Saturday, 11 December 2021 14:19

ከፌስቡክ ገጾች በጨረፍታ

Written by 
Rate this item
(0 votes)

 ይሄ ሰውዬ ምን ተዓምር ነው!?
                           ኢዮብ ምህረተአብ ዮሐንስ


             ‘’Men make history and not the other way around. In periods where there is no leadership, society stands still. Progress occurs when courageous, skillful leaders seize the opportunity to change things for the better.’’
[Harry S. Truman]
መሪን ማወደስ አይጥምም። ምላስ የሚቆረቁር ነገር አለው። በተለይም ‘በእርሳቸው’ ሃሳብ አፍላቂነት’’፣ ‘’በእርሳቸው ቆራጥ አመራር’’፣ ‘’በእርሳቸው ልዩ አነሳሽነት’’ የሚል ዋቴያም አክቲቪስት በሞላው የሳይበር አለም ላይ መሪህን ስታደንቀው - ከፎጋሪዎች እና ከአሙቂልኞች ተርታ እንዳትመደብ ትሰጋለህ።
(ግን)
ነገር ግን አሁንም ለጠቅላዩ Credit ልንሰጥ የተገባ ነው። ይሄንን ሰውዬ ልናደንቀው የተገባ ነው። ልንደግፈው፣ ከጎኑ ልንሆን፣ ልንገረምበት የተገባ ነው።
(ስጥ ፍርድህን ጌታዬ!)
ጃዋር አብሮት የለም። ለማ መገርሳ አብሮት የለም። አሳምነው ፅጌ አብሮት የለም። ሠዓረ መኮንን ከጎኑ የለም። ኦነግ እንደገባ ተሸበለለበት። አሜሪካን ከዳው። EU ቻፓ ቀጣው። UN በፈጣጣው ካደው። አባይ ግድብ በሱዳን አስወጋው። ያወደሰው የፈረንጅ ሚድያ ወረደበት። ጁንቲት አፈር ልሳ ተነሳችበት። ዓለም ፊቱን አዞረበት።
(እሱ)
እሱ ኢትዮጵያን፣ ኢትዮጵያውያንን፣ ኢትዮጵያዊነትን፣ የአገር አንድነትን፣ አርበኝነትን፣ የእናት አገር ፍቅርን ብሎ ገገመ። የሙጢኝ አለ። አኞ ሆነበት። . . . ብረት በለው!
¤
ጁንታዎቹ ተጠጉ፣ ቀረቡ፣ ደብረሲና ገቡ፤ ጠቅላዩ ይሸሻል ወይንስ እጅ ይሰጣል? ስንል አራት ኪሎን ትቶ ጦር ሜዳ ወረደ። እንደ ወንድ፣ ከወንድ ሜዳ ወረደ። Battle Field ሄዶ ጦሩን እየመራ ገጠማቸው።
(አቸነፈም)
ያቸነፈው ግን ውጊያውን ብቻ አይደለም። ያቸነፈው የጦር ሜዳ ገድልን ብቻ አይደለም። ያቸነፈው ደሴንና ኮምቦልቻን፣ ጋሸናንና ጭፍራን ብቻ አይደለም።
(አይደለም)
የኢትዮጵያውያንን አእምሮ፣ ልብ፣ ነፍስና ስጋ ማቸነፍ ችሏል። የዳያስፖራውን፣ የኤሊቱን፣ የፋራውን፣ ያራዳውን፣ የድሃውን፣ የባለ ሃብቱን፣ የከተሜውን፣ ያርሷደሩን፣ የአርቲስቱን፣ የእስላሙን፣ የክርስቲያኑን፣ ያርብቷ’ደሩን፣ የፌዴራሊስቱን፣ የአሃዳዊነቱን - የሠፊውን ሕዝብ እስትንፋስና ልብ አንድ ላይ አሰባስቦ ከሱ ጎን ማሰለፍ ችሏል። . . . እኛን አቸንፏል።
(ፍረዳ!)
ኢህአፓም፣ ሜኤሶንም፣ ደርግም፣ ሻእቢያም፣ ግንቦት ሰባትም፣ እኩሌታ ኦነግም፣ የንጉሣዊው ስርዓት ደጋፊዎችም Endorse ያደርጉታል። ሃይሌ ገብረስላሴ፣ ካሳዬ ጨመዳ፣ ቴዲ አፍሮ፣ ሌሊሳ ፈይሳ፣ አንዳርጋቸው ፅጌ - እኒህ ፈፅሞ የተለያየ Background ያላቸው VVIP ሰዎቹ ጠቅላዩን አምነውበት አብረውት ከጦር ሜዳ ወርደዋል።
¤
ለምን ታመነ?
ለምን ተወደደ?
ለምን ተፈቀረ?
ለምን ተሳካለት?
¤
አለቀለት ሲባል የሚነሳው፣ አይረባም ሲባል የሚረባው፣ ተቸነፈ ሲባል የሚያቸንፈው፣ አገር በታተነ ሲባል አገር አንድ የሚያደርገው፣ ሕዝቡ ጠላው ሲባል ሕዝቡ እጥፍ የሚወድደው - ከቶ ምንድር ነው ይሄ ሰውዬ?! ከየት ተማረው ይሄንን ተጋፋጭነት? ከየት አመጣው እንዲህ ያለ አይበገሬነት?
¤
አብይ አህመድና አሊ . . . ።
¤
‘’All of the great leaders have had one characteristic in common: it was the willingness to confront unequivocally the major anxiety of their people in their time. This, and not much else, is the essence of leadership.’’
[John Kenneth Galbraith]

__________________________________________

                          አንድ የታዘብኩትን ነገር ልናገር!

                           «አማን መዝሙር»
                                ( ዘውድአለም ታደሠ»)

           «አማን መዝሙር»
አሁን ባለው ግርግር ውስጥ ሾልከው የሚወጡ የትግራይ ተወላጆች ላይ ያነጣጠሩ የጥላቻ ንግግሮች ያስፈሩኛል። በብዙ ሐገራት ላይ እንዳየነው አሰቃቂ ተግባሮች ሁሉ የሚጀምሩት ከንግግር ነው። ሩዋንዳን ብንመለከት አንድ ሚሊየን ሰው ከፈጀው ጭፍጨፋ በፊት በሬዲዮና በጋዜጣው ሁሉ «እነዚህ ቱትሲዎች መጥፋት አለባቸው፣ እነዚህን በረሮዎችን እንጨፈልቃቸዋለን፣ ሁሉም ቱትሲ-- » ገለመሌ የሚሉ የጥላቻ ንግግሮች ከየአቅጣጫው ይሰሙ ነበር። በግዜው ያን የጥላቻ ንግግር የሚናገሩ ሰዎች ሐገር ወዳድ ይመስሉ ነበር። ጊዜው ሲያልፍ ግን የጄኖሳይድ አቀንቃኝ ተብለው ወህኒ ወርደዋል!
ለሐገር መቆም መልካም ሆኖ ሳለ ለህውሓት ያለን ጥላቻ ገደብ አልፎ የትግራይ ተወላጆችን በሙሉ ጠላት ወደ ማድረግ እንዳያድግ እፈራለሁ። አሁን አሁን በተለይ ሰለጠነ በምንለው በከተማው አካባቢ በተለይም «እነሱኮ አንድ አይነት ናቸው፣ ለምንድነው አስረን የምንቀልባቸው፣ ሁሉም ሲፋቅ ወያኔ ነው፣ የእባብ ልጅ እባብ ነው፣ እባብ ለመደ ተብሎ በኪስ አይያዝም፣ ሁሉም .....»
ማይ ብራዘር «ሁሉም» የምትለው ቃል የጥላቻ ንግግር ነች! የጭፍጨፋና የማግለል ሳይረን ነች። የፈለገው ያህል የህውሓት ግፍ ቢያንገፈግፍህም፣ ቁጭትና እልህህ አንድን ዘር መርጠህ እንድትፈርጅ እንዳያደርግህ ተጠንቀቅ። መንግስታዊ ተቋማትም ነገ የሚባል ቀን አለና «የትግሬ ወራሪ» ምናምን ከሚሉ ንግግሮች መቆጠብ አለባቸው።
ጠባችን ስልጣንና ጥቅም ከቀረበት አሸባሪው ህውሓት ጋር ነው። ይህ ሃይል የትግራይ ወጣቶችን በውድም ሆነ በግድ ከጎኑ አሰልፏል። ልክ ኦነግ የተወሰኑ የኦሮሞ ወጣቶችን ከጎኑ እንዳሰለፈ ማለት ነው። በዚህ ሃይል የተነሳ በመላ ኢትዮጵያ የሚኖሩ የትግራይ ተወላጆች፣ አረጋውያን፣ እናቶች፣ የሚሸማቀቁበትም ሆነ ስጋት ላይ የሚወድቁበት ምንም ምክንያት የለም። ስለዚህ ንግግራችንና ቅስቀሳችን ዘር ላይ ያነጣጠረ አለመሆኑን እርግጠኛ እንሁን!

_______________________________________

                     ሀገር ምሰሶዋ ተስፋ ነው !
                          (ዮሴፍ ተገንያ)

      ከ3 አመት በፊት ግድም “The last ship” የሚል ተከታታይ ፊልም አይቼ ነበር። በ5 ምዕራፎች የተከፋፈለ፣ ካልተሳሳትኩ ከሞላ ጎደል 5ቱም ምዕራፎች የተለያየ ይዘት ያላቸው ታሪኮች የተከወኑበት ፊልም ነው፤ ዋና ገፀባህሪያቱ ሳይቀየሩ።
ከምዕራፎቹ አንደኛው ምዕራፍ ጉስታ ቮ በሚባል “ደቡብ አሜሪካን አንድ አድርጌ እንደ ሰሜን አሜሪካ ጠንካራ የተባበረ አገር አደርጋለሁ!” ብሎ በተነሳ ወታደራዊ የኮሎምቢያ መንግስት መሪ እና ያው በሰሜነኛዋ አሜሪካ (US) መካከል ስለሚደረግ የኃይል ፍትጊያ ነበር የሚተርከው። ፊልሙ ጓድ ጉስታ ቮ አሜሪካ ባልጠበቀችውና ባላሰበችው ሰዓት በአየር ሲደበድባት፤ ከዚያም አንድ የጦር መርከብ ካፒቴን በወሰደው የመልሶ ማጥቃት ዘመቻ የጉስታ ቮ መንግስት ሲሽመደመድ ያሳየናል፤ ጉስታ ቮ በዚህ ጊዜ ለምክትሉ እንዲህ ሲለው ይሰማል፦
“ We can’t let [the Americans] have hope. And we can’t let our people have doubt.”
------
ሀገር ምሶሶዋ ተስፋዋ ነው። ሀገር ተስፋ ከሌላት እጀታ እንደሌለው ክራንች ናት፤ የክራንች እጅታ ተስፋ ነው። እግር የመሆን ተስፋ። እግርን የመተካት ተስፋ።
በምስሉ ላይ የምትታየው እናት ለልጇ እንደ ክራቹ እጀታ ናት። ልጇ ነገ እግር እንዲኖረውና ነገ እግር ሲኖረው ወደፈለገበት እንዲራመድ ዛሬን እጀታው ሆና ለመሰዋት የተዘጋጀች ጊዜያዊ እግሩ። የሷ እግር ግን ልጇ ነው! ተስፋዋ!
ድምጻዊ ኢዮብ መኮንን “ነገን ላየው እጓጓለሁ” ብሎ የዘፈነው ለምን ይመስልሃል? ማንም ዛሬን እየኖረ ያለ ሰው ተስፋው ነገ ስለሆነ ነው።
እኚህ እናት ልጅ ነበሩ፣ ልጅ እያሉ ነገ’አቸው ወጣት መሆን ነበረ፤ ወጣት ሲሆኑ ደግሞ ነገ’አቸው ጎልማሳነት ሆነ። ከዚያም እናት፣ ከዚያም አያት፣ ከዚያም ቅድመ አያት ከዚያም ከዚያም እያለ “ነገ’ነት” ደረሰባቸው። ነገ ደግሞ ሀገር ነው። ተስፋ።
እስራኤሎች መዝሙራቸውን “ሀቲክቫ (ተስፋ)” ብለው ነው የሚጠሩት። መዝሙሩን የጻፈው ሰው የዛሬይቷን እስራኤል እንደ ሀገር ቆማ አላያትም። በልቡ የቀረፀውን ተስፋ ነበር የፃፈው። ዛሬ ግን ተስፋው እውን ሆኖ፣ “ተስፋው” የተስፋ ሀገሩ መዝሙር ሆኖ ቀጥሏል!
መዝሙሩ ላይ እንዲህ የሚል ሀረግ አለ፦
“ለ2 ሺ አመት ያልጠፋው ተስፋ…”
ህእ!
_______________________________________________


                          “ኢትዮጵያ ደግሞ... አጉል ትመፃደቃለች!”
                                    (ህይወት እምሻው)


                ይሄ ለስራ የመጣሁበት አፍሪካዊ ሃገር የእንግሊዝ ቅኝ ግዛት ነበር፡፡ መቼ እለት ነው… የዚህ አገር ዜጋ ከሆኑ የስራ ባልደረቦቼ ጋር ሻይ-ቡና ስንል የ‹‹በቃ›› ወይም # #No More; ንቅናቄ በወሬ ወሬ ተነሳና ብዙ ነገር ሲያስመዝዘን አመሸ፡፡
በዚያ ሰሞን የበቃ ንቅናቄ ጀማሪዎቹ ኢትዮጵያዊያንና ኤርትራዊያን ፣ “እንደውም ለምን እኛ ብቻ…? ድፍን አፍሪካ አዲሱን የእጅ አዙር ቅኝ ግዛት አሻፈረኝ ማለት አለበት “ ብለው ጉዳዩን ከኢትዮጵያ ወደ አፍሪካ ከፍ ሲያደርጉት እዚሁ ነበርኩ፡፡
በዚህ ጥሪ ግን ከዚህ አገር ጓደኞቼ መሃከል ደስ ያላላቸው ነበሩ፡፡ ያበጠው ይፈንዳ ብለው በግልፅ፣ ‹‹ኤጭ! ኢትዮጵያ ደግሞ አጉል ትመጻደቃለች….›› ያሉኝም ነበሩ፡፡
አንዳቸው ለአንዳቸው ተደርበው፣
‹‹እርግጥ ነው፡፡ ኢትዮጵያ የአፍሪካ የነጻነት ቀንዲል ናት፡፡ ኩዋሜ ንክሩማ ሳይቀር ‹ትነሳለች› ብሎ በቅኔ የተነበየላት…የምንኮራባት ሃገር…›› ብለው ጀመሩ፡፡
ቅቤ መቀባቱ ግን አልዘለቀም፡፡
ወዲያው፣
‹‹ግን እውነቱን አፍርጪው ካልሽን፤ ኢትዮጵያ አሁን ባለችበት ሁኔታ እንኳን አፍሪካን ለአዲስ ነፃነት የማነቃነቅ ጉልበት፣ የራሷን አንገትም መሸከም ያቃታት ሃገር ናት፡፡ ጭራሽ እኛን እንዲህ ሁኑ፣ እንዲህ አድርጉ የማለት የሞራል ልእልና የላትም…በእርግጥ ያኔ እናንተ ሳትገዙ እኛ ተገዝተን ሊሆን ይችላል። ግን አሁን ነፃ ነን.. እናንተ ግን ዛሬ እርስ በርስ እየተባላችሁ ነፃ ነን ማለት ትችላላችሁ?; እያሉ በብዙ ቃላት፣ ለብዙ ደቂቃዎች አንጀቴን አቆሰሉት፡፡
ሃገሬ ለአፍሪካና ለጥቁር ህዝብ የዋለችውን ውለታ፣ትሩፋቷን ልዘረዝርላቸው የሚገባ አይነት ሰዎች አይደሉም፡፡ የተማሩ፣ የነቁና በንባብ ብቻ ሳይሆን በጉዞ መሃይምነታቸውን ያከሙ ናቸው፡፡  ስለዚህ ጊዜያዊ ችግራችንን አይተው የዘመናት ችሮታችንን ማሳነሳቸው፣ በአደባባይ እናታችን በሚሏት ሃገር ላይ በየሻይ ቤቱ መሳለቃቸው፣ የአንበሳነት ታሪካችንን በፍጥነት ለመሰረዝ መሽቀዳደማቸው ፣ እኛማ አሁን ነፃ ነን ብለው መመፃደቃቸው ግን ነደደኝ፡፡
ያኔ ነው….በንዴቴ መሃል…የምለውን እያሰላሁ፣ ለመልስ ምት ስዘጋጅ ካፍቴሪያው ውስጥ ተከፍቶ ከነበረው ቲቪ ላይ አይኔ የተሰካው፡፡ ከመጣሁ ጀምሮ ሱስ የሆነብኝን የሃገሩን ተወዳጅ ተከታታይ ድራማ እያሳየ ነበር፡፡ ታሪኩ የጠበቆች ነው፡፡ በዚያች ደቂቃ ይታይ የነበረው ትእይንት ደግሞ ምን ነበር? እንግሊዛዊያን ከሃምሳ አመታት በፊት ቅኝ ግዛታቸውን ጣጥለው ወደ ሃገራቸው ሲመለሱ ትተውት የሄዱትን ጠበቆችና ዳኞች ችሎት ሲታደሙ የሚያጠልቁት ወርቃማ ዊግን ያጠለቁ ጥቋቁር ሰዎች፡፡
ይሄ ዊግ ዝነኛው የእንግሊዝ ንጉስ ጆርጅ ሶስተኛውን ጨምሮ ይሄን ሃገር ጠፍንገው ሲገዙ የነበሩ እንግሊዛውያን የህግ ሰዎች ለዘመናት ፍርድ ቤት ሲያጠልቁት የነበረ ከፈረስ ጠጉር እንደ ሹሩባ ተገምዶ የተዘጋጀ የኮፍያ ዊግ ነው፡፡ እንደሰማሁት ፣ ምቾት ከመንሳቱ የተነሳ እንግሊዞቹ ራሳቸው ከአመታት በፊት ትተውታል፡፡ ወርቃማው ዊግ ግን ዛሬ ድረስ፣ ነፃ ወጥተናል በሚሉ የቀድሞ ቅኞቻቸው የህግ ሊቆች ጥቁር ራስ ላይ በኩራት ተቀምጦ ይገኛል፡፡
እነዚህ ሰዎች ናቸው ‹‹እኛ ነፃ ወጥተናል፡፡ ኢትዮጵያ መጀመሪያ ለራሷ ትሁን›› ብለው ረጅም ስርአትና ታሪክ ያላትን ሃገሬን የሚሰድቡት፡፡
ያቺን ሰአትና ያንን ትእይንት ያገጣጠመ የኢትዮጵያ አምላክ ክብር ምስጋና ይግባውና፣ ስድባቸውን ከዊጉ አያይዤ ‹‹እስቲ መጀመሪያ ይሄንን ዊግ አውልቁ›› አልኳቸው፡፡
ለነጻነት የሞቱት አያቶቻቸው ይሄን ቢያዩ ምንኛ እንደሚያፍሩባቸው እስከ ፑንት ድረስ ነገርኳቸው፡፡
ከሁሉ የቆጨኝ ግን ይሄን ሁሉ ሃተታ ትቼ በሚገባቸው ቋንቋ፣
‹‹የጎባጣ አሽከር ጎንበስ ብሎ ይሄዳል
ምነው ቢሉት ጌታዬን ለመምሰል ይላል››
ማለት አለመቻሌ ነው፡፡

_____________________________________________

                         የሻንጣ ሥራ ክልከላ ለምን?
                              (ሙሼ ሰሙ)


            ዛሬና ትናንት የብዙ ሰዎችና የመገናኛ ብዙሃን ትኩረት የሳበ ጉዳይ በመሆኑ የግል ምልከታዬን እነሆ:-
ዜጎች ሰርቶ የመብላትና ሕልውናቸውን የማስቀጠል መብታቸው በመመርያ የማይጣስና የማይገሰስ ነው። የመንግስት አንዱና ዋነኛው ተግባር፣ ዜጎች ሰርተው የሚኖሩበት ሁኔታዎች ማመቻቸትና እድል መፍጠር ነው፡፡ መንግስት ‘ራሱ የስራ እድል መፍጠርም ሆነ በግል ዘርፉ አማካኝነት ስራን ማመቻቸት ካልቻለ፣ ዜጎች ለእርዳታ ተቀባይነትና ለማህበራዊ ቀውስ እንዳይዳረጉ ሲባል ኢ- መደበኛ ስራዎችን ቢቻል ከታክስ ነጻ በማድረግ ወይም በጣም በዝቅተኛ ታክስ ሰርተው የመኖር “እድል” ሊነፍጋቸው አይገባም፡፡
ይህ ደግሞ ከጎረቤቶቻችን ጀምሮ በብዙ ሀገሮች የተለመደ ነው።
Reserve Army of labour ከሚባለው ሁልቆ መሳፍርት የሌለው ስራ አጥ በተጨማሪ፣ ኢትዮጵያ በየዓመቱ ከአንድ ነጥብ አምስት ሚሊዮን በላይ ለሆኑ ዜጎቿ የስራ እድል መፍጠር ይጠበቅባታል፡፡
እንደሚታወቀው ግን ሀገራችን እንኳን አዲስ ሥራ ፈላጊውን ይቅርና፣ ለነባሩ ሥራ አጥም በቂ የሥራ እድል መፍጠር የቻለች ሀገር አይደለችም፡፡
ይህ ነባራዊ ሀቅ ባፈጠጠባትና ባገጠጠበት ሀገር ተቆጥረው በገደብ እንዲገቡ በሕግ የተፈቀዱ አልባሳትና ቁሳቁሶችን እጅግ ፈታኝ በሆነ መንገድ ጥሪት አብቃቅተው ትንሽ ትርፍ ለማግኘት ከሚበላ፣ ከሚጠጠና ከትራንስፖርት ቆጥበውና ተዳብለው እያደሩ ቤተሰቦቻቸውን ዳቦ ለማብላት የሚታገሉ በተለምዶ የሻንጣ ሰራተኛ የሚባሉ ኢ-መደበኛ ለፍቶ አዳሪዎችን፣ በዚህ ፈታኝ ጊዜ ስራቸውን ማገድ ስራ አጥነትን በማባባስ ማህበራዊ ቀውስንና ሁከት ከመቀስቀስ ውጭ ምን ትርፍ እንዳለው ለመገመት አዳጋች ነው፡፡ ዜጎች እኩል ናቸው በሚባልበት ሀገር ስሞታቸው በልዩነት የተሰማላቸው አስመጭዎችስ በተለይ የውጭ ምንዛሪ የማግኘት፣ የማስመጣትና ዝቅተኛ ታክስ የመቀረጥ ሞኖፖሊ እንዴት ሊኖራቸው ቻለ?
መንግስት እነዚህን አነስተኛና ጥቃቅን እቃዎችን በመቅረጥ ከሚያገኘው ገቢ ይልቅ ኢ- መደበኛው ስራ ከሚፈጥረው የስራ እድል፣ ከስራ እድሉ ከሚገኘው ግብርና የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከሚሰበስበው ገንዘብ ወዘተ ጋር ሲነጻጸር የተሻለ መሆኑ በየትኛው ጥናት ተፈትሾና ሚዛን ደፍቶ መንግስትን ጎድቷል፣ በዝብዟል እንዳስባለ ግራ የሚያጋባ ነው ? መንግስት ማለት ሕዝብ መሆኑንስ እንዴት ተረሳ? የተራበ፣ በማህበራዊ ቀውስ የተመታ፣ በድህነት ክብሩን ያጣ ተመጽዋች ዜጋ የሞላበት ሀገርና መንግስት ላይ የሚካሄደው ዓይን ያወጣ ተጽእኖ ምን እንደሆነ በግልጽ እየታየ እንደዚህ ዓይነት አካሄድ መከተል ለምን ተመረጠ? እድሜው ለስራ ከደረሰው ከከተማ ነዋሪ ውስጥ 50% ስራ አጥ ሆኖ እያለ በመቶ ሺህ ለሚቆጠሩ ዜጎች በቀጥታና በተዘዋዋሪ መንገድ ስራ የፈጠረ ዘርፍን ማሻሻልና ማጎልበት እየተቻለ ያለ ቅድመ ሁኔታና ዝግጅት በማገድ ተጨማሪ ዜጎችን ስራ አጥና ምጽዋተኛ በማድረግ ወዴት ለመድረስ ይታሰባል ? አፋጣኝ መልስ የሚሻ ጉዳይ ነው?!
በዚህ ፈታኝ በሆነና ስራ በተዳከመበት፣ ኢኮኖሚው በተናጋበት፣ ኑሮ በተወደደበት፣ እቃ በጠፋበት፣ የአጉዋ ተጠቃሚና ሌሎች ሰራተኞችን ከስራ በማፈናቀል ሁለንተናዊ ቀውስ ለመፍጠር ሴራ በሚሸረብበትና መንግስት የሕዝብን ድጋፍ በከፍተኛ ደረጃ በሚሻበት ወቅት በድንገት ይህንን ዓይነት ውሳኔ መወሰን ሕዝባዊነቱና ለመንግስት ተቆርቋሪነቱስ ምኑ ላይ ይሆን ?
እስኪ መለስ ብለን ደግሞ ገቢዎች በዚህ ደረጃ የተማረረበትና ዜጎችን አምርሮ የተቆጣበት የሻንጣ ስራ ተጠቃሚዎች እነማን እንደሆኑ እንፈትሽ፡፡
-ዋነኛው የአየር መንገድ ሲሆን አንዱና ከፍተኛ ገቢ በሻንጣ ስራ የተሰማሩ ዜጎችን ማመላለሱ ነው፡፡
-ቀጥሎ የትኬት ሽያጭ ቢሮዎች አሉ
-የሻንጣ ሸቀጥ አስመጭው ዜጋ (ተመላላሽ)
-ሸቀጡን የሚረከበው ሱቅና በሱቁ ውስጥ የተቀጠረው፣ ሱቅ በደረቴውና የመንገድ ዳር ነጋዴ ...
-የሻንጣ ስራውን ለመከወን በስደት የሚገኙ ዜጎች
-የሻንጣ ነጋዴዎችን የሚያመላልሱ ታክሲዎች
-ሱቅ አከራዮች
-የጉምሩክ ሰራተኞችና ቤተሰቦቻቸው ወዘተ ናቸው፡፡
እንግዲህ ከአየር መንገድ ውጭ እነዚህ ሁሉ ዜጎች የመንግስትን እጅ ሳይጠብቁ ከእጅ ወደ አፍ ቢሆንም ሆዳቸውን ለማሸነፍ የሚታትሩ ዜጎች ናቸው። ክልከላው አስፈላጊ ከሆነ እነዚህ ዜጎች ሕልውናቸውን ለማስቀጠል አማራጩ ምንድን ነው?!
የሻንጣ ስራ ለምን የስራ እድል ሊሆን ቻለ? የሻንጣ ኢ-መደበኛ ስራ የግድ የስራ እድል የሆነበት ምክንያት ጉምሩክ የገቢ ቀረጥን በመሰብሰብ ዙርያ ከሚታማበት ሙስና ይጀምራል። ቀጥሎ የውጭ ምንዛሪ አቅርቦት እጦት፣ የቫት ደረሰኝ የማይቆርጡ ነጋዴዎች ተጽእኖ፣ ነጋ ጠባ ብለው ዋጋ የሚቆልሉና እየተመሳጠሩ የገቢም ሆነ የትርፍ ግብር የማይከፍሉ አስመጭዎች ውድድሩን ከንቱ ማድረጋቸውና ውዳቂና ርካሽ ሸቀጥ ያለ አማራጭ በገፍ የሚያግበሰብሱና የግብይት ስርዓቱን በሞኖፖሊ የተቆጣጠሩ አስመጭዎች ተጠቃሽ ናቸው፡፡
ምሳሌያዊ ንጽጽር። ዛሬ ፋና ላይ እንደሰማሁት ከሆነ፣ በጣት የሚቆጠሩ አስመጭና አከፋፋይ ነጋዴዎች ከ32.5 ቢሊየን (የተደረሰበት ነው እንግዲህ) ብር በላይ በሕገ ወጥ መንገድ ደረሰኝ ባለመቁረጥና ሀሰተኛ ደረሰኝ በመስጠት ግብይት በመፈጸማቸው ተከሰው 8 ሚሊዮን ብር ብቻ አስተዳደራዊ ቅጣት ተቀጥተዋል፡፡ ይህ ገንዘብ የሀገሪቱ በጀት 6% ሲሆን የሕዳሴን ግድብን 1/3 ገደማ ይሸፍናል።
ንጽጽሩን እንቀጥል። ሀገሪቱ ውስጥ የሚመላለሱ የኢ-መደበኛ የሻንጣ ነጋዴዎች እንዲያስገቡ በቁጥር የሚፈቀድላቸው 29 አነስተኛና ጥቃቅን ሸቀጥና አልባሳት አይደለም፤ በዚህ ሰንሰለት ውስጥ የሚገኙ ሁሉም ሃይሎች የኢትዮጵያ አየር መንገድን ጨምሮ የሚያስገቡት ገቢ ቢደመር መንግስት በሕገ ወጥ ነጋዴዎች ያጣውን 32.5 ቢሊየን ብር (10%) አያክልም፡፡ ጥቂቶች 32.5 ቢሊየን ብር በሕገ ወጥ መንገድ ግብይት ፈጽመው 8 ሚሊየን ብር ይቀጣሉ፡፡ በመቶ ሺዎች የሚቀጠሩ ዜጎች የስራ እድል የፈጠረ ኢ- መደበኛ ስራ ሰርተዋል በሚል ያውም ሕገ ወጥ ሳይሆኑ በአንድ መስርያ ቤት መመሪያ በሕገ ወጥነት ይፈረጃሉ፣ ተግባራችሁ በሕግ ያስጠይቃል ይባላሉ።
በዜጎች መካከል እንደዚህ ዓይነት ልዩነት እየፈጠሩ በፍርደ ገምድልነት ማህበራዊ ቀውስ ማስፋፋትና ቤተሰብ መበተን? በየትኛው የሕገ መንግስቱና ሕግጋቶቹ ላይ ለየትኛው ባለስልጣንና ሹመኛ የተሰጠ ስልጣን ይሆን?! ስራ ለመፍጠር አቅምና ብቃት የሌለው ሀይል የብዙዎች እንጀራ የሆነውን ኢ- መደበኛ ስራን ለማፍረስና ያለ ቅድመ ዝግጅትና አማራጭ ቤተሰብ ለመበተን የሞራል ልዕልናውንስ ከየት አገኘው?!

__________________________________________


                            የታዘብኩት ፊልምና ተመልካቹ!
                                   (ገመቹ መረራ ፋና)

               እህእ!
ስብሀት ገ/እግዚአብሔርን ከማደንቅባቸው ምክንያቶች አንዱ ተራማጅ (progressive) መሆኑ ነው። እንደ ዕድሜ እኩዮቹ (ኧረ የኛ ዕኩዮችም አሉ ለነገሩ) አንድ ቦታ/ሀሳብ ላይ አልተቸከለም። ስለ ፊልም ሲነሳ ሌሎቹ የቦዘኔ መዋያ ቦታ፣ የዱርዬ ጊዜ ማጥፊያ አድርገው ይወስዱታል። የስቅለት ፊልም እንኳን እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ የጴንጤ ፕሮፓጋንዳ ተደርጎ ይታይ ነበር፡፡
አራዳው ስብሀት ግን ፊልም ይወዳል፣ አሪፍ ነው ይልሀል። ለምን ካልክ “አንብቦ ለመጨረስ ሶስትና አራት ቀናት የሚወስድብህን መፅሐፍ በሁለት ሰዓት ቁጭ ያደርግልሀል!” ይልሀል!
የምታየውን ነገር መምረጥ፣ ማስተዋልና መረዳት ግን የተመልካቹ ድርሻ ነው። ለመዝናናት፣ ለመማር፣ ለሽቀላ፣ ለልጆች ወዘተ ልትፈልገው ትችላለህ። የፊልም ምርጫ የtaste ጉዳይ ሊሆንም ይችላል። አንዳንዱ ግን ያስቃል!
ሰሞኑን ፌስቡክ ላይ “Money Heist” ተብሎ በእንግሊዝ አፍ ተተርጉሞ ስለሚታየው La Casa De Papel የተባለ የስፓኒሽ ፊልም የሚፃፉ ነገሮች እያየሁ ስስቅ ነበር። ለጣፊዎቹ ፊልሙን ባለፈው ካቆሙበት ቀጥለው ጨርሰው “ቶኪዮ መሞቷን አመንኩ” ይላሉ። ቶኪዮ አንዷ ገፀ ባህሪ ነች። ቼክ ሳደርግ ፊልሙ ከዚህ ቀደም የቆመበት ቦታ ላይ ስድስት የእጅ ቦንብ ደረቷ ላይ ደርድራ ተኝታ ቀለበቶቹን ነቅላ አምስት ጠላቶቿን ገድላ ነው የሞተችው።
ተመልካቾች ታዲያ ከስድስት ቦንብ ትተርፋለች ብለው ጠብቀዋል! ስላልተረፈችና ስለሞተች ደሞ አዝነዋል፡፡ እኔ ቶኪዮ ትዳን ትሙት አላውቅም። ፀሀፊው ግን አተረፋት እንበል። ስድስት ቦንብ ደረቷ ላይ አፈንድታ ራቅ ብለው የቆሙ 5 ጠላቶቿን ገድላ እሷ ተረፈች ቢልህ፣ በፊልሙ የማይመስል ሴራ ትደሰታለህ? የምር??
የዚህ ዓይነት ፋንታሲ ነው ፖለቲካውም ላይ ተንፀባርቆ እያጠፋን ያለው። ተመልካቹ (ሕዝቡ) ፊልሙ (የሀገሪቷ ማሕበረ-ፖለቲካዊ ጣጣ) በአንድ ወገን ፍፁም አሸናፊነት የሚጠናቀቀ ይመስለዋል። የነሱ ቶኪዮ ጠላቶቿን ገድላ የምትኖር ይመስላቸዋል።
P.S.
ፊልሙን ያላያችሁ አትዩት። የጊዜና የጉልበት ብክነት ነው።





Read 1890 times