Saturday, 18 December 2021 14:08

የአዲስ አድማስ መሥራች 17ኛ ዓመት - ጊዜው እንዴት ይከንፋል!

Written by 
Rate this item
(0 votes)

 የህይወት ታሪኩ በቪሲዲ ሊወጣ ነው


            ባለ ብዙ ራዕዩ የአዲስ አድማስ ጋዜጣ ፈጣሪና መሥራች የነበረው አቶ አሰፋ ጎሳዬ በሞት ከተለየን 17 ዓመት ሞላው፡፡ ጊዜው እንዴት ይከንፋል! የትላልቅ ህልሞችና የአዳዲስ ሃሳቦች አፍላቂ የነበረው አሰፋ ጎሳዬ፣ በሁነኛ መሰረት ላይ የተከለው "አዲስ አድማስ; ጋዜጣም እነሆ ከተመሰረተ 23ኛ ዓመቱን ይዟል፡፡ በኢትዮጵያ የግል ፕሬስ ታሪክ ለረዥም ዘመን በመዝለቅ ሁለተኛው የአማርኛ ጋዜጣ ነው - አዲስ አድማስ፡፡ አሰፋ በርግጥም ባለብዙ ራዕይ ባለትላልቅ ህልሞች ባለቤት ነበር፡፡ ይሄንንም በህይወት ሳለ እውን ባደረጋቸው የሥራ ውጤቶቹ አረጋግጧል፡፡ ነገር ግን ሌሎች በርካታ ህልሞቹንና ኃሳቦቹን እውን  ሳያደርግ ነው ድንገት ሞት የቀደመው፡፡ (በዚህም ከሱ በላይ እኛ ተጎዳን)፡፡ አሰፋ ተነባቢና ደረጃውን የጠበቀ መጽሔት ለማውጣት በእንቅስቃሴ ላይ ነበር፡፡ ሳምንታዊ የእንግሊዝኛ ጋዜጣም እንዲሁ፡፡ የሬዲዮና ቴሌቪዥን ፕሮግራሞች ለመጀመር በዝግጅት ላይ ነበር፡፡ የአዲስ አድማስ ጋዜጣ የረዥም ጊዜ አምደኛ ኤፍሬም እንዳለ፣ "የአዲስ አድማስ ሰው" በተሰኘው የአሰፋ ጎሳዬ የህይወት ታሪክ መጽሐፍ  ላይ ባሰፈረው አስተያየት፤ "--አሰፋ ቢኖር ኖሮ፣ በአገራችን የፊቸርና የዶክሜንተሪ ፊልም ኢንዱስትሪ ውስጥ ተፅዕኖ ማሳደር የሚችሉ እንቅስቃሴዎች ይኖሩ ነበር ከሚሉት መሀል ነኝ፡፡ አሰፋ ቢኖር ኖሮ፣ በመጻሕፍት ሕትመት ዘርፍ ተፅዕኖ ማሳደር የሚችሉ እንቅስቃሴዎች ይኖሩ ነበር ከሚሉት መሀል ነኝ፡፡--" ብሏል።
አልተሳሳተም፡፡ እሱ ብቻ ሳይሆን ሌሎች አሰፋን በሥራም ሆነ በጓደኝነት የሚያውቁት ብዙዎች፣ በሚገርም ሁኔታ ይህንኑ ይጋራሉ። ዛሬም ከተለየን ከ17 ዓመት በኋላ ስለ አሰፋ ባለ ራዕይነት፣ ተጫዋችነት፣ ለጋስነት፣ ሰው ወዳድነት፣ ብሩህ ተስፈኝነትና ሃሳብ አፍላቂነት -- ተናግረው የማይጠግቡ አያሌ ናቸው፡፡ ከእነዚህም መካከል በ1990ዎቹ አሰፋ በህይወት ሳለ የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ ሆኖ የሰራውና አሁን "ተወዳጅ ሚዲያና ኮሙኒኬሽን" የተሰኘ የግል ድርጅቱን የሚመራው እዝራ እጅጉ ተጠቃሽ ነው፡፡ ከአዲስ አድማስ ወጥቶ የራሱን የግል የማስታወቂያ ጋዜጣ ሲጀምር ያበረታታው አሰፋ እንደነበር የሚያስታውሰው እዝራ፤ ዛሬ ለደረሰበት ደረጃ የአሰፋ አስተዋጽኦና ተጽዕኖ ቀላል አለመሆኑን ይገልጻል፡፡ በድርጅቱ በተወዳጅ ሚዲያና ኮሙኒኬሽን አማካኝነት፣ የሪፖርተር ጋዜጣ መሥራቹን የአማረ አረጋዊና የቀድሞውን አንጋፋ ጋዜጠኛ ሙሉጌታ ሉሌን ጨምሮ  የሌሎች ታላላቅ ሰዎችን የህይወት ታሪክ በቪሲዲ አዘጋጅቶ ለህብረተሰቡ ማድረሱን  የሚገልጸው ጋዜጠኛው፤ የአሰፋ ጎሳዬን የህይወት ታሪክም በቅርቡ ከአዲስ አድማስ ጋር በመተባበር በቪሲዲ ለማውጣት ማቀዱን አስታውቋል፡፡
ጋዜጠኛ ዕዝራ እጅጉ ረቡዕ ታህሳስ 6 ቀን 2014 ዓ.ም በአዲስ አድማስ ጋዜጣ ዝግጅት ክፍል ተገኝቶ ነበር - የአሰፋ ጎሳዬን 17ኛ ሙት ዓመት ምክንያት በማድረግ ይህን ባለራዕይ ለማሰብና ለመዘከር፡፡ "ዛሬ እዚህ የመጣሁት አሰፋ ጎሳዬ በአካል ቢለየንም በሥራዎቹ አሁንም ድረስ ህያው በመሆኑ ነው" ያለው ጋዜጠኛው፤ እስከ ዛሬ ድርጅቱ አዘጋጅቶ ካወጣቸው ወደ 45 የሚደርሱ የተለያዩ ሰዎች የህይወት ታሪክ ቪሲዲዎች 15 ያህሉን ለ"ዕውቀትና ትጋት አሰፋ ጎሳዬ ማህበር" በስጦታ አበርክቷል፡፡ የአሰፋ ጎሳዬን ታሪክ ለአዲሱ ትውልድ ማስተዋወቅና ማስፋፋት ይገባል የሚል እምነት ያለው ዕዝራ፤ በድርጅቱ አማካኝነት የአሰፋ ጎሳዬ አጭር የህይወት ታሪክ በዊኪፒዲያ ላይ እንዲካተት መደረጉን አስታውቋል፡፡ በቅርቡም ከአዲስ አድማስ ጋር በመተባበር አሰፋ ጎሳዬን የሚዘክርና ታሪኩን የሚያስተዋውቅ ታላቅ የኪነጥበብ ዝግጅት በብሔራዊ ቴአትር እንደሚቀርብ ተናግሯል፡፡ በዚህ አጋጣሚ የአዲስ አድማስ ዝግጅት ክፍል፣ ጋዜጠኛ ዕዝራ እጅጉና ድርጅቱ፣ ባለ ራዕዩን አሰፋ ጎሳዬን ለማስተዋወቅና ታሪኩን ለማስፋፋት  እያደረጉ ለሚገኙት ጥረት ሁሉ ከልብ ያመሰግናል፡፡ ዝግጅት ክፍሉ በሚችለው ሁሉ ለማገዝ ያለውን ቁርጠኝነትም ለመግለጽ ይወዳል፡፡
የዚህ ጽሁፍ ዓላማ የአዲስ አድማስ መሥራቹንና ባለራዕዩን አሰፋ ጎሳዬ መዘከር በመሆኑ፣ በሥራና በጓደኝነት የሚያውቁት ከሰጡት ምስክርነት ጥቂቱን ቀንጭበን  እንደሚከተለው አቅርበነዋል፡፡ በርካታ አርቲስቶችና ታዋቂ ግለሰቦች ስለ አሰፋ ጎሳዬ የሰጡትን አስተያየትና  ምስክርነት "የአዲስ አድማስ ሰው" በሚል ርዕስ፣ በ2005 ዓ.ም ለንባብ ከበቃው የህይወት ታሪክ መጽሐፍ ላይ ማንበብ ትችላላችሁ፡፡ መጽሐፉ ብዙ ትምህርትና ቁምነገር ያስጨብጣል፡፡ ለትጋትና ስኬትም ያነቃቃል፡፡ ለጊዜው ግን ቀንጭበን ያጠናቀርነውን አስተያየት እነሆ፡-


ቼ በለው
ሕይወት ጎዳናው ገፁ ሲለወጥ
በጭነት ታክቶ ጀርባው ሲመለጥ
የእንቅፋት አፅሙ ቋጥኙ ሲገጥ
ሸክም ዘንቦበት ትቢያው ሲላቁጥ
ሲሆን ድጥ በድጥ
ሾህ ጭቃ ቅይጥ
ልብህ አይደንግጥ፡፡
በምኞት ቅዠት በስጋት ርዶ
አይፍረስ ግንቡ ወኔህ ተንዶ
ከቆመው ቆመህ ከንፈር ከመምጠጥ
በተስፋ ፈረስ በልጓም ሸምጥጥ፡፡
አያረጅ የለም አይለዋወጥ
ነገን ተማምነህ በመጓዝ ቁረጥ..
ከሩቅ አልመህ ቅርብ አትርመጥመጥ
ሰግተህ ከምትቆም ስትጋልብ ፍረጥ፡፡
(ሰዓሊና ቀራጺ በቀለ መኮንን)


"--ስለ አሰፋ ባለ ልዩ ተሰጥኦ ሰውነት ለመዘርዘር ከመሞከር እግዚአብሔር እሱን ወደ ምድር ያመጣው እንቁልልጭ ሊለን ነው ማለት ይሻላል፡፡ እንደዚያ ባይሆን ኖሮ፣ ሳንጠግበው አይወስድብንም ነበር።  አሰፋን ዝም ብለህ ስታዳምጠው ብትውል አይሰለችህም፡፡ አፍህን ከፍተህ ነው የምትሰማው፡፡ አሰፋን የተዋወቀና ሌላ የሚወደው ጓደኛ ያለው ሰው፣ ሁለቱንም መቼ አገናኝቼ ላስተዋውቅ ብሎ ነው የሚጓጓው፡፡
ይህን ለማድረግ የምትጓጓው እኔ ከአሰፋ ያገኘሁትን ደስታ ሌላኛውም ወዳጄ ቢጋራው በሚል ስሜት ነው፡፡ ለሴት ጓደኛህ ወይም ለሚስትህ ወይም ለልጅህ ጥሩ ነው ብለህ መርጠህ የገዛኸውን ዕቃ ስታበረክት ደስታ እንደሚሰማህ፣ አሰፋን ለሌላኛው የልብ ወዳጅህ ማስተዋወቅም ተመሳሳይ ደስታ እንደሚፈጥርልህ ነው የሚሰማህ፡፡ አሰፋ ምርር ያለ ንዴት ውስጥ ገብቶ አይቼው አላውቅም፡፡ ሲያለቅስም አይቼው አላውቅም፡፡ ከዚህ ዓይነት ሰው ጋር ሥራ ባይበዛበትና ቀኑን ሙሉ አብረኸው ስትዝናና ብትውል ትመኛለህ። በማንኛውም ርዕሰ ጉዳይ ላይ ያለ ችግር የመወያየትና የመጫወት ችሎታ አለው፡፡ ተንኮልና ሸር አይወድም፡፡ ሌላውን የሚጎዳ ነገር ሲደረግ ማየት ይጠላል፡፡ ጥሩ መንፈስ ያለው፣ ባለርዕይና ተስፋ ሰጪ ነገሮችን ማየትና መስማት የሚያስደስተው ሰው ነበር፡፡--"
(አርቲስት ጌታቸው አበራ)
***
"አሰፋ ዘንድ ተጨንቆ የሄደ ሰው ጭንቀቱ ተወግዶ መንፈሱ ታድሶ ይመለሳል፡፡ ነገሮችን
የሚያይበት መንገድ ያስገርማል። በሱ ዘንድ ያለውን ሰላምና ደስታ ወደ ሌላው ያጋባል፡፡
እነዚያን ባህርያቱንና ተፈጥሮውን  ሳስታውስ፣  አንዳንድ ጊዜ፣ ሳቅና ጨዋታ ከአሴ በኋላ ቀረ እላለሁ፡፡ አሰፋ ማኅበራዊ ግንኙነቱም በጣም ሰፊ ስለነበርና ሰዎችን በግልም በቡድንም ወዳጁ ማድረግ
ስለሚችል ሁሉም ተጠይቀው የሚናገሩበት ዕድል ቢያገኙ፣   ስለ  አሰፋ  ብዙ  ብዙ  አስገራሚና
አስደናቂ  ታሪኮችን የሚናገሩ ይመስለኛል፡፡  
በራሱ ዕውቀት ላይ የተለያዩ ባለሙያዎችን ምክርና አስተያየት አካትቶ የመሰረታቸው አድማስ አድቨርይዚንግና አዲስ አድማስ ጋዜጣ፣ አሰፋ ከዚህ ዓለም በሞት ከተለየ በኋላ መቀጠል የቻሉት ሊያስቀጥላቸው የሚያስችል ‹‹ሲስተም›› ቀደም ብሎ ዘርግቶላቸው ስለነበር ነው፡፡ እኔ አሰፋ ይመራው የነበረው ተቋም ምን ያህል ትልቅና ከባድ እንደነበር ያወቅኩት እሱ በሞት
ከተለየን በኋላ ነው፡፡
እሱ የዘረጋውን ‹‹ሲስተም›› ተከትለን ለመጓዝ ብዙ መልፋት ነበረብን፡፡
እኔ በ1978 ዓ.ም ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በአካውንቲንግ በመጀመሪያ ዲግሪ ተመርቄ
ከወጣሁ  በኋላ  በሻኪሶ ማዕድን ማውጫ ጀምሬ በተባበሩት መንግስታት የስደተኞች ቢሮ፣
መንግስታዊ በሆኑና ባልሆኑ የተለያዩ ተቋማት፣ እንዲሁም በግል ድርጅቶች ማማከርን ጨምሮ
በሙያዬ ሰርቻለሁ፡፡
አሰፋ ጎሳዬን የመሰለ ሥራ አስኪያጅና የሥራ መሪ ግን ገጥሞኝ አያውቅም፡፡
የአሰፋን ልዩ ባህርይና ተፈጥሮ መቼም ማግኘት የሚቻል አይደለም፡፡"
(ተፈራ ደምሴ፤ የሂሳብ ባለሙያ)
***
"--አገር እንደ ብዙዎቻችን ‹‹ዛሬን ጠልፈን እንሩጥ እንጂ ነገ የራሱ ጉዳይ›› የሚሉ አይነት
ሳይሆኑ እንደ አሰፋ ጎሳዬ አይነት ቀናት፣ ሳምንታት፣ ወራትና ዓመታት አሻግረው የሚያቅዱ
ሰዎች ያስፈልጓታል፡፡
‹‹ቢኖር ኖሮ›› የሚለው አነጋገር ብዙ ጊዜ አይመችም፡፡ ግን አንዳንድ ጊዜ ለአሰፋ ጎሳዬ አይነት ሰዎች ብንጠቀምበት የሚያስወቅስ አይሆንም፡፡ ስለሆነም አሰፋ ቢኖር ኖሮ፣ በሕትመት ሚዲያው አካባቢ ተፅዕኖ ማሳደር የሚችሉ እንቅስቃሴዎች ይኖሩ ነበር ከሚሉት መሀል ነኝ፡፡ አሰፋ ቢኖር ኖሮ፣ በአገራችን የፊቸርና የዶክሜንተሪ ፊልም ኢንዱስትሪ ውስጥ ተፅዕኖ ማሳደር የሚችሉ እንቅስቃሴዎች ይኖሩ ነበር ከሚሉት መሀል ነኝ፡፡
አሰፋ ቢኖር ኖሮ፣ በመጻሕፍት ሕትመት ዘርፍ ተፅዕኖ ማሳደር የሚችሉ እንቅስቃሴዎች ይኖሩ ነበር ከሚሉት መሀል ነኝ፡፡ ‹‹አሰፋ ቢኖር ኖሮ!›› እያልን በርካታ ገፆች መሙላት ይቻላል። እሱን ማጣት ይህን ያህል ክፍተት ነው የፈጠረው፡፡
በመጨረሻም፣ ጊዜው መቼም ይሁን መቼ ከአሰፋ ጎሳዬ ርዕዮች በጣም ጥቂቶቹ የቀን ብርሃን አይተው ‹‹እነኚህ እኮ የአሰፋ ጎሳዬ የአዕምሮ ውጤቶች ናቸው›› ለማለት እንዲያበቃን እመኛለሁ፡፡
(ኤፍሬም እንዳለ፤ የአዲስ አድማስ አምደኛ)
***
"--አሰፋ ጎሳዬ አለቃዬ ሆኖ ስመለከተው እንደ ዘመኑ (Business man) ገንዘብ ማሳደድ ብቻ ሳይሆን እንደ ጉራጌ ወይም እንደ ይሁዲ ቤተ-ዘመዱን ከማንኛውም ጥቅም የሚያጋራ ወይም የሚያስቀድም ነው፡፡
ይህን ሁሉ ያየሁት የማስታወቂያ ሥራ ኃላፊዋ ገነት ቢሮ እየሄድኩ ስጫወት ነው፡፡
የአድማስ ቢሮ ስለሚርቀኝ ጽሑፌንም  አብራት ለምትሠራው ታናሽ እህቷ ለመስከረም ነው የማስረክበው፤ ደሞዜንም ስቀበል ገነት መዝገብ ላይ እየፈረምኩ ነው፡፡ (የሥራ ክፍፍል) በጊዜ ሂደት በግል ምክንያት ከአድማስ ተሰናበትኩ። ሰውን እናውቀዋለን ማለት አይቻልም፡፡
ይበልጥ እያወቅናቸው በሄድን መጠን አዲስ ይሆኑብናል፡፡ አሴ አዲስ አይሆንብኝም፡፡ እስከ ወዲያኛው አስደመመኝ፡፡ "የጀመርከውን ልብ ወለድ እስክትጨርስ በወር አንድ ሺህ ብር እልክልሀለሁ" የሚል ወረቀት ላከልኝ። አሰፋ ጎሳዬ እኔ ባዶ ልብ ውስጥ እንዲህ የፍቅር ስር ከሰደደ፣ ቤተሰቡ ልብ ውስጥ እንደ ጠዋት ጤዛ፣ እንደ ሰማይ ኮከብ የሁል
ጊዜ ብርሃን መፈንጠቁ ይቀራል!;
(ደራሲ ስብሃት ገ/እግዚአብሔር)
***
"--የጥበብ ሰዎች የሚጎድለን ነገር ምን እንደሆነ በቀዳሚነት ተረድቷል፡፡ ሙያ፣ ዕውቀትና ችሎታችንን ተደራድረን መሸጥ እንደማንችል ከተረዳ በኋላ ለአርቲስቶች ማኔጀር ሆኖ የመሥራት
እቅድ ነበረው፡፡ ‹‹የአርቲስቱን ሕይወት ለመለወጥ ቴአትር ተስፋፍቶ፣ የፊልም ሥራ ጎልብቶ፣ ለሥራው ፈላጊና ተፈላጊውን ለማገናኘት በማኔጀርነት የሚሠሩ ሰዎች ያስፈልጋሉ›› ብሎ ያምን
ነበር፡፡ ..የንግድ ዕውቀት ያለው ማኔጀር ቢኖር እንደ ፈረንጆቹ አገር በእኛም ዘንድ ሙያው፣
ባለሙያውና አገር ይጠቀማል.. ይል ነበር። በአሁኑ ጊዜ ከውጭ አገር ይዘውት በሚመጡት አዳዲስ ሀሳቦቻቸው እንዲሁም በሥራዎቻቸው የሚያስገርሙን ሰዎች አሉ።
አሰፋ በውጭ አገር አልኖረም፡፡ ከዓመታት በፊት ግን በአስገራሚ ሀሳቦቹና ሥራዎቹ ብዙዎችን በማስገረሙ ልዩ ሰው መሆኑን አሳይቷል፡፡ በርካቶችም ተምረውበታል። ከዚህ አንፃር ለሚያውቁትና ለሚቀርቡት ብቻ ሳይሆን ለአገሩም ባለውለታ ሆኗል፡፡"
(አርቲስት ጀማነሽ ሰለሞን)
***
"- አሰፋ ጎሳዬን ለመግለጽ ይከብደኛል፤ በየትኛው መስመር ማየት እንደምችል ግራ ይገባኛል፤ በማንኛውም ዘርፍ አሰፋ ሙሉ ነው፡፡ የቱን ጠቅሼ የቱን እተዋለሁ? በጥበቡ መስመር ሙያተኞችን ከማበረታታት አልፎ የጥበብ አቅማቸውን የሚተገብሩበትን፣ ሠርተው ተጠቃሚ ሊሆኑበት የሚያስችላቸውን፤ በሀሳብ፣ በዕውቀት፣በምክር፣ በሞራል፣ በማቴሪያል፣ በገንዘብ ወዘተ... ማድረግ የሚችለውን ሁሉ ፈጽሟል፡፡ አሰፋ ጎሳዬ ለማንም ጥሩ አሳቢ፣ ወገንና ቤተሰብ ሆኖ ከልቡ ነው ሰውን የሚቀርበው፤ አሴ ከገንዘብና ከማቴሪያል ውጭ ለቀረቡት ሁሉ ፍቅር የመስጠት ትልቅ አቅም አለው፡፡
አሰፋ ጎሳዬን ከሕግጋት ውጭ ባይሆን፣ ፎቶ ኮፒ ሆኖ ማባዛት የሚቻል ቢሆን ኖሮ፣
እንዴት ዕድለኞች ነበርን በማለት፣ አንድ ጓደኛዬ አሰፋን የገለፀችበት መንገድ ምንጊዜም
ከአእምሮዬ አይጠፋም፡፡--"
(አርቲስት አዳነች ወ/ገብርኤል)
***
"አሴ ለኔ አንዴ ብልጭ ብሎ፤ አንድ አገር መብራት ሆኖ፣ ፏ ያለ ብርሃን ሰጥቶ እንግዲህ በዚህ ተጠቀሙ፤ አስፋፉትም፤ አዝልቁትም፤ እኔ ሌላ ጉዳይ አለብኝ ብሎ የሄደ ነው የሚመስለኝ፡፡ አሴ ደስታ ነው፤ ከልብ የመነጨ ሳቅ፡፡ የሳቁን ሀይል መቋቋም አይቻልም፡፡ አኩርፏችሁ ቢሆን እንኳ በግድ ትስቃላችሁ፡፡ እኔ እስቅ ነበር፡፡ ዛሬም አሴን ሳስበው ሙሉ ፈገግታውና ፍቅሩ ይመጡብኛል፡፡ ፏ ብሎ እንደሳቀ እፊቴ ድቅን ይላል፡፡ ለሰው ልጅ ሁሉ ያልተሸራረፈ ፍቅር ያለው ሰው ያየሁት አሴን ነው፡፡ ከሰኞ
እስከ ዓርብ፤ በወር መጀመሪያም ሆነ አጋማሽ አሴ ያው አሴ ነው፡፡ ሥራና ሙሉ ፈገግታ! አሴ ጋ ችግራችሁን ማስወገጃ መፍትሄ አለ፡፡ የአዲስ ሥራ ሀሳብ አለ- ያለ ስስት የሚነገር።--"
(አቶ በኃይሉ ገ/መድህን፤ የሥነ ህዝብ ባለሙያና ጓደኛ)

Read 1794 times