Print this page
Saturday, 18 December 2021 14:01

ዕውነት ያለው ህፃናት አፍ ውስጥ ነው!

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

ከዕለታት አንድ ቀን ታዋቂው ኢትዮጵያዊ ጋዜጠኛ ጳውሎስ ኞኞ፣ “አንድ ጥያቄ አለኝ” የሚል የጋዜጣ አምድ ነበረው። አስቂኝ ጥያቄ ይጠይቃል። አስቂኝ መልስ ይሰጣል። (በዛሬ ጊዜ እንደዛ ያለ ፕሮግራም ወይም አምድ ባለመኖሩ ብዙ ቁምነገር- አዘል ቀልድ አምልጦናል።)
ጥቂቶቹን እናስታውስ፡-
“ለአንድ ጥያቄ አለኝ” አምድ አዘጋጅ
ጥያቄ - ጋሽ ጳውሎስ፣ ይሄ አፍንጫህ ረዝሞ ረዝሞ የት ሊደርስ ነው? - ኤልሣቤጥ ነኝ
ጳውሎስ - የት ስትንከለከይ የእኔ አፍንጫ መንገድ ዘጋብሽ?!
ጥያቄ - ጋሽ ጳውሎስ፣ ይሄ ብርሃንና ሰላም ማተሚያ ቤት ፊትለፊት የቆመው ሮኬት መቼ ነው የሚተኮሰው? (ያኔ በጆንያ ሰጋቱራ (ማገዶ) እየተሞላ በሶስት ጉልቻዎች ላይ ቆሞ ይታይ ነበር)
ጳውሎስ - የእናትህ ምጣድ ሲሰበር ነው!
ጳውሎስ ኞኞ ከፃፋቸው አጫጭር ጭውውቶች የሚከተሉት ይገኙበታል፡-
ዱዱ ስለሚባል ትንሽ ልጅ ነው ትርክቱ።
ዱዱ ከአባቱና ከአባቱ ጓደኛ ፊት ለፊት መሬት ላይ ቁጭ ብሎ ከጓደኛው ጋር ይጫወታል። የአባቱ ጓደኛ ዐይነ-ሥውር ናቸው።
አባት- “ዱዱ” አሉና ጠሩት።
ዱዱ- “አቤት አባዬ?” ብሎ ከሚጫወትበት ቀና አለ።
አባት- “እስቲ ለእኔና ለባልንጀራዬ ሂድና ቢኖ (WINE) ገዝተህ ና።” ብለው ገንዘብ ሊያወጡ ኪሳቸው ገቡ።
ዱዱ- “እሺ አባዬ” አለና ወደ አባቱ ሄደ።
ገንዘቡን ተቀብሎ ከቤታቸው አቅራቢያ ወደሚገኝ ግሮሰሪ ሮጠ። ግሮሰሪው ባለቤት ዘንድ ሲደርስ፤
“ባለ ሱቅ” አለ።
“እህስ ልጄ ምን ፈልገህ መጣህ?” አለና ባለግሮሰሪው ጠየቀው ዱዱን።
ዱዱም፤
“ቢኖ ስጠኝ?” አለው።
“ምን     አይነት?”
“ባለ ሠሌን”
“ቀይ ነው ነጭ ቢኖ?”
“ባክህ የፈለግከውን ስጠኝ- ሰውዬውን ዕውር ናቸው!” አለ።
ባለ ግሮሰሪው በጋዜጣ የጠቀለለትን ቢኖ ይዞ፤ ዱዱ ለአባቱና ለእንግዳው አስረከበ።
አባትና እንግዳው ቢኗቸውን እየጠጡ ሲጨዋወቱ፣ እንግዳው ሰውዬ፤
“ወቸ ጉድ! ይሄ ዱዱ እኮ ታምረኛ ልጅ ነው!” አሉ።
ይሄን አባባል የሰማው የዱዱ ጓደኛ ቀና ብሎ ወደ እንግዳው እያየ፤ “አባባ ታምረኛ ማለት ምንድን ነው?” ሲል ጠየቀ። ይሄኔ ዱዱ ጣልቃ ገብቶ፤
“ና እኔ ልንገርህ?” ይለዋል።
ልጁም እሺ ብሎ ወደ ዱዱ ሲመጣ፤ ዱዱ ሆዬ በጥፊ ድርግም ያደርግበታል። ልጁ ምርር ብሎ ያለቅሳል።
ዱዱም፤ “ምን ሆነህ ነው የምታለቅሰው?” አለና ጠየቀው።
ልጁም፤ “አመመኛ!” ይለዋል፡፡
 ዱዱ፤ "አየህ፤ ባያምህ ኖሮ ተዓምር ነበር!" አለው።
*   *   *
“ዕውነት ያለው በህፃናት አፍ ውስጥ ነው” ይላሉ ፈረንሳዮች፡፡ (La Verite est dans La bouche des enfants እንዲል መጽሐፍ) ዕውነት ያለው ቅን- ልብ ውስጥ ነው እንደ ማለት ነው።
አገራችን ቅን ልቡና ያለው ሰው ትፈልጋለች። እድገቷንና ለውጧን ያለ ጥርጥር ሊያመጣ የሚችለው ቅን የሆነ አስተሳሰብ ስለሆነ ነው።
ያገራችን ገጣሚ እንዳለው፡-
… ያኛው ዘራፍ ባለ
ያኛው አይዞን ባለ
ሁሉም ጦር ሰባቂ
ሁሉም ጦር ናፋቂ
ኮርቻ ላይ ወጪ፣… ጋላቢ ከሆነ
እኛም ከገዳይ ጋር፣ ግፋ! በለው! በለው!
የምንል ከሆነ፤
ሌላውን ከመርገም፣ ሀሳባችን ልቆ፣ ምኑ ጋ ዘመነ?!”
የማለትን ጥያቄ ያስዘወትረናል።
አያሌ ተረቶችና አባባሎች የአሁኑን የአገራችንን ሁኔታ ይገልጡታል። ዋንኛው አሳዛኝ ነገር ግን አብዛኛዎቹ ቦታዎቻችን፣ ከጋምቤላ እስከ ምሥራቅ፣ ከሰሜን እስከ ደቡብ፣ የጦርነት፣ የሰቆቃና የእልቂት እንዲሁም የመፈናቀል አውድማ መሆናቸው ነው።
“የሞተ ልጅ እናት፣ የልጄ አንገት ሁለት ክንድ ነው ትላለች” ዓይነት ነው አንዳንዱ ጉዳይ። ዞሮ ዞሮ ልጁ መሞቱ አልቀረምኮ!
ያም ሆኖ ምልጃና ደጅ ጥናት አላጣንም፣ አልለቀቀንም።
“የሞተ ልጇን አዝላ የታመመ የሹም ልጅ ልትጠይቅ ትሄዳለች” የሚለው አሰቃቂ ዕውነትም አለ። ለሹማምንት ማጎብደድ እንደተጠናወተን አለ፡፡
ሮበርት ፍሮስት የተባለው አሜሪካዊ ገጣሚም፤
“ሁላችንም ዙሪያውን እየዞርን! ዳር ዳር እያልን እንገምታለን፤ ዕውነቱ ከማህል ቁጭ ብሎ ይስቅብናል” ብሎናል።
ናፖሊዮን ቦናፓርትም ስለ ጦርነትና ጊዜ ሲነግረን፡-
“የተያዘብንን ቦታ መልሰን መያዝ እንችላለን። ያጠፋነውን ጊዜ ግን ለመመለስ አንችልም” ብሎናል።
 ልብ ያለው ልብ ይበል እንግዲህ!
ዞሮ ዞሮ በጦርነት አኳያ ስናይ፤
“አንበሳና ዝሆን ሲጣሉ የሚጎዳው ሳሩ ነውና” እንደ ኢትዮጵያ ህዝብ  በጦርነት የተጎዳ የለም። ፈጣሪ ደጉን ጊዜ ያመጣልን ዘንድ ፀሎታችን ነው፡፡
በጦርነት የሚወድመው ቤት ንብረት፣ ከወገናችን እልቂትና ከከብት ከእንስሳቱ ሬሳ ብዛት የማይተናነስ ነው፡፡ ዘላን “አንዴም ሳር አንዴም አሳር” ያገኘዋል እንዳልነው፣ ቀላል መከራ ውስጥ አይደለንም፡፡ ዛሬ በረደ ሲባል ነገ የሚፈላ ሁኔታ ውስጥ ነንና፣ ከወጣት እስከ አዛውንት ከገበሬ እስከ ነጋዴ፤ ከጨዋ እስከ ምሁር፣ፆታ ሳይለይ ተረባርቦ መልካሙን ጊዜ ማምጣት አለበት። የሁሉም ጥረት እንጂ የጥቂት ድርጅቶች መፍረምረም ብቻ ፈጣን ሰላም አያመጣም፡፡ ያም ሆኖ የድርጅቶች፤ የፓርቲዎች፤ የተቋማትና የአለሁ- ባይ የማህበረሰብ አካላት ሁሉ፤ መመካከር፣ መደማመጥና መፍትሄ መሻት ይጠበቅባቸዋል;፡፡
እንደ ህጻን ቀና ልብ ይስጠን፡፡ ዕውነት ያለው ህጻናት አፍ ውስጥ ነውና!!

Read 11828 times
Administrator

Latest from Administrator