Saturday, 11 December 2021 14:15

ጠየቀኝ።ቤተመፃህፍቱ?? (ወግ)

Written by  ናሆም
Rate this item
(0 votes)

  ከቀናት በፊት ነው። በአንድ ጉዳይ ላይ ማንበብ አስፈልጎኝ እቃዎቼን ሸካክፌ ከሰፈሬ በቅርብ እርቀት ላይ ወደሚገኝ ቤተ መፃህፍት  አቀናሁ። በራሴ ሀሳቦች እየናወዝኩ ወደ  መግቢያው  በር ስጠጋ፣ “ቁም!” የሚል ድምፅ ተሰማኝ። ከየት አቅጣጫ ማን፣ለምን፣ለማን እንዳለው በቶሎ  ለመረዳት አልተቻለኝም ነበር።
ብቻ ደንዝዤ በቆምኩበት አዲሱን የአዲስ አበባ ፖሊስ  መለዮ ያጠለቀ  ቀጠን ረዘም ያለ ወጣት ፖሊስ፣ ጠመንጃውን እንደወደረ  በድንዛዜ ወደቆምኩበት በር ሲመጣ ተመለከትኩት። ድምፁ ከእርሱ መሆን አለበት አልኩ ለራሴ። ግን ለምን? ኧረ ቆይ ይሄ ቤተ መፃህፍት ደግሞ ከመች ወዲህ ነው በፖሊስ መጠበቅ የጀመረው? ለራሴው ጥያቄዎች መልስ መስጫ በቂ ጊዜ አልነበረኝም። መሳሪያውን ከደረቱ አውርዶ ለሁለት እጆቹ እያመቻቸ “ወዴት ነው?” ሲል አፈጠጠብኝ፡፡
"ቤተ መፃህፍት ልጠቀም ፈልጌ…" ንግግሬን  አንጠልጥዬ ተውኩት። ምን እየተፈጠረ ነው? ይህ ሰው ከኔ ምንድን ነው የሚፈልገው? ቦታ ተሳስቻለሁ እንዴ? እልፍ ጥያቄ...
“መታወቂያ ይዘሀል?”
ከእንቅልፍ እንደ መባነን እያደረገኝ ከሱሪ ኪሴ ውስጥ መታወቂያዬን  አውጥቼ ሰጠሁ።
አንዴ እኔን አንዴ መታወቂያዬን ሲመለከት ከቆየ በኋላ “እዚህ ሰፈር ነው የምትኖረው?” ጠብመንጃውን መልሶ በደረቱ እያነገተ ጠየቀኝ።
በአዎንታ እራሴን ነቀነቅሁ።
“እና ላይብረሪው ጊዜያዊ ማቆያ በመሆን እያገለገለ እንደሆነ አታውቅም?” ፖሊሱ በጥርጣሬ ነው የሚመለከተኝ፤ ምን አስቦ ነው? አይነት ነገር። ሲሰርቅ እንደተያዘ ህፃን ለምን ድንብርብሬ እንደወጣ እንጃ፡፡ ብቻ ነገር አለሙ ተሳክሮብኝ ነበር። ግራ መጋባቴ ግራ አጋብቶኝ እኔም እራሴን መጠርጠር ልጀምር ስል ፖሊሱ በጩኸት ጥያቄውን ደገመው።
ቤተ መፃህፍቱ ጊዜያዊ ማቆያ መደረጉን በፍፁም እንደማላቅ፣ አሁን ትዝ የማይሉኝ ምክንያቶች ደርድሬ አስረዳሁት። መንተባተቤ ይሁን ምክንያቴ ያሳምነው እንጃ ብቻ፣ በፍጥነት አካባቢውን  ለቅቄ እንድሄድ አዘዘኝ።
እነ ማን ናቸው የታሰሩበት? ለምን? ደግሞስ ቤተ መፃህፍት ከመቼ ጀምሮ ነው ማሰሪያ የሆነው? ቦታ ጠፍቶ ነው?  እስር ቤቶች ሞልተው? መልስ የሌላቸው ጥያቄዎችን እራሴኑ እየጠየቅሁ የሰፈሬን ዳገት ተያያዝኩት፡፡
የወጣቱ ፖሊስ ጥያቄ ደጋግሞ በጆሮዬ አቃጨለ፤ “ጊዜያዊ ማቆያ በመሆን እያገለገለ እንደሆነ አታውቅም?” ሁሉም ሰው ሊያውቅ እንደሚችል ማሰብ፣ ያልሰማሁት ነገር ይኖር ይሆን እንዴ ብዬ እንዳስብ አደረገኝ። ምናልባት የየወረዳው ቤተ መፃህፍት ጊዜያዊ ማቆያ ሆነዋል የሚል አዋጅ ታውጆ ሳልሰማ ቀርቼ ይሆን? እዚህ ሀሳብ ላይ ብዙ መቆየት አልፈለኩም።
ይልቅስ ከቤተ መፃህፍቱ የተሻሉ ማቆያዎችን ሰፈሬ ላይ ማሰስ ጀመርኩ... የእድር ቤታችን ሰፊ ግቢ ውልብ አለብኝ። ለጊዜያዊ ማቆያነት ምቹ መሆን አለመሆኑን በምናቤ ወደ ግቢው ዘልቄ መሰለል ጀመርኩ። እንዴት ያለ ምቹ ቦታ ነው ጎበዝ? ችግሩ የእድሩ ሊቀ መንበር  ጋሽ አሰፋ “የእድሩ አባል ያልሆነ ታሳሪን አልቀበልም” ማለታቸው የማይቀር መሆኑ ነው።
ከእርሳቸው ጋር ከነበረኝ የቀድሞ ጭውውት ለመረዳት እንደቻልኩት፣ የቀበሌው መስተዳድር ለእድራችን ያለው ንቀት ያበግናቸዋል። አሁን ስለዚህ ጉዳይ ባማክራቸው “መስተዳድሩ ቢንቀን እንጂ የእኛ እድር ቤት አሁን ለዚህ አንሶ ነው?" እንደሚሉኝ ቅንጣት ጥርጣሬ የለኝም።
ሌሎች ቦታዎችን በምናብ ማሰሱን  ቀጠልኩ፡፡ የቀበሌው ሰፊ መሰብሰቢያ አዳራሽ ትዝ አለኝ። ለአመታት እዛ አዳራሽ ውስጥ ሰብስበው፤ተሰብስበው ያመጡት ለውጥ ባለመኖሩ አዳራሹ ጊዜያዊ ማቆያ ቢደረግ የሚከፋው እንደማይኖር አስባለሁ። የወጣት ማዕከል ብለው የገተሩት ባለ ሶስት ወለል ህንፃ ውል አለብኝ። ሌላው ሁሉ ይቅር ይህ ቦታ ለማቆያነት አንሶ ነው ቤተ መፃህፍቱን የመረጡት? ሞኝ ቢሆኑ እንጂ ታሳሪውም  ቢሆን ፎቅ ላይ መታሰሩን የሚጠላው አይመስለኝም።
ለነገሩ የፖሊሱ የአገላለፅ ችግር እንጂ ቤተ መፃህፍቱ ከማንበቢያነት ወደ ማሰሪያነት ሳይሆን የተቀየረው ስራውን በአዲስ መልክ ነው የጀመረው። ለአመታት ብቸኛ አንባቢው እኔ ነበርኩ፡፡ አሁን በአዲስ መልክ ስራ መጀመሩን ተከትሎ ግን በርካታ ታሳሪ አንባቢያን ይኖረዋል። ልዩነቱ ድሮ እኔ አነብበት ነበር፤ አሁን በርካታ ታሳሪዎች ያነቡበታል።
እነዛ ገላጭ አጥተው የከረሙ መጻሕፍት በአዲሶቹ  ታሳሪዎች ሲገለጡ ታየኝ። አሁን የኔ መብከንከን ለምን እኔ አላነብበትም ከሚል ስግብግብነት እንጂ ለቤተ መፅሐፍት ከመቆርቆር ነው? አያስገቡኝም እንጂ አንዴ ብገባ "በቸርነትህ ነገራትን ታቀናጃለህ" የሚል ጥቅስ ለጥፌ ነበር የምወጣው።
በዳገቱና ሃሳቦቼ ዝዬ ወደ ቤቴ ገባሁ።

Read 1264 times