የገንዘብ ጥያቄያቸው ቢያንስ ለጊዜው በሚገባ የተመለሰላቸው መሰለኝ። በቅርቡ በዋሊያ የመጻሕፍት መደብር (አራት ኪሎ ኢክላስ ሕንጻ) በተዘጋጀላቸው ከአድናቂዎቻቸው ጋር የመገናኘት፣ የመተዋወቅ መድረክ እጅጉን እንደተደሰቱ አወጉኝ፡፡ ለአበርክቶዎቻቸው የክብር ዶክትሬት ዲግሪ የሰጣቸው ወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ ለሌላ ሥነ-ጽሑፋዊ መድረክ በድጋሚ ጋብዟቸው ሊሄዱ መሆኑን ነገሩኝ፡፡ እነዚህ ሁሉ የሆኑት ባለፉት ሁለት ዓመታት ነው፡፡ ይሄም ሁሉ ሆኖ እኒህ ሰው አሁንም ለዘመኑ እያሉ የሌሉ ያህል ሆነዋል፡፡
አሰፋ ጫቦ ‹የትዝታ ፈለግ› መጽሐፉ ላይ  የተጠቀመበት የአሜሪካዊው ጀኔራል ዳግላስ ማካርቱር ‹‹Old Soldiers never die, they simply fade away...›› ይሉት አባባል የሚሰራው ለጦረኛ ብቻ ነው ያለው ማን ነው? የብዕረኛንም ሕይወት አሳምሮ ያፈክራል፡፡ እኒህ ሰው ወይ ዘመኑ ችላ ብሏቸዋል ወይ እሳቸው ዘመኑን ንቀውታል። የስብሃት ገብረ እግዚአብሔር፣ የዳኛቸው ወርቁ፣ የሰለሞን ደሬሳ፣ የአማረ ማሞ... የልብ ወዳጅ የነበሩት ሰው፤ አሁን ለአስራ አምስት ቀናት ከቤት ላይወጡ ይችላሉ፡፡
በእርግጥ ዛሬም በሰማኒያ ስድስት ዓመታቸው በዕቅድ የሚመራ ሕይወት አላቸው፡፡ ያነባሉ፤ ይተረጉማሉ፤ ይጽፋሉ፤ ሬዲዮ ያዳምጣሉ፤ ምናልባት ጎብኚ ከመጣ ጥቂት አፍታ ወስደው ያስተናግዳሉ፡፡ ይኼው ነው፡፡ ውልፊት የለችም፡፡ አሁንም ለመስራት አልሰነፉም፡፡ ተጠናቅቀው በአሳታሚ እጦት እጃቸው ላይ የቀሩ የትርጉምና የፈጠራ ሥራዎች እንዳሏቸው አውቃለሁ፡፡ የዋሊያው መድረክ ላይም ተናግረውታል፡፡        
ወታደር፣ መምህርና ደራሲን የናቀች ያቺ ሀገር ቆማ መራመድ ትችላለችን? ያለፍንበት የሠላሳ ዓመት ሂደት ሀገር የቆመችባቸውን እነዚህን ሦስት ምሶሶዎች ከመሰረታቸው ያናጋ ነበር፡፡ ዛሬም ከእልቂት ላልወጣ የዝንጀሮ ፖለቲካችን ክስረት ከንባብ ውጪ መፍትሄ ያለም አይመስለኝም፡፡ በቅጡ ያልተሰራ አዕምሮ የተሰራ ሀገር ማፍረሱን እኮ በዓይናችን አየነው፡፡
 ‹‹Writing is dogs life. But, the only life worth living.›› ያለው ማን ነበረ? አዎ ፈረንሳዊው Gustave Flaubert…  በየትም ሀገር ባልዛካዊያን አሉ፡፡ በየትም ሀገር በኪነት ላይ ማግጠው የሀብት ማማው ሰምሮላቸው በጠራራ ጸሐይ ስክር ብለው አደባባይ ላይ የሚሸኑ ጥበብ ጠራችኝ ባይ ሔሚንግዌያን አሉ፡፡ በእኛም ሀገር ጭምር… ባልዛክን አወቃችሁት? ይሄ እንኳን ከደራሲያን በድህነት ተወዳዳሪ ያልነበረው፣ ይለብሰው አጥቶ እራፊ የወረቀት ሸሚዝ ይደርብ የነበረው? አዎ ... እሱ ነው፡፡
ይህ ስለ ጋሽ ሣህለሥላሴ ብቻ አይደለም፡፡ ስለ ሁሉም ኢትዮጵያዊ ደራሲያን ምናልባት ስለ እራሴው ቀጣይ ዕጣ ጭምር የተሰነዘረ ቁጭት እንጂ... የሆነ ቀን ከአንድ አዳም ረታን ከሚቀራረብ አንድ ወዳጄ ጋር ስናወራ ‹‹አዳም ረታ ስለምን ጠቅልሎ መጥቶ ጽሑፉ ላይ ብቻ አያተኩርም?›› አልኩት፡፡ የሰጠኝ መልስ የሚያስደነግጥ ሆነ፡፡ ‹‹ጠይቄው ነበር። ሞርጌጁን አልችለውም ብሎኛል›› ሞርጌጅ ቤት ለመግዛት ከባንክ የሚሰጥና በረጅም ጊዜ የሚከፈል ብድር ነው፡፡ አድናቂዎቹ ምንም የተለየ ሐሳብ እንዳናነሳ መተንፈሻ አሳጥተው የሚያዋክቡን፣ አንዳንድ ‹ጂኒየስ› የዩንቨርሲቲ መምህራን ከእርሱ ሥራዎች ውጭ ምን ሲደረግ ብለው ተማሪዎቻቸውን በግዳጅ ለጥናት የሚጠመዝዙለት የሀገሪቱ ፈርጥ ደራሲ አዳም ረታ፣ ከድርሰት የሚያገኘው ገቢ ይሄን ሸክሙን እንኳን የሚያቀልለት አልሆነም፡፡ ዓለማየሁ ገላጋይም የሆነ ወቅት ከአዳር ሥራ ሲወጣ የተነሳውን ፎቶ ዓይቶ ተገርሞ እንደነገረን፣ አዳም በዚህ ሁሉ ውጥረት ውስጥ ሆኖ ነው ጥበቡን የሚያቀልመው፡፡
ሌላ ቀን ዝም ብዬ የብራዚሉን ዝነኛ ደራሲ ፓውሎ ኮኤልሆ ሕይወት የተመለከተ አንዳንድ ነገር በይነ መረብ ላይ ሳስስ ቆይቼ ድንገት ያካበተውን የሀብት መጠን መልከት ሳደርግ፣ በድንጋጤ ጭንቅላቴን መያዝ ነው ያማረኝ፡፡ ይበልጥ እንዲያስደንቅህ ለምን በብር መንዝሬ አልነግርህም፡፡ ብታምንም ባታምንም 22.5 ቢሊዮን ብር አለው። እናስ የእኛ መረገም ምንድን ነው? ጉዳዩ የችሎታ ማነስ ነው እንዳንል ከሞላ ጎደል ዓለም ያደነቃቸውን ከያኒያን የሚስተካከሉ የኪነት ሰዎች ነበሩን፡፡ አሁንም ያሉን ይመስለኛል፡፡ ሎሬት ጸጋዬ ገብረመድኅን ‹አዕምሮ ሚዲያ› ከተሰኘ የድረ ገጽ መድረክ ጋር አድርጎት ባየሁት ቃለምልልስ ላይ ፤ ‹‹አውላቸው [ደጄኔ] በዓለም ደረጃ የመድረክ ንጉሥ ነው ስል ስለሆነ ነው፡፡ ‹ሶዶሚን ሶልቪየ›[?] ይህቺን ታህል አይበልጠውም። ግን ኢትዮጵያ ውስጥ ነው የኖረው... ማን ይወቅለት? እንጀራ እንደራበው ሞተ።›› ብሏል፡፡ ጋሽ ጥላሁን ገሰሰስ ቢሆን ወዶ ነውን ‹‹ሀብቴ የኢትዮጵያ ሕዝብ [ብቻ] ነው፡፡›› እያለ ያለፈው?
እደግመዋለሁ፤ ይህ ስለ ማንም አይደለም። ስለ ሁላችንም ነው። ኢትዮጵያዊ ከሆንክ አስራ አምስት መጻሕፍት ጽፈህ፣ ተርጉመህ በመጨረሻ እንኳን ልትቀናጣ መጻሕፍትን ገዝተህ ለማንበብ ትቸገራለህ። እንደተረሳ አልባሌ እቃ ትጣላለህ። ኢትዮጵያዊ ከሆንክና ዕድል ከቀናህ የሚደምቀው ሕይወትህ ሳይሆን ቀብርህ ብቻ ነው፡፡
…ይሄን ይሄን ሳስብ ከሀገር ሳይሆን ከጊዜ መሰደድ ያምረኛል፡፡ አዎ ወደ ነገ መሰደድ ሳይሻል አይቀርም መሰለኝ፡፡  
እነሆ እየመሸ ይገኛል፡፡ ለዓይንም መያዝ ጀምሯል፡፡ እድሜም እንደ ጀምበር…

Read 1474 times