Print this page
Saturday, 18 December 2021 14:03

"No More - በቃ!" የጫረው እሳት

Written by  አያሌው አስረስ
Rate this item
(0 votes)

    በ1987 ዓ.ም የበርታ ኮንስትራክሽን ድርጅት ከጋሸና እስከ ላሊበላ ያለውን መንገድ እየሰራ ስለነበር የመንገዱን ሥራ ለማየት ወደ ሥፍራው ተጉዤ ነበር፡፡ በወቅቱ አካባቢው ተርቧል ተብሎ የላሊበላ ከተማ በእርዳታ ፈላጊዎች ተጨናንቆ ነበር። እርዳታ ለመቀበል ከተሰበሰቡት ሰዎች አራት ያህሉን አነጋግሬ ነበር፡፡ አንደኛው ታዲያ ወደ እርዳታ ሥፍራው የመጣው የስድስት ሰዓት የእግር ጉዞ አድርጎ ነው፡፡
“በእርግጥ ተርበህ ነው ወደ እዚህ የመጣኸው?” ስል ጠየቅሁት፡፡
“አምስት ኪሎ በቆሎ ማን ይሠጣል!?” ሲል መለሰልኝ፡፡
ለእርሱ አምስት ኪሎ በቆሎ ስለተቸገረ የተቀበለው ሳይሆን አጋጣሚው ስለተፈጠረለት ባለው ላይ የሚጨምረው ሃብት ነበር፡፡
እንዲሁም የተጀመረው እርዳታ ፈላጊነትና ጠባቂነት እየቆየ ስር እየሰደደ ሄደ፡፡ መንግስትም በየዓመቱ የሚራበውን ሕዝብ ብዛትና የሚያስፈልገውን የእርዳታ መጠን መዘርዘር ያዘ፡፡ እንዲያውም #ይህ ካልሆነ የከፋ ችግር ይከሰታል; የሚል ማስፈራሪያ ቃል መናገሩን ገፋበት፡፡ በኋላ ላይ መንግስት እርዳታ የማይጠይቅበትና የማይጠባበቅበት ኢኮኖሚያዊ ማህበራዊና ፖለቲካዊ ጉዳይ ጠፋ፡፡ ሌላው ቀርቶ በአምስት ዓመት አንድ ጊዜ የሚያደርገውን የክልልና አገር አቀፍ ምርጫ ሲያካሂድ የቆየው በእርዳታ ገንዘብ መሆኑም ሳይጠቀስ አይታለፍም፡፡
በየምክንያቱም የመንግስት እርዳታ ጠያቂነትና ጠባቂነት፣ የእርዳታ ሰጪ ክፍሎች ልብ እየተበተ #እኛ እጃችንን ካልዘረጋን አለቀላችሁ; ወደሚል ድምዳሜ እንዲደርሱ አድርጓቸዋል፡፡ በታላቁ የህዳሴ ግድብ ድርድር በታዛቢነት የገባችው አሜሪካ፣ በራሷ ጊዜ ውል አርቃቂ ሆና "ኑ ፈርሙ" እስከ ማለት የደረሰችው "ነፍሳችሁ በመሐል እጄ ውስጥ ነው" ብላ ስላሰበች እንደነበር በተግባር እየታየ ነው፡፡ ኢትዮጵያ አልፈርምም ብላ ድርድሩን ጥላ ስትወጣ ሁሉም አፉን ይዞ የተገረመው፣ "ከየት ያመጡት ድፍረት ነው" በሚል እንደሆነም መገንዘብ አያዳግትም፡፡
“መንግስታችሁ የቆመው እኛ በምንሰጠው እርዳታ ነው” የሚለው የምዕራባውያን ትምክህት፤ አሸባሪው ትህነግ በማዕከላዊ መንግስት ላይ ጦርነት ከከፈተ ወዲህ ባሉት ጊዜያት ሁሉ በሰጠው ድጋፍ ጎልቶ የታየ ጉዳይ ሆኖአል፡፡ ትህንግ ለጦርነት በተዘጋጀበት ጊዜ ሁሉ በቂ ስንቅ እንዳከማቸ፣ የሚላክለትን የእርዳታ እህል ወላጆች ልጆቻችውን ለጦርነት እንዲሰጡት ለማድረግ እየተጠቀመበት መሆኑን እያወቁ፣ መንግስትን “ረሃብን የጦር መሳሪያ አድርጎ እየተጠቀመበት” ነው ሲሉ ይከሳሉ፡፡ እነሱ የሚደግፉት ትሕነግ ግን በሰጡት የእርዳታ እህል ተዋጊ ያጓጉዙበታል፡፡ የሚገርመው ደግሞ የኢትዮጵያ መንግስት “ወደ ትግራይ እርዳታ ጭኖ እንዲገባ ያደረጋችሁት ተሽከርካሪ እንዲወጣ እስካላደረጋችሁ ድረስ ተጨማሪ መኪና ወደ ክልሉ እንዲገባ አልፈቅድም” ብሎ ጠንካራ አቋም አለመያዙ ወይም አለመወሰኑ ነው፡፡
አሸባሪው ትሕነግ ለከፈተው ጦርነት ባለቤቱ ግብጽ መሆኗ የሚጠፋው አለ ብዬ አልጠብቅም፡፡ የአሜሪካ ለትህነግ ሥትል ጨርቋን ጥላ ማበዷም ቢሆን ለግብፅ ሲባል የተደረገ መሆኑ የማይገባው ካለ አዝናለሁ፡፡
አሜሪካና ሌሎች ምዕራባዊ አገራት በኢትዮጵያ ላይ እያደረጉት ያለው ተፅዕኖ፣ ያልታሰበና ያልተጠበቀ "በቃ- No More" የሚል እንቅስቃሴ እንዲወለድ አድርጓል፡፡ የ"በቃ" እንቅስቃሴ "እጃችሁን ከኢትዮጵያ ላይ አንሱ" በማለት ብቻ አልቆመም፤ "የእጅ  አዙር ቅኝ አገዛዛችሁን ከአፍሪካ ላይ  አንሱ" ወደሚልም ተራምዷል፡፡
አሥራ ሁለቱ የቀድሞ የፈረንሳይ ቅኝ ግዛት አገራት በዓመት አምስት መቶ ቢሊዮን ዶላር በፈረንሳይ ባንኮች ያስቀምጣሉ፡፡ ከዚህ ውስጥ በራሳቸው ፈቃድ ሊያዝዙበት የሚችሉት አስራ አምስት ከመቶ የሚሆነውን ብቻ ነው፡፡ ከዚህ በላይ እንጠቀማለን ካሉ የፈረንሳይን ፈቃድ ማግኘት አለባቸው፡፡ ምንም አይነት እቅድ ይዘው ይነሱ ፈረንሳይ  እስካልተስማማች ድረስ ምንም ማደረግ አይችሉም፡፡ በእነሱ ገንዘብ ላይ የመወሰን ሥልጣን ያላት ፈረንሳይ ናት፡፡ ፈረንሳይ "በቃ" የምትባልበት ጊዜ አሁን ነው፡፡ በማሊ ተግባራዊ ሆኖ ውጤት አምጥቷል። የፈረንሳይ ወታደሮች ከአገሪቱ እየወጡ ነው። አፍሪካዊያን ከቀድሞ የፈረንሳይ ቅኝ ግዛት ሕዝቦች ጎን መቆም አለባቸው፡፡
ነፍሳቸውን ይማረውና የቀድሞው የዚምባቡዌ ፕሬዚዳንት ሮበርት ሙጋቤ፣ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ሕጉን እንዲመረመር አሳስበው ነበር፡፡ ዛሬ ከሶስት ቢሊዮን በላይ ህዝብ ያላት አፍሪካ፣ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት ቋሚ መቀመጫ ይኖራት ዘንድ ኢትዮጵያን ጨምሮ የተለያዩ የአፍሪካ አገራት ጥያቄውን እያቀረቡ ናቸው፡፡
 አፍሪካውያን፤ ለምዕራባዊያን "የአፍሪካን ማዕድን መዝረፍ፣ በአፍሪካ ምድር ሴራ በመሸረብ መሪዎችን ማስገደል፣ ከጀርባ ሆኖ የእርስ በእርስ ጦርነት እንዲካሄድ ማድረግ" ወዘተ ከእንግዲህ "በቃ" እያሉ ነው።  ኢትዮጵያ በእሷ ምክንያት የተፈጠረው አፍሪካዊ ንቅናቄ ዳር እንዲደርስ ለማድረግ፣ የማስተባበርና የመሪነት ድርሻዋን መወጣት አለባት፡፡ በተባበሩት መንግስታት የፀጥታው ምክር ቤት ቋሚ ወንበር የማግኘትም ሆነ፣ የአፍሪካ የፖለቲካና ኢኮኖሚ ጥያቄዎች መልስ እንዲያገኙ መስራት ለነገ የሚባል ጉዳይ አይደለም፡፡  ትግሉ ተጀምሯልና!!!
በነገራችን ላይ የምዕራባዊያን ፖሊስ አውጪዎች "ከሰሀራ በታች ያሉ አገሮች ማደግ የለባቸውም፤ ጥሬ እቃ አቅራቢ ሆነው መቀጠል አለባቸው፤ እነሱ አደጉ ማለት አውሮፓ ደሃ ሆነች ማለት ነው" እያሉ መሆኑን ታውቃላችሁ? ጥያቄዬ ነው፡፡


Read 1932 times